አቶ አገኘሁ አዳነ የተወለዱት ጎንደር ከተማ ነው። አባታቸው ጦር ሰራዊት ስለነበሩና በስራ ጠባያቸው ምክንያት የተለየያ የአገሪቱ ክፍል ተዘዋውረው ለማደግ ተገደዋል። አንደኛ ደረጃ እስክ ሶስተኛ ክፍል ጎንደር ፋሲለደስ ትምህርት ቤት ተከታተሉ። ይሁንና አባታቸው በተለያዩ የጦርነት አውዶች ላይ ተካፍለው ስለነበር ለአገር በሰሩት ውለታ ለትምህርት እድል ለልጆቻቸው ሲሰጥ አቶ አገኘሁም ዝዋይ አካባቢ ይገኝ በነበረው ህፃናት አምባ ገብተው ከአራተኛ እስከ 12ኛ ክፍል የመማር እድሉን አገኙ። ትምህርት ቤቱ መሰረታዊ ግብዓቶች የተሟሉለትና ዘመናዊ ትምህርት የሚሰጥ የነበረ ከመሆኑም ባሻገር ተማሪዎቹ ከትምህርትቻው ጎን ለጎን እንደዝንባሊያቸው ታይቶ በኪነጥብና በስነ ስዕል፤ እርሻና ሌሎች ስራዎችንም እንዲሰለጥኑ ይደረግ ነበር። የዛሬው የባህረ ኪን እንግዳችን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር በሚገኘው የስዕል ትምህርት ቤት ገብተው በስነ ጥበብ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በተጨማሪም በስነ ፅሁፍ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል። እንዲሁም በስፔን በዘመናዊ ስነጥበብ ትምህርት ተምረዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በስነፅሁፍ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በመስራት ላይ ይገኛሉ።
መከላከያ ኢንጅነሪንግ ውስጥ ኢንዱስትሪያል ዲዛይነር ሆነው ለሁለት አመት ያገለገሉት እኚሁ ሰው ታዲያ በፀረ ሙስና ኮምሽን የትምህርትና የህዝብ ግኑኝነት አማካሪ ሆነው ለስምንት አመት ሰርተዋል። በነበራቸው የትምህርት ውጤት የተነሳ ላለፉት አስር አመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ጥበብ ትምህርት ቤት ውስጥ በመምህርነት፤ እንዲሁም ካለፉት አራት ዓመታት ደግሞ በትምህርት ቤቱ ዳይሬክተርነት እያገለገሉ ይገኛሉ። የስነጥበብ ትምህርት ቤቱ የእድሜውን ያህል ለአገር ግንባታ አወንታዊ ሚና ይጫወት ዘንድ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በተለይም ካለፈው አንድ አመት ወዲህ በመንግስት በተሰጠው ልዩ ትኩረት ተቋሙን ለአይን የሚስብ ውብና ማራኪ ከማድረግ ባሻገር ተማሪዎቹ በተሟላ መልኩ የሚመሩበትን ህንፃዎችን የማደራጀት ስራ እንዲሰራ ተደርጓል። በዚህና በሌሎችም ስነጥበባዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአቶ አገኘሁ አዳነ ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- የስነጥበብ ትምህርት ቤቱን ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ቢያብራሩልን?
አቶ አገኘሁ፡- እንደሚታወቀው ተቋም የሚመራው በቅብብሎሽ ነው። ይህ ተቋም በዚህ መጠንና ስፋት አገልግሎት እንዲሰጥ የተለዩ ሰዎች በተለያየ ዘመን የራሳቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል። ከመስራቹ አቶ አለፈለገ ሠላም ጀምሮ በየዘመኑ የነበሩ መምህራንና ሰራተኞች ብዙ ሰርተዋል። እኔ ከመጣሁ በኋላም በተቻለ መጠን የድርጅቱን ሰራተኞች አደረጃጀት ማስተካከል ስራ አከናውነናል። በተለይም የሰራተኛውን አቅም ማሳደግና የትምህርት ደረጃቸው እንዲሻሻል ማድረግ ላይ ነው ትኩረት አድርገን ስንሰራ ቆይተናል። ምክንያቱም ተቋም ሆኖ በጥንካሬ እንዲቀጥል ከተፈለገ በውስጡ ያሉት ሰዎች ብቁና ጠንካራ መሆን ይጠበቅባቸዋልና ነው። በዚህ ረገድ ጥሩ ውጤት ያገኘን ይመስለኛል።
ሌላው የትምህርት ቤቱን መሰረተ ልማት የማሳደግ ያደረግነው ጥረት ውጤታማ ነው ማለት ይቻላል። ለትምህርት የተመቸና ለጉብኝት የሚያመች እንዲሆን ተደርጓል። አንዳንድ በትምህርት ዘርፉ ከዚህ በፊት ያልነበሩ የመማሪያ ክፍሎችንም ገንብተናል። በነገራችን ላይ ከዚህ ቀደም የጌጣጌጥ ዲዛይን ትምህርት አልነበረም። በቅርቡ ግን የጌጣ ጌጥና ዲዛይን ስቱዲዮ ከኦስትሪያ አንድ ድርጅት ጋር በመተባበር ለመገንባት ችለናል። አኒሜሽን የሚባለውን የፊልም ቴክኖሎጂ ከስፔን ኤጀንሲ ጋር በመሆን መለስተኛ ስቱዲዮ ገንብተናል። የፊልም ፕሮዳክሽን ክፍል በማስተርስ ደረጃ የሚያስተምር ክፍል ቢኖርም ምንም ያልነበረውና በባዶ ነበር የሚሰራው። ይህ ክፍል ለሀገሪቱ የፊልም ዕድገት አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት በሂደት እያደገ ይሄዳል የሚል ተስፋ ተደርጎ የተጀመረ ነው። ከተጀመረ በኋላ ግን የሌሎች አገሮች ድጋፍ እንደጠበቅነው አልሆነም። እሱን ስቲዲዮ የመመስረትና የተደራጀ ሆኖ ተማሪዎቹ ለተግባር እንዲማሩ ለማስቻል ሙከራ አድርገናል። ስቱዲዮውን ገንብተናል፤ ግን በቂ አይደለም፤ ብዙ ስራ ይፈልጋል። ምክንያቱም የፊልም ግብዓቶች ምንያህል ውድ እንደሆነ ይታወቃል።
የእኔ ዋነኛ አላማ ከምዕራብ አገር አቻ የስራ ተቋማት ጋር ከሚደረገው ግንኙነት ይልቅ የአገሪቱ ፖሊስ አውጪ ትኩረት እንዲሰጥ ማስቻል ነው። ለምሳሌ ያህል ብትወስጂ ብዙዎች ይህንን ተቋም አያውቁትም። ይህ ትክክል አይደለም። ይህ ተቋም በህዝብ ገንዘብ የሚተዳደር የህዝብ ትምህርት ቤት ነው። ከአፍሪካ አንጋፋ የስነጥበብ ትምህርት ቤት እንዳለው የአገሪቱ ህዝብ ማወቅ አለበት። ግንዛቤው እንዲያድግ በዚህ ደረጃ የስነጥበብ ትምህርት እንደሚሰጥ ህዝቡም ሆነ ፖሊሲ አውጪዎች ሊያውቁ ይገባል። ይህንን ለማስቻል የተለያዩ የማስተዋወቅ ስራዎች መስራት ይጠበቅብናል። እንዳልኩሽ በተለይ ፖሊሲ አውጪዎች ትኩረት እንዲሰጡት ለማስቻል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ሌሎችም በተለያየ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥረት ተደርጓል። በተወሰነ ደረጃ የተሳካ ይመስለኛል። ግን ወደፊት የበለጠ ስራ መስራት ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አኳያ ታዲያ ከእናንተ ጥረት ባሻገር በመንግስት በኩል በቂ ትኩረት እየተሰጠው ነው ማለት ይቻላል?
አቶ አገኘሁ፡- ከዚህ አንፃር በተለይም እኔ ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ የመንግስት ሃላፊዎች ተቋማችንን እንዲጎበኙና ስላሉበት ችግርና በውስጡ ስላለው እምቅ አቅም ዙሪያ ውይይት አደርጋለሁ። ደግሞም ያለሁትም ይህንን ለመስራት ነው። በዚህ ጥረት ውስጥ ዶክተር አብይን በተለያየ የስራ አጋጣሚ የማግኘት እድል ነበረኝና ያንን አጋጣሚ ተጠቅሜ በጣም እድሜ ጠገብና በቀኝ ገዢዎች ያልተመሰረተ የስነጥበብ ትምህርት ቤት ስለመሆኑ አብራራሁላቸው። በውስጡ ስላለው እምቅ አቅምም አስረዳኋቸው። በዚህ አጋጣሚም ዶክተር አብይ እንዲመጡና እንዲጎበኙ ጠየኳቸው። እኔ እንደማንኛውም ሰው ነው የጋበዝኳዋቸው። በነገራችን ላይ እኔ እንደአጋጣሚ ከኮረኔል መንግስቱ ጀምሮ በርካታ መሪዎችን የማየት እድሉ አጋጥሞኝ ነበር። እንደ ዶክተር አብይ አይነት ለሰብአዊነት የቀረበ ሰው ግን አላጋጠመኝም።
በእውነትም ሲመጡ በጣም በስነምግባር የታነፁ ሰው መሆናቸው ለማስተዋል ችያለሁ። እኔ በሄድኩባቸው ቦታዎች ሁሉ ስለእሳቸው የምመሰክርላቸው ለምን መሰለሽ? ይህ ተቋም ትልቅ እንደመሆኑ ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጋር ተነጋግሬ በተቋሙ ማህተም በደብዳቤ ብጠይቃቸው ብዙም አይገርመኝም ነበር። ምክንያቱም ስራቸው ነው። እንዲመጡ ስጠይቃቸውም ማንም አልሰማንም፤ «እመጣለሁ» ሲሉኝም ሌላ ምስክር የለም። ከዚያ በኋላ ቃል ከገቡልኝ አንድ ወር ያህል ጊዜ ነው የፈጀባቸው። ለእኔ ለብቻዬ የገቡልኝ ቃል መጡና አከበሩ። ባለፈው አመት ግንቦት መጀመሪያ ላይ ነው የመጡት። በመጡበት እለት ትላልቅ ከሙዚቃ ትምህርት ቤት ቫዮሊን ተጫዋቾችን አመጣሁ፤ የምጠራቸው ሰዎች ግን ማን እንደሚመጣ አያውቁም ነበር። ዝም ብዬ ጥቁር እንግዳ አለብኝ ነበር ያልኳቸው። በዚያ መሰረት ጥቂት እንግዶችን ብቻ ጋበዝን። ዶክተር አብይም የስዕል ኤግዚቪሽን፤ የተማሪዎች መማሪያ ክፍሎችን ተመልክተው አጠቃላይ ጊቢውን በጣም ወደዱት። ሙዚቃ ተጫዎቹ ጥሩ መዚቃ ተጫወቱ፤ በቀለ መኮንን «ቼ በለው» የሚል የቆየና በጣም ግሩም የሆነ ግጥሙን አቀረበላቸው።
ከጉብኝቱ በኋላ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግር ማውራት እንደማልፈልግ ነገር ግን እኛ ለመንግስት ልንሰጠው ስልምንችለው ድጋፍ ለማውራት ቀጠሮ እንዲይዙልን ስጠይቃቸው፤ «ብትነግረኝ ከማየው በላይ ምን ትነግረኛለህ? ሁሉንም ችግር አየሁት እኮ» አሉኝ። ስለዚህ ምንም ሳልናገር ግቤን መታሁ። በነገራችን ላይ ይህንን ተቋም መሪ ሲጎበኘሁ ከአፄ ሃይለስላሴ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ይህም ለሁላችንም ትልቅ ደስታ ፈጥሮልን አልፏል። በተለይ እኔ ደስታው ሊለቀኝ ስላልቻለና ልቤ ስለተነካ ዝግጁቱ ካለቀም በኋላ እዚሁ ነበር የቆየሁት። እንደምታውቂው መሪዎቹ ሁልጊዜ የሚታመኑትም ሆነ የሚተቹት በቃላቸው ምክንያት ነው። ዶክተር አብይ ያደረጉት ነገር ቃላቸውን የሚያከብሩ መሆናቸውን ከመረዳት ባሻገር ለህይወቴ የሚቀር ትምህርት ሰጥተውኛል።
በእኔ እምነት እኚህ ሰው ቶሎ የቦታውን አቅም መረዳት የቻሉት ጥበባዊ ስስ ልብ ስላላቸው ነው። በተጨማሪም ዩኒቲ ፓርክ፥ ሸገር ፕሮጀክትና እንጦጦ ፓርክን ስትመለከቺ ከእይታዊ ጥበብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲሁም ለባህል ዘርፉ ላይ ልዩ ምልከታ እንዳላቸውና የዘርፉ አስፈላጊነት በሚገባ እንደገባቸው ሳይደውሉልኝ ወደ ከሰዓት አካባቢ ተመልሰው መጡ። ሲመጡ ታዲያ ብቻቸውን አልነበረም። ቀያሾችንና አትክልተኞችን ከነመሳሪያቸው ይዘው እንጂ። በእለቱ እንዳልኩሽ ደስታ ስላሰከረኝ ቶሎ አልሄድኩም ነበርና ሲያዩን በጣም ተገረሙ። እናም ከዚያ ቀን ጀምሮ የአትክልት ስፍራው እንዲሰራ ተደረገ። አሁን ያለው አስገራሚና ውብ ገፅታ እንዲኖረው ከፍተኛ ጥረት አደረጉ።
በሌላ በኩል ዩኒቲ ፓርክ በሚሰራበት ጊዜ የእኛ ተማሪዎች አብዛኛውን የስነጥበብ ስራ እንዲሰሩ መደረጉ ለዘርፉ መነቃቀትና መጎልበት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል ባይ ነኝ። ዶክተር አብይ በዩኒቲ ፓርክ ስራ ተማሪዎቹ ባስገኙት ውጤት የገንዘብና የመኪና ሽልማት ሰጥተዋቸዋል፤ አሁን እነዚያ ተማሪዎች ተደራጅተው ንግድ ፈቃድ አውጥተው መስራት ጀምረዋል። ይህም ለዘርፉ ትኩረት መሰጠቱን ማሳያ ነው። ሌላው እንጦጦ ፓርክ ውስጥ የመጀመሪያው የህዝብ ኤግዚቢሽን እንዲከፈት ተደርጓል። ስዕል የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርስ አካልና ባህል ነው። ሆኖም በቅርብ የተፈጠሩት የኪነጥበብ ዘርፎች ናቸው ትኩረት ሲሰጣቸው የቆየው።
የስነ ጥበብ ዘርፉ ያለውን እምቅ አቅምና ለአገር እድገት ሊያበረክት የሚችለውን አስተዋፅኦ ለፖሊሲ አውጪዎችም እኛ ካላሳወቅናቸው ሊረዱት አይችሉም። ለዚህ ነው በኃላፊነት ዘመኔ ዘርፉ ለሰብአዊ ልማት ያለውን አስፈላጊነት ማስገንዘብ ላይ ትኩረት አድርጌ እየሰራሁ ያለሁት። የሰው ልጅ የሥነጥበብ ዋጋ የሚገባው የስነጥበብ ትምህርት በለጋ እድሜው ጀምሮ ሲማር ነው። በስነጥበብ ያልታነፀ ትውልድ ውይይት አያውቅም። መከባበር፥ አንድነትና ልዩነት ምን እንደሆነ አያውቅም። ስለዚህ የስነጥበብብ ትምህርት በስርዕተ ትምህርታችን ውስጥ በየደረጃው እያደገ የሚሄድ ሆኖ መቀረፅ አለበት። አሁን የምናየው ነውጥ ትልቁ ምክንያት በውሸት ትርክት መገንባቱ ብቻ አይደለም ሰብአዊ ዋጋ እንዲያውቁ የሚያደርግ የስርዓተ ትምህርት ባለመኖሩ ነው።
ለዚህ አንድ ምሳሌ ልስጥሽ፤ የፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ 106 ነጥብ 2 ስኬር ሜትር ነው የቆዳ ስፋቷ። በከተማዋ ውስጥ ባለው የሴን የሚባል ትልቅ ወንዝን ተከትሎ ዋና ዋና የሚባሉ 200 የስዕል ዓውደ ርዕዮች (ጋለሪዎች) አሉ። ይህም በግለሰቦች የተከፈቱ አነስተኛ አውደርዕዮችን ሳይጨምር ማለት ነው። ፈረንሳይ ትልቁ የአመት ገቢዋ ከዚህ ዘርፍ የሚገኝ ነው። የአለም ህዝብ በየጊዜው የሚጎርፈው ይህንን የስነስዕል ጥበብ ለማየት ነው። በተጨማሪም ትላልቅ የአደባባይ ላይ ቅርፆች ከአንድ ሺ በላይ አላት።አዲስ አበባ በስፋቷ ከፓርሲ በአምስት እጥፍ ትበልጣለች። ይሁንና አንድ የህዝብ የስዕል አውደርዕይ የለም። በግለሰቦች የተገነቡ ብቻ ናቸው ያሉት። እነሱም በብዙ ውጣውረድ ነው የሚንቀሳቀሱት። ዶክተር አብይ ከመጡ በኋላ ከብዙ አመት በኋላ የመጀመሪያውን የህዝብ የስነስዕል አውደርዕይት እንጦጦ ላይ እንዲገነባ አደረጉ።አሁን ላይ ይህ ዘርፍ የመንግስት ጉዳይ ሆኗል ማለት ይቻላል። በአንድ ጊዜ ሁሉንም ነገር መለወጥ ስለማይቻል በሂደት ዘርፉ ለአገር ያለውን ፋይዳ እያስተዋወቅን ከሰራን የተሻለ ለውጥ ይመጣል ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በአጠቃላይ የኪነጥበብ ዘርፉ ህዝብን ለተለያዩ አላማዋች ለመቀስቀስ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ይታወቃል፤ አሁን ላይ ካለው አገራዊ የፖለቲካ ችግር አንፃር ትውልዱ የሰላም መንገድ እንዲከተል ከማድረግ አኳያ ከዘርፉ ምን ይጠበቃል ይላሉ?
አቶ አገኘሁ፡- በጣም መሰረታዊና ወሳኝ ጉዳይ ነው ያነሳሽው። ኪነጥበብ ለሰላምም ሆነ ለአገር ግንባታ ትልቅ ፋይዳ ነው ያለው። የሰው ልጅ በተፈጥሮ የሚናገር፤ የሚያስብ፥ የሚሰማ፤ የሚያይ ፍጥረት ነው። የሚያይ ከሆነ በዘመናዊ ሳይንስ የታገዘ እይታዊ ጥበብ ልምምድ ያስፈልገዋል። ምክንያቱም የሰው ልጅ እንደተወለደ ሁሉንም ነገር ማየት አይችልም፤ ልምምድ ካደረገ በኋላ ነው አይኑ የሚሰለጥነው። በስነጥበብ የተቃኘና የሰለጠነ አይን የሚያየውን ነገር እንዴት እንደሚያስተዳድር ያውቃል። እይታዊ ባህሉ ከፍ ያለ ይሆናል። ልክ እንደዛፍ ተንጋዶ (ተንሸዋሮ) ያደገ አይን ካደገ በኋላ አይመለስም። ስለዚህ የሰው ልጅ ሲፈጠር እይታዊ ጥበብ ማዋጣት አለበት። የሰው ልጅ እዝን ((ጆሮ) አለው፤ ይሰማል። ድምፅ ማስተዳደር ልምድ ባደረገ ቁጥር ጆሮው የሰለጠነ ዜጋ ይፈጠራል ማለት ነው። የትውልዱ መልካም ስብእና ሲሰራ እነዚህ መሰረታዊ የስሜት ህዋሶቻቸው በዚህ መንገድ መሰልጠን አለባቸው ማለት ነው። ስነፅሁፍ፤ ነባቢ ነው፤ ይተረክለታል። የሰው ልጅ ቋንቋን እያወቀ በመጣ ቁጥር ራሱን መግለፅ ይማራል። ይህ ግን አስቀድሜ እንዳልኩሽ ከታች ገና ማቆጥቆጥ ሲጀምር ነው መሰራት የሚገባው።
ስለዚህ በዚህ ሁኔታ ያልታነፀ ማህበረሰብ ይፈጠርና ግትርና ስርዓት አልበኛ ይሆናል። ያልሰለጠነ አይን ስላላቸው የሚያስቀይምና የሚያስደስት አይለዩም። አሁን ላይ በየአካባቢው ሁከት የምንሰማው በአግባቡ ያልታነፀ ማህበረሰብ ስላልተፈጠረ ነው። የትኛው የነገረ ኪን ፍልስፍና ሰው በእህል ብቻ እንደማይኖር ያስረዳናል። የሰው ልጅ እህል የማይሞላው ሰብአዊ ጠባይ አለው። ያ እህል የማይሞላው ሰብአዊ ጠባይ የሚሞላው በኪነ ጥበባት ነው። ያ ሰብአዊ ጠባይ ካልተሞላ ሁከት ይፈጠራል። ለሁሉም ነገር «ሆ» የሚልና ምክንያታዊ ያልሆነ ትውልድ ይፈጠራል። ሰው ለመግደል የማይሳሳ ልቦና ይኖረዋል። የስሜት ህዋሳቶቼ ከሰለጠኑ ግን እኔ የአንቺን ዋጋ አውቃለሁ። ምክንያቱም የሰው ዋጋ ሊከፈል የማይችል ነው። ስነጥበብ ይህንን አስተሳሰብ ለመቅረፅ ያስችላል። ስነጥበብ የተማረ ሰው ውይይትን ያውቃል።
ለምሳሌ ህፃናት ስዕል ለመሳል ሲቸከችኩ፤ ሲያጠፉ ሂስ እየተለማመዱ እኮ ነው። ውይይት በተግባር እየተማሩ ነው። በስእል ውስጥ ደግሞ በጣም ብዙ ቴክኒካል ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ ሚዛንን፥ እኩል ማካፈልን ይማራል። ምክንያታዊነትን ያውቃል። አንድ ሰው ከቀለም፥ ከጭቃ፥ ከድንጋይ ከእንጨት ጋር ሲጫወት ሃሳብ ማስተዳደርን ይማራል። በአንድነት ውስጥ ልዩነትን ይረዳል። በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነትን ይገነዘባል። በአንድ ሰሌዳ ላይ የህዝብ አስተተዳደርን፥ ፍትህን፥ ፖለቲካዊ ድርድርን ይማራል። ለዚህ ነው ያደገው አለም ልጆችን ከህፃንነታቸው ጀምሮ በኪነጥበብና ስነ ጥበብ ታንፀው እንዲያድጉ የሚያደርጓቸው። እኛ ጋር ግን ሙዚቃ ማጫፈሪያ ነው፤ ስዕል የፕሮፖጋንዳ መሳሪያ ነው። በደርግ ጊዜ ኪነጥበብ ህዝብ መቀስቀሻ መሳሪያ ነበር። ኪነት ለአብዮቱ ተብሎ መቀስቀሻ መሳሪያ ነበር።
ኢህአዴግም ሲመጣ ኪነጥበብ ለልማት ማዋል ይገባል አለ፤ ዳቦ ካላመጣችሁ የራሳችሁ ጉዳይ አለና ያለውን ሰብአዊ ጠባይ ገድፎ የልማት ባሪያ አደረገው። እርግጥ ነው ጥበብ የገቢ ምንጭ ሊሆን ይችላል፤ አስቀድሜ የነገርኩሽ የፓርሲ ሁኔታ ይህንን የሚያሳይ ነው። ስነጥበብብ ለዳቦም አይሰንፍም፤ ነግርግን አንዱ ጠባዩ ነው። ግን አንድና ብቸኛ ጠባዩ አይደለም። በዳቦ የማይሞላ ሰብአዊ ጠባይ ስምምነት የሚደረግበት ነው። በዚህ ረገድ እኔ አፄ ኃይለስላሴን አልወቅስም። ምክንያቱም ለብዙዎቹ የትምህርት ተቋማት በእሳቸው የተመሰረቱ በመሆናቸው ነው። ዶክተር አብይም ተመሳሳይ ቁመና ያላቸው ሰው ናቸው። ስለዚህ ከዚህ በኋላ ዘርፉ በፖሊሲ አውጪው ልዩ ትኩረት ከተሰጠው በአገር እድገትም ሆነ ለሰላሙ ቀጣይነት የላቀ ሚና ይጫወታል የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ። አቶ አገኘሁ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም
ማህሌት አብዱል