
የዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ካለፉ የአዲስ ዘመን ትውስታዎች መካከል በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ለንባብ የበቁ ዘገባዎችን ያስቃኘናል። በእህል ሠፈራ ወቅት ከጣሳው ውስጥ ጨርቅ እየጠቀጠቁ ስለሚያታልሉት ቸርቻሪዎች፣ ከሌላኛው ዘመን ላይ ደግሞ “አዲሱን የለቅሶ ዜማ የመንደር አልቃሾች ተቃወሙ” ሲል ያወጣውን ዘገባ እናስታውስበታለን፡፡ ከጋዜጦች ላይ ውዝግብ የፈጠረችው ሰዓት የምታቆመዋ ቃልቻሳ እንዴት ያለችው ትሆን…ለዛሬ እነኚህን ርዕሰ ጉዳዮች መርጠናል፡፡
በእህል ሠፈራ ያታለሉት
ቸርቻሪ ተቀጡ
ድሬዳዋ (ኢ.ዜ.አ)፡- በዓለም ማያ ከተማ ገበያ ውስጥ የእህል ቸርቻሪ ነጋዴ የሆኑት 2 ሰዎች በሚሰፍሩበት ጣሳ ውስጥ ጨርቅ ጠቅጥቀው ትልቅ በማስመሰል ገበያተኛውን ሕዝብ ሲያታልሉ በመገኘታቸው፣ 85 ብር መቀጫ እንዲከፍሉ የዓለም ማያ ፍርድ ቤት ፈረደ፡፡
አቶ ዓለማየሁ ወልደ ማርያምና ወይዘሮ ከዲጃ አደም የተባሉት እህል ቸርቻሪዎች እህል የሚሰፍሩበትን ጣሳ ጨርቅ ጠቅጥቀው ሲያታልሉ በዓለም ማያ ማዘጋጃ ቤት ሠራተኞች ቁጥጥር ስለተደረሰባቸው፣ ተይዘው ዓለም ማያ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ፤ ተከሳሾቹ ጥፋታቸው በማስረጃ ስለተረጋገጠባቸው ሰማንያ አምስት ብር መቀጫ እንዲከፍሉ ተፈርዶባቸዋል፤ ሲሉ የዓለም ማያ ማዘጋጃ ቤት ሹም አቶ ቦጋለ ሥዩም አስታወቁ፡፡
(አዲስ ዘመን ኅዳር 12 ቀን 1960 ዓ.ም)
አዲሱን የለቅሶ ዜማ የመንደር አልቃሾች ተቃወሙ
የቤተሰብን ጤንነትና አካል እንዲጠብቅ ተብሎ በፀሎት መልክ የቀረበውን አዲሱን የኅዘን ዜማ አንዳንድ የመንደር አልቃሾች መቃወማቸውን አቶ አብረሃም መኮንን በኢትዮጵያ መንበረ ፓትሪያርክ የወጣቶች አንድነት ማዕከላዊ ጽ/ቤት ዋና ፀሐፊ አስረዱ፡፡
አዲሱን የለቅሶ ዜማ የመንደር አልቃሾች ኮርስ ወስደው እንዲያጠኑ ተጠይቀው ፍቃደኞች አለመሆናቸውን ዜና ሰጪው ተናግረዋል፡፡
አዲሱ ዜማ አንድ ሰው ሲሞት በኅብረት ዝማሬ እየተዜመ ሙታንን ለመሸኘት የሚያስችል ነው፡፡
በተለይ አንድ ሰው በሞተ ጊዜ የሟች ቤተሰቦች ደረት በመደለቅ፣ ከመሬት በመፈጥፈጥ፣ ፊት በመንጨት የሚደርስባቸውን ከባድ ጉዳት የሚያስወግድና ሥርዓትና መልክ ያለው መሆኑን አቶ አብረሃም ገልጠዋል፡፡
በዚህ መሠረት ሰባት ዓይነት ልዩልዩ በኅብረት የሚዜሙ የለቅሶ ዜማዎች ተዘጋጅተውና ተፈልስፈው ይገኛሉ፡፡
ዜማዎቹን የደረሱት አቶ አብረሃም ሲሆኑ እነዚህኑ ዜማዎች በኮርስ መልክ የመንደር አልቃሾች እንዲያጠኑ 8 ያህል አልቃሾች ማነጋጋራቸውን ዜና ሰጪው ተናግረዋል፡፡
ከስምንቱ አልቃሾች ሁለቱ ወንዶች ሲሆኑ ጥቂቶቹ አልቃሾች ዜማውን ለማጥናት ኮርስ ከገባን ዜናውን እስከአጠቀርነው ድረስ በወር 25 ብር ክፈሉን በማለት አቶ አብረሃምን የጠየቁ መሆናቸውን ዜና ሰጪው አስረዱ፡፡
ቀጥለውም ‹‹ካነጋገርኳቸው ጥቂቶቹ የመንደር አልቃሾች ዘንድ ብዙ ወቀሳ ደርሶብኛል፡፡ ብላችሁ ብላችሁ በእንጀራችን ገባችሁ አሉኝ፡፡ ቄሶች በአንድ በኩል ያወግዛሉ፡፡ እኛ ሥራችን ነው በማለት ተቃውሟቸውን ገለጡ፡፡ ኮርስ ግቡና በወር 5 ብር ልክፈላችሁ አልኳቸው 25 ብር ካልሆነ ብለው ሀሳቤን ሳይቀበሉ ቀሩ›› ሲሉ አቶ አብረሃም ተናግረዋል፡፡
አዲሱ የልቅሶ ዜማ ሙታንን እንዴት መሸኘት እንደሚገባ ትምህርትና ምክር የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል። ይህም ዜማ ካሁን በፊት በደብረ ገሊላ አማኑኤል ቤተክርስቲያን ዜማውን ባጠኑ ተማሪዎች በቴያትር መልክ ተዘምሮ ታይቷል፡፡ በሁለቱም ቀኖች የተገኘው ሕዝብ በብዛት የሚቆጠር መሆኑንና በተመለከተው ሕዝብ መደገፉን አቶ አብረሃም ተናግረዋል፡፡
(አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 1974 ዓ.ም)
ሰዓት የምታቆመው ቃልቻ
የጋዜጦች ውዝግብ ፈጠረች
ቀጣፊ ናት በማለት አንድ የሌኒንግራድ ጋዜጣ የወነጀላትን ሴትዮ ታሪክ የመስኮብም ጋዜጣ ዐቢይ ወሬ አድርጓታል፡፡ የመስኮብና የሌኒንግራድ ጋዜጦች ታሪኳን የሚያበጃጁላት መካከለኛ ዕድሜ ያላት የሰዓት እንቅስቃሴ በዐይኗ የምታቆም አታላይ ቃልቻ መሆኗ ይነገራል፡፡
ፕራቮዳ የሚባለው አንድ የመስኮብ ጋዜጣ ወኪል ስለ ኔልያ ሚካሄሎቫ ባለፈው ወር የጻፈ የመጀመሪያው ጋዜጠኛ ነው፡፡ ከትናንት ወዲያም ይህችኑ ሴትዮ ከአራት ዓመታት በፊት ጀምራ የሕዝብን ገንዘብ እያታለለች ስትበላ የኖረች ቀጣፊ ቃልቻ ናት በማለት የሌኒንግራድ ፍርድ ቤት በይኖባታል፡፡ ቃል አቀባዩ በሰጠው ዜና ውስጥ ቢሆን ኖሮ የፍርድ ብያኔም ሆነ ተግሣጹ ሚካሄሎቫ ካላት እዚህ አምልኮና እምነት የለወጣት አይመስልም፡፡
የመስኮብ ፕራቭዳ ይህን ታሪክ ብልጭ ካደረገ ከአንድ ወር ወዲህ የሌኒንግራድ የምሽት ጋዜጣ ደግሞ ሚስስ ሚካሄሎቫ ከ11 ሺህ አንድ መቶ የኢ/ት ብር በላይ በማጭበርበር ከሕዝብ ሙልጭ አድርጋ የበላች መናፍስት አምላኪ አታላይ ቃልቻ ናት ብሏታል፡፡
ይኸው የሌኒንግራድ ጋዜጣ ሲያትት ተአምራቶቿን የምትሠራባቸውን ማግኔቶች (መስሕቦችን) እየደበቀ በያይነቱ የሚያቀርብላት ባሏ ነው ብሏል፡፡ ጋዜጣው የወንጀል ቃሉን አራዝሞ ሲያሰማ፤ ሴቲቱ የሰዓቷን እንቅስቃሴ የምታቆመው አንድ የኮምፓስ መርፌ ትሠራና ያንን መርፌ በፋውንቲይቴን ክዳን ውስጥ ሠውራ በማይታይ አኳኋን ከሰው ዓይን ደብቃ ነው ብሏል፡፡
የመስኮብ ፕራቭዳ ጋዜጣ ጉዳዩን በዝርዝር ለማብራራት እምቢ ቢልም፣ ተመልካቾች በበኩላቸው፤ ይህች ሴት የማግኔትነት ባሕርይ የሌላቸውን ነገሮች ዳቦ፣ የመጠጫ ብርጭቆዎችና የክብሪት እንጨቶች ታደርጋለች ሲል ይኸው ጋዜጣ ቃሉን ሰጥቷል ይላሉ፡፡
የመስኮብን ፕራቭዳ ወሬ ጫን ባለ ተቃውሞ በመጻረር፣ የሌኒንግራዱ የምሽት ጋዜጣ በሰጠው መልእክት፤ ሚስስ ኩላጊና የተባለችው ተባባሪዋ ሦስት ዓመታት ሙሉ ወህኒ ቤት ከርማ፣ በ1965 ዓ.ም እንደገና በሌኒንግራድ ላቦራቶሪ ውስጥ ገብታ በጥብቅ ተመራምራለች ይላል፡፡ በዚሁ ምርመራ አንድ የክብሪት እንጨት እንኳን መሥራት አለመቻሏ ተረጋግጧል ሲል አበቃ፡፡
(አዲስ ዘመን ጥቅምት 27 ቀን 1960 ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 27 ቀን 2017 ዓ.ም