ዓድዋን በሙዚቃ ጅረት

ዜማ እንደ ዥረት ወርዷል ካሉ እዚህ ዓድዋ ላይ ነው:: ግጥም ተገጣጥሞ ለታሪክ ድልድይ ተዘረጋበት ቢሉም እሱም እዚሁ መንደር ውስጥ ነው:: መንደሩም በታላቁ የዓድዋ ተራራ አናት ላይ ተንጣሎ፣ ሰማይ ጠቀስ የሙዚቃ ካስማ ተተክሎበታል:: በደመናው ለሚቀዝፈው ግዙፍ መርከብ፣ መልህቁን ተራራው አሳርፏል::

ዓድዋ የዓለም ሕዝብ ሁሉ ካለበት ሆኖ የሚመለከተው፣ የጥቁሮች ደማቅ የፀሐይ ብርሃን ነው:: የሐበሻ የኩራት ሜልኮን፣ የውበት ጥግ ጨረቃ ነው:: ዓድዋ ሲሠሩትም፣ ሲያወሩትም ለአፍ የሚጣፍጥ የድል ማር ወተት ነው::

ዓድዋ በጥበብ ያልተነሳበት፣ ሽቅብ ወጥተው ቁልቁል ያልተንደረደሩበት የለም:: ኪነ ጥበብ ፈርጠም ብሎ በግርማ ሞገሱ ጎልያድን የሚያስንቅ ሆኖ የሚታየው ከየትኛውም በላይ ዓድዋ ላይ ነው:: ራሱ ዓድዋም ቢሆን የዳዊትን ጠጠር አስወንጭፎ…ከኋላ ከፊት እልፎች ከበው በዝማሬ ሲያወድሱት፣ የታላቅነት ጥጉ የሚገለጠው በጥበብ ነው::

ጥበብ ጃኖውን አልብሳ፣ ካባውን ስትደርብለት ለማየት የማይጋፋ አንድም የለም:: የጀግንነት ጀብዱ፣ ክንደ ብርቱ የእሳት ነበልባል፣ ዘውዱን ጭኖ በንግሥና ሲንጎማለል ዓለም ሁሉ በርከክ ብሎ፣ ለክብሩ እጅ ይነሳል:: “ዓድዋ!” ሲባል እንኳንስ ላየው ስሙን ለሰማም ያስደነግጣል:: እናም ጥበብም ለዓድዋ ትዘምራለች:: በሙዚቃ ስንኝ አዋዳ “ዓድዋ ትናንት! ዓድዋ ዛሬ!” እያለች በብርሃን ጸዳል፣ ወደፊት ታዘግማለች:: ሁሉም ከፊት፣ ሁሉም ከኋላ እያጀበ ዓመት ዓመት ይዘክረዋል::

የዓድዋና ሙዚቃ ቁርኝት የተጀመረው ከድል አጥቢያው መልስ አይደለም:: ትውውቃቸው ከዚያው ከዓድዋ የጦር ሜዳና ጦርነት ይጀምራል:: እንደዛሬው ዘመናዊ የሚባሉ የሙዚቃ መሳሪያዎች ባይኖሩም፤ እነ መሰንቆ፣ በገናና ክራር ከአዝማሪው እጅ ላይ ነበሩ:: አዝማሪው ዘመናዊ የሚባል ሙዚቃ ባያውቅም፤ በባህላዊው የአዝማሪ ቅኝት፣ ጀግኖቹን ሲያጀግን ነበር::

በያዘው ክራርና መሰንቆ ጀግናን ከየመንደሩ ከማትመሙም፤ እስከ ጦር ግንባር ሄዶ በወኔ ቀስቃሽነት ሲያዋጋ ነበር:: የእያንዳንዱን የአርበኛ ልብ ውስጡን ሳይቀር የሚመለከቱ ነበሩና ግጥሞቻቸው ከአፍ እስኪወጡ በጉጉት የሚጠበቁና ከወጡም መሬት ጠብ የማይሉ ናቸው:: “አዝማሪ ምን አለ?” ሲባል የነበረውም እቅጯን በቅኔ ስለሚናገሯት ነው::

ብዙኃኑ አዝማሪን የሚንቅ የነበረ ቢሆንም፤ አዝማሪ ያለውን ግን እንደ እግዜር ቃል ያምንበታል:: በዓድዋ ጊዜ ስለነበረው ነገር በጉልህ ባይስተዋልም፤ በእንዲህ ያሉ ጦርነቶች መሃል የእረኞች ዋሽንት የዋዛ አይደለም:: እረኞች ሩቅ ለሩቅ ማዶ ለማዶ ሆነው፣ ያሉበትን ሁኔታና የአካባቢያቸውን ድባብ፣ በዋሽንት ዜማ የሚነጋገሩበት የራሳቸው የሆነ ቋንቋ ነበራቸው::

ሙዚቃን በዓድዋ ውስጥ ለመፈለግ ስንነሳ፤ የምናገኘው በሽለላ ውስጥ ነው:: ሽለላ፤ በትንሹ እስከ ሦስት የሚደርሱ የኪነ ጥበብ ቀለማትን ሰብስቦ የያዘ ነው:: በግጥምና ዜማው ሙዚቃ ነው ልንለው እንችላለን:: ወኔ በተሞላበት የሰውነት እንቅስቃሴውና በፊት ገጽታው(ፋሻል ኤክስፕሬሽን) ደግሞ ተውኔትን ያስመስለዋል::

ጥልቅ የሆነ የግጥምና የቅኔ ችሎታንም የሚጠይቅ ነው:: እንደ ሽለላ ባይሆንም በቀረርቶና ፉከራ ውስጥም ተመሳሳይ ነገሮችን እናገኛለን:: ሙዚቃ በብዙ አቅጣጫ፣ የዓድዋ ድምቀትና ወኔ ነበር:: ከአዝማሪዎቹ በመለስም ሆነ ጎን ለጎን፤ ዛሬም ድረስ አይረሴ ሆነው የዘለቁ ሙዚቃና ሙዚቀኞች ደግሞ አሉ:: ለአብነትም፤ ባለ ክራሩ ካሳ ተሰማ አንደኛው ነው:: ክራሩን ከደረቱ ላይ ሰቅሎ፣ በውብ የትዝታ ዜማ “ፋኖ ፋኖ…ኧረ! ፋኖ ፋኖ” እያለ በዓድዋ መንፈስ ውስጥ በስሜት ይንጠናል::

የዚህ ሙዚቃ ግጥምና ዜማ ያልገባበትና ያልተነካካበት የለም:: ራሱን እየደጋገሙም የተጫወቱት በርካቶች ናቸው:: በአሁኑ ጊዜ በሰፊው የሚደመጡት የጂጂ “ዓድዋ” እና የቴዲ “ጥቁር ሰው” በእድሜ የቅርብ እንደመሆናቸው፣ ቀደም ባሉት ጊዜያቶች በዓድዋ ላይ እንደ “ፋኖ” የነገሠ አነበረም::

ሙዚቃ በዓድዋ ውስጥ ከአጽናፍ አጽናፍ ተንጣሎ የሚታይ ውቅያኖስ፣ ፈሶ የማያልቅ ዥረት ነው:: አርበኛ አያትና ቅድመ አያቶቻችን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከያሉበት ለአንድ ዓላማ፣ ወደ አንድ አቅጣጫ ተመዋል:: ሙስሊም ክርስቲያን፣ ብሔር ጎሳ ሳይል፣ ተሰባስቦ ዓድዋ ላይ ተገናኘ::

ሙዚቃም ከግጥምና የዜማ ቅኔዎች እስከ ልዩ ልዩ የሙዚቃ መሳሪያዎች፣ በአንድ አጣምሮና አዋህዶ ከአርበኛው ጋር ዓድዋ ላይ ተገናኘ:: አንዱ ከአንዱ ተግባብቶና ተዋዶ፣ በአንድነት መንፈስ ውስጥ ጣፋጭ ድልን መቀዳጀታቸው፤ የሙዚቃን ሙዚቃዊ ፍሰትን የመሰለ ነው::

ሙዚቃ በዓድዋ ዕድሜው ቢገፋም፣ ሙዚቃ በዓድዋ ዛሬ ውስጥም መልኩ የቆነጀ ነው:: እርጅናን የማያውቀው የዓድዋ ታሪክ፣ ከዘመናዊ የሙዚቃ ስልትና ምት ጋርም ለመጣጣም አልተቸገረም:: በዚህ ውስጥ ስለ ዓድዋ የተዜሙ እጅግ በርካታ የሙዚቃ ሥራዎችን እናገኛለን::

ይሁንና ለዛሬው ግን ቅኝታችንን በሁለቱ ላይ ብቻ እናድርግ… በዘመናዊው የዓድዋ ሙዚቃዎች ውስጥ ሁለት ወርቃማ መልኮች፣ ከብዙኃኑ ፊት ያንጸባርቃሉ:: በታሪክ፣ በግጥምና በዜማ ፍሰት አወቃቀራቸው ለየት ያሉ ስለመሆናቸው የሚመሰክር ብዙ ነው:: ዓድዋን ከነ ክብሩና ግርማ ሞገሱ በስድስትና ሰባት ደቂቃዎች ሙዚቃ ውስጥ መልኩን ለማየት መቻል የጥበብን ታላቅነት ያስመሰከረም ጭምር ነው::

ዓድዋ በመጣ ቁጥር ሁሉ የሁለቱ ከያኒያን ሥራዎች፣ የዓድዋን ሰማይ እንደ ፀሐይ ያበሩታል:: ልብን ብቻ ሳይሆን ምድርንም ያሞቁታል:: በዓድዋ ጀንበር እኚህን ሙዚቃዎች ማድመጥ፣ የኤርታሌን እሳተ ጎሞራ የሚያስንቅ የወኔ ትንታግ ውስጥን ፈንቅሎ ይወጣል::

በዚህ ታሪካዊ የድል መስኮት አሻግረው ወደ ሙዚቃ ማዶ ሲመለከቱ፤ እጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ) እና “ዓድዋ” የተሰኘው ሙዚቃዋ ይታያሉ:: በግጥምና በዜማ፣ በምስልና በውብ ድምጽዋ፣ ከሙዚቃ መሳሪያ አዋህደው ብቻ የተሠሩት አይመስልም:: አንዳችን የነብስና የመንፈስ የሆነ ነገር አለው:: ለመውጣት የማይዳፈሩት ግዙፍ ተራራ፣ በትንሽዬ የካሜራ ዓይን፣ በአንዲት ወረቀት ቁልጭ ብሎ እንደሚሰፍር ሁሉ፣ ዓድዋን ያህሉን እልፍ መጻሕፍት ተከፋፍለው የማይጨርሱትን ታሪክ ከነነብሱ መመልከት መቻል ያስደምማል::

ገና መግቢያው ላይ እንዲህ ነው የምትለው…

“ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን

ሰውን ሊያከብር

በደግነት በፍቅር፣ በክብር ተጠርቶ

በክብር ይሄዳል ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ”

እኚህ ስንኞች እንደዋዛ በጆሮ ብቻ የሚደመጡ አይደሉም:: “ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን” በዚህች ምድር ላይ የሰው ልጅ ለሰው ሊከፍል የሚችላቸው ብዙ ዓይነት መስዋዕትነቶች አሉ፤ እጅግ ልብን የሚነኩ የሚሰብሩ:: ከእነዚህም የመጨረሻው የመስዋዕትነት ጥግ ራስን ከመስጠት በላይ ያለውን ነብስ መስጠት ነው::

የጂጂ ሙዚቃ፣ የመጀመሪያው ስንኝም የሚናገረው ስለዚሁ መስዋዕትነት ነው:: ቀጥላ ደግሞ፤ ይህ እንዴትና በምን ምክንያት እንደሆነ ትነግረናለች:: “በደግነት በፍቅር…” በቃ ሌላ ምንም አይደለም:: ይህን ሲያደርጉ ከእኛ ምስጋናና ክብር ሽተው አሊያም ከፈጣሪያቸው ዘንድ ጽድቅን ለማግኘት አይደለም:: ለዚህ ያህሉ ከባድ ውሳኔ ምክንያታቸው ደግነትና ፍቅር ብቻ ነው::

ምን ዓይነቱ ታላቅነት፣ እንደምን ያለው ልብ ነው የእኛ አባቶች የነበራቸው? ምን ያህል ደግ፣ የቱንም ያህል የዋህ ቢሆን፤ ሰው ለሰው ያለውን ይሰጣል እንጂ እንዴትስ አንድ ያለችውን ነብሱን ይሰጣል…”…በክብር ተጠርቶ በክብር ይሄዳል” ያ ሁሉ ወደ ዓድዋ ሲተምና በችኮላ ሲገሰግስ የነበረ ሕዝብ ነጭ በነጭ ለብሶ ሲታይ ለሠርግ እንጂ ለጦርነት አይመስልም ነበር::

ሲያስብ የነበረው ሞትን ቢሆን ኖሮ እንዲያ አምሮና ደምቆ ባልታየ ነበር:: ነገሩ ለዓይንም ለልብም የሚከብድ ነገር ነው:: በተደረገለት ንጉሣዊ ጥሪ እጅግ ደስተኛ ነበር:: ሞትን ፊት ለፊቱ እየተመለከተው ግን ግድ አልሰጠውም:: የተጠራው በክብር ለክብር ነውና ገድሉም ይህ እንዲሆን ነው የሚሻው:: በዚህ ገድል ውስጥ አንድ ነብሱን ሰጥቶ እልፎችን በማኖር፣ በእነርሱ ህይወት ውስጥ መኖር ነበር አላማው::

ጂጂ የአርበኞቹን ገድል እንዲያ ከተረከችው በኋላ፤ ትውልድ ከፍሎ የማይጨርሰው እዳና ውለታ እንዳለብን ታስረግጥልናለች:: ያገኘነው በነጻ ቢሆንም፤ የመጣው ግን ከመስዋዕትነት በላይ አልፎ ነው::

“የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነጻነት

ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት”

በነጻነት እንድንኖር የተከፈለው ዶላርና ፍራንክ፣ ሺልንግ አሊያም ብር አይደለም:: አርበኛው ያለውን እርስትና ሀብት ሁሉ ሰጥቶ ወደ ድህነት አይደለም የሄደው፤ ይልቅስ አንድ ነብሱን ሰጥቶ ወደ መቃብር ነው የወረደው:: በዚህ ሰው ለሰው በተከፈለበት ህይወት ውስጥ ሁለት ነገሮችን እንመለከታለን::

አንደኛው ምድራዊ ክብራቸውን ጥለው ለኛ ክብር በመዋደቅ ከባርነት አስመልጠው መንፈሳዊ የአዕምሮ ነጻነትን አስገኝተውልናል:: በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እኛ በሰላምና በህይወት እንድንኖር ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን በመከስከስ፣ የእኛን ውጫዊና አካላዊ ደህንነት ለመጠበቅ መስዋዕት ሆነዋል:: እንግዲህ እነርሱ ስለ እኛ ሲሉ የከፈሉት መስዋዕትነት ነብስ ከስጋ፣ አጥንት ከደም የሆነ ሁለንተናዊ የመስዋዕትነት ጥግ ነው::

ጥበብ አካለ ስጋዋን ለብሳ የተገለጠችበት ሁለተኛው የዓድዋ መልህቅ “ጥቁር ሰው” የሚለው የቴዲ አፍሮ መልከ ብዙ ሙዚቃ ነው:: እንደ አንድ ታሪካዊ ሙዚቃ በተዋጣለት ግጥምና ዜማ ከመሠራቱ ባሻገር፤ ተንቀሳቃሽ ምስሉን ወደ ጥንቱ የዓድዋ መንፈስ ለመመለስ ጥበባዊ መስዋዕትነት ተከፍሎበታል:: ከስምንት ላነሱ ደቂቃዎች በዚህን ያህል ደረጃ ሲለፋበት ለሀገራችን የኪነ ጥበብ ኢንዱስትሪም የመጀመሪያው ነው::

በኢንዱስትሪው ውስጥ ለሚሠሩ ባለሙያዎችም አዕምሯዊ የቤት ሥራን ያስገነዘበ ነው:: የአልበሙ መጠሪያና የዓድዋ ተምሳሌት ባደረገው “ጥቁር ሰው” ሙዚቃ ውስጥ ቴዲ አፍሮ በግጥሞቹ ከምናውቀው በላይ ተጠቦበታል:: ዜማው አንዳች እንከን እስከማይፈለቀቅበት ድረስ ጥንቅቅ ያለ ረቂቅ ሥራ ነው:: በአንድ ሙዚቃ ውስጥ ስለ አንድ ታሪክ እያነሱ መዝፈን፣ ታሪኩን በመጽሐፍ ላይ እንደመጻፍ ማለት አይደለም:: ግጥም በተለይ ደግሞ የሙዚቃ ግጥም በታሪክ ፍሰት ሊቀዳ አይችልም::

በታሪካዊ የሙዚቃ ሥራ ውስጥ ትልቁ ነጥብ፣ ሙሉ ታሪኩን ያማከለ ጭብጥ፣ ትዕይንትና ባለታሪኮችን ማውጣቱ ላይ ነው:: በዚህ በጨረፍታና በቁንጽል መንገድ ውስጥ ሁሉንም ነገሮች ቅንጭብጭብ ተደርገው ለአብነት እንጂ ለታሪክነት ላይሆኑ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው:: ቴዲ አፍሮና እጅጋየሁ ሽባባው ዓድዋን ከነነብሱ አስመለከቱን ስንል እይታችን ከምን አንጻር ነው የሚለውን ማወቅ አለብን::

ሙዚቃ በጣት የሚቆጠሩ ደቂቃዎች እንደመሆኑ፤ ታሪኩ ምን ያህል ተገልጾበታል ለሚለውም ልኬታችንም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት:: ከዚህ አንጻር ቴዲ አፍሮ በሙዚቃ ውስጥ ምን ያህል ገለጸበት? “ጥቁር ሰው” የሚለው አጼ ምኒልክን ብቻ የሚገልጽ አድርገን መውሰድ የለብንም:: የገለጸው የአንዱን የምኒልክ መልክ አይደለም:: በአንዱ ምኒልክ ውስጥ የጠራው መላውን ጥቁር ሕዝብን ነው::

ለዚህ እንደ አንድ ማሳያ በሙዚቃ ውስጥ የሚጠራው ስም የምኒልክ ብቻ አለመሆኑ ነው:: ገና ጅምሩ ላይ አጉልቶ ባነሳው ድምጽ የሚናገረው ስለ ባልቻ አባ ነፍሶ ነው:: “ዳኛው ያሉት አባ መላ ፊት ሀብቴ ዲነግዴ፣ ሰልፉን በጦር አሰመረው ፊት ሆኖ በዘዴ” የሚለው ለማን ነው? ለጀግናው የጦር መሪ ለፊት አውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ነው::

ከዚህ ስንኝ ቀደም ብሎ ባለው ዜማ ውስጥ “ጊዮርጊስ ፈረሱ ቆሞ ሳይ ድል ቀናኝ ሳልል እዋ፤ አባቴ ወኔውን ተኮሰው ምኒልክ ጥቁር ሰው” ይላል:: ስንኙ ለምኒልክ ብቻ ሳይሆን አስቀድሞ “ፊት ሀብቴ ዲነግዴ” ሲል ለጠራው ጀግና፣ ገሚስ የማንነት ነጸብራቁን፣ እንደ ደምስር በቀጠነ ጥበባዊ የቅኝት ቱቦ አፍሶበታል:: በአስተውሎት ስንመረምረው፣ የምናስተውለው ብዙ ነገር ቢኖርም፤ “ጊዮርጊስ” እና “አባቴ” የሚሉትን ቃላት ብቻ ከላይኛው ስንኝ ጋር ተመልክተን፣ ራሳችን ያወቅነውን እንድንረዳው ልተወው::

ከዓድዋ የሙዚቃ ተራራ በስተጀርባ አንዳች ማጉረምረም ይሰማል…እኚህን ጉርምሩምታዎች የሚያሰሙም፣ “ሁለቱ የሙዚቃ ሥራዎች በእዚህን ያህል ደረጃ ዓድዋን የሚገልጹ አይደሉም” የሚል የአንዳንዶች የትችት ጦር ነው:: አንዳችንም ጋሻውን ሳንይዝ፣ ጦር ተወራውረን ማናችን እንደምንተርፍ እግዜሩ ይወቀው::

በመቆርቆር ያገባኛል ብለን አስተያየቶቻችንን ማስፈር መልካም ሆኖ ሳለ፤ አስተያየትን ሰበብ አድርጎ አቁሳይ ጦር መወርወር ግን ልክ አለመሆን ብቻ ሳይሆን ልቅነትም ጭምር ነው:: ‹ክብረ በዓሉ የዓድዋ ሳይሆን የሙዚቀኞቹ ነው የሚመስለው› እስክንል የሚያደርስ ነገር፤ በግሌ ያለ አይመስለኝም::

በአንድ ወቅት ይህንን ርዕሰ ጉዳይ አድርገውና በሁለት ጎራ ተሰልፈው በየማህበራዊ ሚዲያው የሚፋጩትን ስመለከት፤ በመገረምና በመሳቅ ውስጥ የነበረኝ ስሜት፣ ለኔም በቅጡ ያልገባኝ ነበር:: አንዳችም አበርክቶ ባላደረግንበት የዓድዋን ያህሉ ሥራና ታሪክ፤ ለብሔርና ቋንቋ እየቸበቸብን ስንሸቅጥበት ምን ለማለት እንደሚቻል ግራ የሚያጋባ ነው::

ኪነ ጥበብ ከሌላው የሚለየው አንደኛው ነገር እንደወረደ የማይተረጎም መሆኑ ነው:: በጥቁር ሰው ሙዚቃ ውስጥ አንዳንዶች የሚያነሱት የትችት ሃሳብ ውሃ የሚያነሳ አይደለም:: “ባልቻ አባቱ ነፍሶ፤ መድፉን ጣለው ተኩሶ” በሚለው ስንኝ፣ መድፉ የሚገባው ለባልቻ ሳይሆን ለእገሌ ነው ብሎ የሚፋጠጠውንም ተመልክቻለሁ::

የሚገባው ለባልቻ ሳይሆን ለእገሌ ነው ከማለት፤ የእገሌም ስም ቢጠቀስ ኖሮ…ቢል፤ የጤነኝነት አስተያየት ነው:: እንዲህ ዓይነቶቹን አርቲ ቡርቲ ሃሳቦችን ማንሳቱም ተገቢ ባይሆንም፤ አስተያየቶቻችንን ስንሰነዝር፣ በሙያዊና ከምንም በነጻ አዕምሮ መሆን አለበት የሚለውን ሃሳብ ለማስቀመጥ ነው::

በእንዲህ ያሉ የጥበብ ሥራዎች ውስጥ በአመክንዮ የሆኑ ትችቶች ትልቅ ዋጋ አላቸው:: ጭፍን ተቺዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ጭፍን አድናቂዎችም ከዚያ ባልተናነሰ መልኩ የተጋረደባቸው ይሆናሉና ሙዚቃን ከሙዚቃው ማንነት ጋር ነጥሎ መመልከት የሁለቱም ፈንታ ነው::

ሙዚቃ ግን፤ በዓድዋ ሰማይና ምድር የምትወጣ እንጂ የማትጠልቅ ፀሐይ ናት:: ደምቃ እንደበራች በውጋጋን ሌሊት የምትጓዝ እንጂ የማትቆም ጨረቃ ናት:: ዓድዋ፤ የአርበኛ አባቶቻችን የአንድነት ህብረ ዝማሬ፣ የእኛ የልጆቻቸው የነብስ አዱኛ ነው:: የጀግኖቻችን ደም ለሁሉም የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ዥረት ገባር ነውና የሚሰማን ኩራት ነው!!

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You