
ቡና ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚጠጡት የአብሮነታቸው መገለጫ ነው:: ‹‹ነው አልኩ እንዴ?›› የለም የለም አሁን እንኳን ነበር ማለት ሳይሻል አይቀርም:: ምክንያቱም ከጎረቤት ጋር ቡና መጠጣት፣ ማህበራዊ ግንኙነትን ማጣጣምና ለማህበራዊ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ማምጣትኮ ድሮ ቀረ:: ዛሬ ጊዜ አግኝቶ ከማጀት ውሎ ቡና የሚያፈላ ትውልድ የለም:: ቡና የሚያፈላ ትውልድ ቢኖርም ‹‹ኑ ቡና ጠጡ›› እያለ የሚጠራራና የአብሮነት መገለጫነቱን የሚያረጋግጥ ጎረቤት ማግኘት ከባድ እየሆነ ነው::
ለዚህ ብዙዎች ሰዎች ጊዜ ከማጣታቸው ባለፈ ዋጋው እየጨመረ የመጣው የቡና ዋጋ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ይስማማሉ:: ታዲያ በዚህ ጊዜ ‹‹ኑ ቡና ጠጡ›› ብሎ የሚጠራራ ጎረቤት ማግኘት እንዴት ቀላል ይናል፤ የኢትዮጵያውያን የአብሮነት መገለጫ የሆኑ በርካታ እሴቶች እየጠፉ ያሉትም በዚሁ ምክንያት ሳይሆን ቀረ ብላችሁ ነው…
ቡና የኢትጵያውያን አብሮነት መገለጫ ለመሆኑ ብዙ ማሳያዎች አሉ:: ሰዎች ተሰባስበውና ከበው በሚጠጡት ቡና ብዙ ችግሮቻቸውን ነቅሰው በማውጣት መፍትሔ ይሰጡ ነበር:: አሁን ላይ ግን በቤት ውስጥ ከሚጠጣው ቡና በላይ በየመንገዱ የሚጠጣው ቡና በብዙ እጥፍ በልጦ አብሮነት እየተሸረሸረ ነው:: ለዚህም ሰዎች በቤት ውስጥ ከሚያሳልፉት ጊዜ በበለጠ ለሥራ ከቤታቸው ርቀው የሚሳልፉት ጊዜ የበለጠና የተለጠጠ መሆኑንም ሌላው ምክንያት ነው::
ከዚህ አንጻር አሁን ላይ ሰው ቤቱን እየኖረበት ነው ለማለት አያስደፍርም:: በተለይማ አዲስ አበቤ ገና ወፍ ሲንጫጫ ጀምሮ ሞልቶ የማይሞላውን የኑሮ ሽንቁር ለመሙላት ቤቱን ጥሎ ሲባዝን ውሎ ሲባዝን ያመሻል:: ሰማይና ምድሩ በወጉ ሳይላቀቅ ወደ ሥራ በሚተመው ሰው መንገዱን ሙሉ ያጥለቀልቀዋል:: ይህን ላስተዋለ ሰው ታዲያ በአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤት እጥረት ‹‹ይህ ሁሉ ሰው ቤት አለው?›› የሚል ጥያቄን ያስነሳል:: ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታቸው ለመድረስ ከመኖሪያ ስፍራቸው ርቀው መጓዝ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው በመሆኑ እንደ ወላጆቻቸው ሁሉ ነጋ አልነጋ ብለው ይወጣሉ፣ አመሻሽተው ይመለሳሉ::
ታዲያ እነዚህ ሰዎች ቤት ቢኖራቸውስ ቤታቸውን ኖሩበት ነው አደሩበት የሚባለው፤ መልሱን ለናንተ ትቻለሁ:: በጣም የሚገርመው ደግሞ መኖሪያ መንደሩ፣ ሥራ ቦታውና ትምህርት ቤቱ አራምባና ቆቦ የሆነባቸው አብዛኞቹ አዲስ አበቤዎች ወር እስከ ወር ተግባራቸው ተመሳሳይ ነው:: ጠዋት መውጣት ማታ መግባት::
ዕለት ዕለት በምግብ ሸቀጦች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት አሁን ላይ ፈርጣማ ክንዱን ቡና ላይ ያሳረፈ ይመስላል:: በዚህ ሁኔታ ቡና የቅንጦት መጠጥ እንዳይሆን ስጋት አለኝ። ስለዚህ ቡና አምራቹም ሆነ ቡና ነጋዴው ቆም ብሎ ሊያስብበት ይገባል እላለሁ:: ምክንያቱም ቡና ማለት ለኢትጵያውያን አነቃቂ መጠጥ ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገር ነው:: እርግጥ ነው ቡና የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት ነው:: ማህበራዊ ግንኙነትን በማጠናከር ረገድም እንዲሁ የማይተካ ሚና አለው:: ኢትዮጵያዊ በሆነ የቡና አፈላል ሥርዓት ውስጥ የሚስተዋለው ባህላዊና መንፈሳዊ እሴቶችም እንዲሁ ያላቸው አበርክቶ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለምና የቡና ዋጋ ቢረጋጋ መልካም ነው::
የዛሬን አያድርገውና የኢትዮጵያውያን የአብሮነት መገለጫ በሆነው ቡና ኢትዮጵያውያን ማህበራዊ ጉዳዮቻቸውን አንስተው ይወያዩበታል:: በውይይታቸውም አንድነታቸውን በማጠናከር ችግሮቻቸውን ሲፈቱበት ኖረዋል:: ዛሬ ዛሬ ግን ብዙ የምናተርፍባቸው በጎ እሴቶቻችን እየጠፉ የውጭ ባህል በሆነው ግለኝነት እየተወረረ እንደሆነ ይስተዋላል:: ጎረቤታሞች በጋራ በሚጠጡት ቡና ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ሳይቀር አንስተው ያወጋሉ:: በዚህም ማህበራዊ አንድነታቸውን ያጠናክራሉ:: ከሁሉም በላይ ግን ለበርካታ ማህበራዊ ችግሮቻቸው በርካታ መፍትሔዎችን ሲጋሩ ኖረዋል:: ይሁንና ዛሬ ላይ ሁሉም ነገር ነበር ሆኖ እንዳይቀር ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል::
ይህም ሲባል ከማጀት ወጥቶ አደባባይ የዋለውን የኢትጵያውያን የአብሮነት መገለጫ የሆነው ቡና ወደ ቤቱ መመለስ ይገባል:: እርግጥ ነው የጀበና ቡና በየመንገዱ ለገበያ መቅረቡ ኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው በጎ ተጽዕኖ ስለመኖሩ አይካድም:: ይሁንና ቡና አደባባይ መውጣቱ ለማህበራዊ አንድነቱ መሳሳትና ለኑሮ ውድነቱ እንደምክንያት የሚያነሱም አልጠፉም:: እርግጥ ነው አሁን አሁን አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በክልል ከተሞች ሳይቀር ‹‹ኑ ቡና ጠጡ›› የሚሉ ታፔላዎች እዚህም እዚያም ይስተዋላሉ:: ከታፔላው ስር ችምችም ብለው የተሰደሩት ስኒዎችና የሚንተገተጉት ጀበናዎችም የሰውን ቀልብ ሰርቀው እዛው አስቀርተዋል::
ታዲያ ሰው ጊዜና ገንዘቡንስ ቢያገኝ በየት በኩል አልፎ ቤቱ ቡና ያፍላ፤ ቢያፈላስ ማንን ይጥራ፤ ቡና በቤት ውስጥ አፍልቶ ከሚጠጣው ሰው በላይ በየመንገዱ ከሚንተገተገው ጀበና በስኒ እያስቀዳ የሚጠጣው ሰው ቁጥር በእጅጉ የላቀ ነው:: የአንድ ስኒ ቡና ዋጋም ከአስር ብር ተነስቶ 15፣ 20፣ 25 እያለ ቀስ በቀስ ወደ 30 ብር እየተንደረደረ በመሆኑ ልጓም ሊበጅለት ይገባል::
ያ ካልሆነ ግን የዋጋ ንረቱ ከኑሮ ውድነቱና ከጊዜ ማጣቱ ጋር ተደማምሮ የኢትጵያውያን የአብሮነት መገለጫ የቡና ጠጡ ባህል ጨርሶ እንዳናጣው ያሰጋል:: ስለዚህ አደባባይ የወጣውን ቡና ወደ ማጀት በመመለስ እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ የኢትዮጵያዊነት ልዩ ጣዕም የሆነውን ቡናን በጋራ በመጠጣት የአብሮነት መገለጫነቱን እናረጋግጥ እያልኩ አበቃሁ!”
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም