ክፍል ሁለትና የመጨረሻ
ባለፈው ሳምንት በነበረን ቆይታ ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ በፍቅር እስከመቃብር መጽሐፋቸው አስቀምጠውታል ስለተባለው ትንቢት የሥነ ሕይወት መምህሩ ገብረሀና ዘለቀ ያቀረቡትን ጥናት ማቅረባችን የሚታወስ ነው። እነሆ ዛሬም ቀሪውን የባለጥናቱን ዳሰሳዎችና በጥናቱ ላይ ስለተነሱት አስተያየቶች በከፊል እንቃኛለን።
የአራዊቱ ተምሳሌት በፍቅር እስከመቃብር
አባ አለምለምኔ ደክሟቸው በአባይ በረሃ ጎናቸውን እንዳሳረፉ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወሰዳቸው። ሲነቁ ጨረቃ ወጥታለች፡፡ መጀመሪያ ጅብና ተኩላ ከተለያዩ አቅጣጫዎች መጡ፡፡ ወዲያውኑ ሲሸሹ አዩአቸው፡፡ በምትኩ ነብር መጣ፡፡ ነብሩ ሲሸሽ ደግሞ አንበሳ ታያቸው፡፡ አንበሳው ነብሩን ሲያሳድድ በሌላ በቀጭን ዛፍ ላይ ተንጠላጥለው ከዋርካው ዛፍ ቅርንጫፍ ውስጥ ገብተው ተደበቁ፡፡ አንበሳው ግን ሌሊቱን ሙሉ ሲጠብቅ አድሮ ሲነጋ፣ ሞቅ ሲል ረጋ ብሎ ወደ አባይ ወንዝ ወረደና ከአይናቸው ተሰወረ፡፡
ጥናት አቅራቢው ገብረሀና ዘለቀም ይህን ታሪክ በሚከተለው መልኩ የትንቢት ተምሳሌት አድርገው ያስቀምጡታል።
ተኩላ የኢጣሊያ አርማና ክፉ አውሬ ነው፡፡ ጅብ ደግሞ በሆዳምነቱ ይታወቃል፡፡ ደራሲው ተኩላና ጅብ በአንድ ጊዜ ከሁለት አቅጣጫ መከሰታቸው የጣሊያን የባንዳዎችን አገር አጥፊ ህብረትን ያመለክታል:: ሁለቱንም ያሳደዳቸው ነብር ደግሞ የቁጡዎቹ የኢትዮጵያ አርበኞች ምሳሌ ነው፡፡ አንበሳ የኢትዮጵያ የዘውድ ሥርዓት ምሳሌ ሆኖ ያገለግል ነበር፤ የዘውድ ሥርዓትም ምሳሌ ነው፡፡ የዘውድ ሥርዓት ሲመለስ ግን ሥልጣኑ አርበኞችን ያገለለና ያባረረ እንዲሁም ውለታ ያልቆጠረ ነበር።
ዋርካ ሀገር፤ ቅርንጫፍ ደግሞ ሕዝብ ነው፡፡ ሰብለ ዋርካው ላይ የወጣችው በራሱ በዋርካው ላይ አይደለም። በሌላ ቀጭን ዛፍ ላይ በመሸጋገር እንጂ:: ይህም ኢትዮጵያን ከጣሊያን መንጋጋ ለማላቀቅ የእንግሊዝ ረዳትነት ማስፈለጉን በምሳሌ ያሳያል።
የሰብለ ወንጌል የመቃብር ኑሮ
ሰብለወንጌል ከበዛብህ አስከሬን ጋር፤ አስከሬን እየጠበቀች፣ የአስከሬን ማረፊያውን እያጸዳች፤ጎሀጽዮን ሕይወቷን ስትገፋ እናገኛታለን፡፡ ከምትወደው ጋር ቆርባም የምትወደው በዛብህ በክንዷ ላይ አረፈ። እስከመጨረሻው ላትለየው የመቃብሩ ጠባቂ ሆነች፡ ፡ ይህ ማለት በኢትዮጵያና በሚወዷት ልጆቿ መካከል ያለው ቃል ኪዳን እንደ ቅዱስ ቁርባን የከበረ፣ የተቀደሰ፣ የተባረከ መሆኑንና የትንሳኤ ዘመን ብስራት ተደውሎ እስኪሰበሰቡ ድረስ ከክንዷ(ከአፈሯ) ላይ እያስገደለች፣ ከማህጸኗ እያስተኛች፣ የሰቆቃ፣ የዋይታና የድቅድቅ ጨለማ ዘመን እየገፋች እንደሆነ ይነግረናል። ይህ እውነታም እንዳይሰቀጥጠን ሰውኛ አድርጎ በሰውኛ የፍቅር ቀጭን ኩታ ጠቅልሎ ስለሆነ ይህ መጋረጃ እስኪገለጥልን እንድንጠብቅ ፈርዶብናል፡፡
የሰብለወንጌል እግር እሾህ አወጣጥ
«አባ አለምለምኔ» በሽሽት ጊዜ እግራቸውን የወጋቸው ጋሬጣና እሾህ በሁለት አካላት በሁለት ጥበብ ሲወጣ እናነባለን፡፡ የመጀመሪያዎቹ ቀፎ አውራጆች ናቸው፡፡ ቀፎ አውራጆቹ የ«አባ አለምለምኔ»ን እግር እስከ ደምስራቸው የወጋቸውን አሾህ በወረንጦ እያደሙ የተወሰነውን ያወጡላቸዋል፡ ፡ ከዚያም ከያዙት ጨርቅ ጫማ ሰፍተውላቸውና አድርገውላቸው ይሄዳሉ።
ሁለተኛዎቹ እሾህ አውጭዎች ይሁን በፈቃዱና በዛብሽ ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ምግብ አበሏቸው፣ እንቅልፍ ሲወስዳቸው እግራቸውን ለማጠብ የቀፎ አውራጆቹን ጨርቅ ሲፈቱ እግራቸው የተሸከመውን ጋሬጣና እሾህ ይመለከቱና በሞራ ያጅሉታል፡፡ በማግስቱ ጠዋት ከፀሐይ ላይ ተቀምጠው እግራቸውን በጨው ውኃ ውስጥ ሲዘፈዝፉት እሾሁ ያለምንም ችግር በራሱ ኃይል ይወጣል፡፡ ይህ በጥበብ የታገዘ፣ ህመም የሌለበትና ሁሉንም እሾህ ከእግራቸው ያስወገደ ዘዴና ብልሀት ነው፡፡
«አባ አለምለምኔ» ወይም ሰብለወንጌል ኢትዮጵያ በፊውዳላዊ ባላባታዊ ሥርዓት ስር የታሰረችው ለእድገቷ ማነቆ የሆናት አገር ሙሉ ግፈኛ፣ ገራፊ፣ ገዳይ፣ አሳሪና ገፋፊ መሆኑን ለማመላከት ነው። በእሾህና ጋሬጣ የተመሰለው በሚወገድበት ጊዜም ኢትዮጵያን የሚጎዳ ወረንጦ ከሆነና ለውጡ ጥገናዊ ከሆነ የሕዝቧ አልያም የልጆቿ ረሀብና ጉስቁልና ይቀጥላል ለማለት ነው፡፡
በእንደነ በዛብሽ ዓይነት ብልሀተኛ ልጆቿ ጋሬጣውና እሾሁ እግር ሳያደማና ሳይጎዳ በዘዴ ይወጣል፡፡ ይህም ስርነቀል የሆነ የሥርዓት ለውጥን ያመላክታል፡፡ እንዲህ ከሆነም ኢትዮጵያ እድገቷ፣ ብልፅግናዋና ሰላሟ ዋስትና ያገኛል፡፡ የፀሐይ መውጣትም የብሩህ ዘመን ብስራትን ያመለክታል፡፡
ከበዛብህ የተያያዙ ህልምና ምሳሌዎች
የበዛብህ የህልም ታሪክ እንዲህ ይጠቁማል። የኋሊት በገመድ ሁለት እግሮቹን ከግንድ ጋር ታስሮ፤ ቆርጦ ለመሄድ ባለው አቅሙ ሁሉ ታግሎና ተሸንፎ ሊወድቅ ሲል አንዲት ርግብ ከማንኩሳ ቤተክርስቲያን ከአዕዋፍ መሀል ትነሳና ስትዞር ቆይታ እታሰረበት ዛፍ ላይ ታርፋለች። ከዚያም ቀስ ብላ ወርዳ የታሰረበትን ገመድ ቆርጣ እፊቱ ላይ ጉድጓድ ቆፍራ ትቀብርና፣«የታሰርህበት ገመድ ያው…ተቆርጦ ተቀበረልህ፤ እንግዲህ ወደ ፈለግህበት ሂድ ትለዋለች»
ጥናት አቅራቢው ደራሲው የእናትና አባቱን የዘር ሀረግ በዛፉ ግንድ መስለውታል ይላሉ፡፡ የታሰረው ከግንዱ ጋር ነው፡፡ ግንድ በስር፣ ከመሬት ጋር ተጣብቆ ቅርንጫፍን፣ ቅጠልንና አበባን ይሸከማል፡፡ በዛብህም ከግንዱ ጋር በገመድ ታስሯል፡፡ በራሱ ሊበጥሰው ባልቻለ ገመድ፡፡ ገመዱ ቤተሰቡ ለእግዚአብሔር ስለት ሲሰጡት የገቡት የቃልኪዳን ውል ነው።
በዛብህ አንድም በመካንነት የወለዱት የእርሱና የወላጆቹ ደም ትስሰር፤ አንድም የህያዋንና ሙታን ነፍሳዊ ትስስር፤ በሌላም በኩል በእርሱ ምኞት (ማግባት፣ ባለሀብትና የቅኔ መምህር መሆን) በድንግልና መካከል ያለ ትስስር ሊሆን ይችላል:: ቤተክርስቲያን ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ የሚሰፍንባት ተምሳሌት ነች።
ርግብ ሰላም፣ ደህንነትና የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ምሳሌ በመሆን ትጠቀሳለች። በራሱ መበጠስ ያልቻለውን በጣጥሳ ከፊቱ ትቀብርና ነፃነቱን ትነግረዋለች፡፡ ይህም ማለት በዘር፣ በአፀደ ስጋ ከሳሽ፣ ወቃሽ የሌለው መሆኑንና እግዚአብሔርም በነፃ ሀሳቡና በጥሪው እንዲኖር መፍቀዱን ይገልፃል፡፡
የሦስት ሰዎች ሞት
አበጀ በለው ሀሳቡም እምነቱም አንድ ሰው ሳይሞት የፊታውራሪን እጅ መያዝ ነበር፡፡ ጥናት አቅራቢው መምህር ገብረሀናም ደራሲው «ወደፊት የሚመጣው ለውጥ ያለምንም ደም መፋሰስ ሊሆን እንደማይችልና እልቂቱን አስቦ ማስቀረት እንደማይቻል ደራሲው በተሰጣቸው ተምሳሌታዊ ትንቢት ቀድመው አስጠንቅቀውናል» ባይ ናቸው። «ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም» ብሎ የተነሳው የለውጥ ኃይል እንዴት ወደ አሰቃቂ ደም መፋሰስ፣ እንደገባም በድርጊት ማረጋገጥ ተችሏል ይላሉ፡፡
ወይዘሮ ውድነሽ በጣሙ ያገቧቸው ሦስቱም ባሎች በየተራ ሞተውባቸዋል። እሳቸውም እንዳያገቡ ወስነው ተቀምጠው ነበር፡፡ ውድነሽ በተደጋጋሚ ቀብረው ማግባታቸው እና እንደገና ለማግባት መወሰናቸውን ስንመለከት እርሳቸው የሀገር ምሳሌ ሲሆኑ ባሎቻቸው የሀገር መሪዎች መሆናቸውን ያመለክተናል፡፡መሪ ይነግሳል፣ ይሞታል፣ ሀገርም ልክ እንደ ሌላ ባል ከአዲስ መሪ ጋር ትቀጥላለች፡፡
የሦስት ቁጥር መደጋገም
ደራሲው ሦስት የሚለውን ቁጥር ይደጋግማሉ:: እመት ውድነሽ በጣሙ ሦስት ባሎች በየተራ አግብተው ሞቱባቸው። ውድነሽ ባለቤታቸው በተቀበሩ በሦስተኛው ቀን አረፉ። በዛብህ ደብረወርቅ መጽሐፍ በመቀፀል ላይ እያለ በሦስተኛው ዓመት ደብተራ በየነ መጣና የወላጆቹን ሞት አረዳው። በዛብህ በሦስተኛው ቀን ታላቁን የቅኔ መምህር አለቃ ክንፉን ተገናኘና እያስተማረ እንዲማር ተፈቀደለት።
ሦስቱ ጉልቶቻቸው ነፃ ወጡ። ፊታውራሪ መሸሻን ለመያዝ በተደረገው ወጥመድ ሦስት ባላገሮች ሞቱ። ፊታውራሪ መሸሻ ሦስት ዋሶች ጠርተው እምቢ ተባሉ። በዛብህ፣ እማሆይ ሰብለወንጌልና ካሳ ዳምጤ ሦስቱ በአንድ መቃብር ተኙ፡፡ ጥናት አቅራቢው ትንቢት ነው ያሉትን እውነት በዚህ መልኩ አስቀምጠውታል።
የገባር ሥርዓቱ ሦስት መዋቅሮች ማለትም ንጉሱ ከላይ ሆነው መሳፍንቱ፣ መኳንንቱ፣ ልዑላኑና ካህናቱ መሀከለኛውን ሲይዝ ገባሩና ጭሰኛው ደግሞ የታችኛው አካል ማለት ሊሆን ይችላል። አንድም ሀዲስ አለማየሁ ሦስት ቁጥርን የደጋገሙት፤ ሦስቱን አብዮተኞች ማለትም ካሳ፣ በዛብህና ሰብለወንጌል፣ አንድም የሦስቱን ብቸኛ ልጆች ቤተሰባዊነት ለመግለጽ፣ ሌላም በኢትዮጵያ ህገ ልቦና፣ ህገ ኦሪትና ህገ ወንጌልን የተተገበረባት የታላቋ አገር ዜጎች መሆናችንና በዚህ የእውቀት ሀብት ለመለወጥም አለመዘጋጀታችንን በቁጭት ሲያስቡት ነው።
በሌላም በኩል ሦስቱን የዕድሜ ደረጃዎችን ማለትም ልጅነትን፣ ወጣትነትንና ጎልማሳነትን የሚያልፈው ሕዝባችን እያንዳንዱን የዕድሜ ደረጃ እንደሚገባው ሳይሰራበት በገዢና ተገዢ ተቀፍድዶ ዘመናት መብከታቸውን ለማሳሰብ፣ነው። በሌላ መልኩም ፊታውራሪ መሸሻ ከተወለዱ ጀምሮ ያሳለፏቸውን ሦስት ነገስታት ማለትም አፄ ምኒልክ፣ ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱንና አፄ ኃይለሥላሴን ለመግለፅ የተጠቀሙበት ስልት ሊሆን ይችላል፡፡
አቀባበር
ፊታውራሪ መሸሻና ወይዘሮ ጥሩአይነት በአንድ ቀን ሞቱ። በአንድ ላይም ተቀበሩ ፡፡ ደራሲው እርስ በእርሱ የተጋመደው የቤተክርስቲያን መዋቅራዊ አስተዳደርና የባላባታዊው/ንጉሳዊ/ ሥርዓት አስከፊ ውድቀት ላይ መሆኑንና የሁለቱ ትስስር ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በአንድ ተጠራርጎ እንደሚቀበር በምሳሌ ያረዱናል።
ሰብለወንጌል ከበዛብህ ጎን ተኛች፡፡ ከዚያም ካሳ ዳምጤ ከጎናቸው አንቀላፋ ፡፡ መጽሐፉ ከባሏ ጎን አስተኛት እንጂ ቀበራት አይልም፡፡ ደራሲው ሰብለወንጌል (ኢትዮጵያ) ትንሳኤዋ ተበስሮ እስከምትነቃ ከሞት የሚስተካከል እንቅልፍ ወስዷት መተኛቷን ገልፀው ድርሰታቸውን ይጨርሳሉ፡፡
ጥናታዊ ዳሰሳውና የተደራሲያን አተያይ
የሀዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው ሰባተኛው አገር አቀፍ አውደ ጥናት ላይ የተሳተፉ ተደራሲያን በጥናቱ ላይ የራሳቸውን አስተያየት አስቀምጠዋል። በርካቶቹ ጥናቱ የቀረበው የሥነጽሑፍ ባለሙያ ባልሆኑት የሥነ ሕይወት መምህር መሆኑ ብቻ አድናቆታቸውን የላቀ አድርጎታል። መምህር ገብረሀና ብዙዎች ሊቃኙት በማያስቡት አቅጣጫ ተጉዘው የደራሲውን ትንቢት በፍቅር እስከመቃብር ገጾች ሊያሳዩ መቻላቸው ጥበባዊ ችሎታቸውን አመላካች ስለመሆኑ ይመሰክራሉ።
በተቃራኒው ደግሞ የመጽሐፉ ጥናታዊ ዳሰሳ ትንቢት ከመባል ይልቅ ተምሳሌታዊ ትንተና ቢባል የተሻለ እንደሚሆን የሚናገሩ ወገኖች አሉ። ለዚህም የሚያስቀምጡት ምክንያት ዳሰሳው ከትንቢት ይልቅ ትንታኔው የሰፋና ጥልቀት ያለው መሆኑን ነው።
ጥናት አቅራቢው እንደተለመዱት የሥነጽሑፍ ሕጎች ምልሰትን በአግባቡ ያለመጠቀማቸው የጥናቱን ዳሰሳ ሊያሳሳው እንደሚችል የሚናገሩም አልጠፉም። ከዚህ እውነታ ይልቅ ትንቢታዊ መሠረት ላይ አተኩረዋል። ትንቢት ሲባል ደግሞ የወደፊቱን አመላካችና ገማች መሆኑ ግልጽ ነው። ጥናት አቅራቢው ግን ወደ ኋላ ተመልሰው የጥንቱን ታሪክ ጭምር ሊነግሩን ችለዋል። ይህ ደግሞ ከትንቢትነቱ ይልቅ ታሪክ አስታዋሽነቱን ያጎላዋል ባይ ናቸው።
አዶስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ1/2011
መልካምስራ አፈወርቅ