ከሰሞኑ በሁሉም መሰረታዊ ፍጆታዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ተስተውሏል፡፡ በተለይ ደግሞ ብዙ ዳቦ ቤቶች በዱቄት እጥረት በሚል ምክ ንያት ተዘግተዋል፡፡ አገልግሎት የሚሰጡትም በእያ ንዳንዱ ዳቦ ላይ በፊት ከነበረው ዋጋ የአንዳንድ ብር ጭማሪ አድርገዋል፡፡ የሸቀጦች እና የፍራፍሬ ዋጋም በተመሳሳይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ከቀን ወደ ቀን እያሳየ መሆኑን ተዘዋውረን ባነጋገርናቸው ሸማቾችና ቅኝት ባደረግንባቸው የንግድ ቦታዎች አረጋግጠናል።
የአራት ኪሎ አካባቢ ነዋሪ መሆናቸውን የነገሩን ወይዘሮ አስቴር አያሌው በሁሉም እቃ ዎች ላይ በየቀኑ የዋጋ ጭማሪ እያዩ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይህም ሁኔታ የኑሮ ውድነቱ ወዴት ሊደርስ ነው በሚል እያሳሰባቸው መሆኑን አጫወቱን። ”ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምንገዛቸው ዳቦዎች ወድ ከመሆናቸው ባሻገር መጠናቸውና ጥራታቸው የወረደ ነው“ ሲሉ ይናገራሉ ፡፡ የሸቀጦችም ሆነ የፍራፍሬ ዋጋ ከመጠን በላይ መጨመሩ በተለይ ለደሀው ህብረተሰብ አሳሳቢ ነው በማለት ሃሳባቸውን አካፍለውናል።
በሾላ ገበያ በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ተሾመ ጥላሁን በሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን አምነው፤ ይሄንን የዋጋ ጭማሪ ያደረገው ግን ቸርቻሪው ሳይሆን እቃው ከመነሻው ከሚመጣበት የተደረገ ጭማሪ መሆኑን ጠቅሰዋል። ቸርቻሪ ነጋዴዎች ባመጡት እቃ ዋጋ ላይ የራሳቸውን መጠነኛ ትርፍ ጨምረው ይሸጣሉ፤ ይሄም ተገቢ ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር እንዳወቅ አብጤ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በግንባታ እቃዎች፣ በእህል፣ በጥራጥሬና በአትክልት ላይ በተለየ ሁኔታ የዋጋ ጭማሪ መታየቱንም አምነዋል። ለዚህም እንደ ምክንያትነት የሚነሳው የግብርና ምርት እጥረት፣ ህገ ወጥ ደላሎች መበራከት፣ ያለአግባብ እህሎችን በመጋዘን ማከማቸትና የህብረት ስራ ማህበራት በትክክል አለመስራት መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
እንደ ምክትል ከንቲባው ገለፃ፤ ይህ ሁኔታ ቀጣይነት እንዳይኖረው በሁለት መንገድ የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው፡፡ አንደኛው በህገወጥ መንገድ የተሰማሩ ነጋዴዎችን ህጋዊ እንዲሆኑ ማድረግና ፍቃደኛ ባልሆኑት ላይ ደግሞ ግብረሃይል በማዋቀር እርምጃ መውሰድ ሲሆን ሁለተኛው ስልት ከአማራ፣ ከኦሮሚያና ከደቡብ ክልል የግብርና አምራቾች ጋር ትስስር በመፍጠር፣ የህብረት ስራ ማህበራትን ድጎማ በማድረግ የአቅርቦት ስርአቱን በማስተካከል ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድና የክስ ምርመራ ክትትል ቡድን መሪ አቶ ሀብታሙ ጥላዬ፥ ሕገ ወጥ ንግድና የኮንትሮባንድ መስፋፋት በአጠቃላይ በህብረተሰቡና በህጋዊ ነጋዴዎች ላይ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በንግድ ስርአቱ ግልፀኝነት አለመኖር፣ የጥራት፣ የመጠንና የኮንትሮባንድ ችግር በመዲናችንና በሁሉም ክፍለ ከተማዎች መስፋፋት በመቻሉ ጤናማ የሆነ የገበያ ስርአቱን እያወከው መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ሌላው በከተማችን የሚስተዋለውና ለኑሮ ውድነት ምክንያት የሆነው የንግድ ፍትሀዊነት አለመኖር ነው፡፡ ግማሹ የንግድ ፍቃድ አውጥቶ ለመንግስት ግብር እየከፈለ ሲሰራ የተቀረው ደግሞ ያለ ንግድ ፍቃድ በመስራት ህጉን ተከትሎ ከሚሰራ በላይ ትርፋማ መሆናቸውን አንስተ ዋል፡፡
በአትክልትና በስጋ መሸጫዎች ላይ የልኬት ማጭበርበር መኖሩ ህብረተሰቡን ከዋጋ ጭማሪና ከጥራት ማነስ በላይ ተጎጂ እያደረገው መሆኑንምአመልክተዋል፡፡ አግባብነት የጎደለው በእህልና በፍራፍሬ ላይ የሚታይ የዋጋ ጭማሪ የህብረተሰቡን የእለት ተዕለት ኑሮ ከማስተጓጎል ባሻገር በጥቅሉ ሰላማዊ የሆነ ገበያ እንዳይኖር በማድረግ በሀገር ላይ ከፍተኛ ችግር እንደሚያደርስ ጠቁመዋል፡፡ የዳቦ ዱቄትን በተመለከተ የአቅርቦት ችግር አለ፡፡ ለማቅረብ ከታሰበው ውስጥ ስልሳ አራት ፐርሰንቱን ብቻ መቅረቡን አብራርተዋል፡፡ ይህም ለዳቦ እጥረቱ ምክንያት መሆኑን አረጋግጠዋል።
በህገ ወጥ ንግድ ላይ በተሰማሩ አንድ መቶ ሀያ ሦስት ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን የጠቆሙት አቶ ሀብታሙ፤ ለአስራ ሰባት ወፍጮ ቤቶችና ለሰባ አትክልት ቤቶች የጹሑፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ሰባት ዳቦ ቤቶችንና ሁለት ፋብሪካዎችንም ሙሉ ለሙሉ ከገበያ ትስስር እንዲወጡ ማድረጋቸውን አስገንዝበዋል፡፡
እርምጃ አወሳሰዱ በእኩልና በተገቢው ጊዜ አለመሆን፣ ዳቦ ቤቶችን ከትስስር ለማስወጣት ከመንግስት በኩል ፍርሃት መኖርና በደረሰኝ ከመገበያየት ይልቅ በእምነት መገበያየት በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ያለውን ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያባባሰው መምጣቱን አቶ ሀብታሙ አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2011
ሞገስ ፀጋዬ