«ሰላም እና ነፃነት የምንጠብቃቸው እንጂ የሚሰጡ አይደሉም» ዶ/ር ተፈራ በላቸው

ዶ/ር ተፈራ በላቸው ተመራማሪ እና የመልካም ስብዕና አሠልጣኝ

በሕክምና እና በፍልስፍና ሁለት የተለያዩ ዶክትሬት ዲግሪዎችን ሠርተዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸው ከ30 በላይ የጥናት ጽሑፎችንም ለንባብ አብቅተዋል፡፡ WHY SHOULD I LISTEN TO GOD? (አምላክን ለምን እሰማለሁ?) በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ በሀገር ውስጥ እና በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በመዘዋወር ወጣቶችን በመልካም ስብዕና አንጸዋል፡፡

ትውልድ እና እድገታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ አጠና ተራ ልኳንዳ አካባቢ ሲሆን፤ አሁን በምሥራቅ እና በደቡብ አፍሪካ ሀገራት በሚገኝ የሕክምና ጥናት የምርምር ተቋምን በዳይሬክተርነት እየመሩ ይገኛሉ፡፡

ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ከሆኑት ከዛሬው የዘመን እንግዳ ዶ/ር ተፈራ በላቸው ጋር የተደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡አዲስ ዘመን:- እንዴት የሕክምና ዘርፍን መረጡ? ስኬትስ ለእርስዎ ምን ማለት ነው?

ዶ/ር ተፈራ:- ሐኪም የሆንኩት በፍላጎቴ አይደለም። ብዙ ብር ያስገኛል ስላሉኝ ነው። ስኬት ሲጀምር በራሱ ተበላሽቶ ሲጀምር እንዴት እንደሆነ በእኔ መመልከት ትችላለህ። ሐኪም መሆን እንደስኬት ልንቆጥረው እንችላለን፤ በእኔ እምነት መሆን የነበረብኝ ኢንጂነር ነው። ኢትዮጵያ ባልወለድና አዕምሮዬ ክፍት ሆኖ እንድመረጥ ቢፈቀድልኝ ኖሮ ኢንጂነር፣ አሜሪካዊ ብሆን ኖሮ ደግሞ ምናልባትም ናሳ ውስጥ እገባ ነበር።

ከተመረቅኩኝ በኋላ በሕክምና ሙያ የሠራሁት ለሰባት ዓመታት ነው። ያለፉትን 20 ዓመታትም በኢትዮጵያ አልኖርኩም። ወደኖርዌይ በመጓዝ ሁለተኛ ዲግሪዬን ሠራሁ። በመቀጠልም ወደቦትስዋና በመቀየር ለ19 ዓመታት ኖሬያለሁ።

ለስኬት ቁልፍ ከምላቸው መካከል አለኝ የምንለውን ሃይማኖት በሥርዓቱ አክብረን መኖር አንዱ ጉዳይ ነው። ስኬት ከማግባት ጋርም ይገናኛል። የሚያገባ ሰው ጤነኛ ነው፤ የተረጋጋ ሕይወት ይመራል። ረጅም ዕድሜም ይኖራል። ኢኮኖሚውም የተሻለ ነው። ለስኬታችን ትዳር መመሥረት ይገባናል። ከሀገር አቀፍ ወደዓለም አቀፍ ማማተርም ለስኬት አስፈላጊ ነው።

አዲስ ዘመን:- በአሁኑ ወቅት የሚሠሩት በየትኛው ሙያ ነው?

/ ተፈራ:- በሙያ ከሄድን የቤልጅየም ድርጅት ውስጥ የኢትዮጵያ የሞዛምቢክና ታንዛኒያ የደቡብና ምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሪሰርች ኦርጋናይዜሽን የሪጂናል ዳይሬክተር ሆኜ እየሠራሁ ነው። በተቋማችን ምርምሮችን ይሠራሉ።

ከዚህ ውጭ ፓስተርም ነኝ። በቤተክርስቲያን ውስጥ በመጋቢነት አገለግላለሁ። ከድሮም ጀምሮ ቤተክርስቲያን እያገለገልኩ ነው ያደግኩት። ከስድስት ዓመታት በፊት በ2018 እ.አ.አ ፓስተር ሆኛለሁ።

ጥሪዬ ነው ብዬ የማስበው ወጣቶችን ማሠልጠን ነው። እድሜዬም ከ50 ስላለፈ የእኔን ኖሬ ጨርሼ አሁን ለሰው መኖር አለብኝ የምለው ጊዜ ላይ ነው ያለሁት።

አዲስ ዘመን:- ፍልስፍና ሲባል ዋና ማሕቀፉ ምንድን ነው? ሳይንሱስ መነሻ የሚያደርገው ምንድን ነው ?

/ ተፈራ:- ፍልስፍና ሰፊ ጉዳይ ይይዛል። ለምሳሌ ሜዲካል ዶክተር ሲባል የሰውን ጤና መከላከል፣ ሲታመሙ ደግሞ በሽታውን አክሞ ማዳንና ጤናማ ሕይወት እንዲኖሩ ማድረግ ነው። ፍልስፍና ግን የተደበቀን፣ ጠባብ ግን ጠለቅ ያለ ነገር ውስጥ ገብቶ ፈልፍሎ በማውጣት ሃሳብን ለሰዎች ማጋራት ነው።

ብዙ ሰዎች ያዩታል ጥቂት ሰዎች ግን ይገቡና የተደበቀን ያወጣሉ። ልክ ከመሬት ውስጥ ውሃ እንደማውጣት መውሰድ ይቻላል። አንድ ሰው በፍልስፍና ፒ ኤች ዲ አለው ሲባል ያ ሰው የእዛ ጉዳይ ሊቅ ነው ማለት ነው። ማንም ሰው ፈላስፋ መሆን ይችላል። ሃሳብ በማምጣት ጠልቆ በመግባት እውነትን ፈልፍሎ በማውጣት ለሰው ማካፈል ተደርጎ ሊታይ ይችላል።

አዲስ ዘመን:- ከሥነልቦና ጋር ተያይዞ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች በበዙበት በዚህ ወቅት ድንገት የሚጋጥሙ አስጨናቂ ሁኔታዎችን ለማለፍ ምን ቢደረግ ይሻላል?

/ ተፈራ: ያለዝግጅት የትም አይደረስም። ቀውሶችንም ባግባቡ ለመምራት ዝግጅት ያስፈልጋል። አደጋ ሲመጣ ምን ማድረግ አለብኝ ተብሎ መታሰብ የሚገባው አደጋ ሳይመጣ ነው። ካልመጣ እሰየው። ቢመጣ የሚለውን በየጊዜው እያሰብነው መኖር አለብን። ሥነልቦና የሚጀምረው ከእዚህ ነው።

ወደዚህ ከመምጣታችን በፊት ግን ወደኋላ መለስ ብሎ ሰው ማነው? ከሚለው መጀመር ያስፈልጋል። ሰው በእምነት እሳቤ ሲታይ በእግዚአብሔር አምሳያ የተሠራ መሆኑ ይታወቃል። ወይንም ዝግመተ ለውጥ የፈለገውን ቢለውም ከእንስሳ የሚለይበት ነገር አለ። እናስባለን፣ እናስተውላለን፣ እንመራመራለን፣ ተግባቦታችን ይለያል።

ነገር ግን እድገታችንም እንደእንስሶች አካላዊ ብቻ አይደለም። ብዙ ዓይነት እድገት አለን። ሥነልቦናችን፣ ስሜታችን፣ ኢኮኖሚያችን፣ ዓለማዊ እውቀታችን፣ መንፈሳዊ መረዳታችን፣ ማኅበራዊ ግንኙነታችንም ያድጋል።

ነገሮችን በጊዜው እና በሰዓቱ ጀምረን ሂደቱን በትክክል ካላስኬድን ድንገተኛ ነገር ቢከሰት ሰውነታችን፣ አዕምሯችን፣ ስሜታችን መቋቋም ያቅተዋል። ማኅበራዊ ነገርን መቋቋም ሲያቅተን፣ ሲምታታ እና ሲጋጭ ደግሞ ጭንቀት ይፈጠራል፣ ይረብሻል፣ ሰላም ያሳጣል፣ ድብርት ውስጥም ያስገባል። እንቅልፍ ይነሳል፣ እየተባባሰም ይቀጥላል። ችግሩን የሚያስወግድለት ይመስለውና ያጠራቀመውን ኢኮኖሚ የሚያበላሽም አለ።

ሰዎች የማይፈልጉት ቦታ የሚሄዱት፣ የሚጠጡት፣ የሚያጨሱትም ለዚህ ነው። ድርጊቱ የሚፈጸመው በጤናማ አዕምሮ ሳይሆን፤ ከጭንቀት የሚመጣ ነው። ይሄ ሁሉ እንዳይሆን የጎደለውን አይቶ በጊዜ የምናስተካክልበትን ነገር ማድረግ አለብን።

እኔና አንተም ጤናማ እንመስላለን። ነገር ግን የሥነ ልቦና ችግር ሁሉም ሰው ተሸክሞት የሚዞረው ነው። በተለይ ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ ሀገራት ጥሩ ነው ብዬ የማስበው መለስ ብሎ ራስን መገምገም መቻል ነው፡

አዲስ ዘመን:- እንዲህ አይነት የሥነልቦና ችግር ውስጥ ላለመግባት ምን ማድረግ አለብን? ችግሩ እንዳለ እና እንደሌለ የሚታወቀውስ በምን አይነት ግምገማ ነው?

/ ተፈራ:- ሐኪም እንደመሆኔ ከችግር መጀመር አልፈልግም። የተማርኩበት ፐብሊክ ሄልዝ ዘርፍ የማኅበረሰብ ጤና እንክብካቤ ላይ ያተኩራል። ሰዎች አስቀድመው ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ ነገሮች ላይ መሥራት አለባቸው።

ስለሁኔታው ለመመርመር ሙሉ ለሙሉ ሰላም ነኝ ወይ፣ ደስተኛ ነኝ ወይ ብለህ ትጀምራለህ። የምትፈልገው ነገር ሁሉ እንዳለህ ራስህን ትጠይቃለህ። ከሌለህ ያላደገ ነገር መኖሩን የሚነግርህ የሌለህ ነገር ነው።

ብዙ ጊዜ ብስጭጭት የሚያደርጋቸው፣ ራሳቸውን መቆጣጠር የማይችሉ ሰዎች አሉ። ይሄ immotional in­telligence (ስሜትን መረዳት) የሚባል ክፍል ውስጥ ራስን መግዛት መቻል ያስፈልጋል።

አመራር መሆን የሚችለው የሚመራቸውን ሰዎች ዓመል ካልቻለ ችግር በተፈጠረ ቁጥር መሄጃ ያጣል። የሚመራቸውን በሁሉም አግባብ ደስተኛ አድርጎ መምራት ካልቻለ ስህተት ነው።

መድኃኒቱ በመምራት እውቀት ራሱን ማሳደግ ነው። በማንበብ፣ አማካሪ በመቅጠር ወይም ሌላ አማራጭ በመፍጠር ሊሆን ይችላል። ያቃተ ነገር ባለ ቁጥር ያላደገ ነገር አለ። ያቃተንን አውቀን ካሳደግነው ስኬት ማለት እርሱ ነው። የሚያስፈልግህ ነገር በምትፈልገው ሰዓት እና ልክ ካለህ ስኬታማ ነህ። እንጂ ስኬት ማለት የገንዘብ ብዛት አይደለም።

አዲስ ዘመን:- ለስኬት ተግዳሮት የሚሆኑ ነገሮች ምንድን ናቸው ?

/ ተፈራ:- እኔን ብትመለከት ባለቤቴና ልጆቼ አሜሪካ ይኖራሉ። እዛ ቤት አለኝ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ቤትም መኪናም አለኝ። የምሠራው ውጭ ሀገር ነው። ብዙ ሀገር ሄጃለሁ። አንድ ሰው እንዲህ ካልሆንኩ ብሎ ቢመኝ የተሳሳተ አካሄድ ይሆናል። ያ ሰው ከየት መጣ፣ እንዴትስ እዚህ ደረጃ ላይ ደረሰ፣ እኔስ እዛ ደረጃ መድረስ እችላለሁ ወይ ብሎ መጠየቅ አለበት።

ስለዚህ ወጣቶች መጀመሪያ ማን እንደሆኑ ማወቅ አለባቸው። ሁሉም ሰው ልዩ ነገር አለው። ስኬት እንደማንኛውም የተሰጠ ነገር መሆኑን በማወቅ ሥራን በጊዜው መሥራት የቻለ ማንም የደረሰበት ቦታ ላይ ይደርሳል። የቤት ሥራን መሥራት ሳይቻል ከችግሩ ጋር መጋፈጥ ለማለፍ ሊያስቸግር ይችላል። አንዱ የሰው ተግዳሮቱ የራስ ዝግጅት ማነስ ነው።

የሁኔታዎች፣ በሲስተም እና በዓለም አቀፍ ሁኔታ የሚከሰት ተግዳሮትም አለ። ሌላው ተግዳሮት ደግሞ ሰው ነው። ሰው ይገድላል፣ ያሳድጋል ወይም ይጥላል። በራስ ላይ ዋጋ ከሚጨምር ሰው ጋር ብቻ ነው ግንኙነት መፍጠር የሚገባው። ወይ ከማነሳው፤ አልያም ከሚያነሳኝ ሰው ጋር መሆን ጥሩ ነው።

ሰው አታልሎኝ ሰባት ሺህ ዶላር ወስዶብኝ ያውቃል። ሲወስድ መሬት ሆኖ፣ አሳዝኖኝ ነው ያበደርኩት። በኋላ የለኝም ክሰሰኝ አለኝ። ጥፋቱ የእኔ ነው። ጠልቄ ለማላውቀው ሰው ይሄንን ነገር ማድረግ አልነበረብኝም። የነበረ ግንኙነትም ስለነበር ራሴን አልከስም። ግንኙነቱ ጤናማ ሳይሆን ማመን፣ አብሮ ለመሄድ መሞከር ትክክል ላይሆን ይችላል፤ መካካድ ስላለ።

ሌላው ተግዳሮት ሰዎች ወደ ፕሮጀክትህ የሚመጡበት መንገድ ነው። ያሳተምኩትን መጽሐፍ ለመጻፍ ስነሳ መጽሐፍ ልጽፍ መሆኑን ያማከርኩት ወንድሜ ‹‹መጽሐፍ ዝም ብሎ አይጻፍም›› አለኝ። ይዘቱ ምን እንደሆነ ቢጠይቀኝ ምናለበት። እኔ ግን ወደውስጤ አላስገባሁትም።

ከውጭ የሚመጣው ተግዳሮት የማይቀር ነው። ሁሌም ሰው ተስፋ እንድትቆርጥ ያደርግሃል። ይህንን ለማለፍ በራስ መተማመንን መንፈስ በበቂ ሁኔታ ማሳደግ፤ አማካሪንና ከማን ጋር መገናኘት እንደሚያስፈልግ ማወቅ ያስፈልጋል።

ሌላው ተግዳሮት ሲስተም ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ መማርና መነገድ፣ አሜሪካ ወይም አውሮፓ ሆኖ መማርና መነገድ አንድ አይደለም። ያለህበት ቦታ የሚያመቻችልህ ወይም የሚያሳጣህ ሁኔታ አለ። ኢትዮጵያ ሆኖ እኔ የማውራውን እንደልብ ለማድረግ ያስቸግራል።

አዲስ ዘመን:- የኢትዮጵያውያን ወጣቶች ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? ከተግዳሮቶቹ መውጣትና ድህነትን መሻገር ያልተቻለውስ ለምንድን ነው?

 / ተፈራ :- የዕውቀት ማነስ አንድ ነገር ነው። አውቆም ለመጠቀም ያለመወሰንም ሌላ ችግር ነው። ከላይ ከአስተዳደር፣ ከአመራርና ከመሪነት መጀመር ትችላለህ፣ ወደታች ወርደንም ከቤተሰብ፣ ከግለሰቦች መነሳት ይቻላል። መሐልም ከማኅበረሰብና ከሁኔታ ጋር በማስተያየት መናገር ይቻላል።

መስፈርቱን ካነሳን በዓለም ላይ መልካም የኑሮ ሁኔታ ያላቸው በሚል በዓለም ላይ ውድድር ይደረጋል። ባብዛኛው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የሚወጡት ኖርዌይ፣ ስዊድን፣ ፊንላንድ፣ ዴንማርክ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳና አሜሪካ ናቸው።

ለምሳሌ ኖርዌይ ሦስት ዓመታት ኖሬያለሁ። እዛ የተወለደ ሰው እንዴት እንደሚያድግ አውቃለሁ። ልጄ ሲወለድ ስድስት ሺህ ዶላር ተሰጥቶናል። ገንዘብ ባይኖረን ልጁ በአስተዳደጉ እንዳይጎዳ አስፈላጊ ግብዓቶች እንዲሟሉለት በማሰብ ነው።

እንዲህ ተደግፌ የማሳድግበት ሥርዓት ካለ ልጁ እያደገ ሲመጣ የሚያሳስበው ስለሚበላውና ስለሚጠጣው ሳይሆን ስለምርት፤ ስለግል ጉዳይ ሳይሆን ስለሀገር፣ ስለዛሬ ሳይሆን ስለወደፊት ነው። ሲጀምርም ችግሩ ተወግዶለት ነው የሚጀምረው።

ወደእኛ ሀገር ስትመጣ ደግሞ በእኛ ሀገርም ለሰው ልጅ ያስፈልጋሉ የሚባሉ ትምህርት፣ ጤና፣ ደኅንነትን፣ ሰብዓዊ መብት የሚባሉት በተሟላ ሁኔታ አይገኙም። እነዚህ ከተሟሉ ማንም ሰው ሰላማዊ ሆኖ ማደግ ይችላል። ከሃሳብ ነው የሚጀምረው እችላለሁ ብለህ ትጀምራለህ። ለልጄ ‹‹ገና በሕጻንነትህ መንግሥት ይሄን ያህል ዶላር ሰጥቶናል›› ካልኩት የተመቻቸ ነገር እንዳለ እየነገርኩት ነው።

‹‹ስትወለድ እናትህ ባግባቡ ስላልታረሰች አንተን ባግባቡ ጡት ማጥባት አልቻለችም። ተቸግረን ነው ያሳደግንህ›› ብትለው የችግር አስተሳሰብን በውስጡ ዘርተህ ነው የምታሳድገው። አዕምሮው ተከፍቶ የሚፈልገውን ያገኛል ለማለት ያዳግታል።

ኢትዮጵያውያን ካለንበት የማንወጣው ማድረግ የሌለብንን ስለምናደርግ በተቃራኒውም ማድረግ ያለብንን ስለማናደርግ ነው። ወጣቶች ላይ የማተኩረው የአፍሪካ እና የኢትዮጵያ ሁኔታ ሳይገባኝ ቀርቶ ሳይሆን የማንለውጠውን ነገር ትተን የምንለውጠው ነገር ላይ እንድንሠራ ለማድረግ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ስኬታማ መሆን ይቻላል። የራሳችንን ውሳኔ ወስነን የቤት ሥራችንን ከሠራን ነገሮችን ማስተካከል እንችላለን። ወጣቶች በቀጣይ ጊዜያቸው ተስፋ እንዲሰንቁ አሠለጥናለሁ። ያላቸውንና የሌላቸውን እንዲለዩ አደርጋቸዋለሁ። ማደግ ያለባቸው በየትኛው መስክ እንደሆነ እጠቁማቸዋለሁ።

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የገባ ሰው ሥራ እንዲሠራ አበረታታለሁ፤ ቢያንስ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት። እድገት ገንዘብ ብቻ ማግኘት አይደለም ማኅበራዊ መስተጋብር ራሱ ሀብት ነው። ይሄ መንገድ ብዙ ጥቅም ያስገኛል።

አዲስ ዘመን:- በሀገር ሰላም እንዲሰፍን፣ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንስ እንዴት ማስወገድ ይቻላል፣ በጦርነት የሚፈጠሩ የሥነ ልቦና ቀውሶችን እንዴት ማከም ይቻላል?

/ ተፈራ: ማድረግ የሚገባንን ካደረግን ሁሉም ነገር ይስተካከላል። ሰላም ይሰፈናል። የምትፈልገው ነገር በምትፈልገው ጊዜ ከሌለህ ሰላም ታጣለህ። የሰላሙን ማጣት የፈጠረው ላይ ሠርተህ ችግርን ከመፍታት ይልቅ ወደሰው ጣት መጠቆም ትጀምራለህ። ይሄ ሌላ ውጊያ እንድትጀምር ይገፋፋል። ባንተ ምክንያት የተፈጠረ ነው ከማለት ይልቅ ሁኔታዎች እንዲህ አድርገውናል ማለት የተሻለ ነው።

ችግሩ ትክክል ቢሆንም ባይሆንም ራስን ወይንም ሌላውን መኮነን ተገቢ አይደለም። የሁሉም ነገር ችግር ፈጣሪ አለመስማት ነው። ለሀገር ሰላም መስፈን ከመኮነን መውጣት ይገባል። ለምሳሌ ይቅርታ ማድረግ ቀላሉ ነገር ነው። ለደረሰብህ ነገር ምላሽ ላለመስጠት ወይም ላለመበቀል መወሰን ያስፈልጋል።

ሰውዬው ባይጠይቅም የተበደለው ሰው ይቅርታ መጠየቅ ይችላል። ይቅርታ ለማድረግ መለማመድ ይገባል። ለሕዝብ የሚያስብ መንግሥት ካለ፣ ሕዝብና መንግሥት ከተዋሓደ ፍቅርና ሰላም የማይኖርበት ምክንያት አይታየኝም። ይሄ ነገር ከሌለ መንግሥት ጋር ወይም ሕዝብ ጋር ችግር አለ።

አሁን ሀገር ላይ የመጣው ሰላም ሽንገላ፤ እንጂ የምር አይደለም። በሳል የሆነው ችግሩን ለመፍታት የመጀመሪያውን ርምጃ መውሰድ አለበት። በብዙ መልኩ አቅም ስላለው መንግሥት ሥራውን ቢሠራ የተሻለ ነው። ለሰላም ችግር የሚሆነው ይቅር አለመባባልና ራስን አለማወቅ ነው።

ራስን መውደድም ሌላው ችግር ነው። ተበድያለሁ የሚለው ተበድሎ እንኳ ቢሆን ጥሩ ነገር ለማምጣት ዕድሉ በእጅ ካለ ማድረጉ ይጠቅማል። ሰላም እና ነፃነት የሚጠበቁ እንጂ የሚሰጡ አይደሉም።

ጦርነቱን አንመልሰውም። ጥፋተኛው ይሄ ነው፤ ያ ነው በማለትም ጊዜ አናጠፋም። ሁሌም ካለንበት ተነስተን መጀመር አለብን። የጎደለውን እንሞላለን። ማንበብ፣ ማማከር አለብን። በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱ የድሮ ንጉሦች ሁሉም አማካሪ አላቸው። መጀመሪያ በዙሪያቸው የሚያደርጉት ጠቢባንን ማዘጋጀት ነው። አንዳንዶቹ ጠንቋይ ጠቢባን ያዘጋጃሉ፣ አንዳንዶቹ እግዚአብሔርን የሚፈራ ያዘጋጃሉ።

በብሉይ ኪዳን 39 ንጉሦች ነበሩ ከነዚህ መካከል ስምንቱ ብቻ ናቸው እግዚአብሄርን ይፈሩና ይከተሉ የነበሩት። ቀሪዎቹ ከእግዚአብሔር ሃሳብ በተቃራኒው ይጓዙ ነበር። 31ዱም ንጉሦች እድሜያቸውን ሙሉ በሰላም አላሳለፉም። ስምንቱ ንጉሦች ግን ረጅሙን እድሜ በሰላም ነው ያሳለፉት። ሰላም ከፈጣሪ ጋር እንደሚገናኝ በነርሱ መመልከት ትችላለህ።

የምንፈጥረው ችግርም አለ። በጦርነት ጠባሳ የተጎዱ እንዲታከሙ ራሳቸውን፣ ሰው መሆናቸውን እንዲያውቁ ማድረግ ነው። ሰው አራት አይነት ስለሆንን የሚሰማን፣ የሚሰጠውም መልስ አንድ አይነት አይደለም።

ከሚስትህ ጋር እንኳን አንድ ላይ እየኖርክ አንድ ዓይነት ዕይታ አይኖርህም፣ ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይም አትደርስም። አንድ ዓይነት ስሜት የላችሁም። ስለዚህ በባሕሪ ራስን ማወቅ አለብህ። ከአራት ዓይነቱ መካከል በባሕሪያቸው ደፋሮች የሆኑ አንዱ ናቸው።

በተፈጥሯቸው እንደዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመሪነት ፀጋ ያላቸው ዓይነት ናቸው። እነዚህ ሰዎች የሚያደርጉትን ነገር ላያውቁ ይችላሉ። ለምን እንደሚያደርጉ ካወቁ ግን ሕዝቡ ባይረዳቸውም የጸጸት መንፈስ እንዳይሰማቸው ያደርጋል። የሚፈልጉትን ማድረግ እንጂ፤ ለሰላም ግድ የላቸውም። ሥራ ላይ የሚያተኩሩ ናቸው።

ከነርሱ ተቃራኒ የሚያደርጉ ደጋፊ፣ ሰው እንዲነካ የማይፈልጉ፣ ሰላም ፈላጊ ሥራ ላይ ሳይሆን፤ ሰው ላይ የሚያተኩሩ አሉ። ሲጀመርም አስተሳሰባችን ይለያል። የተሰማቸውን ሳንክድ ራሳቸውን እንዲያውቁ በማድረግ ራሳቸው እንዲመለከቱ ማድረግ ነው።

እንደባሕሪያቸው እንዲረዱትና ሁልጊዜም ሰውን ከመወንጀል ይልቅ ወደውስጥ እንዲመለከቱ ማድረግ ይገባል። የቡድን ሥራ እንዲሠሩ፣ ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲያወሩ ማድረግም አስፈላጊ ነው። በደቡብ አፍሪካ የተደረገው ገዳይና የሟች ቤተሰብ ፊት ለፊት እንዲነጋገሩና ተማምነው ይቅር እንዲባባሉ ነው። ቁጭቱም የጸጸት ስሜቱም ከሁለቱም ወገን ይወጣል። ተመሳሳይ አስተሳሰብ ይዘው ይለያያሉ። ሀገራዊ ምክክሩ በራሱ በጎ አስተዋፅዖ ያበረክታል። ነገሮችን ስንጀምር ከመነሻው አስተካክሎ መጀመር ያስፈልጋል። በቁስል ላይ ሆኖ መጀመር ተገቢ አይደለም።

ለሰላም መስፈን የግጭት አፈታት ሥርዓትን ማወቅ ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታል። አራት ዓይነት የግጭት አፈታት ሥርዓቶች አሉ። የመጀመሪያው የግጭት ዓይነት እውነታ ላይ የተመሠረተ ችግር /fact based conflict/ አንዱ ነው። መሬት ነች ፀሐይን የምትዞረው ወይንስ ፀሐይ ነች መሬትን የምትዞረው? የሚል ጥያቄ ቢነሳ መሬት እንደምትዞር ሁሉም ሰው ያውቃል።

ነገር ግን እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን ፀሐይ ነች የምትዞረው ተብሎ ይታመን ነበር። ይሄንን ጉዳይ ጋሊሊዮ የተባለ ሰው በቴሌስኮፕ ተመልክቶ ለካቶሊኮች ነገራቸው። በወቅቱ በእውቀት እንበልጣለን ብለው ያምኑ ስለነበር ለዘጠኝ ዓመት ቤቱ አስረውት በስብሶ እንዲሞት አድርገዋል። ማንም ሰው ይሄንን እውነት ሊቀይር አይችልም። እውነት ተኮር መረጃ ይረጋገጣል እንጂ ሊያጋጭም አይገባም።

ቢያጣላ የሚያጣላው ሁለተኛው /value based con­flict/ አንድን እስላም ክርስቲያን ሁን ብትለው በተቃራኒው እሱ ደግሞ ሙስሊም ሁን ይልሃል። አንተ እየሱስ ክርስቶስ ነው አዳኝ ትላለህ እርሱ ደግሞ ነብዩ መሐመድ ነው ይልሃል። ቀኑን ሙሉ ስትነጋገሩ ብትውሉ መቋጫ ላይኖር ይችላል። ምክንያቱም ሃይማኖት ሰዎች እስከሞት ድረስ የያዙትን ላለመተው የሚወስኑት ነገር በመሆኑ ነው። በዚህ መጣላት አይገባም፤ ላለመስማማት ተስማምቶ መለያየት መፍትሔ ነው። ሰላም ከፈለግን በልዩነት መከባበር አለብን።

ምሳሌ የማነሳልህ በራሴ አለባበስ ነው። ብርድ ሲሆን ያስለኛል። በዚህ ምክንያት ሳገባ እናቴ ለባለቤቴ አደራ የሰጠቻት ሳል እንዳልቸገር ነው። ጠዋት ተነስቼ ወደሥራ ልሄድ ስል ባለቤቴ ቢዘንብ ቀዩንና ወፍራሙን ሹራብ ልበስ ማታ ያስልሃል ትለኛለች። ባጋጣሚ ቀይ ቀለም ወይም ወፍራም ልብስ አልወድም፤ ቢጫውን ሳሳ ያለውን ነው የምለብሰው ስል አይቻልም ትለኛለች።

ሁለቱም ሹራብ ናቸው በዚሀ መጣላት የለብኝም። ስለዚህ የማልፈልገውን ሹራብ ይዤ ወደመኪና እጓዛለሁ። ስለያት አውልቄ እወረውረዋለሁ። ድንገት ከዘነበ ደግሞ አንስቼ እለብሰዋለሁ። ከባለቤቴ ጋር ግን ሰላም ፈጥሬ ወጥቻለሁ በሰላም እመለሳለሁ። የዚህ ዓይነት የማይጎዱንን ነገር ብንተዋቸው ጥሩ ነው። ለሰላም ሲባል መተው ያለብን ነገርም መተውም ሌላው ጉዳይ ነው። ከኋላ ነገር ጋር አንጣበቅ፣ መተው ያለብንን በመተው የወደፊታችን ላይ ማተኮር ይገባናል።

አዲስ ዘመን:- የስብዕና ሥልጠና ምንድን ነው? የሚያስፈልገውስ ለምንድን ነው?

/ ተፈራ: ከላይ ካነሳነው ሃሳብ ጋርም ይሄዳል። የሰው ልጅ አፈጣጠሩ ተደባልቆ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘፍጥረት 11 የሰው ልጅ ሁሉ በኃጥያት ሲያስቸግር በኖህ ውሃ ስምንት ሰው ብቻ መርጦ አትርፎ ሁሉንም እንዳጠፋው ተጽፏል። ሲያድጉ ክፉ ነገር አደረጉ። ለራሳችን ግንብ እንገንባ፣ ስማችንን ከፍ እናድርግ ሲሉ ከሰማይ እግዚአብሔር አይቶ ተቆጣ።

የሰው ልጅ አንድ ቋንቋና አነጋገር ካለው ማድረግ የሚያቅተው የለም። ስለዚህ እንዳይግባቡ ቋንቋቸውን እንደባልቅባቸው ብሎ በተናቸው። ባሕሪያችን ተደባልቋል። ሊያጠፋን አልፈለገም፤ ነገር ግን ከጉድለታችን ጋር ለቅቆን እንድንፈልገው አድርጎናል።

ከባለቤቴ ጋር ለ12 ዓመታት ስንኖር አንድም ቀን በውይይት ተስማምተን ጨርሰን አናውቅም ነበር። በሰላም ጀምረን ሳንስማማ ይቋጫል፣ ወይም ያለስምምነት ጀምረንም መቋጫው እንደዛው ይሆናል። ንዴት የሚሆን ነገር ውስጥ እንገባለን። የባሕሪ መደበላለቅ ስላለብን ነው።

ይህንን ሃሳብ ከተረዳሁ በኋላ ግን ጥፋቱ የኔ እንደሆነ ተቀብያለሁ። ከተጣላንም ቆይተናል። ምክንያቱም ድካ ሟንም ጥንካሬዋንም አውቃለሁ። ጥንካሬዬን ነግሬያታለሁ። ጥንካሬዬን ታውቃለች። በድካሜ ትረዳኛለች እንጂ እንደድሮ አትኮረኩመኝም።

ስለዚህ ችግሩ የመጣው ከእዛ ነው የሰው ልጅ ሁሉ ቋንቋው፣ ባሕሪው ተደባልቋል። የስብዕና ሥልጠናው የተደበቀን፣ ጥንካሬንና ድካምን፣ ልዩ ማንነትን ለማውጣት ያስችላል። በንግግራችን ሰው ላይ መልካም ነገርን በመዝራት ጀምሮ መጨረስ ተገቢ ነው። ድካምህን ብነግርህ ጠላት ትሆናለህ፤ በርካታ በጎ ነገር አለብህ እርሱን ብነግርህ ነው የሚበልጠው። ሁሉም ካቃተህ ከምትጎዳ ዝም ብትል መፍትሔ ነው።

አዲስ ዘመን:- ሥራ ፈጣሪ ከመሆን ይልቅ ተቀጣሪነትን ምርጫ የሚያደርጉ ወጣቶች በርካቶች ናቸው። ይህ እንዴት መስተካከል አለበት ?

/ ተፈራ :– በኢትዮጵያ ውስጥ በሕክምና ሙያ ተምረው ሥራ አጣሁ የሚሉ እየበዙ የመጡበት ትዕይንት ተመልክቻለሁ።

በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ባለበት ሁኔታ አንድ ሐኪም በኢትዮጵያ እንዴት ሥራ ያጣል? ሥራው ወደቢዝነስ ስለተቀየረ ዕድሉ ተበላሽቷል። አሜሪካ ያለው ግን ከዚህ ይለያል። አሜሪካ ወይንም አውሮፓ ባለመወለዴ ደሃ ሆኜ መኖር የለብኝም። የትም የሚኖር ሰው ደሃ መሆን የለበትም ብዬ አምናለሁ።

ምድሩ ምንም ችግር የለበትም። ቻይና እስከ 1974 እ.አ.አ መጨረሻ ደሃ ሀገር ነበረች። አሁን አሜሪካንን በልጣለች። ሀገሩ፣ ሕዝቡ ምድሩ ምንም ችግር የለበትም። ስኬታማ መሆን ይቻላል። እንደሰው ስንፈጠር ውጤታማ ሆነን እንድንኖር እምቅ አቅም ይዘናል። ዋናው ጉዳይ የተሰጠንን አቅም መለየት አለብን።

በየትኛውም ሙያ አቅም ከተፈጠረ እና ስሙን ከጠበቀ ተፈላጊነቱ በጣም ይጨምራል። ፈላጊ ሳትሆን ተፈላጊ ትሆናለህ። ዕድል ለሁሉም ክፍት አይደለም፤ በዚህ ሂደት ግን ሰፊ ይሆናል። ዕድል ከሰፋ ስኬት ቀላል ነው።

ራስህ የምትፈጥረውና የምታሰፋው ዕድልም አለ። እኔ ሐኪም ብቻ አይደለሁም ፓስተርም ነኝ። እሱ ብዙ ነገር ይጠቅመኛል። ለምሳሌ መጽሐፍ እንድጽፍም ምክንያት ሆኖኛል። መጽሐፌ አንድ ሚሊዮን ቅጂ ቢሸጥ ከእያንዳንዱ አንድ ብር ባተርፍበት አንድ ሚሊዮን ብር አገኛለሁ።

ንግድም አለኝ፤ በወር እስከ 90 ሺህ ብር የማገኝበት ሥራ ፈጥሬያለሁ። ቤት አከራያለሁ፣ አዲስ መኪና ገዝቼ ራይድ አሠራለሁ። ከራሴ አልፌ ለሰው ሥራ ፈጥሬያለሁ። ፍላጎትህ ተጨማሪ ሲጠይቅህ ሕይወትህ በምትፈልገው ሰዓት እና መጠን ማደግ እንዳለብህ እየነገረህ ነው።

በደመወዝህ የቤት ኪራይ መክፈል ሲያቅትህ ቤት ለመልቀቅ ማሰብ ሳይሆን ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ሌላ አማራጭ ገቢ መፍጠር ያስፈልጋል። አንድ ብቻ ሳይሆን አማራጮችን ማስፋት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ውስጥም ይቻላል።

አዲስ ዘመን:- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ!

/ ተፈራ:- እኔም ለተሰጠኝ ዕድል ማመስገን እፈልጋለሁ።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You