እኔማ ከዚህ በኋላ ጥናት አላምንም! ደግሞ እኮ የሬዲዮ ጣቢያዎች ወሬ ‹‹ጥናቶች እንደሚጠቁሙት›› እየተባለ ነው፡፡ ጥናት እንዲህ ከሆነስ ይቅርብኝ!
ሰሞኑን የሥራ ቦታዬ ላይ እያለሁ አንድ የጥናት መጠይቅ እንዲሞላ ተሰጠኝ፡፡ ጥናቱን የሚሰሩት ሰው ከመገናኛ ብዙኃን የመጡ ናቸው (ጾታ ላለመግለጽ ብየ እንጂ ለአንቱታ አልደረሱም)፡፡ መጠይቁን ሳነብ በጣም ግራ ተጋባሁ፤ ግራ የተጋባሁት መጠይቁ ችግር ስላለበት እንጂ ብዙ የጥናት መጠይቆችን ሞልቻለሁ፡፡
መጠይቁ በምርጫ ብቻ የሚሞላ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት የምርጫ ብቻ መጠይቆች ሲመጡ ደስ ይለኛል፤ ምክንያቱም ለስንፍና ያመቹኛል፤ ማለቴ መጻፍና ማብራራት ሳያስፈልግ ዝም ብሎ ማክበብ ብቻ ነው፡፡
ይሄኛው መጠይቅ ግን አናደደኝ፤ እንዲያውም እንደ ትምህርት ቤት ፈተና ‹‹ኮሬክሽን›› ልጠይቅ ነበር፤ ግን የመጠይቁ ባለቤት ሰጥተውኝ ወጣ ብለዋል፡፡ በዚያ ላይ ያሉት አማራጮች የተሰጡት ብቻ ናቸው፤ ሌላ ቅጽ አይሞላልኝ እንግዲህ!
የሚጠየቀው ጥያቄና የተሰጠው አማራጭ ሀሳብ አይገናኙም፤ ማለት አማራጮች ጥያቄውን ለመመለስ ምቹ አይደሉም፡፡ እንዲህ አይነት አጋጣሚ ሲኖር ማብራሪያ መኖር ነበረበት፡፡ መልስ የሚሞላው ሰው ያለበትን ምክንያት ግልጽ የሚያደርግበት አማራጭ መኖር አለበት፡፡ ጥናቱ ላይ ያለውን ጥያቄ ላለመግለጽ ሀሳቡን የሚገልጽ ተመሳሳይ የሆነ ጥያቄ ፈጥሬ ልጠይቃችሁ፡፡
እሳት ይጎዳል ብለው ያስባሉ?
ሀ/ በጣም እስማማለሁ ለ/ እስማማለሁ ሐ/ አልስማማም መ/ በጣም አልስማማም
አሁን ይሄ ጥያቄ እንዴት ነው የሚሞላ? እርግጥ ነው እስማማለሁ (ይጎዳል ማለት ነው) ብሎ መመለስ ይቻላል፤ ወይም አልስማማም (አይጎዳም ማለት ነው) ብሎ መመለስ ይቻላል፡፡ ይሄ መልስ ግን የተጠያቂውን ሀሳብ አይገልጽም፡፡ የእሳት መጉዳት አለመጉዳት ‹‹እስማማለሁ አልስማማም›› በሚል የሚገለጽ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ለጉዳቱም ለጥቅሙም ምክንያት አለው፡፡ ቢያንስ እኮ ምርጫው በከፊል እንኳን የሚል መኖር ነበረበት (ይሻል ነበር ማለቴ እንጂ በእርግጥ ይሄም አይገልጸውም)
በዚህ ጥናት ውጤት እንግዲህ ይህን ያህል ሰው እሳት ይጎዳል አለ፤ ይህን ያህል ሰው ደግሞ እሳት አይጎዳም አለ ተብሎ ይገለጻል ማለት ነው፡ ፡ ዳሩ ግን የተጠኚዎች ስሜት አልተገለጸም፤ ምክንያቱም ለአንድ ሰው ሁለቱም መልስ ሊሆነው ይችላል፡፡ መቼም ሁለት መልስ ለመሞላት ‹‹እስማማለሁ›› እና ‹‹አልስማማም›› የሚለውን አልሞላም፡፡ ሀሳቤ ግን እሳት እንደሚጎዳም እንደሚጠቅምም ነው፤ ምክንያቱም ሁለቱም መልስ መሆን ይችላል፤ እሳት ይጎዳልም ይጠቅማልም፡፡
ይሄው መጠይቅ አስከትሎ ደግሞ እሳት ይጠቅማል ብለው ያስባሉ? ብሎ ይጠይቃል፤ ያሉት አማራጮች እነዚያው ናቸው፡፡ ሲጀመር የመጀመሪያው ጥያቄ እኮ ለሁለተኛው ጥያቄ መልስ ይሆናል፡፡ እሳት ይጎዳል የሚለው ላይ እስማማለሁ ብየ ከሞላሁ በእኔ እምነት እሳት አይጠየቅምም ማለት ነው፤ ስለዚህ ሁለተኛው ጥያቄ አያስፈልግም! እንዲህ አይነት መጠይቅ በማብራሪያ እንጂ በእስማማለሁ አልስማማም የሚሞላ አይደለም፡፡
እሳትን ምሳሌ ስላነሳሁ የእሳት ነገር ትዝ አለኝ፡፡ በዚህ ዘመን የእሳት አገልግሎት በኤሌክትሪክ ስለተተካ አይጠቅምም የሚለው ብቻ ይታሰብ ይሆን እንዴ? ብየ ሰጋሁ፡፡ ዳሩ ግን ገጠር አካባቢ አሁንም አገልግሎት እየሰጠ ያለ እሳት ነው፡፡ ለነገሩ አዲስ አበባም ቢሆን መብራት በፈረቃ ከሆነ ወዲህ (ከዚያ በፊት ግን አይጠፋም ነበር አይደል?) ባለውለታችን እሳት ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ምሳሌውን እንደምሳሌ ውሰዱት (ምሳሌውን እኔ ነኝ የፈጠርኩት ብያችኋለሁ)፡፡
የእንዲህ አይነት ጥናቶች ችግር ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ መጠይቁን የሚሞሉት ሰዎችም ችግር አለ፡፡ በተረጋጋ ቀልብ አንብበው አይሞሉትም (ኧረ ጭራሽ ሳያነብ የሚሞላም አይጠፋም)፡፡ በተለይ የሚጻፍ ነገር ካለው በጥሞና አንብቦ በጥሞና አይጽፍም፤ ለጥናቱ ጠቃሚው ደግሞ የሚጻፈው ነበር፡፡
አጥኚዎች ደግሞ ሰው የተሰባሰበበት ቦታ ሄደው ነው የሚያስሞሉት፤ ሰው የተሰባሰበበት ቦታ ላይ ደግሞ የተረጋጋ ቀልብ አይኖርም፡፡ እዚህ ላይ ግን በአጥኚዎች የማንፈርድበት አንድ ነገር አለ፡፡ ሰዎች የተሰበሰቡበት ቦታ የሚሄዱት ጥናቱ ለሚመለከታቸው ሰዎች መሰጠት ስላለበት ነው፡፡ የሚመለከታቸውን ሰዎች ለማግኘት የግድ የሚሰሩበት ቦታ ነው መሄድ ያለባቸው፡፡ ለምሳሌ ጥናቱ የባንክ ሰዎችን የሚመለከት ከሆነ የባንክ ሰዎች የሚገኙት የግድ ባንክ ቤት ነው፡፡ መናፈሻ ውስጥ ተረጋግቶ ቁጭ ያለን ሰው ‹‹የባንክ ሰራተኛ ነህ?›› ተብሎ አይጠየቅም፡፡ እርግጥ ነው መጠየቁ ችግር የለውም፤ ግን አይደለሁም ቢል የባንክ ሰራተኛ ከየት ይገኛል? እንዲህ እንዲህ እያሉ የሚመለከተውን ሰው ማግኘት ደግሞ ከፍተኛ ጊዜና ገንዘብ ይፈጃል፡፡
አሁን ደግሞ አንድ የህክምና ዶክተር የነገረኝን ላካፍላችሁ፡፡ የደም አይነቴ የሚፈልጋቸውን የምግብ አይነቶች ኢንተርኔት ላይ እያነበብኩ ነበር፡፡ አስፈላጊ ናቸው ብሎ የሚዘረዝራቸው ምግቦች እኔ ብዙም የማልወዳቸው ናቸው፤ የምወዳቸውን ደግሞ እንደማይመከሩ አስቀምጧል፡፡ የህክምና ዶክተሩ ጓደኛዬ ስለነበር አንድ ዕለት በጨዋታ መሃል አነሳሁለትና ጠየቅኩት፡፡ እንዲህ አይነት ጥናቶች ብዙም አስተማማኝ እንዳልሆኑ ነበር የነገረኝ፡፡ ምክንያቱም በተወሰነ ሰው ላይ የሚሰሩ ናቸው፡፡
ጥናት ሁሉ ውሸት ነው እያልኩ አይደለም፤ ችግሩ ግን የሚሰሩበት መንገድ ቀደም ሲል የጠቀስኩት አይነት ነው፡፡ በተለይም በእኛ አገር ደግሞ ችግሩ የከፋ እንደሚሆን ነው፤ ምክንያቱም የገንዘብና የጊዜ ችግር አለ፡፡ ለሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ጥናት የሚሰሩ ሰዎች ከመደበኛ ሥራቸው ጋር ነው የሚሰሩት፤ ስለዚህ ጥናቱ የሚሰራው የይድረስ ይድረስ ነው፡፡
ጥናቶቻችንን በተመለከተ ጥናት መሰራት አለበት!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 24/2011
ዋለልኝ አየለ