ቀኑንና ወሩን በትክክል አላስታውስም(ታኅሣሥ ወር ውስጥ ይመስለኛል)። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ለመሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች አንድ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጀ። ያው እንግዲህ በቀጣይ ዓመት ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ወደ ሱስ እንዳይገቡ ማስተማሪያ መሆኑ ነው። የግንዛቤ ማስጨበጫው በመጤ ባህሎችና አደንዛዥ ዕፆች አሉታዊ ጉዳት ላይ ነው። ጽሑፎች ቀረቡ፤ ታዋቂ ሰዎች ምክር አዘል ንግግር አደረጉ።
ታዲያ ከግንዛቤ ማስጨበጫ መንገዶች አንዱ ድራማ ነበር። ድራማው መታየት ጀመረ። ገጸ ባህሪያቱ በአራዳ ቋንቋ ያወራሉ። ጫት እየተቀባበሉ ይቅማሉ። ጫቱ ትክክለኛ ጫት ይሁን ሌላ ቅጠል ነገር ባላረጋግጥም ትክክለኛ ሲጋራ ግን ተጨሰ። ልብ በሉ በአዳራሹ ውስጥ ያሉት የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው።
ድርጊቱ አላማረኝም ነበርና ግራና ቀኝ ዞር ዞር እያልኩ የተማሪዎችን ፊት ማስተዋል ጀመርኩ (ያው እንግዲህ በፊት ገጽታ የሰውን ስሜት ማንበብ እንችላለን አይደል?) አንዳንዶቹ ይስቃሉ፤ አንዳንዶቹ የመገረምና የመበሳጨት ስሜት ይነበብባቸዋል። እንዲያው ስሜታቸውን ግልጽ ያድርግልህ ሲለኝ ጭራሽ ቃላት አውጥተው የሚያወሩ አጋጠመኝ። ‹‹ኤጭ! ምንድነው ወረቀት ጠቅልለው ማሳየት አይቻልም እንዴ?›› ስትል አንዲት ተማሪ በብስጭት ስትናገር ሰማኋት። ከጎኗ ያሉ ተማሪዎችም ሃሳቧን እንደደገፉ ለድርጊቱ ያላቸውን ንቀት በፊታቸው ገጽታ ማንበብ ይቻላል።
ድራማው አልቆ ለሻይ ዕረፍት ሲወጣ ተማሪዎችን አናገርኳቸው። ከድራማው ምን እንደተማሩ ስጠይቃቸው ጥቂቶቹ ጥሩ ነው፤ አስተማሪ ነው አሉኝ። አንድ ላይ ሰብሰብ ያሉት ውስጥ ገብቼ ስጠይቅ ግን በሲጋራው በጣም እንደተበሳጩ ነገሩኝ። በተለይም ከፊት የነበሩ ተማሪዎች ተረብሸውም እንደነበር ነገሩኝ። በዚያ ላይ ስለ ሲጋራ ጉዳት ጠንቅቀው ያውቃሉ።
እንግዲህ ልብ በሉ! እነዚህ ተማሪዎች ገና ልጆች ናቸው። እንደማንም ሰካራም በየግሮሰሪው የሚዞሩ አይደሉም። እርግጥ ነው ተማሪዎች ሁሉ ጨዋ ናቸው፤ ምንም ነገር አያውቁም እያልኩ አይደለም። የደንብ ልብሳቸውን እንኳን ሳይቀይሩ በየመጠጥ ቤቱ እንደሚታዩ ሰምተናል። ስለዚህም ትምህርቱ አያስፈልግም ማለት አይደለም፤ ዳሩ ግን የቀረበበት መንገድ ወደዚያ ነገር እንዲገቡ የሚገፋፋ እንጂ የሚያርቅ አልነበረም።
እዚያ መድረክ ላይ ለመጡ ተማሪዎች ይሄ ሀሺሽ፣ ሺሻ፣ ጋንጃ…. የሚባል ነገር ሁሉ ቃሉ ራሱ ለእነርሱ አዲስ ነው። ድራማው ላይ ግን ‹‹ሀሺሻችንን አጭሰን፣ ጋንጃችንን ምገን….›› እየተባለ ሲነገር ነበር። እሺ እነዚህ ልጆች ይሄ ነገር ምን ዓይነት ይሆን? እስኪ እንሞክረው ቢሉስ?
ከዚህ ይልቅ አስከፊነቱን መናገር ልጆቹ እንዲፈሩት ያደርጋል። በልጅነታችን የተነገረን ነገር ያስፈራናል። ለምሳሌ ልጅ እያለን ይህን ካደረክ ትሞታለህ፣ እንዲህ ትሆናለህ ከተባልን እውነት ነው የሚመስለን።
እርግጥ ነው በድራማው መጨረሻ ላይ አደንዛዥ ዕፅ ጎጂ እንደሆነ ለማሳየት ሞክረዋል፤ ያንን ግን ልጆቹ ገና ድራማው ሳያልቅ ያውቁታል። እነዚያ ተማሪዎች እኮ ሲጋራ ሲጨስ ለማስተማሪያ መሆኑን አልሳቱትም፤ ግን የማያውቁትን ነገር ነው እያስተዋወቀ ያለው።
ደፈር ብዬ ልናገርና የብዙ መጤ ባህሎችና አደንዛዥ ዕፆች አስፋፊ ኪነ ጥበብ ነው። እንደምታዩት ፊልሞቻችን ያለስካርና ዝሙት አይሠሩም። ወጣቶች ደግሞ አርዓያ እያደረጉ ያሉት ተዋናይን ሆነ። እሱ እዚያ ፊልም ላይ ሲጃጃል ማየት አሁን ምኑ ያስቀና ነበር?
አሁን አሁን ልጆች ምን መሆን ትፈልጋላችሁ ሲባል ዶክተር፣ ኢንጂነር፣ ፓይለት… ማለት እየቀረ ነው። በተለይም ሴት ልጆች ላይ የምታዘበው ነገር ነው። ምን መሆን ትፈልጊያለሽ ሲባሉ አክትረስ፣ ሞዴሊስት… ነው የሚሉት። ይሄ ጫና የተፈጠረባቸው ከፊልም ነው።
ኪነ ጥበብ ትልቅ ዋጋ እንዳለው አምናለሁ፤ በእኛ አገር ግን የዋጋውን ያህል አልተሠራበትም። ሳይንስና ቴክኖሎጂን የሚያሳይ፣ የምርምር ሥራዎች ያሉበት፣ የአገራችንን ታሪክና ባህል የሚያስተዋውቅ፣ ስነ ምግባርን የሚቀርጽ ፊልም የለንም፤ ካለም በጣም በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። የዝሙትና የስካር ሥራዎች የሸፈኗቸው ናቸው። ይሄንን ነው እንግዲህ ልጆች እየተመኙ ያሉት።
ሰሞኑን በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ አንድ ሲትኮም ድራማ ተጀምሯል። ድራማው ሲትኮም ስለሆነ በመጀመሪያዎቹ ክፍልም አስታያየት መስጠት ይቻላል። የድራማው ይዘት የዘመኑን ሁኔታ ማሳየት ነው። እዚያ ላይ ግን ጥሩ ያልሆኑ ነገሮች አሉ። አንድ ያስቀየመኝን ነገር ብቻ ጠቅሼ ልለፍ።
አባትየው የልጆቹን እናት ትቶ ሌላ ሴት ያመጣል። ያችን ያመጣን ሴት ልጆቹ ይመኟታል፤ እሷም ከልጆች ጋር መወስለት ትፈልጋለች።
ይሄ በጣም ነውር ነው፤ ሲጀመር በኢትዮጵያ ባህል ውስጥ ይሄ የለም። ካለም በእንዲህ ዓይነት መረን ለቀቁ ፊልሞችና ድራማዎች የመጣ ነው። በተለምዶ ‹‹እንጀራ እናት›› ይባላል። እንጀራ እናት እንደ ወላጅ እናት ስለማትሆን በክፉ ዓይን ነው የምትታየው። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን እዚያ ድራማ ላይ ያለው ፀያፍ ድርጊት አይታሰብም። ልጆችም ልክ እንደ እናታቸው ነው የሚያዩዋት። ምናልባት በአገራችን እንዲህ ዓይነት ድርጊት አለ ብሎ ለማሳየት ከሆነ መጀመሪያውኑም ያመጡት እንዲህ ኣይነት ሥራዎች ናቸው።
ኪነ ጥበብ እንዲህ አጉል ከሆነ ይቅር! በነገራችን ላይ ‹‹አጉል›› የሚለው ቃል ጠብቆ ሲነበብ ትርጉሙን ግልጽ ያደርግልናል። አጉድል ወይም የሚያጎድል ማለት ይሆናል። ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ሥራዎች እየጨመሩልን ሳይሆን እያጎደሉብን ነው ማለት ነው። የማይጠጣ ሰው ሰካራም ከሆነ፣ የማያጨስና የማይቅም አጫሽና ቃሚ ከሆነ፣ የሳይንስ ተመራማሪ ሊሆን የነበረ ታዳጊ ቄንጠኛ አጫሽ ተዋናይ መሆን ከተመኘ፤ ይሄ ጉድለት ነው። ስለዚህ አጉል የኪነ ጥበብ ሥራዎች ለተማሪዎችና ለታዳጊዎች ባይታዩ!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 17/2011
ዋለልኝ አየለ