ሆድና እግር

እንደወትሮዬ ሁሉ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ አልጋዬ ላይ ጋደም ብዬ ከሸገር ራዲዮ “ጨዋታ” የተሰኘውን ዝግጅት እያዳመጥሁ ሳለ ገርበብ ያደረግሁት በሬ ተንኳኳ፤

“ማነው?” “እኔ ነኝ!” አይኖቼን ስወረውር በቀጭን አንገት ላይ የተሰካና፣ ባላቶሊ ፀጉር “ስታይል” ተቆርጦ ብቅ ያለ ጭንቅላት በበሩ ግርበብ ታየኝ።

“ቲቸር ጲላጦስ ሮናልዶ ነኝ ልግባ?” “ግባ!” ገባ። ተቀመጥን ሳይጠብቅም ካልጋዬ ትይዩ ካስቀመጥኩት ብቸኛው ወንበሬ ላይ ተሰቀለ። ቀጭ የሰነጣጠቃቸው ረጃጅምና ሞጋጋ ቅልጥሞቹ ባየር ላይ ሲንጠለጠሉም ሸፋፋና አረንጓዴ ኤርገንዶ ጫማዎቹ ተንሸራተው ወለቁና አቧራ የጠገቡትና እንቅፋት ያጎነቆላቸው እግሮቹ ተጋለጡ። “ምን ፈልገህ ነው ሮናልዶ?” “እንትን . . . ማለቴ እ . . . እንትን . . .”

“እንትን ፈልጌ እ . . . ምንድነው? እንትን . . .”መሬት የራቃቸው እግሮቹን ማወዛወዝ ቀጠለ። እኚያ ሞጋጋ ቅልጥሞቹ በሰፊው ቁምጣው ውስጥ ሲታዩ ከጎላ ድስት ውስጥ ቁሌት የሚማሰልበት ማማሰያ ይመስላሉ። ሮናልዶ ቀንደኛ የማንችስተር ደጋፊና አፍቃሬ ክርስቲያን ሮናልዶ ነው። በካልሲ ኳስ አብዶ ሲሠራም ለጉድ ነው። በዚህም ምክንያት የቆሎ ጓደኞቹ ሮናልዶ አሉት። እንጂማ ቤቶቹ ያወጡለት ስም ተስፋዬ ነው። ተስፋዬ መክቴ። ከጀርባዋ ሮናልዶ ብሎ በተንጋደደ አማርኛ ፊደል በቀይ እስኪብርቶ የጻፈባት፣ ፀሐይ ያወየባትና ሲያወልቃት ታይቶ የማይታወቅ አዳፋ ቢጫ ካናቴራ አለችው። አንድም ቀን አውልቋት አይቼው አላውቅም። ተማሪ ቤት ሲሄድ ከደንብ ልብሱ ስር፣ ቤትና ሰፈር ሲውል ደግሞ ከጠሟጋ ገላው በላይ ትውላለች። ራዲዮ ማዳመጤን እንዳያናጥበኝ ስለፈለግሁ፣

“ሮናልዶ እስኪብርቶ አስፈለገህ እንዴ?”

“ኧረ ባለፈው ያሻርከኝ አለ ቲቸር ጲላጦስ”

“ታዲያ. . . የሒሳብ ማሰቢያ ወረቀት?”

“ኧረ አባቴ ይሙት ነፍ አለኝ!” የቀኝ አውራ ጣቱን ቆልምሞ አገጩን እየነካ።

ሮናልዶ የ4ኛ “ሐ” ክፍል ተማሪ ነው። እኔ ደሞ የክፍል መምህሩና ጎረቤቱ ነኝ። ጎረቤቱ በመሆኔ በጣም ይኮራል። ታዲያ ከክፍል ወደ ክፍል ሲያልፍ፣ ያባቱ ወዳጆች፣ “አንተማ እድሜ ለቲቸር ጲላጦስ በል!” ይሉታል። “እንዴት?” “ሮናልዶን ቀጥ አርጎ ይዞልሃል”

“አዎ ቲቸር ጲላጦስ እግዚሐር ዕድሜና ጤና ይስጠው!” ይላል መክቴ። ግን ለሮናልዶ ይሄን ያህል የሚያስመሰግን

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም

ገጽ 8

ዓለም አቀፍ

መዝናኛ

የብዕር ጠብታ

ነገር አድርጌለት አልነበረም። ያቺው አንዳንዴ የስኪብርቶና የእርሳስ ምፅዋቴ ናት፤ ግፋ ቢል ጊዜ ሳገኝ ያልገባውን አሳየዋለሁ፤ በቃ።

ሮናልዶ ግን መላ ቀልቡ ማንቸስተርና ክርስቲያኖ ሮናልዶ ላይ በመሆኑ በቀኙ የሰማውን በግራው ያፈሳል።

አንድ ቀን ምርር ሲለኝ፣

“ሮናልዶ!” ጮኩበት

“አቤት ቲቸርዬ” “እንዳባትህ መሆን ትፈልጋለህ?”

“ማለት?”

“አባትህ የሰው በር የሚጠብቀው ስላልተማረ ነው”

ሰላላ አንገቱን በገባኝ ወዘወዘ።

“ስታድግ የማንንም መሐይም ሀብታም በር መጠበቅ ትፈልጋለህ?” “አልፈልግም!”

“እና?” ” እንደሮናልዶ ኳስ ተጫዋች መሆን ነው የምፈልገው፣ ለዚያውም የማንቼ! እነ ቼልሲ አርሴ ምናምን እንቅጠርህ ብለው ቢያባብሉኝ ግን አልሰማችሁም ነው ምላቸው!”

“ስማኝ እንደሮናልዶ ለመሆንም እኮ በትምህርትህ ጎበዝ መሆን አለብህ”

“ኳስ ለማንከባለል ትምህርት ምን ያረጋል፣ ቡሌ እንጂ፣ ፀዳ ያለ ቡሌ ባገኝ ጡንቻዬን አዳብርና ከዚያ እንደሮናልዶ እሆን ነበረ፣ በነገራችን ላይ ጋሽ ጲላጦስ ዛሬ ጌም አለ፣”

“ሮናልዶ ኳስ ላት አይሆን ባት ምንያረግልሃል ዋናው ፊደል ነው ወዳጄ” “ግን ቀውጢ ጨዋታ ነው ጋሽ ጲላጦስ እግዛቤርን፣ የናቴን ቀን ይስጠኝ!” እናቱ እሱን ስትወልድ ነው እስከወዲያኛው ያሸለበችው፤ ምጡ ጠንቶባት ነው ይባላል። እንደናትም እንዳባትም ሆኖ ዘጠኝ ዓመት ሙሉ ያሳደገው አባቱ ነው፣ መክቴ። የሰው በር እየጠበቀ::

“ሮናልዶ መክቴ አያሳዝንህም?” “አያሳዝነኝም!”

“ለምን?” “አረቄውን ሲጠጣ እኔን ይረሳኛል፣ አሁንማ ምርር ነው ያለኝ፤ ውጭ ሀገር የሚወስደኝ ባገኝ ጥርግ ብዬ እሄድ ነበረ”

“መክቴን ጥለህ ሮናልዶ?” “የራሱ ጉዳይ! ግን ውጪ ሄጄ እንደሮናልዶ የማንቼ ተጫዋች ከሆንኩ ያለሁበት ሀገር እወስደዋለሁ፣”

“አልፈልግም ካለስ?” “መቼስ አልፈልግም የሚለው ውጭ ሀገር አረቄ የለም ብሎ ነው አይደል? እንደዚያ ከሆነ እዚህ ያረቄ ፋብሪካ እከፍትለታለኋ!”

“ወይ ሮናልዶ!”

“ጋሽ ጲላጦስ ዛሬ ጌም አለኮ”

“ማ ከማ?”

“ማንቼና ማድሪድ ብዬህ ነበረኮ”

የኳስ ፍቅር ስለሌለኝ የሚላቸውን ቡድኖችም ሆነ ተጫዋቾች አላውቃቸውም። እሱ ግን አብጠርጥሮ ያውቃል። እነርሱ ግን እስከነመፈጠሩስ ያውቁ ይሆን? . . . እንደሚወዳቸው፣ ሕልሙና ቅዠቱ እነርሱ ብቻ እንደሆኑስ? . . . በጭራሽ አያውቁም!! እንኳንስ እሱን የሰው በር ጠባቂ አባቱን መክቴን አያውቁትም፣ እኔን የክፍል መምህሩ ጋሽ ጲላጦስን ጭምር። . . . እሱ ግን የሚበሉትን የምግብ ዓይነት፣ ሳምንታዊ ገቢያቸውን፣ መዝናኛቸውን፣ ሞዴልና አክትረስ ፍቅረኞቻቸውን፣ ያለፈና ያሁን ታሪካቸውን . . .

“ሮናልዶ” “አቤት ጋሽ ጲላጦስ”

“ስላገርህ ኢትዮጵያ ታሪክ ምንታህል ታውቃለህ?”

“ታሪክ ሆድ አይሞላም ጋሽ ጲላጦስ!”

“ታዲያ ስለነማንቼ ማወቅ ነው ሆድ የሚሞላው?”

“ቢሞላማ ነው ጠቅላላ ሬዲዮና ቲቪው ስለነሱ ነጋ ጠባ የሚለፈልፈው”

ዝም አልኩ። ሮናልዶ “ሀትሪክ” አስገባልኝ።

ምንድነው ያለው?. . . “ታሪክ ሆድ አይሞላም!” እውነቱን ነው “ታሪክ ጭንቅላት እንጂ ሆድ አይሞላም! ”

የሮናልዶ ጥያቄ መሠረታዊ ጥያቄ ነው፣ የሆድ ጥያቄ። ሰው ደሞ መሠረታዊ ጥያቄው ሳይመለስለት አክሱም ላሊበላ ቢባል ትርፉ የገደል ማሚቱ ነው።

“እህህህ . . . ” ሮናልዶ ቀኬ ያዛገው ጉሮሮውን ሞረደ። በሐሳብ ጭልጥ ማለቴን ሲያይ እንድሰማው ፈልጎ ነው።

“አቤት የዛሬው ጌም ቀውጢ ነው ጋሽ ጲላጦስ”

“ቀውጢ ስትል?”

“የጨሰ ለማለት ፈልጌ ነው”

“እንዴት?”

“ክርስቲያን ሮናልዶኮ ድሮ ለማንቼ ነበረ የሚጫወተው”

“ዘንድሮስ?”

“ዘንድሮማ ለማድሪድ ስለሆነ ከእናት ክለቡ ጋ ሲጫወት አገር ቀውጢ ይሆናል!”

“ባሸባሪነት አይያዝም?” “ማ?”

“ክርስቲያን ሮናልዶ?” “ለምን?”

“ሀገር በሱ ምክንያት ቀውጢ ሲሆን?” እስኪያስለው በሳቅ ተንፈራፈረ። ረጅም ሳቅ፣ የሚያባራ የማይመስል። በባዶ አንጀት ሳቅ እንዴት ይቻላል? . . .

“ጋሽ ጲላጦስ”

“አቤት”

“እዚያ አስፋልቱ ዳር አዲስ የተከፈተው ካፌ የለም?”

“አለ” “ዲሽ አላቸው” “የምን ዲሽ?”

“እግር ኳሱ የሚታየውኮ እዚያ ነው”

“የምን እግር ኳስ?”

“የማንቼና የማድሪድ ነዋ!”

“እህህህ . . . የማ ደጋፊ ነህ አንተ?”

“የማንቼ ነኛ ግን ሮናልዶንም ስለምወደው ማድሪድ ቢያሸንፍም ጣጣ አይሰጠኝም”

ሮናልዶ ከሚበላበት የማይበላበት ቀን ይበልጣል። ትምህርት ቤት ከሚሄድበት የማይሄድበት ጊዜ ይብሳል። እርሙን ቢሄድ ደሞ፣ ቢጤዎቹ “አፍህ ይሸታል!” ብለው ያገሉታል። ግና እንደነሱ በጠዋት በፍርፍር ሆዱን ቆዝራ የምሳ ሰሃን ቋጥራ የምትሸኘው እናት እንደሌለው ማን ያስተውላል? . . . ዘበኛ አባቱ መክቴ የካቲካላ መለኪያውን የሚያስታውሰውን ያህል ሮናልዶን ልብ እንደማይለው ማን ይረዳል? ይሁንና ሮናልዶ አንድም ቀን ይርበኛል የሚል ቃል ሲናገር ሰምቼው አላውቅም። ምን ያደርጋል ታዲያ የሆዱን ባዶነት እንዳይናገር አፉን ቢለጉመውም፣ አሳባቂ ገመምተኛ ፊቱን፣ ጭው ያሉ ዓይኖቹን፣ ኩበት ከናፍሮቹንና ከባዶ አፉ የሚወጣ ጠረኑን መደበቅ አይችልም።

“ታዲያ ጨዋታውን መመልከት ፈልገህ ነው ሮናልዶ?”

“አዎ፣ ግን በነፃ አያሳዩም፣ በብር ነው”

“ስንት ይላሉ?”

“አምስት ብር”

“አምስት ብር?” “አዎ”

“ሮናልዶ”

“አቤት”

“ከነጋ እህል ባፍህ ዞሯል?”

“አዎ፣ አይ፣ አዎ፣ አይ፣ አዎ፣ ማለቴ . . .” ከተጋደምኩበት ተነሳሁና አንድ ኮሳሳ የተደፈጠጠ ዳቦ አንግቦ ግድግዳ ላይ ከተሰካ ምስማር ላይ ከተንጠለጠለ ፌስታል አውርጄ፣ “እንካ በውኃ እያማግህ ብላ”

“በልቻለሁኮ ቲቸር ጲላጦስ”

ጉልበቱ ላይ አስቀምጬለት አልጋዬ ላይ ተመልሼ በጀርባዬ ተጋደምኩ።

በዳዊት ወርቁ (ጥቅምት 2005 አዲስ አበባ ኢትዮጵያ)

አዲስ ዘመን ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You