ኢትዮጵያ በሰብአዊ መብት አያያዝ ስትወቀስ ኖራለች፡፡ በተለይ በፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት እንዲሁም በጋዜጠኞች ላይ ይደርስ የነበረው የሰብአዊ መብት ጥሰት ገጽታዋን ክፉኛ አበላሽቶት ቆይቷል፡፡
ሀገሪቱ በለውጥ ጎዳና መጓዝ በጀመረች ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ይህን የጠለሸ ስም ለመቀየር የሚያስችሉ እርምጃዎችን ወስዳለች፡፡ በሀገሪቱ በማረሚያ ቤቶችና በመሳሰሉት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ይፈጸም እንደነበር በማመንም ይህን ለመለወጥ ተሰርቷል፡፡
የተከናወኑት ተግባሮችም ስኬቶችን ማስመዝገብ ጀምረዋል፡፡ በተለያየ ምክንያት እየተፈረደባቸው በእስር ይማቅቁ የነበሩ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና አባላትን እንዲሁም ጋዜጠኞችን ከእስር በመፍታት የጀመረው የመንግስት እርምጃ፣ ከእስር የተለቀቁት ወገኖች ምንም አይነት ገደብ ሳይጣልባቸው በሀገራቸው ፖለቲካዊና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ውስጥ በንቃት የሚሳተፉበትን እድል ፈጥሯል፡፡
ከለውጡ ወዲህ ባለው አንድ አመት ብቻ ወደ ስምንት ሺ ታራሚዎች ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በይቅርታ ተፈትተዋል፡፡ በክልሎችም ተመሳሳይ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡
በሚከተሉት የፖለቲካ አመለካከት የተነሳ ሀገር ጥለው የወጡትም ሆኑ ለትጥቅ ትግል በዱር በገደሉ የነበሩትም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው አመለካከታቸውን በሰላማዊ መንገድ የሚያራምዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህን ተከትሎም ኑሯቸውን በውጭ ሀገር እና በየጫካው ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣አክቲቪስቶች፣ወዘተ፣ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡
ሀገሪቱ ሰብአዊ መብትን ለማክበር የወሰደችው ተጨባጭ እርምጃ በአለም አቀፍ ደረጃ ጭምር አድናቆት ተቸሮታል፡፡ የጋዜጠኞችን መብት በማክበር በኩል የወሰደችውን እርምጃ ተከትሎም የዘንድሮው የአለም የፕሬስ ቀን በኢትዮጵያ እንዲከበር መደረጉም ይታወሳል፡፡
ለውጡ በማረሚያ ቤቶች ምን ያህል የሰብአዊ መብት ጥሰት ይፈጸም እንደነበር ግልጥልጥ አድርጎ አሳይቶታል፡፡ በማረሚያ ቤቶች ዘግናኝ ወንጀል ይፈጸም እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም ፤ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ሰዎች ይታሰሩ እንደነበርም ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡ የማረሚያ ቤት አባላት የማያውቋቸው ድብቅ በሆነ መልኩ የሚታሰሩ ሰዎችም ነበሩ፡፡
ይህን ለመለወጥ የማረሚያ ቤቶች ኃላፊዎችን ከመቀየር አንስቶ የተለያዩ የሪፎርም ስራዎች ተካሂደዋል፡፡ ይህም በማረሚያ ቤቶች ላይ ለውጦች እንዲመጡ እያስቻለ ነው፡፡ የታራሚዎች የሰብአዊ መብት አያያዝ መሻሻል እያሳየ መጥቷል፡፡ ይህንንም ከታራሚዎች፣ ከማረሚያ ቤት ኃላፊዎችና አቃቢ ህግ የተገኙ መረጃዎች አረጋግጠዋል፡፡
ታራሚዎች እንደ ፊቱ መደብደብ ብሎ ነገር ከቶ እንደማይታሰብ ጠቅሰው፣ ነገሮች በውይይት እየተፈቱ መሆናቸውን ነው የሚገልጹት፡፡
የታራሚዎች ጥያቄ የሰብአዊ መብት አያያዝ ተጓደለብን ሳይሆን ታርመናል፤ የምንፈታበት ሁኔታ ይመቻች፣ በልዩ ልዩ ሙያ ሰልጥነናልና እናመሰግናለን፤ ሴቶች ላይ የሚጣለው ቅጣት ተፈጥሮን ያገናዘበ እንዲሆን ይደረግ የሚሉ ሆነዋል፡፡ ቅሬታቸው እንዴት እንደተከሰሱና እንደተፈረደባቸው እንጂ ማረሚያ ቤቱ የሰብአዊ መብት እየፈጸመብን ነው የሚል አይደለም፡፡
ጠቅላይ አቃቢ ህግ ከለውጡ በኋላ አደርኩት ባለው ግምገማም አሁን ያለው የማረሚያ ቤቶች የሰብአዊ መብት አያያዝ ከበፊቱ ጋር ሲተያይ ተጨባጭ ለውጥ የታየበት መሆኑን አረጋግጧል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ታራሚዎች እውቅና መስጠታቸውንም በመልካምነት አይቶታል፡፡ እንዲያም ሆኖ መዘናጋት እንደማያስፈልግ፣የታራሚዎችን ሰብአዊ መብት አያያዝ በሚመለከት አሁንም የቤት ስራዎች እንዳሉም አመልክቷል፡፡
ታራሚዎችን ለመደብደብ የሚዳዳቸው ጥበቃዎች እንዳሉ አንዳንድ ታራሚዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህም በጥበቃዎች በሰብዓዊ መብት መርሆች ላይ የጠለቀ እውቀት እንዲያገኙ የማድረግን አስፈላጊነትን ያመለክታል፡፡ ይህን ግምት ውስጥ ያስገባ ስራ መስራት ይገባል፡፡
ከሀገራችን ማረሚያ ቤቶች ያለፉት አመታት ታሪክ አንጻር ሲታይ አሁን ያለው ለውጥ በእርግጥም ትልቅ እምርታ ነው፡፡ ሀገሪቱ በሁሉም መስክ በለውጥ ጎዳና በመራመድ ባካሄደችው ርብርብ ተሰርቶ የተገኘ ውጤት ነው፡፡
በማረሚያ ቤቶች ሲስተዋል የቆየው ችግር ዘመናትን ሲሻገር የመጣ እና ውስብስብም እንደመሆኑም ባልተሰሩ ተግባሮች ላይ በማተኮር እንዲሁም የተሰሩትን ይበልጥ በማጠናከር የለውጡን ዘላቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
ከይቅርታው ጋር በተያያዘ ያለውን ሁኔታ ለማረሚያ ቤቶች ለማስገንዘብ መሰራት ይኖርበታል፡፡ ታራሚዎች ይቅርታ የሚደረገው ምን ሲሆን ነው? የሚለውን እንዲረዱ ተከታታይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሰራት ይኖርበታል፡፡ ታራሚዎች አሁን ለምን ይቅርታ አይደረግልንም ሲሉ የሚያቀርቡት ቅሬታ ለመፍታት ያስችላል፡፡ ይቅርታ በጅምላ እንደማይሰጥ ቢታወቅም፣ ባለው አሰራር መሰረት ታራሚዎችን ይቅርታ በሚያገኙበት ሁኔታ ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መስራትም ያስፈልጋል፡፡
እነዚህ ሁሉ በማከናወን በማረሚያ ቤቶች የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ የታየውን እምርታ ዘላቂ ማድረግ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2011