የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የ2011 በጀት ዓመት የስምንት ወራት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ እንደጠቀሰው በስምንት ወራት ውስጥ ከዳያስፖራው የተገኘው ሬሚታንስ ሶስት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ነው። ይህ መጠን ከፍተኛ ቢሆንም ኢትዮጵያ በውጭ አገራት ካላት ሶስት ሚሊዮን የሚጠጋ የሰው ሃይሏ አንጻር ሲታይ።
የዓለም ባንክ መረጃዎች እንደሚያሳዩት አንዳንድ አገራት በውጭ አገራት ከሚገኙ ዜጎቻቸው ከአጠቃላይ ምርታቸው እስከ 37 ከመቶ የሚሆነውን ያገኛሉ። በዚህ ረገድ ከአፍሪካ ናይጄሪያ ተጠቃሽ ናት። ናይጄሪያ በ2018 በውጭ አገራት ከሚኖሩ ዜጎቿ 22 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን መረጃው ያሳያል። የናይጄሪያ የስደተኞች ቁጥር ግን ከ1ነጥብ 3 ሚሊዮን የዘለለ እንዳልሆነ መረጃው ያመለክታል። በሌላ በኩል በዓለም ላይ ሜክሲኮ 30 ቢሊዮን፣ ቻይና 16 ነጥብ 14 እንዲሁም ህንድ 11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር በማግኘት የመሪነት ስፍራውን ይዘዋል።
ምሁራን እንደሚገልፁት በተለያዩ መንገዶች ከውጭ የሚገባ የውጭ ምንዛሪ በአገር ኢኮኖሚ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። በተለይ እንደኢትዮጵያ ባሉ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛ ችግር እየሆነባቸው በሚገኝባቸው አገራት ከውጭ የሚገባ ገንዘብ መጨመሩ ለኢኮኖሚው እድገት የሚኖረው ፋይዳ የላቀ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ከውጭ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ አነስተኛ መሆኑ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ መላኩ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደተናገሩት፤ ከውጭ ዶላር ለማግኘት ካሉት አማራጮች ውስጥ በተለያዩ መንገዶች ወደ አገር ውስጥ የሚገባው የውጭ ምንዛሪ (ሬሚታንስ) አንዱ ነው።
ነገር ግን በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ የዚህ ገንዘብ አነስተኛ መሆን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባንን እንዳናገኝ አድርጓል። ይህ ደግሞ አሁን ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከማባባሱም በላይ ከውጭ የሚገቡ እቃዎች ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የማስገባት አቅምን ይገድባል።
በሚፈለገው ልክ እቃዎች አልገቡም ማለት ደግሞ በአገር ውስጥ ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንደሚያዳክመው አቶ ተስፋዬ ይገልጻሉ። በተጨማሪም ከውጭ የሚላክ ገንዘብ ጠብቀው የሚተዳደሩ ሰዎች ገንዘቡ (ሬሚታንሱ) በቀነሰ ቁጥር ገቢያቸው ይቀንሳል። ይህ ደግሞ በሌላ ጎኑ ድህነትን ያባብሳል።
መንግስት ከውጭ የሚላክ ገንዘብ እንዲጨምር የተለያዩ ማበረታቻ ፖሊሲዎች መውጣት እንዳለበትም አቶ ተስፋዬ ጠቁመዋል። በጥቁር ገበያው የሚዘዋወሩ ገንዘቦች ሊኖሩ ስለሚችሉ የገንዘብ ዝውውሩ ወደ መደበኛ የባንክ ስርዓት እንዲመለስ መደረግ እንዳለበትም አስረድተዋል። እነዚህ ነገሮች መተግበር ከጀመሩ ችግሩ እንዳይባባስ መፍትሄ ሊሆን ይችላል።
በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ፍሬዘር ጥላሁን በበኩላቸው፤ ከሬሚታንስ የሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ግብዓት ሆኖ እንደሚያገለግል ገልፀዋል። የሬሚታንስ ገንዘብ ለመቀነሱ በአገር ውስጥ ያለው የዶላር እጥረት እንደማሳያ ማንሳት ይቻላል። ይህ ደግሞ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
አቶ ፍሬዘር እንደሚሉት አገራዊ ጉዳዮችን ግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን በመጥቀስ፤ በአገሪቱ ያለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ተፅዕኖ ፈጥሯል። ከትረስት ፈንድ መዋጮ ሲጀመር በከፍተኛ ሁኔታ እንቅስቃሴ እንደነበረውና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይገኝበታል ተብሎ የታሰብ ቢሆንም በሚጠበቀው ልክ አይደለም።
የሬሚታንስ መቀነስ ኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ ከመፍጠር ባሻገር የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲመጣ አድርጓል የሚሉት ምሁራኑ ኢትዮጵያ ከውጭ በብዛት የምታስገባ አገር እንደመሆኗ ከውጭ እቃ መግዛትና መሸጥ ላይ ተፅእኖ በመፍጠር የዋጋ ንረት እንዲመጣ ማድረጉን አብራርተዋል።
እንደ አቶ ፍሬዘር ገለፃ፤ ከውጭ የሚላክ ገንዘብ በሰዎች በጎ ፈቃድ የሚደረግ ነገር ነው። በፖሊሲ ተቀርፆ በግዴታ የሚሆን ነገር አይደለም። በመሆኑም ኢኮኖሚው በነዚህ ገንዘቦች ላይ እምነት መጣል የለበትም። እንደተጨማሪ ኢኮኖሚ አቅም ሊታዩ ይገባል። ገንዘቡ ሲመጣ ሀይል ሲቀር ደግሞ የማይጎዳ እንዲሆን የሚያስችሉ የፖሊሲ ማዕቀፎች ያስፈልጋሉ። ከውጭ የሚገዙ እቃዎችን መቀነስ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ አገር ውስጥ በማምረት፣ በአገር ምርት መጠቀም እንዲሁም ከውጭ መገዛት ያለባቸውን መርጦ መግዛት ይገባል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2011
መርድ ክፍሉ