የሰው ልጅ ማህበራዊ ፍጡር ነው በማህበራዊ ፍጡርነቱና ኑሮውን ለማሳካት የእርስ በእርስ ግንኙነት ያደርጋል። ይህ የእርስ በእርስ ግንኙነት እንከን አልባና ለስላሳ ሳይሆን በግጭት የተሞላና ትግል ያጠላበት ነው። ስለሆነም አንዱ የአንዱን መብት እንዳይጥስና ጉልበተኛው አቅም የሌለውን እንዳይደፈጥጥ ሚዛኑ የሚጠበቀው ሕግ በሚሉት ማሰሪያ ገመድ ይሆናል።
በዓለም የትኛውም ክፍል አብዛኛው ሕዝብ ሃይማኖቱንና ሕግን የሚያከብርና ለሚያወጡት ህግጋት የተገዛ መሆኑ እውነት ቢሆንም ጥቂት አፈንጋጮች እንደሚኖሩም ሳይታለም የተፈታ ነው። ስለሆነም ሕግ አስፈላጊነቱ እነዚህን አፈንጋጮች መስመር ማስያዝና የኅብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ያለምንም መስተጓጎል እንዲቀጥል ማስቻል ነው። በሌላ አነጋገር ሕግን ማክበርና ማስከበር የሰው ልጆችን ህልውና ማስቀጠያ ቁልፍ መሣሪያ ነው ማለት ነው።
ሕግ ከሌለበት ዴሞክራሲዊ አገር በአምባገነን የምትመራ አገር ትሻላለች የሚባለውም አምባገነንነት እንደጥሩ ነገር ተወስዶ ሳይሆን የሕግን መኖርና አስፈላጊነት ምን ያህል ወሳኝ መሆኑን ለማስረዳት መሆኑ ይታመናል። ሕግና መንግሥት በሌለባቸው አገራት የሚከናወነውን ተግባርና በሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰቆቃ ስንመለከት የሕግ ፋይዳ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ግልጽ ይሆንልናል። ይህ ደግሞ ሁሉም ዜጋ ለሕግ መከበር ከምንም ነገር በላይ መስራት እንዳለበት የሚያስገነዝብ ነው። ይህ እውን የሚሆነው ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ ሕግ ሲያከብርና ሲያስከብር ይሆናል።
ከላይ እንደተመላከተው የሕግ መኖርና የሕግ ማስከበር ፋይዳው እጅግ የገዘፈ ቢሆንም ሕግን ተገን አድርጎ ጉልበትን ማሳየትም የሚደገፍ ተግባር አይደለም። ለማናችንም ግልጽ እንደሆነው የሕግ ተቀዳሚ ዓላማ ሕግን መተላለፍ ዋጋ እንደሚያስከፍል ተገንዝበው አጥፊዎች ከጥፋት ተግባር እጃቸውን እንዲሰበስቡ ማስቻል ነው። ቅጣቱ የመጨረሻና በማን አለብኝነት ለሚፈጸም ጥፋት የሚከፈል ዋጋ ነው የሚሆነው።
ሕግ የፍትህና የህሊና ጉዳይ ነውና በማንኛውም ወገን ከሚደረግ ጣልቃ ገብነትም የጸዳ ሊሆን ይገባል። ከዚህ በተቃራኒው ሄዶ የዳኝነት ሥርዓቱ በመንግሥትም ሆነ በሌላ አካል ፍላጎት የሚጠመዘዝና የሚመራ ከሆነ ሕዝብ በፍትህ ሥርዓቱ እንዳይተመማን ስለሚደርገው ጉዳቱ አስከፊ ይሆናል።
ከዚህ አንጻር በአገራችን ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረው በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ጣልቃ የመግባት ሁኔታ ሕዝብን ምን ያህል ለምሬት እንደዳረገና ለለውጥ እንዳነሳሳም የሚረሳ አይደለም። ሰዎችን ታሳቢ አድርገው በአንድ አዳር ሕጎች ሲወጡ እንደነበርም ተደጋግሞ ሲገለጽ የነበረ ጉዳይ ነው። ከዚህም የተነሳ ዜጎች በፍትህ ሥርዓቱ ላይ የነበራቸው አመኔታ እጅግ የቀነሰበት ሁኔታም ተፈጥሮ ነበር።
የሕዝቦች ትግል ውጤት የሆነውና በአገሪቱ የተከሰተው የለውጥ አመራርም ይህ ችግር በእውነትም ያለ ችግር መሆኑን በማመንና በፍጥነት ካልተስተካከለም ለአገሪቱ ህልውና አደጋ መሆኑን ተገንዝቦ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል። ዳኞች ከማንኛውም ተጽእኖ ነፃ ሆነው እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታን መፍጠር፣ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ እንደሆኑ የታመነባቸው ግለሰብን የፌዴራል ከፍተኛ ፕሬዚዳንት አድርጎ መሾምና ማረሚያ ቤቶች ከማሰቃያነት ወጥተው እውነተኛ ማረሚያ እንዲሆኑ ለማድረግ የተጀማመሩ እርምጃዎች መንግሥት ገለልተኛና ታማኝ የፍትህ ሥርዓት ለማስፈን ያለውን የማያወላውል አቋም የሚያመላክት ነው።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በቅርቡ ከሕግ ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይትም መንግሥት በፍትህ ሥርዓቱ ውስጥ እጁን የሚያስገባበት ምንም ዓይነት ሁኔታ እንደማይኖር ማረጋገጣቸውም የሚመሰገንና ተስፋችንን በእጅጉ የሚያለመልም ነው።
ይሁንና ተዓማኒና ገለልተኛ የሆነ የፍትህ ሥርዓትን ለማስፈን የሚቻለው በመንግሥት ጥረት ብቻ እንደማይሆን ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል። ተዓማኒና ገለልተኛ የፍትህ ሥርዓት ከምንም ነገር በላይ የሕዝብን ድጋፍና ንቁ ተሳትፎ ይጠይቃል። እኛ ኢትዮጵያውያን ሕግን አከብረን በመተዳደር ረጅም ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን።
ቀደም ባሉት ዘመናት ሕግ አስከባሪ ኖረም አልኖረ በሕግ አምላክ ከተባለ ማንም ሰው ለዚህ ትዕዛዝ ይገዛ እንደነበር ብዙዎች ይመስክራሉ። ስለሆነም አሁንም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሕግ ማክበርና ለሕግ መገዛትን ከራሱ በመጀመር ሊያሳይ ይገባል። ከዚህም በላቀ በማንኛውም አካል ሕግ ሲጣስ ሥርዓት ባለው ሁኔታ በመቃወም ለፍትህ ሥርዓቱ ዘብ መቆም ይገባል።
በአጠቃላይ ሰርተን ለመኖርም ሆነ በሰላም ወጥተን ለመግባት የሕግ መከበር ወሳኝ በመሆኑ መንግሥትና ሕዝብ በተለይም በፍትህ ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ተዋናዮች የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው እንላለን!
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2011