የመጽሐፉ ስም፡- የቆረኑ ጉዞ
ደራሲ፡- ወይንሽት በየነ ዘውዴ
የህትመት ዘመን፡- 2012 ዓ.ም
የገጽ ብዛት፡- 206
ዋጋ፡- 101.50 ብር
በብዙ የስነ ጽሑፍ የውይይት መድረኮች ላይ የምሰማው ነገር ‹‹ረጅም ልቦለድ ጠፋ›› የሚል ወቀሳ ነው። አንዳንዶቹ አንባቢ የለም ለማለት ዘመኑ የቴክኖሎጂ መሆኑን ሲወቅሱ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ የለም ደራሲ ጠፍቶ እንጂ ዘመኑ የቴክኖሎጂ መሆኑ አንባቢ አያሳጣም ይላሉ። በሌላ በኩል በዚህ የረቀቀ የቴክኖሎጂ ዘመን ልቦለድ መጻፍ እንደማያነሳሳ የሚናገሩም አሉ። እነዚህኞቹ ወገኖች ምክንያታቸው፤ ዓለም ከልቦለድ በላይ ቀልብ አንጠልጣይ ሆናለች የሚል ነው። የገሃዱ ዓለም ታሪኮች ራሳቸው ሁልጊዜ አዳዲሶች ናቸው። እውነተኛ ክስተቶች ከልቦለድ በላይ አጃኢብ የሚያሰኙና አፍን የሚያስይዙ ሆነዋል።
አሁን በየገበያው ላይ የምናየው ወቅታዊ የፖለቲካ መጽሐፍ ነው፤ ከዚያ ቀጥሎ የሚታየው የግጥም መጽሐፍ ነው። ረጅም ልቦለድ የምናገኘው በረጅም ዓመት ውስጥ ነው፤ ለዚያውም በአንባቢ ዘንድ ብዙም ሲባልላቸው የማይሰሙ ናቸው። አንድ ገጠመኝ ተናግሬ ወደ ዛሬው መጽሐፍ እይታዬ እገባለሁ።
ከዓመት በፊት ነው። አንድ ዳጎስ ያለ ገጽ ያለው የረጅም ልቦለድ መጽሐፍ ተሰጠኝ።ደራሲዋን ባላውቃትም የሰጠችኝ ጋዜጠኛ በሥራ አጋጣሚ ስለምንተዋወቅ እስኪ ተመልከተው ብላ ነው የሰጠችኝ። እኔም ረጅም ልቦለድ በማግኘቴ ደስ ብሎኝ ጀመርኩት። ከንባቤ በኋላም የተሰማኝን ምንም ሳላስቀር መጽሐፉን ለሰጠችኝ ጋዜጠኛ ነገርኳት። መጽሐፉ ሙሉውን የፌስቡክ ቋንቋ ነው።አንዳንድ ቦታ ላይ በቃላት መካከል ክፍተት (Space) እንኳን የለውም። እንዲህ አይነት ጽሑፍ ደግሞ ለማንበብ ምቾት አይሰጥም። የግድ አስፈላጊ የሆኑ ሥርዓተ ነጥቦች ከሌሉ ትርጉሙን ለመረዳት እንኳን ያስቸግራል። መጽሐፉ የተጻፈው ከኢንተርኔት በተሰበሰቡ ጽሑፎች ነው። ከዘመነ ፌስቡክ ወዲህ የሚጻፉ መጽሃፎች የስነጽሁፍ ውበት የራቃቸውና በአንድ ጀንበር በለብለብ የሚጻፉ ደራሽ መጽሐፎች ናቸው።
ወይንሸት በየነ ዘውዴ በምትባል ጸሐፊ የተጻፈ ‹‹የቆረኑ ጉዞ›› የሚል መጽሐፍ በአንድ የሥራ ባልደረባዬ ተሰጠኝ። በመጽሐፉ ጀርባ ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች (ብለርብ) ጸሐፊዋ ጋዜጠኛ እንደሆነች አይቻለሁ። እርግጥ ነው ጋዜጠኛ መሆኗን የመጽሐፉ አተራረክም ይመሰክራል። ከልቦለዳዊ ፍሰት ይልቅ ዘገባዊ አጻጻፍ ይጫነዋል።አተራረኩ የእውነተኛ ታሪክ አተራረክ ነው። ከቀልብ አንጠልጣይነት ይልቅ እውነታውን ለመናገር ይፈጥናል።ጸሐፊዋ በቀጥታ ያስተዋለችውን ነገር እየዘገበች ይመስላል።
የቃላት መፍቻ (ሙዳዬ ቃላት) ጨምሮ 206 ገጾች ያሉት ይህ መጽሐፍ የትውፊት ሰነድ መሆን የሚችል መጽሐፍ ነው። ቀደም ብዬ በፌስቡክ ቋንቋ የተጻፉ መጽሐፎችን ማንሳት የፈለኩት ይህ ‹‹የቆረኑ ጉዞ›› መጽሐፍ ስላስታወሰኝ ነው። መጽሐፉ ከፌስቡክ ቋንቋ መጽሐፎች ፍጹም ተቃራኒ ነው።ምናልባት የታሪኩ መቼት ስለማይፈቅድላት ነው ይባል ይሆናል፤ ዳሩ ግን የደራሲዋ ጥንቃቄም ያስታውቃል። ምንም እንኳን አንዳንድ ቦታ ላይ ያላስፈላጊ ዘዬ ቢገባም ገጸ ባህሪያቱን የምትናገርበት ቋንቋ በትክክል የአካባቢው ቋንቋ ነው። ታሪኩንም በማጥናት ሳይሆን በመኖር እንደምታውቀው ያስታውቃል፤ በማጥናት ከሆነም በጣም የሚያስደንቅ ጥናት ነው። የሰሜን ሸዋ አካባቢ ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋን በቅርበት ስለማውቀው መጽሐፉን ሳነብ የማውቃቸው ሰዎች እውነተኛ ታሪክ እየመጣ ድቅን ይልብኝ ነበር።
የታሪክ፣ የባህልና ትውፊት ባለቤት የገጠሩ ማህበረሰብ ነው ቢባልም ማንም የጻፈለት ግን የለም። አሁን ላይ እናትና ልጅ የማይግባቡበት ቋንቋና ባህል እየተፈጠረ ነው። ከዩኒቨርሲቲ የሚመጡ ተማሪዎች ከወላጆቻቸው ጋር የማይግባቡበት ደረጃ ላይ እየደረሱ ነው። በእንዲህ አይነት ሁኔታ የገጠሩን ባህልና ትውፊት እንዲህ ጠንቆቆ መጻፍ ከጥበብ ትውፊቱ
ባሻገር የዜግነት ግዴታንም እንደመወጣት የሚቆጠር ነው። አንዳንድ ቃላት እና ባህሎች ‹‹እንዲህም ይባላል እንዴ!›› እስከምንል ድረስ የተረሱ ሆነዋል፤ የቆረኑ ጉዞ እነዚህን ቃላት እና ባህላዊ ድርጊቶች ያስታውሱናል።
የታሪኩ መቼት ራሳ በምትባል በሰሜን ሸዋ እና አፋር አዋሳኝ ላይ በምትገኝ አካባቢ ማህበረሰብ ላይ ነው። ዋና ታሪኩም በራሳ እና በአፋር ማህበረሰብ መካከል ያለውን ፍቅርና ግጭት የሚገልጽ ነው። እነዚህ የተሳሰሩ ማህበረሰቦች በግጦሽ ሳርና በመሳሰሉት የተነሳ ለግጭት ይዳረጉ እንደነበር ፤ በአንፃሩ ደግሞ አንደኛው ከአንደኛው ጋር የተሳሰሩና የተፋቀሩ እንደሆኑ መጽሃፉ በውብ ቃላት ይተርክልናል።
በመጽሐፉ ውስጥ አንድ ያደነቅኩት ነገር አለ።ይሄውም ደራሲዋ ያየችውንና ያጋጠማትን በትክክል መጻፏ ነው። ይሄን ለማለት ያስደፈረኝ የአገራችን የፖለቲካ ባህሪ እና ወቅታዊ ሁኔታ ነው።የአገራችንን የብሽሽቅና የብሄር ፖለቲካ በመፍራት ብዙዎች ለማቻቻል ሲሉ እውነታውን ይደብቃሉ። ለምሳሌ በፖለቲከኞች ቢሆን ኖሮ የአፋርና አማራ ማህበረሰብ ተጋጭቶ የማያውቅ፣ ሁሌም ፍቅር ብቻ እንደሆነ ተደርጎ ይጻፍ ነበር። ወይም በተቃራኒው ሁሌም ግጭት ብቻ፤ ግጭቱም ብሄርን መሰረት ያደረገ ተደርጎ ይጻፍ ነበር። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የምንረዳው ግን ግጭቱ ልማዳዊ መሆኑን ነው።
ነገሩን ግልጽ ለማድረግ አንድ እውነተኛ ገጠመኝ ላስታውሳችሁ።
እንደሚታወቀው ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በአገራችን ህዝባዊ አመጽ ተቀጣጥሎ ነበር። በወቅቱም ‹‹ኦሮማራ›› የሚባል የኦሮሞና የአማራ ወዳጅነት የየሚዲያውና የየመድረኩ ማድመቂያ ሆኖ ነበር። አገሪቱ በዚህ የኦሮማራ አጀንዳ ውስጥ እያለች 2009 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል አንድ አካባቢ (ለጊዜው ቦታውን ዘነጋሁት) ሁለት ሰዎች ተጣልተው አንደኛው ሌላኛውን በጥይት ይገድለዋል። ሟችና ገዳይ አንደኛው ኦሮሞ አንደኛው አማራ ናቸው። ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ወዲያውኑ የብሄር መልክ አስይዘው ነገሩን አጯጯሁት።የወቅቱ የኦሮሚያ
ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ የነበሩት አቶ አዲሱ አረጋ ነገሩን አብራርተው በፌስቡክ ገጻቸው ጻፉ።
በጽሑፋቸው ማብራሪያ ሁለቱ ሰዎች የረጅም ጊዜ ወዳጆች ነበሩ። ሁለቱም ማን የማን ብሄር እንደሆነ አያውቁም። ያፋቀራቸው የሥራ እና የህይወት ግንኙነት ብቻ ነው። በዚህ የወዳጅነት ቆይታቸው አንደኛው ከሌላኛው ብር ይበደራል። በተባለው ጊዜ ባለመመለሱና ብዙ በመዘግየቱ ወደ አለመግባባት ይሄዳሉ። ያ አለመግባባት ወደ ቅጽበታዊ እልህ መጋባት ሄዶ ለመገዳደል አበቃቸው።
እንግዲህ ልብ በሉ! ጎጃም ውስጥ ወይም ጎንደር ውስጥ አማራና አማራ ሲጣላ፤ሲገዳደል ነው የሚውለው፤ ወለጋ ውስጥ ወይም አምቦ ውስጥ ኦሮሞና ኦሮሞ ሲጣላና ሲገዳደል ነው የኖረው። ሌላ አንድ ልብ ማለት ያለብን ነገር አለ።
በገጠር አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦች መሰረታቸው ብሄር ሳይሆን ጎሳ ወይም አካባቢ ነው። ለምሳሌ ሰሜን ሸዋ ውስጥ መርሃቤቴና መራኛ ሊጣሉ ይችላሉ። ጎንደር ውስጥ ደባርቅ እና ዳባት ሊጣሉ ይችላሉ።ኦሮሚያ ውስጥ አምቦ እና ወለጋ ሊጣሉ ይችላሉ። ከአንድ አካባቢ እንኳን የእነ እገሌ መንደር የእነ እገሌ መንደር ተባብሎ መቧደኑ በገሃድ ያለሃቅ ነው።
የወይንሸት መጽሐፍ በርካታ አዳዲስ ጉዳዮችን ይነግረናል። ኢትዮጵያዊነት ከብሄር አልፎ አፍሪካዊ ጠርዝ እንዳለውም ያሳየናል። አንድ ሰው መጤ የሚባለው በብሄሩ አይደለም።ለምሳሌ ሰሜን ሸዋ አማራ ነው፤ በራሳ በኩል ከአፋር ጋር ይዋሰናል። ለእነዚህ አማራዎች ከአፋር ከመጣው ይልቅ ከጎንደር የመጣ ሰው መጤ ሊባል ይችላል። በብሄር ቢያስቡ ግን የሚቀርባቸው ከጎንደር የመጣው አማራ ነበር። የእነርሱ መለኪያ ብሄር ሳይሆን ቅርበት ነው።የስነልቦና ቅርበት፣የባህል፣የጉርብትና ቅርበት ዋነኛው መለኪያ እንጂ በስመ ብሄር ሩቅ ያለውን የእኔ ብሎ በልዩ አይን አይመለከተውም።አሁን ወደ ወይንሸት መጽሐፍ እንመለስ።
መጽሐፉን ስታነቡ የገጸ ባህሪያቱ ምልልስ ልክ ገጠር መንደር ውስጥ እንዳላችሁ ይሰማችኋል። የሚጠቀሟቸው ቃላት፣ የአካባቢያቸው ዘየ፣ የኑሮ ሁኔታቸው፣ ስነ ልቦናቸው ሁሉ በአይን የሚታይ መስሎ ተጽፏል።ደራሲዋ ሴት ናት። የወንዶችን ውሎ እና የወንዶችን ተፈጥሯዊ ስነ ልቦና በሚገባ ተረድታዋለች።
አንድ ያልተዋጠልኝ ነገር ግን አለ።አቶ ተፈራ በአካባቢው አለሁ አለሁ የሚል እና የሚፈራ ሰው ነው። ሚስቱ ግን ከብዙ ወንዶች ጋር ትወሰልታለች። በጣም ስለሚወዳት አይናገራትም።አቶ ተፈራ የሚፈራ ሰው ከሆነ ደፍሮ የእሱን ሚስት የሚያወሰልት አይኖርም። እንዲያውም የሚፈራ መሆኑ አንዱ ማሳያ የአቶ ተፈራ አይነት ሰዎች እንኳን ሚስታቸው ከብቶቻቸውን እንኳን ደፍሮ የሚነካ የለም። ደራሲዋ በአካባቢው የምታውቀው እውነተኛ ታሪክ ኖሮ ከሆነም እንዲህ አይነት ታሪክም አለ ማለት ነው። ከፈረንሳዊው አመጸኛ ናፖሊዮንና ከሚያፈቅራት ጆሴፊን ጋር የተነጻጸረበት መንገድ ግን የወይዘሮ ባንቺይርጋ እና የጆሴፊን ስነ ልቦና በጣም ይለያያል። ጆሴፊን ለዝና ነው የተጠቀመችው።
መጽሐፉ ራሱን ችሎ ፎክሎር ነው።የጠፉ ቃላት እና የተረሱ ባህላዊ ድርጊቶች ሁሉ ይገኙበታል። ለዚያውም ከነማብራሪያቸው። ለባህልም ለቋንቋም አጥኚዎች ብዙ ነገር ይገኝበታል። ኦሮምኛ ከአማርኛ፣ አማርኛ ከአፋርኛ ያላቸውን ውህደት ያሳያል። በባዕድ አምልኮ ወቅት የነበሩ ድርጊቶች ይብራሩበታል። የሽምግልና ክብር እና የማግባባት አቅም ተገልጾበታል።
መጽሐፉን በወፍ በረር ነው ያስተዋወቅናችሁ። ብዙ ነገሮች ስለሚገኙበት ሌላ ጊዜ ገጽ በገጽ እናየዋለን። እንዲህ አይነት መጽሐፎች ግን ይለመዱ። የነገ የታሪክ ምስክር የሚሆኑ በእንዲህ አይነት አገር በቀል ባህል እና በአገር በቀል ቋንቋ የተጻፉ ናቸው። በመዝገበ ቃላት ውስጥ ብቻ የሚገኙ ቃላት እንዲህ ወጣ ብለው በመጽሐፍ መልክ መገኘታቸው የራስን ቋንቋ ማበልጸግ ነው።በተረፈ ቀሪውን ከመጽሃፉ ታገኛላችሁና እንድታነቡት እንጋብዛለን።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2012
ዋለልኝ አየለ