በጠዋት ተነስቼ ከቤት ወደ ሥራ ቦታ የሚወስደኝን ትራንስፖርት ለመያዝ ወደ ዋናው መስመር እሄዳለሁ:: እዚህ ቦታ ላይ ሁሌም የሚያጋጥመኝ ጽዳቶች በኃይል የሚጠርጉት እንደ ጉም ዕይታ እስከሚጋርድ የሚጨስ አቧራ ነው:: የተቆፋፈረ መሬት ለምን እንደሚጠርጉት አይገባኝም፤ ምክንያቱም የተቆፋፈረ ነውና የቱንም ያህል ቢጠርጉት አቧራው አያልቅም:: አጠገባቸው የደረሰ ሰው ሮጦ ካላለፈ ዓይናቸው እያየ እግሩ ላይ ሊጠርጉበት ይችላሉ፤ የሆነ እልህ ነገር ያለባቸው ይመስለኛል::
የሥራው ባህሪ ነውና ያ ሁሉ መንገደኛ እስከሚያልፍ ድረስ ሥራቸውን እያቆሙ ያሳልፉት የሚል ጅልነት የለኝም:: እነርሱ ሥራቸውን እየሠሩ ነው:: ዳሩ ግን በዝግታ ሲጠርጉ የነበሩ ሰዎች ልክ መንገደኛ አጠገባቸው ሲደርስ ኃይላቸውን ጨምረው ወደ መንገደኛው እግር ሥር የሚጠርጉ አሉ:: መንገደኛው እንዲናገራቸው የሚፈልጉ ሁሉ ይመስለኛል:: ከዓመታት በፊት ያጋጠመኝን አንድ ገጠመኝ ላንሳ::
ወደ ሥራ ቦታ ለመሄድ ስጣደፍ ወደ ዋናው መስመር የሚያስገባው ቀጭን መንገድ ላይ ጽዳቶች ያጸዳሉ:: መጥረጊያው በሌለበት በኩል ላልፍ ስል በምን ቅጽበት እንደዞረች አላውቅም (ሆን ብላ አይመስለኝም) ልክ ስራመድ መጥረጊያው የምረግጠው ቦታ ላይ አረፈ:: ይህኔ የመጥረጊያዋን ጫፍ ረገጥኩት:: ደንግጬ ‹‹ይቅርታ!›› ስል፤ ጽዳቷ ግን እንደ ጉድ አበደች:: የነውረኝነቷ ነውረኝነት መጥረጊያውን አዙራ በእንጨቱ በኩል ልትመታኝ ሲገባ (ምንም እንኳን ይሄም ነውር ቢሆንም) ቆሻሻና አቧራ ስትጠርግበት በነበረው ጫፉ ጀርባዬ ላይ መታችኝ፤ እንደ ልመናም እንደ ቁጣም እያደረኩ ‹‹ኧረ እባክሽ…..›› ስል በዚያው በቆሻሻው በኩል እግሬ ላይ መታ አደረገችኝ:: ዋና ፍላጎቷ አቧራና ቆሻሻውን በደንብ መበካከል መሰለኝ:: ይህ ስሜቷ የመጣበት ሆን ብዬ ስለረገጥኩት መስሏት መሰለኝ::
እሷ ይህን ስታደርግ ጓደኞቿ ይቆጧታል ብዬ ነበር:: ጭራሽ መጥተው የራሳቸውን ብሶት እየተናገሩ ከበቡኝ:: ‹‹እኛን እዚህ እንደ እንትን ነው የምታዩን….›› አይነት ብሶት እያወረዱ ‹‹ደግ አደረገችህ!›› አይነት ቁጣ ይቆጣሉ:: ምንም እንኳን ያደረገችው ነገር እጅግ በጣም ነውር ቢሆንም ሆድ የባሳት መሆኑ ስለገባኝ ጭክን ብዬ ሽሽት በሚመስል ሁኔታ ፍጥነቴን ጨምሬ፣ የሚንጫጩትን የማልሰማ መስዬ ሄድኩኝ::
በዚሁ በትዝብት ዓምድ ደጋግሜ እንደገለጽኩት እንደ ጽዳት ሠራተኞች የሚያሳዝነኝ የለም:: ማንም ያበላሸውን ነገር እንደ ማስተካከል የሚያሰለች ሥራ አይኖርም:: ‹‹እንዲያው ልጆቻቸውን ያስተምሩ ይሆን?›› ብዬም አውቃለሁ:: ምክንያቱም ‹‹የተማረ ሰው እንደዚህ የሚሆን ከሆነ ልጆቻችንን ለምን እናስተምራለን?›› የሚሉ ይመስለኛል:: በተለይ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ የጽዳት ሠራተኞች ማለቴ ነው::
በዚያ ላይ በጣም አማኝ እና ሥልጡን ናቸው:: ‹‹ይህን ያህል ሺህ ብር ወድቆ አግኝተው አስረከቡ….›› የሚል ዜና የምንሰማው ከጥበቃ እና ከጽዳት ሠራተኞች ነው:: አንዲት የጽዳት ሠራተኛ ወድቆ ያገኘችውን ብዙ ሺህ ብር ወደ ኪሷ ብትከተው ማንም የኔ ነው ብሎ ሊከራከራት አይችልም:: ዳሩ ግን ታማኝነቷ ለማንም ሳይሆን ለህሊናዋ ነው:: ይህ በሠለጠኑት ሀገራት የምንሰማው ልማድ ነው:: በኢትዮጵያ ግን ‹‹የተማረ›› ከሚባለው(በተግባር ግን መሐይም) ክፍል ይልቅ በጽዳት ሥራ ላይ የተሰማሩት ሥልጡን እና የህሊና ሰው ናቸው::
ያም ሆኖ ግን አንዳንድ ብሶተኞች ደግሞ አሉ:: በተለይ ጠዋት ጠዋት ጎዳና የሚያጸዱ ሠራተኞች ለምን እልኸኛና ብሶተኛ እንደሚሆኑ አይገባኝም:: ቀደም ሲል እንዳልኩት መንገደኛውን ሁሉ መጥረጊያ አቁመው ያሳልፉ እያልኩ አይደለም፤ ዳሩ ግን ሰው አጠገባቸው ሲደርስ የበለጠ ኃይል ጨምረው ወደ እግሩ ሥር የሚያጨሱት ለምን ይሆን?
በመጥረጊያው በኩል የመታችኝ ሴትዮ ሆን ብላ ልብሴን ለማበላሸት ነው:: ይህ ስሜት የመጣባት አቧራ እንዳይነካኝ መጠንቀቄ አናዷት ይመስለኛል:: ‹‹እኛ እንዲህ አቧራ ውስጥ ሆነን እየሠራን እሱ ጫፉ እንኳን እንዳይነካው….›› በሚል ስሜት ነው:: የመፀየፍ እና የመናቅ አድርጋው ነው:: ሥራዬ ግን ምን እንደሆነ አታውቅም::
የብዙዎቻችን ችግር የሥራ ባህሪ አለማወቅ ነው:: ለምሳሌ፤ የኔ ሥራ ከደንበኛ ጋር የሚያገናኝ የቢሮ ሥራ ነው እንበል:: ስለዚህ በዚህ የሥራ ቦታ የቆሸሸ ልብስ ለብሼ መታየት የለብኝም:: የሥራው ባህሪ እንደዚያ አይደለማ! ያቺ ጽዳት ዘናጭ ልብስ ለብሳ፣ ሂል ጫማ አድርጋ፣ ሜካፕ ተቀባብታ ብታጸዳ መሳቂያ ነው እንጂ የምትሆነው ማራኪ አትሆንም፤ የሥራው ባህሪ አይደለማ!
አንድ የባንክ ሠራተኛ ከራቫቱ ሁሉ ሳይቀር በጭቃ ወይም በአቧራ ወይም በሌላ ቆሻሻ ነገር ተበላሽቶ መስኮት ላይ ተቀመጠ እንበል:: አንዲት የጽዳት ሠራተኛ ሥራዋን ጨርሳ፣ የክት ልብሷን ለብሳ፣ ዘንጣ ይህ ሰው የሚሠራበት ባንክ ሄደች እንበል:: ይህ የባንክ ሠራተኛ እንደዚያ ተበለሻሽቶ ብታገኘው መገረሟ ይቀራል? የሥራው ባህሪ አይደለማ! ጠዋት በአጠገቧ ሲያልፍ አቧራ እንዳይነካው ሲጠነቀቅ ብታየው ግን ተናድዳ ይሆናል:: እሷ እዚያ ቦታ ላይ አቧራ የምታጨሰው የሥራው ባህሪ ስለሆነ ነው::
ይህንን ላለማመን ግን አንድ ሙግት አለባት:: የሥራ ባህላችንና አመለካከታችን ኋላቀር ስለሆነ ሥራን የደረጃ መለኪያ አድርገነዋል:: ጽዳት መሥራት እንደ ዝቅተኛ፣ ቢሮ መዋል ግን እንደ ትልቅ ስለሚታይ ነው:: በዚህ ዘመን ግን ይህ አይሰራም:: አንድ ተደራራቢ ዲግሪ ያለው፣ የዓለምን ጓዳ ጎድጓዳ የሚያውቅ፣ የሳይንስን ምሥጢራት የሚተነትን… ‹‹ጽዳት አጽዳና ይህን ያህል ሺህ ብር ይከፈልህ›› ቢባል ዓይኑን አያሽም:: ምክንያቱም ሥራ ነዋ! ዋናው ነገር የሚያስገኘው ውጤት ነው:: በሠለጠነው ዓለም እንደዚህ ነው!
እዚህ ላይ የአትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴን ገጠመኝ መጥቀስ የግድ ይላል:: ዓለም አቀፉ ኃይሌ በአውሮፓ አንድ ቅንጡ ሆቴል ውስጥ አርፎ ከጽዳቷ ጋር ሃሳብ ይለዋወጣሉ:: በጨዋታ መሃል ጽዳቷ የሆቴሉ ባለቤት እህት መሆኗን ትነግረዋለች:: ‹‹ወሬ አማረልኝ ብዬ›› ይላል ኃይሌ ራሱን ሲወቅስ:: ‹‹ወሬ አማረልኝ ብዬ እንዴት የዚህ ትልቅ ሀብታም እህት ሆነሽ ጽዳት ያሰራሻል? አልኳት›› ይላል:: ኃይሌ ይህን ገጠመኙን የተናገረው የሥራ ባህልና አመለካከታችን ኋላቀር መሆኑንና ከሠለጠኑት ሀገራት የቀሰመውን ልምድ ለመናገር ነው:: በሠለጠኑት ሀገራት እንዲህ አይነት የሀብታም ቤተሰብ ሆኖም የጽዳት ሥራ ይሠራል::
በጽዳት ሥራ ላይ አቧራና ጭቃ የያዘ ልብስ የሚለበሰው የሥራው ባህሪ ስለሆነ ነው:: የጋራዥ ሠራተኛ ጋዝና ጥላሸት ያጠቆረው ልብስ የሚለብሰው የሥራው ባህሪ ስለሆነ ነው:: መምህር የጠመኔ ዱቄት ተለቅልቆ የሚወጣው የሥራው ባህሪ ስለሆነ ነው:: ሁሉም በየራሱ ውበት ነው:: የደረጃ መለኪያ ሳይሆን የሥራ ባህሪ መገለጫ ነው::
ለምሳሌ፤ አንድ ሐኪም ዓለም ላይ አለ የሚባል ብራንድ ሸሚዝ ለብሶ ከአልጋ ክፍል ወደ አልጋ ክፍል ቢሄድ፤ ምንም የሐኪምነት ግርማ ሞገስ አይኖረውም:: የሐኪምነት ግርማ ሞገሱ የሚመጣው ነጭ ጋዎን ለብሶ፣ በኪሱ ወይም በአንገቱ ከህክምና ጋር የተያያዙ መሳሪያዎች ይዞ ሲዞር ነው:: የአንድ ወታደር ውበት ሬንጀሩን ሲለብስ ነው:: ስናየው አንዳች ሀገራዊ ስሜት ውርር የሚያደርገን በቀልጣፋ አቋሙ ሬንጀሩን ለብሶ ስናየው ነው:: ይህ ወታደር በዓለም ላይ አለ የሚባል ውድ ሱሪ ለብሶ መንገድ ላይ ብናየው ግን ከምንም አንቆጥረውም::
ችግሩ ግን አዕምሯችን ላይ በተቀረጸ ኋላቀር ልማድ የያዙትን ሥራ ከማክበርና በሥራው ከመኩራት ይልቅ ‹‹እኔ እንደዚህ ስለሆንኩ ነው…›› የሚል ስሜት ይፈጠርብናል:: ሥራን የደረጃ መለኪያ የማድረግ ባህል አልፎበታልና የሥራ ባህሪ እንወቅ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም