የጥበብ ነገሥታቱ

ዓለማችን ካፈራቻቸው ነገሥታት አንዷ ነበረች። በትንሹም፣ በትልቁም፤ በሴቱም በወንዱም፤ በጥቁሩም በነጩም፣ በቢጫውም ዘንድ ትታወቃለች። በመሪዎች አፍ ተደጋግማ ከመጠራትም ባለፈ የንግግር – ክርክራቸው ማጥበቂያ፤ መቆሚያ መሰረት የነበረች (በዚህ በኩል “ነች” ማለትም እንችላለን) ስትሆን፤ ፍሬ-ከናፍሮቿም ተጠቃሽ ናቸው።

ስዊዘርላንድ (ዙሪክ ከተማ አቅራቢያ) በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ማረፏ ሲሰማ ዓለም “በሞትኩት” ያለላት ንግሥቲቱ በ“አንቺ” ትጠራ እንጂ “አንቺ”ታው ከፍቅር የመነጨና ከ“አንቱታ”ም የገዘፈ፤ መነሻና መድረሻውም ፍቅርና አድናቆት ነው። በመሆኑም በ“አንቺ”ታው ተደንቃ፤ በእሱው ተጠርታ . . . “ሊጋባው በየነ / እንደ ኮራ ሄደ እንደ ተጀነነ” እንዲል ዜማው እንዳማረባት ይህችን ዓለም ተሰናብታለች። በወዳጅ አድናቂዎቿም “በገነት . . .” ትኖር (ያኖራት) ዘንድም ለላይኛው “አቤት” ተብሎላት የስንብቱ መጨረሻ ሆኗል።

ስምንት ግራሚ ሽልማቶችን ያሸነፈችው ይህች ንግሥት በበርካታና ታላላቅ መሪዎች ዘንድ ትታወቅ ዘንድ ስራዎቿ ያስገደዱ ሲሆን፤ ከሚያውቋት፣ ከሚያደንቋትና ከፍሬ-ከናፍሯ የወደዱትን ከጠቅሱላት መሪዎች አንዱም የእኛው፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነበሩ።

መቼም በወቅቱ ለአቅመ ምርጫ ደርሶ ከነበረው “ምርጫ 97”ን የማያስታውስ አይኖርምና ይህንን “ምርጫ” ተከትሎ በሀገሪቱ ነግሶ የነበረውን የፖለቲካ ውጥረት እና በኢህአዲግ እና በተቃዋሚዎች (በተለይም በቅንጅት ፓርቲ) ሰፈር የነበረውን ጡዘት እዚህ ማንሳቱ ተገቢ አይሆንምና ወደ ንግስቲቱና ፍሬ-ከናፍሯ እንመለስ።

“ምርጫ 97” ለታሪክ ካበቃቸው በርካታ ጉዳዮች አንዱ የተለያዩ የፖለቲካና ሌሎች ስብዕናዎች ያላቸው ሰዎች ስም ዝርዝራቸው የምርጫው አካል ሆኖ እንዲሰፍር ማድረጉ ሲሆን፤ አቶ መለስ ዜናዊ፣ ወይዘሮ አና ጎሜዝ (ጎሜዝ በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ የፖርቹጋል ተወካይ ሲሆኑ በ1997ቱ ሀገራዊ ምርጫ ህብረቱን (EU-EOM) በመወከል የኢትዮጵያን ሀገራዊ ምርጫ መታዘባቸው ይታወቃል)፤ እጅግ ከተዋጣላቸው ዝነኛ ድምጻውያን አንዷ የሆነችው ንግሥት ነበረች።

የሮክ ኤንድ ሮል ሙዚቃ ተወዳጅነት ባተረፈባቸው በ1950ዎቹ የሙዚቃውን ዓለም የተቀላቀለችው ንግሥት ቲና “የሮክ ኤንድ ሮል ሙዚቃ ንግሥት” ትባል ዘንድ ካስቻሏት ዜማዎች መካከል ዋናውና በብዙዎች ተዝወትሮ የሚጠቀሰው፤ “What’s love got to do with it?” (“ፍቅርን እዚህ ምን አመጣው?” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል) የሚለው ሲሆን፤ አቶ መለስም ይህንኑ በጽሑፋቸው (“Easy to remove the garbage that has covered lumps of truth” በሚል ርእስ ለንባብ የበቃ፣ ሰፊ (13ሺህ 222 ቃላት) ጽሑፍ በመጥቀስ ነበር ጎሜዝን (ሕብረቱንም ጭምር) የጉሎ ዘይት ለማጠጣት የሞከሩትና ለከረረ ብስጭትና የከፋ የፖለቲካ ግጭት ውስጥ እንዲገቡ ያደረጉት (ጽሑፉ በማስታወቂያ ሚኒስቴር አማካኝነት በቡክሌትም ታትሞ እንደ ገና ተሰራጭቷል)።

በአይነቱ የመጀመሪያ በተባለለት የአቶ መለስ ዜናዊ የ“ዘ ኢትዮጵያን ሄራድ” (31st August 2005) ጽሑፍ የተላለፈው መልእክት የሚያጠነጥነው በሴትየዋ ፖለቲካዊ ሰብዕና፣ ጣልቃ ገብነትና ያልተገባ ወገንተኝነት ላይ ሲሆን ውገናቸውም ለቅንጅት መሆኑ ላይ አምርሮ ክስ የሚያቀርብ ጽሑፍ ነው።

 በችግረኛ የገበሬዎች ማኅበረሰብ ውስጥ አድጋ ከዚያም ባለቤቷ ከነበረው ከአይክ ተርነር ጋር ጥቃት የተመላበት የትዳር ህይወት ያሳለፈችው፤ ከሙዚቃ ዓለም ራሷን በጡረታ አግልላ የስዊዘርላንድ ዜግነት የወሰደችው ይህች የ83 አመት (እድሜ) ባለፀጋ ንግሥት፤ ጀርመናዊውን የሙዚቃ ኩባኒያ ሥራ አስኪያጅ አርዊን ባክን አግብታ (2ኛዋ ነው) ትኖር የነበረች ሲሆን፤ የሕይወቷ የመጨረሻ ምእራፍን

 በዛው ምድር ሊጠቃለል የቻለ መሆኑን ጠቅሰን (የሀገረሰብ ሙዚቃ ንግሥት ዶሊ ፓርተንን፤ እንዲሁም የሶል ንግሥቷን አስቴር አወቀን፤ የደቡብ አፍሪካዊቷ ማሪያም አኬቫን በእግረ-መንገዳችን አስታውሰን) ወደ ራሳችን ንግሥት ደግሞ እንምጣ።

ጓደኞቹ ጋር በሰሩት “ያልደረቀ ዕንባ” በተሰኘው ፊቸር ፊልም ላይ የፊልሙን ሳውድ ትራክ የጂጂን “ኢትዮጵያ” ሙዚቃ ያደረገው፤ በጂጂ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አሰጣጥ ሥነሥርዓት ላይ፣ የሕይወት ታሪኳን ያቀረበው ጥበቡ በለጠ “የጂጂ ሙዚቃዎች በግጥም ስልታቸው ተራኪ ስንኞች (Narrative Verses) ናቸው፡፡ የታሪክን፤ አንድ የተወሰነ ጉዳይን፤ የነበረ ጉዳይን በሙዚቃዎቿ ትተርክልናለች፡፡ በዚህም ሳንወድ በግዳችን በፍቅር እናደምጠዋለን”:: ለዚህም “አባይ”፣ “ካህኔ”፣ “ናፈቀኝ” እና ሌሎችም በርካታ ዘፈኖቿ ይጠቀሳሉ።” ያለላትን፤ ዶክተር ፈቃደ አዘዘ፣ ረዳት ፕሮፌሰር ብርሀኑ ገበየሁ ሌሎችም አብዝተው ያቆለዻዸሷትን፣ የእኛዋ ንግሥት ከነጮቹ ንግሥት ጋር በሙያና ፆታ ይመሳሰሉ እንጂ በስራዎቻቸው ይዘትና ቅርፅ ግን የተለያዩ ናቸው። “ምክንያት?” ከተባለ፣ የዛችኛዋ ንግሥት ስራዎች ትኩረታቸው እራሳቸው ላይ ሲሆን፤ የኛዋ ንግሥት ስራዎች ደግሞ እኛውና ድሎቻችን፣ ችግሮቻችን፣ ህፀፆቻችን . . .፤ እንዲሁም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን ከፍ ከፍ ማድረግ ላይ ይሁነኝ ተብለው የተሰሩ መሆናቸው ነው። አድዋን፣ ወዴት ዘመም ዘመም፣ ህ(እ)ማማ . . .ን መጥቀሱ ብቻ ከበቂ በላይ ነውና ወደ ሰሞኑ፣ ንግሥቲቱን የተመለከቱ ጉዳዮች እንምጣ።

ሰሞኑን በአየር ምድሩ ሲናኝ የሰነበተው ዜና “ለአርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) የክብር ዶክትሬት ሊሰጣት ነው”፤ “እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ለአርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሊሰጣት መወሰኑን አስታወቀ” እና የመሳሰሉት ነበሩ። በመጨረሻም፣ “እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ለአርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) የክብር ዶክትሬት ሰጠ” የሚል ነበር። “ለምን?”

ድምፃዊት፣ ገጣሚ፣ ባለቅኔ፣ የዜማ ደራሲና ተዋናይት የሆነችው፤ በቅርቡ፣ ለ15ኛ ጊዜ በተካሄደው የአማራ ክልል ባህልና ኪነጥበባት ፌስቲቫል ላይ የዕውቅና ሽልማት (ጌትነት እንየውና አበበ ብርሃኔን ጨምሮ) ያገኘችው፤ ሁለገቧ አርቲስት ጂጂ (ከዛኛው ሀሙስ በኋላ ዶክተር)፣ የሀገሯን ባህልና ሙዚቃ ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና የተጫወተች በመሆኗ፤ በኪነ-ጥበብ ሥራዎቿ÷ የአዊን ሕዝብ ቋንቋ እና ባሕል በማሳደግ ላበረከተችው አስተዋፅኦ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ትልቅ ደረጃ ካደረሱት ድምፃዊያን መካከል ፊት መሪ በመሆኗ፤ ከመንዙማ፣ ከአሚናዎች፣ ከጉባኤ ቃና የተፈለቀቁ ሙዚቃዎች የምታንቆረቁር በመሆኗ፤ ስራዎቿ የእውቅ ሲኒማዎች ማጀቢያ በመሆናቸው፣ ከማንም በላይ ስራዎቿ የሙዚቃ፤ የሥነግጥም እና የሥነጽሑፍ ሃያሲያንን ትኩረት የሳበ በመሆኑና ሰፊ የጥናትና ምርምር ስራዎች የተሰሩባቸው (ትንታኔዎች

 የቀረቡባቸው) መሆናቸው፤ ልክ እንደ ቲና ሁሉ የጂጂ ስራዎችም በተለያዩ ግዙፍና አገር ተኮር ስራዎች ውስጥ ሲጠቀሱ መታየታቸው (ወይም የጥናትና ምርምር “አጋዥ” መሳሪያ መሆናቸው) ወዘተርፈ ለዚህ ታላቅ ክብርና ሽልማት እንዳበቃት ተነግሯል። (“እልልልልል . . .” ያላለ ካለ ያልሰማ ብቻ መሆን አለበትና ሲሰማ ያደርሰዋል።)

ጂጂ ሌሎች ምልክቶች (አሻራዎች)ም ያላት ሲሆን አንዱና ቀዳሚውም ሃያ ዘጠኝ ሺህ ፈረሰኞችን ጨምሮ ከመቶ ሺህ እስከ መቶ ሃያ ሺህ የሚገመት አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ የተጓዘ የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት በወታደራዊ አካዳሚ የሠለጠነውን የአውሮፓ ወራሪ (ፋሺስት) ጦር የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ማለዳ አሥራ አንድ ሰዓት ግድም ገጥሞ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ድባቅ የመታበትን፤ “የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል” መሆኑ ዘወትር የሚነገርለት የአበሻ ድል በ“አድዋ” ዜማዋ ማንቆርቆሯ ሲሆን፤ ዜማ (የብሄራዊ መዝሙር ያህል ዋጋ ያለው) ቅንጫቢ ስንኞቹም የሚከተሉት ናቸው።

የሰው ልጅ ክቡር፣

ሰው መሆን ክቡር

ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን፤

*************

የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነጻነት፣

ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት

**********

የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነጻነት፣

ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት፣

ስንት ወገን ወደቀ በነጻነት ምድር

ትናገር ዓድዋ ትናገር ትመስክር!

ትናገር ዓድዋ ትናገር ሀገሬ

እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ።

 የአድዋን ድል አስመልክቶ “ዓለም አቀፍ ግርማ ያገኘ፣ የታሪክ ሰነዶችን ያጣበበ የዓለማችን ታላቅ ገድል” ነው፤ “በደም ውስጥ ሕይወት አለ፤ ሕይወት ለነጻነት ተከፍሏል፤ ለባርነት ስርየት ፈስሷል። ምሱን የተቀበለው የዓድዋ ምድር ርስትነቱ ፀንቷል። ቦታው ዓድዋ፣ ኪዳኑ መስዋዕትነት ነው። ሰንደሉ ትውልድ ጤሶ እስከ ዛሬ በሀገርና በዓለም አድማሳት ይናኛል። …ዛሬም ለእኛ የሽቶ ያህል መዓዛ፣ ለማይወዱን ደግሞ የሞት ያህል ክርፋት ሆኖ ይኖራል። አባቶቻችን ጠባሳው ሕመም እንዳይሆን፣ በድል የክብር ቀለም ቀብተው፣ ከፍ አድርገው ሐውልቱን ከታሪክ ጋር ገምደውታል።” የሚለው የአዲስ አድማሱ ደረጀ በአንድ ወቅት እንዳሰፈረው፣ እጅጋየሁ ሽባባው በ“ዓድዋ” – – – ተራራው -አድዋ – ሰማዩ ፣ ሰማዩን የሳመው የተራራው ከንፈር … ከውስጡ የሚመነጨው የትዝታ ገሞራ – ፊታውራሪ ገበየሁ – ገብቶ ሲነድድ – መዓዛው ለዛሬ ጣፋጭ- የነጻነት ዜማ … የባርነት ስርየት ነው። የመትረየስ እሳት ምላስ ያነደደው ተራራ፣ አፈሩን የዛቀው መድፍ ግራና ቀኙን የተጎሰመው ነጋሪት ድምጽ ያሸበረው ቁጥቋጦ የተሳከረውን ድብልቅልቅ ዋጋ፣ ስሌቱን የታሪክ ድርሳናት ብቻ ሳይሆኑ ዓድዋ ራሱ ይተርከው ነው ምትለው።

ጂጂን ተንተርሰን ጥቂቶቹን እንጥቀስ እንጂ፣ የኢትዮጵያ ነገሥታት እነዚህ ብቻ አይደሉ። ከአዝማሪ ፃዲቄ ጀምሮ (ዘመኑ የክብር ዶክተሬት ዲግሪ የሚያስገኝ ባይሆንም)፤ በቀድሞው ዘመን፣ ልክ እንደ ዝነኞቹና የክራር ንግሥቶቹ ሜሪ አርምዴ እና አስናቀች ወርቁ ሁሉ፤ በቅርቡም እንደ የሙዚቃው ንጉስ ጥላሁን ገሠሠ፣ የትዝታው ንገሥታት መሀሙድ አህመድ እና በዛ ወርቅ አስፋው ሁሉ፣ ለሌች በርካቶችም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ከፍ አድርገዋልና እዚህ፣ ቢያንስ ስማቸው ሊጠራ ግድ ይላል።

መልካሙን ሁሉ ለዶክተር አርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) እንመኛለን!!!

 ግርማ መንግሥቴ

 አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 20 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

One Comment to “ የጥበብ ነገሥታቱ”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *