ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ፈረንሳይ ለጋሲዮን በሚባለው አካበቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው ምስካየህዙናን መድሃኒያለም ገዳም ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ የካቲት12 (መነን) ትምህርት ቤት ውስጥ ነው የተከታተለው። ዩኒቨርሲቲም በቀጥታ የገባው ጎረቤት በሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስድስት ኪሎ ጊቢ ነው።
እዛም በቋንቋና ስነፅሁፍ ከዚያም በጋዜጠኝነትና ኮምዩኒኬሽንም ተምሯል። ከትምህር ቤት እንደወጣም በቀጥታ ወደ ማስተማር ስራ ገብቷል። ግን ደግሞ እሱ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ወቅት የነበረው የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ባልጠበቀው መልኩ የማስተማር ስራውን በመተው ወደ ፖለቲካው መስመር እንዲገባ ምክንያት ሆኖታል።
በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ በአንደበተ ርዕቱነታቸው ስማቸው ጎልተው ከሚጠቀሱ አባላት መካከል አንዱ ነው። በተለይም በ2007ዓ.ም አገር አቀፍ ምርጫ ወቅት ፓርቲውን ወክሎ የኢህአዴግን ተፎካካሪዎች ወጥቶ የሚሞግት ጠንካራ ወጣት ስለነበር በብዙዎች አእምሮ የማይዘነጋ ግለሰብ ነው።
ይኸው ወጣት ፖለቲከኛ በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጓል። ከአንድ አመት በፊትም ከስድስት ዓመት የእስር ቤት ቆይታ በኋላ በምህረት ተለቋል። የዛሬው እንግዳችን የቀድሞው የሰማያው ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃሃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ነው። ከእሱ ጋር ያደረግነው ቆይታ እንደሚከተለው እናቀርበዋለን።
አዲስ ዘመን፡- የልጅነት ህይወትህን እስቲ አስታውሰን?
አቶ ዮናታን፡- እናትና አባቴ ከአዲስ አበባ ውጭ በሆነ አካባቢ ነው ትውልዳቸው። ቤተሰቦቼ የተገናኙት በሃይማኖታዊ በሆነ ማህበር ውስጥ ነው። ሁለቱም የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እንደመሆናቸውና መንፈሳዊ ህይወታቸውም ጠንካራ የሚባል ስለነበር በተቻላቸው መጠን እኔና እህቴን በስነምግባር ታንፀን እንድናድግ ጥረት አድርገውልኛል። በተለይ እኔን በማሳደግ ውስጥ የእግዚአብሄር ፀጋ አልተለያቸውም የሚል እምነት ነው ያለኝ። ምክንያቱም አመፀኛና ግትር የምባል ልጅ ስለነበርኩ ነው።
ከዚያ በተረፈ ግን አስተዳደጌ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልጅ ጭቃ አብኩቼ አፈር ፈጭቼ ነው።የቤተሰቦቼ ዋነኛ ፍላጎት ሰው እንድሆን ብቻ ነበር። እነሱ ከወጡበት ማህበረሰብ በተሻለ ሁኔታ እንድንኖር ነበር ዋነኛ መሻታቸው። በተለይ ደግሞ ቅድም እንዳልኩት እነሱ በመንፈሳዊ ህይወታቸው ጠንካራ ስለነበሩ ክርስቲያናያዊ ህይወት እንዲኖረን በተለይ ደግሞ ሰው ለማገልገል ቅድሚያ እንድንሰጥ ይመክሩን ነበር። ሰንበት ትምህርትንም እከታተል ስለነበር አብዛኛውን የልጅነት ህይወቴ ከመፅሀፍ ቅዱስ ጥናት ጋር የተያያዘ ነው። የሚገርመው እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ሌላ መፅሃፍ እንዳነብም አይፈቀድልኝም ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ግን ደግሞ ከዚያ ከመሰለ መንፈሳዊ ህይወት ውስጥ ወጥተው ወደ ፖለቲካው ዘው ብለህ ገብተሃል?
አቶ ዮናታን፡- ወደ ፖለቲካ ውስጥ ዘው ብዬ ገብቻለሁ ለማለት ይከብደኛል። በተለይ የመሰናዶ ተማሪ እያለው በ1997ዓ.ም እና 1998ዓ.ም አካባቢ በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ መንፈስ በተለይም ደግሞ አፍላም ስለነበርኩ ስሜቴን የሚገዙ የተለያዩ ትችቶችን እሰማ ነበር። ያን ጊዜ ነበር ቀልቤንም ሆነ ጆሮዬን ለአገራችን ፖለቲካ መስጠት የጀመርኩት። በእርግጥ ቀደም ብለው የነበሩት እንደ ጦቢያ የመሳሰሉ ጋዜጦች አባቴ ገዝቶ ይመጣ ስለነበር አነብ ነበር።
በ1997 ዓ.ም የምርጫ ቅስቀሳና በአደባባይ ስብሰባዎች ሲደረጉ በተቻለኝ መጠን እከታተል ነበር። የምማረውም ስድስት ኪሎ በሚገኘው መነን ትምህርት ቤት ስለነበር አካባቢው ለተማሪዎቹም ሆነ ምሁራን በብዛት የሚገኙበት እንደመሆኑ እኔም ከአንዳንዶቹ ጋር ቅርበት ነበረኝ።
በዚህም ምክንያት ስለፖለቲካ የነበረኝ ግንዛቤ እያደገ መጥቷል። እናም 1997ዓ.ም ምርጫ ሲካሄድ የቅንጅት ቅስቀሳውና አጠቃላይ የፖለቲካ ፓርቲው የፉክክር ሂደት የብዙዎቻችንን ቀልብ ገዝቶ ስለነበር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር በመሆን የተለያዩ በራሪ ፅሁፎችን በመበተን ተሳትፎ አደርግ ስለነበር ያን ጊዜ ነው ስሜቱ የተጋባብኝ ብዬ አስባለሁ።
ከዚያ በኋላ በነበረኝ ሂደት ደግሞ ሁሉም ነገር ጨለማ ሲሆንና ድብታ ውስጥ ስንገባ በአብዛኛው ሳይኮሎጂ መፃሃፎችን አነብ ነበር። እያደር ግን ነገሮች እየባሱና እየከፉ መሄዳቸው እኔን አይደለም ማንም ሰው ሳይወድ በግዱ ፖለቲካውን ወደ መቃወም ይገባል። በእኔ እምነት እኔም ሆንኩ ሌሎች ወጣቶች ፖለቲካው በአግባቡ ገብቶን ወይም ደግሞ በዛ ውስጥ መኖር ፈልገን አልነበረም እንቅስቃሴ ስናደርግ የነበረው። የነበረው አፈና እንደዚህ ያለውን ስርዓት ተሸክመን መሄድ አንችልም ከሚሉ ወገኖች ጋር የተወሰነ እንቅስቃሴ አደርግ ነበር።
ከእንዲህ አይነት ኑሮ ነፃነት የምታስከፍለውን ዋጋ መክፈል እንደሚገባን እናምን ነበር። በተለይ በ2001ዓ.ም አካባቢ ይመስለኛል በፌስቡክ የተለያዩ አስተያየቶችን እፅፍ ነበር። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ካረፉ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አገሪቱ ያስተዳድሩበት የነበረው መንገድ ፖለቲካውን ከድጡ ወደ ማጡ አደረገው። የነበረውን የአፈና ቀንበር መሸከም ባለመቻላችን ለነፃነታችን ስንል ተደራጅቶ መታገልን መረጥን።
በግሌ ግን ማንም ሰው የራሱን ሃሳብ እንዲጭንብኝ ስለማልፈልግ መንግስት በፅኑ እቃወም ነበር። በመጨረሻም 2008ዓ.ም ላይ ስታሰርም አንዱ ክስ ሆኖብኝ የመጣው ስለእኔም ሆነ ስለህዝቡ ነፃነት በይፋ መንግስትን መቃወሜ ነው። ዛሬ ላይ በወቅቱ እኛ ስናነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎች በጥቂቱም ቢሆን እየተመለሰ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- እስቲ እግረ መንገድህን ወደ ሰማያዊ ፓርቲ የገባህበትን አጋጣሚና የነበረህን ቆይታ አጫውተን?
አቶ ዮናታን:- ፓርቲው ሲጀመር እንግዲህ የራሱ ታሪክ አለው። እኔ ግን የምነግርሽ መሳተፍ ከጀመርኩ ወዲህ የማውቀው ነው። አስቀድሜ እንዳልኩሽ የነበረውን እንቅስቃሴ በቅርበት ከመከታተል አልፌ የእዛ እንቅስቃሴ አካል መሆን እንዳለብኝ ስለተሰማኝ ሰማያዊ ፓርቲ በሚያካሂዳቸው መድረኮች እገኝ ነበር። ከዚያ ፓርቲው በሚያደርጋቸው ሰልፎችና ስብሰባዎች ላይ መሳተፍ ጀመርኩ።
በፓርቲው ውስጥ ለመብታቸው ቀናኢ የሆኑ፤ ለዛም ደግሞ ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ የሆኑ ወጣቶች በብዛት ነበሩበት። በተለይ ከ1997ዓ.ም ምርጫ በኋላ የነበረውን የፖለቲካ ድብታን የመግፈፍና ሰውን የማነቀቃት፥ ወደ ፖለቲካ ተሳትፎ እንዲገባ የማድረግ መብቱን እንዲጠይቅ፤ አፈናን አልሸከምም እንዲል የማነሳሳት ስራ ነበር ስንሰራ የነበረው።
በወቅቱ ወደ ፓርቲው የሚመጡ የነበሩት በጣም የቆረጡ የደፈሩ ወጣቶች ብቻ ነበሩ። ስለዚህ ከእነሱ ጋር መታገል አማራጭ ሳይሆን ግዴታ የሆነበት ሁኔታ ነው። በዚያ መሰረት ከነበረኝ ተሳትፎ አንፃር ቶሎ ነበር ወደ ኃላፊነት ቦታ የመጣሁት። መጀመሪያም በወጣቶች ጉዳይ ስራ አስፈፃሚ ሆኜ በኋላም ቃለአቀባይና ህዝብ ግንኙነት ሆኜ ለፓርቲው ሰርቻለሁ። 2007ዓ.ም በነበረው ምርጫ ስንገባም ብዙ መውደቅ መነሳት ነበር። ብዙ ወንድሞቻችን ጥቃት ደርሶባቸዋል፤ ተደብድበዋል።
ምርጫው እየተቃረበ ሲመጣ ደግሞ ፓርቲው ውስጥ ልዩነት ይታይ ጀመር። አንዳንዶች ልክ ጤናማ ፖለቲካ ሁኔታ እንዳለ አይነት ቆጥረው ፓርላማ ውስጥ የመግባት ፅኑ ፍላጎት ነበራቸው። ስለዚህ ምርጫውን ህዝቡን የማንቃት አካልና የነፃነት ትግሉን የሚያጣጥፉበት አንድ ቀዳዳ አድርገው ይቆጥሩ ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ ቀዳዳዎች ሁሉ ተደፍነው ስለነበር ነው። እነዚህ ሰዎች ፓርቲውን ምርጥና የበቃ ተፎካካሪ ድርጅት አድርገው የሚያስቡ ነበሩ። በዛ ውስጥ ደግሞ እኔን ጨምሮ የተወሰኑ ሰዎች ሃሳቡን ተቃርነን ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ሃሳቡን ተቃርነን ነበር ስትል ምን ማለትህ ነው? ምንስ ነበር የእናንተ ፍላጎት?
አቶ ዮናታን፡- እኛ ምርጫውን ህዝቡን የማንቂያ ደውል አድርገን ነበር የምንቆጥረው። መንግስት ለስሙ የፈጠረውን የመወዳደር እድል ተጠቅሞ ትግሉን ማፋፋም ይገባል የሚል እምነት ነበረን። በአጠቃላይ ስርዓቱ አፋኝ ነው ብለን ስለምናምን ስርዓቱን የማስወገድ አጀንዳ አንድ መንገድ አድርገን ነበር የምንቆጥረው። ሌላው ቡድን ግን ዋና አላማቸው ፓርላማ የመግባትና የመታገል ነበር።
እኛ ደግሞ ፓርላማ መግባት ከማሟሟቅ ውጭ ምንም እንደማይፈይድ ነበር እምነታችን። አንዳንዶች እንዳውም ኢህአዴግ በፍፁም ምርጫውን ፍትሃዊ አድርጎ እኛ ምክር ቤት የምንገባበትን እድል እንደማያመቻች ጥሩ ታይቷቸው ነበር። በወቅቱ ፓርቲ ውስጥ ብዙ ዓይነት ፍላጎቶች ነበሩ። በእኔ እምነት እንዳውም በስተመጨረሻው በመካከላችን መበተንና መለያየት የተፈጠረው በዚህ የሃሳብ ልዩነት ምክንያት ነው።
በተለይም አንዳንዶቻችን ተወዳድሮ ፓርላማ መግባት የኢህአዴግ ድራማ ውስጥ መግባት ስላልፈለግን ምርጫውን እስከመጨረሻ ድረስ ገፍተን ከዚያ ሩጫችን የመግታት አላማ ነበረን። ከምርጫው በኋላም ደግሞ በወቅቱ በነበረው ሊቀመንበርና በሌሎች የፓርቲው አመራሮች መካከል ደግሞ አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር። ብዙዎቹ ጉዳይ ግላዊ በመሆኑ እዛ ጉዳይ ውስጥ ገብቼ ማውራት አልፈልግም። ምክንያቱም አለመግባባቱን ለመፍታት በቂ ጥረት ያላደረግን በመሆኑ ሁላችንም ከተጠያቂነት ስለማያድነን ማለት ነው።
በነገራችን ላይ ፓርቲው ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው መከፋፈልን የማየው አጠቃላይ አገሪቱ ውስጥ ተቋም የመገንባት አቅም ያለመፈጠሩ ውጤት እንደሆነ ነው። እዚህ አገር ውስጥ የጎበዝ አለቃ መከተል እንጂ ተቋም የመገንባት ችግር አለ ። ስለዚህ እኛ ጋር የነበረውንም ችግር የዚያ አካል አድርጌ ነው የማየው።
ኢህአዴግ ከዚህ ማህበረሰብ ወጥቶ አምባገነን እንደሆነው ሁሉ ይሄኛው ስብስብ ከማህበረሰብ ወጥቶ እንደዚህ አይነት ተቃርኖች በመካከሉ ተፈጥሯል። ግን እኛ ደግሞ ተሽለን ካልሄድን ተጠያቂ ከመሆን አንድንም። የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ሲካሄድም ኢንጅነር ይልቃል ጌትነትን ለማውረድ የሚሰሩ ድራማዎች ነበሩ። ይሁንና በአብላጫ ድምፅ ኢንጅነር ይልቃል
ሊቀመንበር ሆኖ ቀጠለ። በተጨማሪም ገንዘብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ነበሩ። እርግጥ የረባ ገንዘብ ኖሮ አልነበረም፤ እርስበርስ የነበረው ቅራኔ ወደ ስሜት የሚከቱ ሆነው እንጂ።
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ ፓርቲው ውጭ ባሉ አካላት ከፍተኛ ድጎማ እንደሚደረግለት ነው ሲገለፅ የነበረው?
አቶ ዮናታን፡- ድጎማ መደረጉ እውነት ነው። ግን እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። እኔ ሰውም እንዲያውቀው የምፈልገው አንድ እውነት አለ። ይኸውም ሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ስንሰራ ከፅህፈት ቤት ሰራተኞች በስተቀር የፖለቲካ ውሳኔ የምንሰጥ ሁላችንም አባላት ተከፋይ አልነበርንም። እንዳውም ከኪሳችን አውጥተን ነበር የምንሰራው። እኔ በተለይ በህዝብ ግንኙነት በምሰራበት ጊዜ ከራሴ ብዙ ተጎድቻለሁ።
ግን ደግሞ ተጎድቻለሁ ማለትም አልፈልግም። ምክንያቱም ለራሴ ነፃነት የፈልኩት ዋጋ አድርጌ ስለምቆጥረው ነው። ደግሞም አንድም ወደ እኔ የመጣና አይምሮዬን የሚቆጠቁጠው ነገር የለም። በዚያ ደስተኛ ነኝ። በድጎማ የሚመጣውም ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ስራ ላይ ነበር የሚውለው። አንድ ጊዜ
እንዳውም የማስታውሰው በሳውዲ ያሉ እህቶቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ለማውገዝ ሳውዲ ኤምባሲ ጋር ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ አስበን ከውጭ ድጋፍ ሳይደርስልን ቀርቶ በራሳችን መዋጮ ብቻ ማግኘት የቻልነው ስድስት ሺ ብር ብቻ ነበር። ያገኘነውንም ብር ለመኪና ኪራይ፤ ለባነር ማሰሪያ እና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች አውለነው ባዶ እጃችንን ነው ሰልፍ የወጣነው። በእርግጥ የምርጫ ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ የተገኙ ገንዘቦች ነበሩ፤ ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ለምርጫ እንቅስቃሴ ነበር ያዋልነው።
ስለዚህ ኪስ ውስጥ ሊገባ የሚችልበት አጋጣሚ ሁሉ አልነበረም። እኔ በፓርቲው ውስጥ ገንዘብ እንደ ትልቅ ጉዳይ ሲነሳ በጣም ይገርመኝ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ ከውጭ እንደሚባለው አልነበረም ድጋፍ ይደረግልን የነበረው። በጣም የሚገርመው ከመካከላችን አንድ መኪና እንኳ የነበረው ሰው አልነበረም። ሁላችንም በታክሲ እየተጋፋን ነበር የምንቀሳቀሰው። እንዳውም አንዳንዴ ህዝቡ የሚከፍልልን ጊዜ አለ። ስለዚህ በሚባለው ደረጃ ፓርቲው ተዝናንቶ የሚሰራበት ሁኔታ አልነበረም።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ለፓርቲው መዳከምና ልዩነት መፈጠር የኢህአዴግ እጅ አልነበረበትም ባይ ነህ?
አቶ ዮናታን፡- ልክ ነው፤ የኢህአዴግ እጅ ያልነበረበት ነገር የለም። ነገር ግን ሁልጊዜ ኢህአዴግን ብቻ መውቀስ ከችግር አያወጣንም። አስቀድሜ እንዳልኩሽ የተቋም ግንባታ በራሱ አገራዊ ነው። ሁላችንም እዚህ ተሰብስበን ስለ ተቋም ግንባታ ማድረግ የሚገባንን ነገር አድርገናል ብዬ አላስብም።
ይህም የነፃነት ትግላችን ላይ የሚያጠላው ጥላ ነበር። በተመሳሳይ ሰዓት በግል በነበሩ ቅራኔዎች ለኢህአዴግ ዱላ ያቀበልነው ራሳችንን ነን ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ኢህአዴግም ሆነ ሌላው ቀዳዳ ካልፈጠርሽ ማንም አይነካሽም። ዋናው የራስሽ ጥንካሬ የሚወስነው። ግን በዛ ሁኔታ ውስጥ መሄዳችን የነበረን መንፈስ መዳከሙ ኢህአዴግ ዱላ አቀብሏል፤ ኢህአዴግ ተጠቅሞበታል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለውን በቅርቡ የከሰመውንና አንተ በታሰርክበት ወቅት ተፈጥሮ የነበረውን የሰማያዊ ፓርቲ እንዴት ነው የምትከተለው? በተለይ ከተነሳበት ራዕይና አላማ አንፃር?
አቶ ዮናታን፡- እኔ በታሰርኩበት ወቅት የነበረው ሰማያዊ ፓርቲ እኛ ከነበርንበት ሰማያዊ ፓርቲ ጋር በርዕዮተ አለምም፤ በአስተሳሰብም ፈፅሞ
የተለየ ነው። ይህም ማለት በፊት ከነበርነው አባላቶች ውስጥ አብዛኞቻችን ለዘብተኛ ሌቤራሊዝም ነበር የምንከተለው። የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ ወግ አጥባቂ የሚባሉት ደግሞ ኢንጅነር ይልቃል ወደሚመራው የኢትዮጵያ ህዝቦች ንቅናቄ ሄደዋል። (ወግ አጥባቂ ስንል በራሱ ክፋት አለው እያልኩ አይደለም)። ኢህን የሚጠቀመው የኢትዮጵያ ካርታ ኤርትራንም ጭምር የሚያጠቃልል መሆኑ ፓርቲው አገራዊ ብሄርተኝነቱን በምን ያህል ደረጃ ከፍ እንዳደረጉት የሚያሳየው ነው። በእነ የሽዋስ አሰፋ የሚመራው ሰማያዊ ደግሞ በአንፃሩ ትንሽ ቀዝቀዝ ያለ ነው።
ይህም ማለት ሶሻል ዲሞክራት ርዕዮተ አለም የሚመስል ባህሪ አለው። ይህ ባህሪው በቅርቡ ራሱን አክስሞ ወደ ኢዜማ ሲገባ የተወው ይመስለኛል። ኢዜማ ውስጥ ያሉ ፖለቲከኞች አሁን ያለውን የለውጥ ሂደት በመልካም ተቀብለው በዚህ ውስጥ ውጤት ሊመጣ ይችላል ብለው መንግስትን ያመኑ ኃይሎች አድርጌ ነው የምቆጥራቸው። በፊት የነበረው ሰማያዊ ግን ይሄ መንግስት ለውጥ ሊያመጣ አይችልም የሚል አመለካከት የነበረውና መንግስት መጠራጠር ብቻ አይደለም የፈረጀም ነው። እንግዲህ ወደፊት ምን እንደሚሆን አብረን የምንታዘበው ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንዶች እንደ ኢዜማ ያሉ ፓርቲዎች በዚህ መንግስት ላይ እምነት ማሳደራቸው በየዋህነት እያስነሳቸው ይገኛል። እንዳውም የምርጫው ውጤት ሲገለፅ እንደ ቅንጅት አይነት ሁኔታ ሊያጋጥመው ይችላል የሚል ፍራቻ አላቸው። አንተ በዚህ ላይ ምን አይነት አስተያየት አለህ?
አቶ ዮናታን፡- በጥቅሉ ሲታይ ካለው የፖለቲካ ሁኔታ አንፃር እውነት ይመስላል። ግን እንደዛ አይደለም። አሁን ብዙ ነገሮች ተቀይረዋል። ለምሳሌ አሁን በዶክተር አብይ የሚመራው የኢህአዴግ መንግስት ከዚህ ቀደም ከነበረው መንግስት ለዴሞክራሲ የነበረው እይታ የተለየ ነው። በእኔ እምነት በተለይ አገራዊ እይታ ያለው ፓርቲ መሆኑ በራሱ በመሰረታዊ የሆነ ለውጥ እንዳለው ያመላክታል።
ሁለተኛ ደግሞ የፖለቲካ ባህላችን ያሳደረብን መጥፎ የሆነ ተጠራጣሪነት በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ውስጣችን አለ። አሁን የመጣው መንግስት ያንን ለማጥፋት የሚወስዳቸው ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎች አሉ። በተለይ ደግሞ ወደ መጀመሪያ አካባቢ የወሰዳቸው እርምጃው በጣም የሚደነቁ ነበሩ። ያ በተወሰነ መልኩ በባህል ይዘነው ነው የመጣነው የመጠራጠር መንፈስ እየገፈፈ
ነበር ለማለት እችላለሁ።
ኢዜማ ውስጥ ያሉት አመራሮች ከዚያ አይነት የፖለቲካ እሳቤ ለመላቀቅ የሚሞክሩ ናቸው። እነዚህ ሰዎች በ1997 ምርጫም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መድብለ ፓርቲ እናድርጋለን ብለው ሲናገሩ አምነው የመጡ ናቸው። ስለዚህ ይህንንም መንግስት ለማመን አልደከሙም። ይህ ደግሞ የዋህ አያደርጋቸውም። ወድቆ መነሳትን በአገር ተስፋ አለመቁረጥን፥ በዚህ አይነት መልኩ አገር መገንባት እንችላለን ብለው በፅኑ የሚታገሉና ለአገራቸው መልካም የሚያስቡ ሰዎች አድርጌ ነው የማያቸው። በሁለተኛ ደረጃ ተወዳድረን እናሸንፋለን ብለው ወደ ውህደት የመጡት መንግስትን ብቻ አምነው ሳይሆን በራሳቸውም ተማምነው ነው።
ያለውን ምቹ ሁኔታ እንጠቀማለን ብለው በማሰብም ጭምር። የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የሚያኮላሽ ነገር እንኳ ቢመጣ ከትግል ወደ ኋላ የሚሉ ሰዎች አይደሉም። ስለዚህ የዋህ አያሰኛቸውም። ይልቁንም ከተጠራጣሪነት መንፈስ የሚመነጨውንና ሁልጊዜ መውደቅን ብቻ እያሰብን ብቻ የምናደርገው ክፉ አስተሳሰብን መሻገር መቻላቸው በራሱ በጣም ክብር ሊያሰጣቸው ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በርካታ ፓርቲዎች ውህደት መፍጠራቸው ለኢትዮጵያ የወደፊቱ ፖለቲካ ምን ምን አንድምታ ይኖረዋል?
አቶ ዮናታን፡- ብዙ ለውጥ ያመጣል። በተለይ ኢዜማ መፈጠሩ ፖለቲካው የሃሳብ ፖለቲካ እንዲሆን ያደርጋል ብዬ አምናለሁ። በቀጣይ ምርጫ ከዚህ ቀደም ያደርጉት እንደነበረው ኢህአዴግን በመክሰስ ላይ የተመሰረተ ውድድር እንደማያደርጉ እምነት አለኝ። ከዚያ ይልቅም ኢህአዴግ አሁን በሚከተለው ርዕዮተ አለም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ችግር ሊፈታ እንደማይችል ያሳዩናል ብዬ አምናለሁ።
ስለዚህ ያ በራሱ አንድ የፖለቲካውን መንፈስ የሚቀይር ነገር ነው የሚሆነው። ለዚህ ደግሞ የዶክተር አብይ መንግስት ወሳኝ ሚና አለው። ግን ከባድ ፈተና እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም። እንደዚህ አይነት የፖለቲካ ክርክር ለማድረግ የፖለቲካ አየሩ ገና አልጠራም። ምክንያቱም አንዳንዶች እንደ ፖለቲካ ንግድ እየተጠቀሙበት ስለሆነ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለው ሁኔታ የብሄር ፓርቲ ለዚህች አገር ያስፈልጋታል ብለህ ታምናለህ?
አቶ ዮናታን፡- እኔ በፊትም ሆነ አሁን ለዚህች አገር የማንነት ፖለቲካ ወይም የብሄር ፖለቲካ ያስፈልጋታል ብዬ አላምንም። ግን ደግሞ ዝም ብሎ የብሄር ፖለቲካ አያስፈልግም ብሎ ማውገዝ ተገቢ አይመስለኝም። በየትኛውም አገር ጠንካራ መንግስትና አገር ለመገንባት ተመሳሳይ የሆነ እሴት ይፈልጋል።
ስለዚህ የቀደሙት ነገስታቶቻችን ይህን ሀሳብ ያራምዱ ነበር። አንድ ቋንቋ፥ አንድ አስተሳሰብ ያራምዱ ነበር። ይህም በወቅቱ ልክ ነበር። ባለፉት 28 ዓመታት ደግሞ ያ ታሪክ ተቀይሯል። አንድ ቋንቋ አንድ ባህል አገር አይገነባም የሚለው አስተሳሰብ በተወሰነ መልኩ ፍሬ አፍርቷል። ግን እነዚህ የአገር መገንባት ሂደቶች ጥያቄዎችን የሚመልሱ እንጂ የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ከስር ከመሰረቱ የሚፈቱ አይደሉም።፡ የማንነት ጉዳይ በፖለቲካ ውሳኔ አግኝቷል። ዜጎች በቋንቋቸው ይማራሉ። ዜጎች ባህላቸውን የሚያሳድጉበት ነፃ ሁኔታ ተፈጥሯል። በአሁኑ ወቅት ግን አንድ ማንነት ያለው ሰዎች ተደራጅተው የሁሉንም ዜጋ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ አይችሉም። ምክንያቱም የማንነት ፖለቲካ በባህሪው የዚያን የተለየ ማንነት አለኝ ብሎ የሚያስብ ስብስብ ጥያቄዎች ለመመለስ የተቋቋመ በመሆኑ ነው።
የፖለቲካ ጥያቄ ውስብስብና ምልዕነትን የሚፈልግ ነው። ስለዚህ ይህ ብሄርንና ቋንቋን መሰረት ያደረገው የፖለቲካ አስተሳሰብ መለወጥ አለበት። የሰው ልጅ ለሚያደርገው እያንዳንዱ ነገር ራሱ ኃላፊነት መውሰድ አለበት። እኔ በግሌ ሊበራሊዝም አስተሳሰብ ነው የምከተለው። ስለዚህ በእኔ እምነት መፎካከሪያ መሆን ያለበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ሊፈታ በሚል ርዕዮተ አለም ሲደራጁ ነው።
ሁሉም በማንነት ላይ ተመስርቶ የሚያቋቁመው ፓርቲ አጠቃላይ አገራዊ ችግርን ሊፈታ አይችልም። ደግሞም አንድ አይነት ማህበረሰብ መፍጠር የሚቻለው ትኩረቱ ሰውን ሲያደርግ ነው። ይህ ነው የመወዳደሪያ አውድ መሆን ያለበት። እንደ አጠቃላይ በማንነት ላይ የተመሰረቱ ፓርቲዎች ከፖለቲካ መውጣት አለባቸው የሚል እምነት ነው ያለኝ። ይህን ስልም ዝም ብሎ አየር ላይ ይበተኑ ማለቴ አይደለም። አይቻልምም። ምክንያቱም ሊመለስ ወደማይችልበት ደረጃ በመድረሱ ነው። ግን ደግሞ መፍትሄም አለ። በቀዳሚነት የማንነትን ጥያቄ የያዙ ፓርቲዎች በሲቪክ ማህበርነት ሊቋቁሙ ይገባል። ለዚህ ደግሞ በጣም ስሙ ገኖ የነበረውን የሜጫና ቱለማ ማህበርን መጥቀስ እንችላለን።
መስራቾቹ ኦሮሞዎች ቢሆኑም ከሱማሌ እስከ ኤርትራ ድንበር ድረስ የተፅእኖ አድማሱን አስፍቶ ነበር። ስለዚህ እነዚህ በማንነት ላይ የተመሰረቱ ፓርቲዎች በዚያ መልኩ ቢደራጁ የብሄራቸውን ጥያቄ እንዲመልሱ ይበልጥ የሚንቀሳቀሱበት እድል ይፈጠርላቸዋል። የፖለቲካ ሹክቻ ውስጥም አይገቡም። ፖለቲካው ሰፊ አድማስ ይኖረዋል። ፖለቲካ ውስጥ ግን ከገባ ሌላው ሁሉም ተነስቶ የእኔም ብሄር አልተጠቀመም ወደሚል ፉክክር ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ደግሞ እስቲ ለእስር የበቃህበት ትክክለኛ ምክንያት በራስህ አንደበት ለአንባቢዎችህ ግለፅ?
አቶ ዮናታን፡- አስቀድሜ አንዳልኩሽ እኔ በፍትህ የማምንና ስለፍትህ ዋጋ መክፈል አለብኝ ብዬ የማስብ ሰው ነኝ። በታሰርኩበት ወቅት በአገሪቱ በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ዙሪያ ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረት ነግሶ ነበር። አሁን ያሉት የኦዲፒ አባላትን ሳይቀር በድርጅታቸው ኢህአዴግ ላይ እምነት ማጣታቸውን በግልፅ የሚናገሩበት ሁኔታም ተፈጥሮ ነበር። እንደውም እንደመታገያ አጀንዳ ከመሆን አልፎ አጠቃላይ አገሪቱን ላጥለቀለቃት ለውጥ እርሾ ነበር ብዬ አምናለሁ።
ይሁንና ያ ማስተር ፕላን ለወጣቶች አመፅ መነሻ ይሁን እንጂ አጠቃላይ ይደረግ የነበረው የፖለቲካ ተፅእኖ፥ ስራአጥነት፥ ስደትና ሌሎች ስር የሰደዱ ችግሮች ነበሩ። ያ ብሶት ነው ገንፍሎ የወጣው። እሱን ደግሞ እነ አቶ ለማ መገርሳም በወቅቱ የህዝቡን ስሜት ያንፀባርቁ ነበር። ያንን እንቅስቃሴ እኔም በሙሉ ልቤ ነበር የምደግፈው። ምክንያቴ ደግሞ ጥያቄው ምንም ይሁን ምን ድንጋይ የሚወረውር ወጣት ግንባር ግንባሩን እየተባለ በጥይት ሊገደል እንደማይገባ በፅኑ ስለማምን ነው።
ይህ አቋም ስለነበነኝ በነበረኝ ግንኙነት ለአለምአቀፉ ህብረተሰብ ለማስተዋወቅ ጥረት አድርግ ነበር። ያነሱት ጥያቄ በራሱ አግባብነት ያለው ነው። እኔ የማውቃቸውና ሄጄም ያናገርኳቸው ከኮዬ ፈጬ የተነሱ አርሶአደሮች ሲነሱ በተገቢው መልክ ካሳ ተከፍሎአቸው አልነበረም። በካሬ ሜትር የሲጋራ ዋጋ እንኳን አይሆንም የተሰጣቸው። መንግስት ግን ያንን የሚሸጠው እጅግ ከፍተኛ በሆነ ዋጋ ነው።
እነዚያ ሰዎች አርሶአደሮች በመሆናቸውና ሌላ ክህሎት የሌላቸው እንደመሆኑ ከገዛ መሬታቸው ተፈናቅለው ወደ ዘቀጠ ድህነት ውስጥ ሲገቡ በማህበረሰብ ልቦና ውስጥ ከፍተኛ ቀውስ ያስከትላል። እኔ አንድ ቤተሰብ ሙሉ ራሱን ያጠፋ ቤተሰብ እንዳለ አውቃለው – ኮዬ ፈጬ ውስጥ። አሁንም ቢሆን ጥናት ለሚሰሩ ሰዎች ይህ ታሪክ በሰነድ ተቀምጦ ይገኛል። ያ የሚፈጥረውን ማህበራዊ ቀውስ ከግምት ያላስገባ ጥናት ያልተደረገበትና በተገቢው መልኩ ለዜጎች ካሳ ያልተከፈለበት ብዙ ውስብስብ ችግር ያለበት ነው። ያንን እኔ ራሴ እቃወመዋለው።
በሌላ በኩል አዲስ አበባ እንድትሰፋ የኔም ፍላጎት ነው። ምክንያቱም ከተማ መስፋፋት በአለም ደረጃ ያለ ነው። በሌላ በኩል መንግስት ያለውን የቤት ችግር መቅረፍ የሚችልበት አንዱ መንገድ በመሆኑ። እዛም ላይ ሃሳቤን እሰነዝር ስለነበር በዚያ ምክንያት ነው የታሰርኩት። የነበረው መንግስት ያንን ተግባሬን ስላልወደደው ሌሎችም ጭምር እንደ መቀጣጫ አድርጎ የወሰደኝ ይመስለኛል። ስታሰር እንደ ክስ ሆኖ የመጣው ሌሎች እንቅስቃሴዎቼ ሳይሆኑ ፌስ ቡክ ላይ የፃፍኳቸው ፅሁፎች ብቻ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ «ቄሮ» የተባለው የኦሮሚያ ወጣት ያነሳ የነበረው ጥያቄ በተወሰነ መልኩ ቢሆን ምላሽ አግኝቶና ግቡን ከመታ በኋላ አሁንም እንቅስቃሴውን አለመቆሙ ለአገር ሰላም ስጋት ይፈጥራል የሚሉ ወገኖች አሉ። አንተ ምን ትላለህ?
አቶ ዮናታን፡- በመጀመሪያ ደረጃ ቄሮ የሚባለው ስያሜ በራሱ በአግባቡ ተተርጉሟል ብዬ አላስብም። ቄሮ ማለት ያላገባ ወጣት ማለት ነው። ያን ግዜ ይደረግ የነበረው ወጥ የሆነ አደረጃጀትና መዋቅር ያለው እንቅስቃሴ አይደለም።
ግን ደግሞ በተለያዩ ሃይሎች ቄሮን ለማደራጀት የሚሞከርበት ሁኔታ ነበር። በዚህ ደግሞ እነጅዋር፥ ኦነጎችና ኦፍዴግ የራሳቸውን ጥረት ሲያደርጉ ነበር። ግን ደግሞ እነሱ ብቻ አይደሉም አሁን ያሉት የኦዲፒ ሰዎችም ትግሉን ረድተዋል። ሁሉም ቄሮን ለመቆጣጠር ጥረት አድርጓል። በተለይ ኦዲፒዎች የህወሓት ተላላኪ የሚባሉበትን ታሪክ ሽረው የራሳቸውን ታሪክ መስራት ይፈልጉ ነበር። ስለዚህ ቄሮን አንድ ወጥ አድርጎ ማሰብ በራሱ ስህተት ነው።
አሁን ያለው መንግስት ሲመጣ ግን የትኛውም ማህበረሰብ ጥያቄ አለው። ግን ደግሞ ጥያቄው ሲመለስለት ወይም ሊመለስለት ወደሚችልበት ሁኔታ ሲመቻች ከዚያ አይነት እንቅስቃሴ ይወጣል። ስለዚህ ከዚህ ተፈጥሯዊ ክስተት ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ ወጣቶች በተለያየ መንገድ ሃሳባቸውን ይገልፃሉ። እዚህ ጋር በጣም ወሳኙ ጉዳይ አብዛኞቹ ተማሪዎችና በጣም የሚበረክቱት ደግሞ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ስራ ያጡ ናቸው።
የሚያደርጉት ግራ የገባቸው፤ በዚያ ምክንያት ትግሉ ከዚያ አይነት ሞት ይሻላል ብለው የተቀላቀሉ ናቸው። ስለዚህ አሁን ያለው መንግስት ለእነዚህ ሰዎች ኢኮኖሚያዊ እፎይታ ሊሰጣቸው አልቻለም። በጣም በርካታ ከመሆናቸው የተነሳ ኢትዮጵያ አሁን ካላት ኢኮኖሚ አኳያ ጥያቄያቸውን መመለስ አልተቻለም። ስለዚህ በዚህም ሆነ በዚያ ለተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች አጀንዳ ተቀባይና አስፈፃሚ ነው የሚሆኑት። ያ ማለት ግን አሁን ሁሉም ማለት አይደለም። ስለዚህ አንዳንድ ቦታ ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በሌላ ማህበረሰብ ላይ ቁጣን ሊቀሰቅስ ይችላል።
ግን ደግሞ ለአገር አንድነት እንቆረቆራለን የሚሉ ወገኖች ሁሉ ያንን ወጣት በጅምላ ሲፈርጁት ጠባብና ብሄርተኛ ያልሆነው ወጣት ሁሉ ወደ እዚያ ሁኔታ ሊገባ ይችላል። ለምሳሌ ባህርዳር ላይ የግንቦት ሰባት አመራሮች ላይ እንደዛ አይነት ጥቃት ሲፈፀም የባህርዳር ወጣቶችን አይወክልም፤ ትግራይም ሆነ በሌሎች ክልሎች የተወሰነ አካል በሚሰራው ጥፋት ሁሉም በጅምላ መጠቅለሉ ስህተት ነው የሚል አቋም ነው ያለኝ። ግን ደግሞ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ያልሆነ ወጣት አገሩን አገሬ ለማለት ይችላል ተብሎ መታመን የለበትም። በዚህ ውስጥ የግጭት ነጋዴዎች ከዚህ ማትረፍ እንደሚፈልጉ እሙን ነው። ያንን ሁሉ ወጣት መጨፍለቅ ግን የራሳችንን ችግር መሸፈን ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡- በእስር በነበርክበት ወቅት በራስህና በቤተሰቦች ላይ ይደርስ የነበረውን ጫና እንዴት ትገልፀዋለህ?
አቶ ዮናታን፡- በቤተሰቤ ላይ የተፈጠረውን ሁኔታ መግለፅ በጣም ከባድ ነበር። በተለይ አባቴ ሲመጣ በጣም ነበር የምሳቀቀው። ይደርስበት በነበረው እንግልት ፊቱ ጠቁሮና አካሉም ከስቶ ስለነበር በጣም ይረብሸኝ ነበር። ግን በጣም ጠንካሮች ስለነበሩ እኔንም አጠንክረውኛል ብዬ አስባለሁ።
ምክንያቱም በፊትም ትግል ውስጥ እያለው ያበረታቱኝ ስለነበር። በየቀኑ በጠዋት እየተቀሰቀስን ለምርመራ ከምንወሰደው፥ ከምንደበደበውና ከዘለፋው በላይ ወላጆቻችን በየቀኑ ሲመላለሱ ማየታችን ነበር ህመም የሚፈጥርብን። በፖሊስ ግልምጫና ግፊያ ሲደርስባቸው በምመለከትበት ወቅት በጣም ነበር ልቤ የሚሰበረው።
መቼም አሁን ያ ጊዜ በማለፉ ፈጣሪ ይመስገን ነው የሚባለው። ለነገሩ በግሌ ብዙ ድብደባ አልደረሰብኝም። እርግጥ ነው አንድ ወቅት ቂሊንጦ ላይ የኦፌኮ ጓደኞቻችን ሲደበድቡት ለምን ትደበድቡታላችሁ ብለን በተነሳው አምባጓሮ ተደብድቤ ነበር።
ከዚያ ይልቅ ግን በስነ ልቦና ረገድ ያደረሱብን ጠባስ ቀላል የሚባል አይደለም። አንዳንድ ጊዜ መደብደብን የምትመርጭበት ሁኔታ አለ። አንቺን በጥያቄ እያጣደፉ ከአጠገብሽ ደግሞ በአሰቃቂ ሁኔታ ሌላውን ሲገርፉ ስትሰሚ በጣም ያማል። እበጂ እበጂ ነው የሚልሽ። በነገራችን ላይ ድብደባ የሚፈጥረው ቁስል ይሽራል፤ የህሊና ቁስል ግን መቼም የማይድን በሽታ ሆኖ ነው የሚቀረው። በተለይ ደግሞ ማንነትን መሰረት አድርገው በየእስር ቤቱ የሚደረገው ማንጓጠጥና ስድብ ዘላለም ከህሊናችን ላይ ታትሞ የሚቀርና መፈጠርን የሚያስጠላ ነው።
በእርግጥ እኔ የአዲስ አበባ ልጅ ስለሆንኩኝ ሊጠቅሱብኝ የሚችሉት ማንነት የለኝም፤ እኔም የማንነት ጉዳይ እንደ ደባል ነገር ስለማየው ማንነቴ ላይ ቢሰድቡኝ ብዙ አይገርመኝም። ሌሎች ግን በጣም ነበር የተጎዱት። ከዚህ ጋር አያይዤ መናገር የምፈልገው ነገር ከእንደዚህ አይነት አሰቃቂ ሁኔታ የወጡ ሰዎች ከህመማቸው እንዲያገግሙ፥ ሳናደርጋቸውና ሳንደግፋቸው ከማህበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ በመደረጋቸው ነው ዛሬ ላይ በፖለቲካው ላይ የምናየውን አስፈሪ ሁኔታ የተፈጠረው።
ይህንን ደግሞ እዛው እስር ቤት እያለሁ ነው ማየት የጀመርኩት። ብዙዎቹ መውጣትን የሚናፍቁት ለመበቀል ነበር። አሁንም ቢሆን ፍርድና ካሳ ያጣመረ ፍትህ ስላላገኙ ከዚያ ስሜት ውስጥ ለመውጣት ይቸገራሉ። ከፍርድ በኋላ ነው ይቅርታ መምጣት ያለበት። እንደዚያ የበደሉን ሰዎች ፍርድ ሳይፈረድባቸውና ፍትህ ሳይገኝ እኛም ተክሰን ይቅርታና ምህረት የምናገኝበት ደረጃ ላይ ስላልደረስን ራሳችንን እናቅባለን። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርታ ስለጠየቁ ብቻ ልባችን ላይ ያለው ጠባሳ የሚሻር አይደለም። በነገራችን ላይ ፍትህ አቋራጭ መንገድ የለውም።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ያለ ገደብ ነፃነት መሰጠቱ በአገሪቱ ሰላም ላይ እያሳረፈ ያለውን አሉታዊ ሚና እንዴት ትገልፀዋለህ? ምንስ መሰራት አለበት ብለህ ታምናለህ?
አቶ ዮናታን፡- አሁን ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት መብት ያለገደብ የተሰጠበት ምክንያት ገና ፍትህ ስላልተገኘ ይመስለኛል። አንቺም እንዳልሽው አሁን ላይ ያለገደብ ነፃነቱን የሚጠቀመው ሃይል ጦርነት ሁሉ የሚቀሰቅስበት ድርጊት ሲፈፅም ዝም የሚባልበት ሁኔታ አለ። በእኔ እምነት ይህ አካል ፍትህን ያላገኘ ነው። የፍትህ ስርአቱ ሳይታደስ እስከ ዛሬ ሲሰራበት በነበረው መንገድ ፍትህን ማረጋገጥ አይቻልም። መዋቅሩ ተስተካክሎ፥ ገለልተኛ የሆነ ፍርድ ቤት ኖሮ፥ ንፁህ ህሊና ባላቸው ሰዎች ፍትህ ሊገኝ ይገባል።
ይህንን ማረጋገጥ ስላልተቻለ ነው ነፃነቱ እንዲበዛ የተፈቀደው። ይሁንና በአግባቡ ካልተያዘ ደግሞ አደጋው የከፋ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም ስርዓት አልበኝነት እየተፈጠረ ስለሚሄድ ማለት ነው። ስርዓት አልበኝነት እየተበራከተ በመጣ ቁጥር የሚጎዳው ህዝቡ ነው።
ህዝቡ በተማረረ ቁጥር ማመፅ የሚችለው ደግሞ መንግስት ላይ ነው። ይህ ደግሞ አሁን ባለው ሁኔታ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ነው የምንገባው። ሁኔታው ወደእዛ እንዳያመራ መንግስት ስርዓት ማስያዝ ይገባዋል። እስካሁን የሆነው ሆኗል፤ በቀጣይ ግን የደቦ ፍርድና ማፈናቀል እንዳይከሰት መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በተለይም የፌደራል መንግስት ይህንን ጉዳይ ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል።
አዲስ ዘመን፡ በቀጣዩ ምርጫ ተስፋና እንደ ስጋት የምታያቸው ነገሮች አሉ?
አቶ ዮናታን፡- ተስፋው ምህዳሩ መስፋቱና ብዙ የፖለቲካ ሃይሎች መግባታቸው ማለት ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን ተስፋ በራሱ ስጋት ይሆናል። ከምህዳሩ መስፋት ጋር ተያይዞ በጣም ጠርዝና ጠርዝ ላይ የቆሙ ሃይሎች አንድ ላይ እዚህ ምህዳር ውስጥ መለቀቃቸው በራሱ ስጋት የሚሆንበት ሁኔታ አለ።
ምክንያቱም መንግስት የሚያደርጋትን ትንሿን ስህተት አጋኖ በማቅረብ እንደማህበረሰብ ችግር የምትቆጠርበት ሁኔታ አለ። በነገራችን ላይ ይህ ችግር በ28 ዓመታት ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ለዘመናት የተከማቸ ነው። ያንን ሁሉ ችግር ፍፁም በሆነ መልኩ መጠበቅ ስህተት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የጋራ ምክር ቤት አቋቁመዋል፤ ሁሉም የሚሳተፉበት ምርጫ ቦርድም እንዲሁ። በተጨማሪም በህዝብ አመኔታ ያላቸው ግለሰብ ተሹመዋል። ይህ ለእኔ ተስፋ የሚሰጥ ጉዳይ ነው።
ይሁንና ጨለምተኛ ነህ አትበይኚና ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ከምርጫው በኋላ ችግር ይፈጠራል የሚል ስጋት አለኝ። አሁን ካለኝ የፖለቲካ አሰላለፍ አንፃርም ችግር እንዲፈጠር የሚፈልጉ ሃይሎች እንዳሉ ይሰማኛል። ምክንያቱም ጥቅማቸውን ሊያገኙ የሚችሉት በዚያ ግርግር አማካኝነት በመሆኑ ነው። ያንን ለማድረግ ችግር የሚፈጥሩ ሃይሎች ከተቃዋሚ ወገን ብቻ አይደለም፤ ከመንግስትም ውስጥ ያሉ ሊሆኑ ይችላሉ።
ግን ቢያንስ በፈረሙት ስምምነት መሰረት በውይይት መግባባት ላይ ከደረሱ ሌላው በጥባጭን በጋራ ሊቆጣጠሩት ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገቡት ቃል መሰረት ላሸነፈው አካል ስልጣን ሊያስረክቡ እንደሚችሉ አምናለሁ። ነገር ግን ፖለቲካ ቆሻሻ ስለሆነ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አሁን ላይ መገመት አንችልም።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ በኋላ ዮናታንን በፖለቲካው መስክ ዳግም እናገኘዋለን?
አቶ ዮናታን፡- አይ እኔ ከዚህ በኋላ የምገኘው ህዝብ ሳገለግል ነው። እንዳልኩሽ እኔ የሊበራሊዝም አቀንቃኝ እንደመሆኔ ይህንን አስተሳሰብ ማራመድ የምችልበት አጠቃላይ ማህበረሰባዊ ለውጥ እስካልመጣ ድረስ ዳግም ወደ ፖለቲካው መመለስ አልፈልግም። ምክንያቱም አሁንም ከቡድናዊነት አስተሳሰብ አልወጣንም። ለሊበራሊዝም የሚሆን የማህበረሰብ ድጋፍ ሳይኖር ዝም ብሎ በባዶ መጮህ ትርጉም ያለው አይመስለኝም።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ምቹ ሁኔታን እየጠበቅ እንደሆነ እንውሰደው?
አቶ ዮናታን፡- እንደዛ ማለቴ አይደለም። እንደምታውቂው የማንነት ጉዳይ እንዲህ በጦዘበት በዚህ ወቅት እኔ ሊበራሊዝምን የሚያራምድ አንድ ፓርቲ አቋቁሜ ምረጡኝ ብዬ ብጮህ የሚሰማኝ አላገኝም። ስለዚህ ማህበረሰቡን ማገልገል የበለጠ ዋጋ ያለው ይመስለኛል።
ለእኔ እዚህ መድረስ አጠቃላይ የማህበረሰብ ድምር ውጤት በመሆኔ በተማርኩበት ዘርፍም ሆነ በመምህርነት አገለግላለሁ። እውነቱን ለመናገር ደግሞ አሁን ያለው መንግስት መደገፍና መታገዝ የሚገባው ነው ብዬ ስለማምን በሙሉ ልቤ እያገዝኩ ነው እየደገፍኩ ነው። ከአምስት አመት በኋላ አሁን ያለው ወጀብ በዚህ ሁኔታ ይቀጥላል ብዬ አላስብም። ባይፈታም ሊቀንስ ስለሚችል የግለሰቦች ፍላጎት ምላሽ ያገኛሉ። ያኔ እኔም አማራጭ ሃሳቤን ይዤ እመጣለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ አንተም ሆንክ ጓደኞችህ ከተቃዋሚነት ጭልጥ ወደአለ ደጋፊነት ገብተዋል እየተባላችሁ እየታማችሁ ነው?
አቶ ዮናታን፡- እንግዲህ የፖለቲካ ባህሉ በጣም የተበረዘ ነው። በተለይ ከ1960ዎቹ ወዲህ ጠላትና ወዳጅ እንጂ አማካኝ የሚባል ስፍራ የለም። እኛንም ጭምር ጠልፎ የያዘን የጠላትና ወዳጅ ስነልቦና ነው። ግን አሁን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ መረዳት ያለብን ይመስለኛል። ኢህአፓና መኢሶን መንግስት መሆን ያልቻሉት ስለቸኮሉ ይመስለኛል። አሁንም የዚያ አይነት መካሰስ ውስጥ መግባት አለብን? ያለው ነገር እንዳለ ፈርሶ እንደ አዲስ ካልተጀመረ ብለን መቆም አለብን? እኔ ትክክል ነው ብዬ አላስብም።
ከታሪክም ደግሞ የወደቅንበትን መንገድ አሁንም እንሂድበትና እንውደቅ ከሚለው ለይቼ አላየውም። ግን ደግሞ መቃወም በሚገባኝ ጉዳይ ላይ ሃሳቤንና ትችቴን ሳልገልፅ ያለፍኩበት ጊዜ የለም። ለምሳሌ ዶክተር አብይ የህክምና ባለሙያዎችን ሰብስበው በተናገሩት ንግግር በጅምላ ሁሉንም መውቀሳቸው እንደማንኛውም ሰው ቅር በመሰኘቴ ቅሬታን ገልጪ ፅፊያለሁ። በተመሳሳይ ደግሞ በሸገር ልማት ላይ የቀረበውን ጥሪ በበጎ መልኩ የማየው በመሆኑ ደግፌ ፅፊያለሁ።
ስለዚህ ነገሮችን ማየት የምፈልገው በሚዛኑ ነው። እንደአጠቃላይ አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ለመፎካከር ራሱ ዝግጁ አይመስለኝም። መጀመሪያ እስቲ አገር እንገንባ ። አሁን ያለው መንግስት በርዕዮተ አለም ደረጃ ምን ዓይነት እንደሆነ አናውቀውም። ገና እንዋሃዳለን እያለ ነው። ግን ደግሞ አገርን በሁለት እግር ለማቆም እየደከመ ያለ ይመስለኛል። ይህንን መደገፍ ደግሞ ስለኢህአዴግ ወይ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዬ የማደርገው አይደለም። የአገር ህልውና ስለሚያሳስበኝና አሁን ያሉት መሪዎች የተሻለ ተስፋ ሰጪ ነገር አለ ብዬ ስለማስብ እደግፋለሁ። በተመሳሰይ ኢዜማንም እደግፋለሁ። ምክንያቱም አካሄዳቸው ለዚህች አገር ይበጃል ብዬ ስለማምን ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍሉ ጋር ረጅም ቆይታ በማድረግህ በአንባቢዎቼ ስም አመስግናለሁ።
አቶ ዮናታን፡- እኔም ከልብ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 24/2011
ማህሌት አብዱል