በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህዝብ ለህዝብ መድረኮች በስፋት እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡ በተለይ የኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ ክልሎች ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ እስካሁንም ከአማራ፣ ከጋቤምላ፣ ከአፋር፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሀረሪ፣ ጋምቤላ ክልል ህዝቦች ጋር ያደረጋቸው የህዝብ ለህዝብ መድረኮች ስኬታማና የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት ይበልጥ ያሳደገ ነው:: ይህ ተግባር ደግሞ በሁሉም ክልሎች እና በመላው የሀገራችን ህዝቦች መካከል ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው መልካም ጅምር ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በፍቅርና፣ በአንድት የሚኖሩባትና ለዓለም ማህበረሰብ ጭምር የሚተርፉ የተለያዩ ጠንካራ ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶች ያላት አገር ናት፡፡ ከአንድ መቶ ሚሊዮን የሚልቁት ህዝቦቿም የቀደምት ስልጣኔና ለሌሎች ጥቁር ህዝቦችም የሞራል ስንቅ የሚሆኑ ድሎች ባለቤቶች ናቸው፡፡ በተለይ አገራዊ ጉዳይ ሲነሳ ያለምንም ማወላወል ህብረታቸው እንደ አንድ ክንድ ተደምሮ ይቆማል፡፡
ለዚህም የመላው ጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት የሆነው የአድዋ ድል አንድ ማሳያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ ጥቃትን ባለመቀበልና ለወራሪዎች እጅ ባለስመስጠት ይታወቃል:: እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ወራሪ ሃይል በመጣ ጊዜም ያለምንም ማመንታት በአንድ ልብ ከፊት ይሰለፋል፡፡ በችግር ወቅት እኔ የተወለድኩት እዚህ ነው፤ ያ ቦታ የኔ አይደለም፤ ወዘተ የሚል ማወላወል ፈጽሞ መገለጫው ሆኖ አያውቅም፡፡
ከዚህም ባሻገር እነዚህ ብሄር ብሄረሰቦች ርስ በርስ ያላቸው መስተጋብር ጠንካራ የአብሮ መኖርና የፍቅር ተምሳሌት ነው፡፡ በማህበራዊ ኑሮ ውስጥ የገነባቸው የአኗኗር ዘይቤዎች በችግርም ሆነ በደስታ ጊዜ አብሮነታቸው እንዳይለያይ አድርጎታል፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የፈጠሯቸው ትስስሮች አንድም በመዋለድ ሲሆን በሌላም በኩል በተለያዩ ማህበራዊ ኑሮ ውስጥ በሚንፀባረቁ የአኗኗር ስልቶች ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ እድር፣ እቁብ፣ ጉዲፈቻ፣ ወዘተ የትስስሩ መገለጫዎች ናቸው፡፡
ከዚህም ባሻገር ግጭቶችን ለመፍታትም ሆነ ትስስሮቹን ለማጠናከር በአገራዊ የሽምግልና ባህሎች የማይፈቱ የግጭት ቋጠሮዎች እንደሌሉ የታሪክ ድርሳናት ያረጋግጣሉ፡፡ ሆኖም እነዚህ የቆዩ እሴቶችና የአንድነት መንፈሶች በተለያዩ ምክንያቶች ሲሸረሸሩና የ”እኔ” ነት እና “እኛ” ነት አስተሳሰቦች እየሰፉ ውጤታቸውም የዜጎች መፈናቀል መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል::
እነዚህ አስተሳሰቦች ደግሞ የቆየውን የህዝቦች የአንድነት መንፈስ ቀስ በቀስ በመሸርሸር አገራዊ አንድነትን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ችግሩ ስር ሳይሰድ መፍታትና ለዘመናት የዘለቀውን የመተሳሰብና መተባበር እሴት መመለስ ከእያዳንዱ አገር ወዳድ ዜጋ ይጠበቃል፡፡ አሁን የተጀመሩት የህዝብ ለህዝብ መድረኮች ደግሞ ለዚህ አደጋ ፍቱን መድሃኒቶች ናቸው:: በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የሚከሰቱትን የዜጎች መፈናቀል ለማስቀረትም ሆነ አገራዊ አንድነቱን ለማጠናከርና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የህዝብ ለህዝብ መድረኩ ጠቀሜታ የጎላ ነው፡፡
በተለይ የኦሮሚያ ክልል አጠናክሮ የያዘው የህዝብ ለህዝብ መድረክ ትልቅ ትርጉም ያለው እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የኦሮሚያ ክልል ከትግራይ ክልል በስተቀር ከሌሎቹ ክልሎች ጋር በአስተዳደር ወሰን የሚገናኝ ከመሆኑም ባሻገር ሁሉንም ክልሎች ከአገሪቱ መዲና ጋር የሚያገናኝ ድልድይ በመሆኑ ከሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ያለው ግንኙነት ሰፊ ነው፡፡
ከዚህ አንጻር የመጀመሪያው የአማራና የኦሮሞ የህዝብ ለህዝብ ኮንፈረስ በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ የተካሄደ ሲሆን ይህም በሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት ላይ ለዓመታት የቆየውን የአብሮነትና የአንድነት መንፈስ ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መሰረት የጣለ ነበር፡፡ በአምቦ ከተማ የተካሄደው የአማራና የኦሮሞ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትም ይህንኑ የቀደመውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ታልሞ የተዘጋጀ መድረክ ነበር፡፡
የዚህ መድረክም ዓላማ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለው ሰላምና፣ የአንድነትና የፍቅር ዘር ፍሬያማ ሆኖ እንዲያድግና ለቀጣዩ ትውልድም የመተሳሰብና የአብሮነት ምርትን ለማውረስ ታልሞ የተዘጋጀ ነው፡፡ ከዚያም በማስከተል የኦሮሚያና የጋቤምላ ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል፡፡ በዚህ መድረክም በሁለቱ ህዝቦች መካከል የነበረውን ታሪካዊ ግንኙነትና በቀጣይም ሁለቱ ህዝቦች አንዱ ለሌላው ደጀንና አጋር በመሆን በጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ትልቅ መነሳሳት ፈጥሮላቸዋል፡፡
ከሌሎቹ ጋር የተካሄደውም ተመሳሳይ ነው፡፡ ሰሞኑን ደግሞ የኦሮሞና የአፋር ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል፡፡ ይህም መድረክ የሁለቱን ህዝቦች የቆየ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችልና በቀጣይም በጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ትልቅ መድረክ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በሌሎች ክልሎች መካከልም የህዝብ ለህዝብ መድረኩ ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ሲካሄድ ሰንብቷል፡፡ ከነዚህም መካከል የሶማሌ፣ የአፋርና የሀረሪ የህዝብ ለህዝብ መድረክም ባለፈው ሳምንት መካሄዱ የሚታወስ ነው፡፡
በአጠቃላይ እንዲህ አይነት መድረኮች አንዱ ማህበረሰብ የሌላውን ባህል፣ አኗኗርና ሌሎች ታሪካዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶችን በጥልቀት እንዲገነዘብና በተሳሳተ መንገድ ከሚተላለፉ የታሪክ ዝንፈቶች ታቅቦ የቀደመውን ግንኙነት ይበልጥ እንዲያጠናክር ወሳኝ በመሆኑ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች አንዱ የሌላው ስጋት ሳይሆኑ ኩራት የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲቀጥል የግጭትን መንስኤ ማድረቅም ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እንዲህ አይነት ግንኙነቶች ጠቃሚ በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2011