የተወለዱት በቀድሞ ወሎ ክፍለ ሀገር ወረኢሉ አውራጃ ገነቴ ቀበሌ ገበሬ ማህበር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው። ስለተወለዱባት አካባቢ ሲናገሩም «የትውልድ ቀየዬ ሙቀትም ሆነ ብርድ የሌላት በመሆኑ ለነዋሪዎቿ ምቹ፥ ለምና አጓጊ ናት» ሲሉ ይጠቅሳሉ። ከገበሬ አባታቸው ሥር ሆነው በእርሻ፥ በእረኝነትና በንግድ ቤተሰባቸውን እየደገፉ ቢያድጉም ለሃይማኖታቸው ያላቸው ልዩ ፍቅር አይሎ ያንን የሚወዱትን ቀዬና ቤተሰብ ጥለው ሃይማኖታዊ ትምህርት ፍለጋ ወደ ማያውቁት አካባቢ ተሰደዋል። የቁርዓን መምህራቸውን ተከትለው ከዛሬ 54 ዓመት በፊም ወደ አገሪቱ መዲና አዲስ አበባ ገብተው ቀርተዋል።
በእነዚህ ዓመታትም በእስልምና ሃይማኖት ትምህርት ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ የሚባሉ የትምህርት እርከኖችን አልፈው በቅዱስ ቁርዓን መምህርነት እንዲሁም በቤተ እምነቱ የተለያዩ ሃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል፤ በማገልገልም ላይ ናቸው። በተገኙበት መድረክ ሁሉ ስለሰላም፥ ፍቅርና መቻቸል በመስበክና ህዝብን ወደአንድነት በማምጣት ጎልቶ ስማቸው የሚጠቀሰው እኚህ ሰው ታዲያ በቅርቡ ደግሞ የኢትዮጵያ ዓሊሞች የአንድነትና የትብብር ምክር ቤት ሰብሳቢ ሆነዋል። ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር እድሪስ። የዛሬው የዘመን እንግዳ ናቸው። በሰላም፥ በአገር አንድነትና ተቻችሎ መኖር ዙሪያ የሚሉት አላቸው። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ስለአስተዳደግዎ፣ ስለልጅነት ህይወትዎ እስቲ ያጫውቱን?
ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር፡- ወላሂ! እኔ የተወለድኩት ገጠር ነው። የገበሬ ልጅ ነኝ። አባቴ በጣም ጠንካራና አስተዋይ ገበሬ ነበር። በዚህም የተነሳ እኔ የእሱን ፈለግ እንድከተል እንጂ ቅዱስ ቁርዓን እንድቃራ አይፈልግም ነበር። አባቴ በተፈጥሮው ባለስልጣንና ሀብታም ይወዳል። እናም ሁልጊዜም «የመቆፈሪያ እጅ ከመሳም የሀብታም እግር መሳም ይሻላል» እያለ ይናገር ነበር።
በልጅነቴ ወደ ቁርዓኑ ሳዘነብል ጊዜ «እርሻዬን ማን ያርስልኛል ብሎ ከቁርዓን መቅራቱ አስቀረኝ። አንድ ወቅት ላይ ግን ተላላፊ በሽታ ወረርሽኝ በቀያችን ገብቶ አባቴ በዚህ በሽታ ይያዛል። ያን ጊዜ መላው ቤተሰብ ተጨንቆ የነበረ ቢሆን ብዙም ሳይቆይ ተሻለውና ቀና ቀና ማለት ሲጀምር ከብት የማግድበት ስፍራ መጥቶ ስለሌሎች ጉዳዮች ሲያወያየኝ እኔም ይህችን አጋጣሚ ተጠቅሜ ዳግም ስለቁርዓን ጥናቴ አነሳሁበት። ታዲያ ያቺ በሽታው ልቡን አራርታልኝ ኖሮ «እንማከራለን» የሚል ምላሽ ሰጠኝ።
እኔም ይህችን ቃል በሰማሁበት ቀን ማግስት ሌሊት ተነስቼ አንድ ጓደኛ ጋር በመሄድ ቁርዓን ከሚቀራበት ስፍራ እንዲወስደኝ ለመንኩት። እሱም ልመናዬን ተቀብሎ ከስፍራው አደረሰኝና ጥናቴን ቀጠልኩ። በወቅቱ በእንጨት እየከተብን ነበር ቁርዓን የምናጠናው።
አብዛኛውን ጊዜ ግን ቁርዓን እቀራ የነበረው ከብት በማግድበት ስፍራ ሲሆን ቁርዓን ትምህርት ቤት የሚሄዱ ተማሪዎችን እየለመንኩ የአረብኛ ፊደሎችን ይከትቡልኛል፤ ሲመለሱ የማገኛቸው ደግሞ ያስጠኑኛል። በዚህ ሁኔታ ታዲያ ወሸምሲ የሚባል አንድ ምዕራፍ ስደርስ ራሴን ችዬ መፃፍ ጀመርኩኝ። ከዚያም ያሲን የሚባል ምዕራፍ ድረስ ቁርዓን ቀራሁ። በወቅቱ ማታ ማታ ቁርዓንን ለማጥናት ይመቸኝ ዘንዳ የማድረው መስጅድ ሄጄ ነው።
በዚህ ሂደት በጣም ሰፊ ጊዜ ወስጄ ነው ቁርዓንን ያጠናሁት። በአጠቃላይ ቁርዓንን ለማጥናት ወደ ሁለት ዓመት በላይ ፈጅቶብኛል። ከዚያ በኋላም ከአባቴ ተሸሸጌ ሌላ ስፍራ በመሄድ ደግሞ የቁርዓኑን እኩሌታ ጨረስኩኝ። በሁኔታው ብዙም ያልተደሰተው አባቴ አሁንም ከሄድኩበት አመጣኝና ከሱ ጋር ሆኜ እርሻውን ማረስ ቀጠልኩ። ለነገሩ በእርሻውም ቢሆን እኔም እንደ አባቴ ዋና ገበሬ ሆንኩ። በዚህም ሳላበቃ በግ፣ በርበሬና የተለየዩ የግብርና ምርቶችን በተለየዩ ቦታዎች እየወሰድኩኝ እነግዳለሁ። ምክንያቱ ደግሞ አባቴ ሰነፍ ልጅ የማይወድ በመሆኑ በዚህ መልኩ ራሳችንን ችለን ቤተሰባችን እንድንደግፍ ይገፋፉ ስለነበረ ነው።
አንድ ጊዜ እንዳውም የማስታውሰው አረም ሳርም፣ እሾህ፣ ወጋኝና ለማውጣት ስታገል አይቶ በጣም ተናዶ «እንዴት ገበሬ ሆነህ እሾህ ወጋኝ ትላለህ?» ብሎ ጭራሽ እሾሁን በእጄ እንድይዘው አስገደደኝ። ያን ጊዜ አካላቱ የለሰለሰ ሰው ሰነፍ ይባላል። ጠላት እንኳ ቢያገኘው ማሸነፍ አይችልም ተብሎ ነው የሚታሰበው። ስለዚህም ጉብዝናችንን ለማሳየት እንኳን በእግራችን ነበር የምንሄደው።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ዳግም ወደ መንፈሳዊ ትምህርቱ ተመለሱ?
ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር፡- ከዚያ በኋላማ አሻፈረኝ ብዬ ወረሂሉ ወደሚባል አገር ሄጄ ቁርዓኔን መቅራት ቀጠልኩኝ። እዛ ደግሞ አንድ ኪታብ እንደቀጠልኩኝ «አባትህ ታሞ ደክሟል» የሚል መልዕክት ደረሰኝ። አባቴ ማሽላ የሚጠብቅለት ሰው በማጣቱ የፈጠረው ውሸት እንደሆነ ስለገባኝ አይ ውሸት ነው ብዬ አልኳቸው። እነሱም መልሰው «ግን አባትህ ቢሞት ትቆጫለህ» ብለው እንድሄድ ጓደኞቼ ገፋፉኝ።
ስሄድ ግን እንዳልኩትም አባቴ ታሞ ሳይሆን ሥራ እንዳግዘው ነበር ይህንን መልዕክት የላከብኝ። ከዚያም የመኸሩን ሰብል አብሬው ካስገባሁ በኋላ ተምለሼ ሄድኩ። ተመልሼ እንድሄድ ደግሞ አብረውኝ የነበሩት ደረሳ ጓደኞቼ ከፍተኛ ግፊት ያደርጉብኝ ነበር። እዛም ወደ ስድስት ዓመት ከስድስት ወር ተቀመጥኩኝ። ከዚያም ወደ «ተፍሲን» የተባለ ምዕራፍ ለማጥናት 1 ዓመት ከ6 ወር ተቀመጥኩኝ። በኋላም ደሴ መጣሁና ሃዲስን አጠናሁ። በዚህም ሳላበቃ በወቅቱ ያስጠኑኝ የነበሩትን ሼህ ተከትዬ አዲስ አበባ መጣሁ። እንግዲህ አዲስ አበባ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እየኖርኩ ነው የምገኘው።
አዲስ ዘመን፡- ዘመናዊ ትምህርት ተምተረዋል?
ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር፡- ወላሂ፤ ዘመናዊ ትምህርት እኔ ተማሪዎቼን ደረሳዎችን አስተማርኩ እንጂ እኔ አልተማርኩም። ግን በራሴ ጥረት ማንበብ እችላለሁ። ያልተማርኩበት ዋነኛ ምክንያትም እኔን ሲያስተምሩኝ የነበሩ መሻሂዎች ዘመናዊ ትምህርትን እንዳልማር የሚያደርግ ጥላቻ በአእምሮ እንዲቀረፅ በማድረጋቸው ነው። ገጠር በነበርኩበት ጊዜ ፊደል የምትባል ነገር እክታብ ውስጥ ከተገኘች ከእስልምና እንደወጣ ተደርጎ «ካፊር» ወይም መናፍቅ ይባላል። በተጨማሪም በእኛ አገር ዘመናዊ ትምህርት የሚማሩ ሰዎች በሴት፥ በስልጣን፥ በጥቅማጥም ይታሙ ስለነበር በዚህ ምክንያት ዘመናዊ ትምህርትን ጠልቼ አደኩኝ። እናም ዛሬም ድረስ ስለዘመናዊ ትምህርት ያለኝ አመለካከት ጥሩ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ቤተሰብ ምስረታው የገቡበትን አጋጣሚስ ምን ነበር?
ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር፡- እንግዲህ ስለጋብቻ ጉዳይ አባቴ የመጀመሪያውን የቁርዓን ትምህርቴን በጨረስኩ ጊዜ ደረስነቴና የቁርዓን ትምህርት ፍላጎቴ በጣም ጠንክሮ ሲያይ «ይሄ ልጅ በሚስት ካልያዝኩት አይታዘዝልኝም» ብሎ አሰበና ሊድረኝ ፈለገ። እኛ በተወለድንበት በንጉሡ ጊዜ መቼም ታላቅ ሀብት መሬት ነበርና አራት አገር መሬት ያላትን ውብ ልጅ አጨልኝ። ቤትም ሠራሁኝ ጎጆም ወጣሁኝ። እኔም እሷን ይዤ በእሱ አስገዳጅነት ሁለት ዓመት ተቀምጫለሁ።
ግን የመንፈሳዊ ትምህርቱ ፍቅር በልቤ ውስጥ ሰርፆ ስለቀረ እነዚያ ሁለት ዓመታትን በግድ ነበር የተቀመጥኩት። እሷ ባለችበት አስቀምጫት ወደ ሌላ ከፍተኛ ትምህርት ጥያት ሄድኩኝ። ያን ጊዜ በቃ ልቤ በትምህርቴ ላይ ፀና እና ሚስቴን መፍታቴን መልዕክት ላኩኝ። እሷም ሌላ አላገባም ብላ ወደ ሦስት ዓመት ተቀመጠች። ሀብታም ቤተሰቦቿ እኛ እንድራታለን ብለው በተደጋጋሚ ቢሞክሩም አሻፈረኝ አለች። ግን የቆረጠች ጊዜ ከሦስት ዓመት በኋላ ሌላ አገባች።
እኔም ደግሞ መጨረሻ ላይ አዲስ አበባ መጣሁኝ። እዚህ ከመጣሁ በኋላም ለረጅም ዓመታት ቁርዓን ትምርቴ ላይ አተኮርኩ። ኋላ ግን እድሜ እየገፋና በእምነቱም እየጎለመስኩ ሲሄድ አንድ ጓደኛዬ ሚስት እንዳገባ ይወተውተኝ ጀመር። አዲስ አበባ ገብቶ ይቀራል የሚል ሥጋት ስለነበረው ከወሎ ሚስት ይለምንልኝ ነበር። እኔ ግን ብዙ ተከላክዬው ቆይቼ በኋላ ሃሳቡን ተቀበልኩት።
እንግዲህ የልጆቼን እናት ያገናኘኝ ይሄ የምልሽ ጓደኛዬ ነው። በወቅቱ ሚስት እንደለመነልኝ ደብዳቤ ላከልኝ። በኋላም ጭቅጨቃው ሲበዛብኝ አንተ ትሆናለች ካልክ ምን ችግር አለ ብዬ ሃሳቡን ተቀበልኩት። ያቺን ሴት ይዤያት እዚህ መጣሁ። ከዚያም እንግዲህ ዛሬ እሄዳለሁ ነገ እሄዳለሁ እያልኩ ለ54 ዓመታት በአዲስ አበባ ቆየሁ።
የሚገርመው እስከዛሬ ድረስ አገሬ ተመልሼ እኖራለሁ የሚል እምነት ነበረኝ። ምክንያቱም የእኔ ህልም አገሬ ተመልሼ እንዳለፉት ኡላማዎች መሆንን ነበር። በነገራችን ላይ የአላህ ፈቃድ ሆኖ ነው እንጂ ዛሬ እንደዚህ ያገኘሽኝ ጭራሹንም ቢሆን የስልጣን ፍላጎት የለኝም ነበር። እናም በዚህ ሁኔታ ያገባዋት ሚስትም 10 ወለደችልኝ። ሁለቱ ሞተዋል አሁን ስምንቱ በህይወት አሉ። የልጅ ልጆችም አሉኝ። ሁለቱ የልጅ
ልጆቼ ከነቤተሰቦቻቸው አሜሪካ ናቸው። እኔ በኑሮ በኩል ችግር የለብኝም። አገሬ ሀብታም ነበርኩ። እዛው ትቼው ቀረሁኝ እንጂ። እዚህ ቢሆን እኔ ምንም የምከጅለው ነገር የለም። ራሴን የቻልኩኝ ነኝ። ይህንን ያህል ደግሞ መዝናናትም አልመኝም። አሁን ልጆቼም ቢሆኑ ለጋብቻ ደርሰዋል።
ባለቤቴም ደግሞ በጣም አላህን የምትፈራ በጣም ጥሩ ሰው ነች። አስር ስትወልድ አንድ ቀን ጫማ ወይም ልብስ ግዛልኝ ብላኝ አታውቅም። ከሳውዲ ይዤ የመጣሁ እንደሆነ ጨርቅ ሳይሰፋ ሁለት ዓመትና ሦስት ዓመት ይቀመጣል። እሷ ከሞት በኋላ ላይ ጉዳይ እንጂ ለምድራዊ ነገር አትጓጓም። እናም በትዳር በኩል የተባረኩኝ ነኝ ብዬ ነው የማምነው።
አዲስ ዘመን፡- ሐጂ ሙፍቲ በባህሪ ምንአይነት ሰው ናቸው? አሁን ላሉበት ማንነት ማንና ምን አስተዋፅኦ አድርጎልኛል ብለው ያምናሉ?
ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር፡- እኔ አሁን ላለሁበት ሰብዕናም ሆነ ደረጃ የመጀመሪያውን አስተዋፅኦ ያበረከተልኝ አባቴ ነው ብዬ ነው የማምነው። አባቴ ጠንካራና በራስ መተማመን ያለው ገበሬ ነበር። የእሱ መጠንከር ነው እኔን ያጠነከረኝ። በሁለተኛ ደረጃ የቀራሁባቸው መሻሂዎች ናቸው አሁን ላለሁበት መልካም ሰብዕና አስተዋፅኦ ያበረከቱት። ቀጥተኛና እውነተኛ እንዲሁም ቸር የሆኑ በጣም ጥሩ ሼሆች ነበሩ። ከሁሉም ሰው ጋር በፍቅርና ተቻችሎ መኖርን ያስተማሩኝ እነሱ ናቸው። እኔን ሙሉ ያደረገኝ ሦስተኛው ነገር ደግሞ ቁርዓን ነው።
በነገራችን ላይ የሃይማኖት ትምህርት በትክክል ሥራ ላይ ካዋሉት (በትክክል አላውል እያሉት እንጂ) ባህሪን በመልካም በመቅረፅ ትልቅ ሚና አለው። ቅዱስ ቃሉን በአግባቡ የምናውቅ ከሆነ ዓለም ላይ ያለውን ስልጣንና ክብረትን ወደ ኋላ እንጥላለን። እኔ እንደማምነው መልካም ሰብዕና ጠባይ የሚገኘው ከእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ ነው። የእስልምና ሃይማኖት ከራስ ይልቅ ለሌላ ማዘንን ነው የሚያስ ተምረው።
ይህም ማለት አንዳንዱ የተማረውን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ያደርጋል፥ አንዳንዱ በከፊል ያውላል፤ ሌላው ደግሞ ሙሉ ለሙሉ የተማረውን ተግባራዊ ማድረግ አይፈልግም። ስለዚህ የእስልምና ሃይማኖት በጣም እውነተኝነትን፥ ቀጥተኝነትን፥ አዛኝነትን፥ ርህራሄን፥ ከራስ በላይ ሌላ ሰው ማስቀደምን የሚያስተምር ነው።
ስለዚህ እኔ በህይወት እተገብረዋለሁ ብዬ አላስብም ነበር። ያቺን ሴት ፈትቼ ከተማ ስመጣ ሴት አላገባም ብዬ ነበር። ልጅም ገንዘብም አልፈልግም ብዬ ነው ከአገሬ የወጣሁት። የእኔ ዋነኛ ህልም በመንፈሳዊ ትምህርት ትልቅ ደረጃ መድረስ፣ አላህን ማመስገንና ለእሱ መኖር ብቻ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ንግዱን እርግፍ አድርገው ተውት ወይስ ከመንፈሳዊ ትምህርት ጋር ጎን ለጎን ይነግዱ ነበር?
ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር፡- እንዳልኩሽ አብዛኛውን ትኩረቴን ያደረኩት መንፈሳዊ ሥራ ላይ ስለነበር የቁርዓን ትምህርቴን እንደጨረስኩ ልክ እንደሌሎች ደረሶችን ማስተማር ቀጠልኩ። ጎን ለጎን ግን ትንሽ ኑሮዮን እንዲደጉምልኝ በማሰብ በኬ በምትባል ከተማ በጨረታ አንዲት ወፍጮ ገዛሁኝና ወደ 30 የሚሆኑ ሠራተኞችን ቀጥሬ ምስር እያሰከካሁ ወደተለየዩ ቦታዎች እሸጥ ነበር።
ነገር ግን ብዙም ሳልጠቀም ለፍቼ ከንቱ ቀርቻለሁ። በተለይም ደግሞ መኪና ስላልነበረኝ ከሰንዳፋ በኬ የምሄደው በእግሬ ስለነበር ትርፌ ድካም ብቻ ሆነ። ከዚያ በኋላም ቦታዎች ገዝቼ አንዳንድ እንቅሳቀሴ ማድርግ ስጀምር ልጆቼ ለሥራ አልደረሱም ነበር። በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለሁ ለመጅሊስ ተመረጥኩኝ። በዚህ ምክንያት በኬ ከሚገኘው ወፍጮ ቤት የነበሩ ሠራተኞች ገንዘቤን እያጠፉ ሲያስቸግሩኝ ወፍጮውም በስብሶ ወደቀ እናም በአሁኑ ወቅት ቦታው ዝም ብሎ ተቀምጧል። ለነገሩ ለመክስሬ ራሴም አንዱ ምክንያት ነበርኩ። ምክንያቱም እኔ የሙስሊሙ ተወካይ ሆኜ እንዴት የግሌ ንግድ ላይ አተኩራለሁ በሚል ጣል ጣል በማድረጌ ሠራተኞቹ ተበተኑ።
የሚገርመው ለራሴ መሬቶች ካርታ ሳላወጣ ለመጅሊሲ ግን ወደ 87 የሚሆን ካርታ ነው ያስወጣሁት። ለመስኪድ ቦታ ያስያዝኩትም ወደ 360 የሚሆን ቦታ ነው። በነገራችን ላይ የእኔን መሬቶች መንግሥት ሊወስድብኝ ሲል ነው በቅርቡ ካርታ ያስወጣሁት። ብዙ ሰው «እንዴት የራስህን ትተህ የህዝብ ታስቀድማለህ?» እያለ ይጠይቀኛል። ግን ለእኔ
ይሄ ጉዳይ ሃይማኖታዊ ነው። በተለይ ደግሞ ሃላፊነት ላይ የተቀመጠ ሰው ራሱን ሊጠቅም አይገባም። ዘመዶቹን ሊጠቅም አይገባውም። ወዳጆቹን ሊጠቅም አይገባውም። ሁሉንም ሙስሊሙን፥ ክርስቲያኑንም፤ ሴቱን፥ ወንዱን በእኩልነት አይቶ ነው መምራት የሚገባው። አለዚያ ከሞት በኋላ አደጋ ያጋጥመዋል።
ስለዚህ አንድ የሃይማኖት አባት ወይም አመራር የራሱን ጥቅም ጥሎ ለሰው የሚቆም ነው መሆን የሚገባው። ታዲያ ሰዎች ሲጠይቁኝ አላህ፥ ነብያችን ፥ ሃይማኖት ሞኝ አድርጎኝ ነው የምላቸው። ምክንያቱም ፈጣሪም ሆነ ሃይማኖቴ የሚያዘው ከእኔ ጥቅም ይልቅ ሌላውን እንዳስቀድም ነው። አንተ ተጎዳ ሌላው ይጠቀም የሚል ነው ሃይማኖታችን።
በዚህ አስተሳሰቤ ምክንያት አንዱ ልጄ ደርሶልኝ ቤተሰቡን የማስተዳደር ሃላፊነት ባያግዘኝ ኖሮ ዛሬ ላይ የምበላውም አላገኝም ነበር። አሁንም እዚህም ከገባሁ በኋላ (መግባት አልፈልግም ነበር) ግን ለሰው እንጂ የራሴን ጥቅም ማስቀደም የለብኝም የሚል አቋም ነው የማራምደው። እኛ በሸሪያችን ድንጋጌ መሰረት ደመወዝ እንኳ ለመብላት ያስፈራናል። ነብያችንም ቢሆን ያስተማሩን በጉልበት ሠርቶ ማደርን እንጂ ጥቅም ማግበስበስ አይደለም። ሥልጣን የኩራት ቦታ አይደለም። ሥልጣን ነፍስን መጥቀሚያ አይደለም። ሥልጣን ቤተሰብ መጥቀሚያ አይደለም።
ሥልጣን ወዳጅን መለያ አይደለም። ሥልጣን ማለት ሁሉንም በእኩል አይቶ ለህዝብ መኖር ነው። ያ ነው እኔ ከራሴ በላይ ለሰው እንዳዝን ያደረገኝ። ቀጥተኛ እንዲሆን፥ እውነተኛ እንዲሆን ነው ያስተማረኝ። እኔ በህይወቴ አንድ ቀን ዋሽቼ አላውቅም። ለዚህ አብነት ካስፈለገ የምጠቅስልሽ ነገር በኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት ለመስኪድ አንድ ቦታ ከሰጡን በኋላ ከዱንና በምትኩ ሌላ ቦታ እንድንወስድና በቴሌቭዥን እንድናስተባብልላቸው ጠየቁኝ። እኔ ግን በህይወት እያለው መዋሸት እንደማልችል ስነግራቸው ዋና ጸሐፊዬን እንዲናገር አደረጉት። እናም እኔ በህይወቴ እያወቅሁኝ ሰው የሚጎዳ ነገር ማድረግ አልፈልግም።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ለእርሶ ምንድነች እንዴትስ ነው የሚገልጿት?
ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር፡- እንዳው በአጠቃላይ አገርን መግለፅ በጣም ከባድ ነው። አገሩን የሚወድ ሰው የሚያደርገው ለአገር ለሰላም መዘጋጀት ስለአንድነት ማሰብ ስለልማት ለህዝብ ደህንነት ማሰብ ነው። ይህም ብዙ ነገሮችን ያጠቃልላል። ወደ እኔ ስመጣ መንግሥትና አገሬን እወዳለሁ።
እኔ በሥራ አጋጣሚ የተለየዩ አገራት ሄጂያለሁ። እዛም የመቆየት እድል ነበረኝ ነገር ግን አገሬን ስለምወድ ወደ አገሬ ተመልሺያለሁ። አገሬን ስለምወድ ነው ለአንድነት የማለቅሰው የምጮኸው። እኔ የምጨነቀው ለሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ነው። ይህም ለአገሬ ያለኝን ጥልቅ ፍቅር የሚያንፀባርቅልኝ አንዱ ነገር ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ የመጡት ሙስሊም ክርስቲያኑ ተዋዶ ተዋልዶ ከሚኖርበት የወሎ አካባቢ እንደመሆኑ ያንን ተቻችሎ የመኖር ባህል እንዴት ይገልፁታል? አሁን እየተሸረሸረ ለመምጣቱስ አያሳስበዎትም?
ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር፡- ወላሂ! ይህ ተቻችሎ የመኖር ባህል በወሎ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የትኛውም አካባቢ ሙስሊም ክርስቲያኑ ሁሉም ወንድማማችና እህታማማች ሆኖ መኖሩን ነው። አብሮ የሚበላና የሚጠጣ፥ በሃዘን በደስታ ጊዜ የሚደጋገፍ ነው። በተለይ በእኛ አገር ወሎ ይህ ባህል ከጥንት ጀምሮ የኖረ ነው። የሚገርመው ሙስሊም ሆነ ክርስቲያን የሆኑ ወጣቶች አንድ ላይ የሚሞሸሩባት የፍቅር አገር ናት ወሎ። የእኔ ወንድም ከክርስቲያኖች ጋር ተጋብቷል።
ለዚህ አንድ አጋጣሚ ልንገርሽና ደሴ ለስብሰባ ሄጄ አንድ ወቅት ላይ የደሴ ጳጳስ መክፈቻ ንግግር እንዳደርግ ጋበዙኝና እኛም ሆነ ክርስቲያኖች የምንለያየው በሥጋ ብቻ መሆኑንና በተቀረ አንድ መሆናችን ተናገርኩ። ነገር ግን በሻይ ሰዓት ላይ «ሐጂ ተሳስተዋል» የሚል ተግሳፅ ከጳጳሱ ደረሰኝ። በሥጋም ቢሆን ሁለታችንም በፈጣሪ ስም አርደን የምንበላ በመሆኑ ልዩነት እንደሌለን ገለፁልኝ።
እንዳውም ቤተክርስቲያንን ለክርስቲያን ብቻ መስጂድን ለሙስሊም ብቻ ማን አደረገው? ሁላችንም ፀሎት የምናቀርበው ለፈጣሪ እስከሆነ ድረስ አንዳችን ከሌላኛችን ዘንድ ሄደን ምስጋና ለፈጣሪ ብናቀርብ ምን ችግር አለው ? ብለው ጠየቁኝ እኔም አስተሳሰቡ ስለተስማማኝ ተግሳፁን ተቀበልኩ። እኛ ተቻችለን መኖር ከቻልን እንዳውም አባቶቻችንን እንበልጣለን የሚል ሃሳብ አለኝ።
አሁን ያንን ለሁሉ የሚያስቀናውን ተቻችሎ የመኖር እሴት ተበላሽቷል፤ ምን አበላሸው ካልሽም ያበላሸ አበላሽቶታል ነው መልሴ። ለነገሩ አንቺም ብትሆኚ ሳታውቂው አትቀሪም፤ ይህንን እሴት ያደረፈሰው ፖለቲካ ነው ባይ ነኝ። ነብያችን መሃመድ እንደሚናገሩት የሰው ልጆች እንደመሪያቸው ነው የሚሆኑት። መሪዎች በአንድነት ይኖር የነበረውን ህዝቡን ለያዩት።
በብሔር በቋንቋ ለያዩት። አሁን ደግሞ ጊዜው ሆኖ የተከበሩ ዶክተር አብይ አህመድ አንድ የሚያደርገንን ሀሳብ ይዘው መጡ። ነብያችን ቢሆኑ በብሔር መለያየት ግም ነው፤ እንዳትከተሉት፤ የሰው ልጅ እንደማበጠሪያ ጥርስ እኩል ነው እያሉ ነበር የሚያስተምሩት። የሚለያየው አላህ በሚሰጠው ፀጋ ብቻ ነው፤ ይሄ ደግሞ ሊያስፈርጀውም ሆነ የበላይነት ሊሰማው አይገባም ብለውናል። አሁን ደግሞ አንድ እንሁን የሚል መሪ ደግሞ ተፈጥሯል፤ቁርዓን ሆነ ሐዲሳችን የሚያዘን አንድ እንድንሆን ነው።
ነብያችን ቤተክርስቲያኖቻቸው የፈረሱባቸ ውን ክርስቲያኖች ያድሱላቸው ነበር። አዲስ የሚሠሩ ከሆነ ይሠሩላቸዋል። እስልምና ሁሉንም በእኩል አይን ነው የሚያየው። አሁን ልዩነቶቻችንን እንጣልና አንድ እንሁን የሚል መሪ መጥቷል። እኔ እንደዚህ አይነት መሪ በታሪክም አልሰማሁም። ወደፊትም ይመጣል ብዬ አልገምትም። ግን ይህንን ለማስተከካል በጣም ብዙ ጊዜ ይፈልጋል።
ቢያጥቡትም ቶሎ አይጠራም። ግን ይህን ለማስተካከል ጊዜያት ይጠይቃል። አሁን ያበላሸው ነገር አዕምሯችን በስልጣንና በገንዘብ ጥም ስለተበከለ ነው። ያንን ለማስተካከል ብዙ ጊዜ ይፈልጋል። ስለዚህ መሪም ተመሪውም፤ ወንዱም ሴቱም፤ ተማሪም አስተማሪውም ወላጆችም ልጆችም ሁሉም ሊተባበሩበት የሚገባና መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው። የሰው ልጅ የራሱን ወገን እንዴት ያፈናቅላል? እንዴት ብሎ ነው የሚያደማው? ለምንስ ነው የሚገድለው? ራሱን ቢገሉት ቢያደሙት ይፈልጋል? ሌላውን እንደራሱ አድርጎ ነው ማየት ያለበት። ስለዚህ መስተካከል ያለበት ጉዳይ የቀደመውን አንድነታችንን ተቻችሎ የመኖር ባህላችን የመመለስ ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎም እንደሚያ ውቁት ይህ የመለየየትና የመከፋፈል ጉዳይ በቤተ እምነቶችም ሰርፆ ገብቷል፤ በተለይ በሙስሊሙ ዘንድ ተፈጥሮ በነበረው ልዩነት የእርስዎ አቋም ምን ነበር?
ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር፡- እንደም ታስታውሺው ለመከፋፈላችን ዋነኛ ምክንያት የነበረው በእስልምና ውስጥ በነበረው አስተምህሮ ልዩነት ነበር። የእኔ አቋም ሱፊ በበሚለው ነበር። በኢትዮጵያም በአጠቃላይ ለዓመታት ሰርፆ የቆየው ይኸው አስተምህሮ ነው። እርግጥ ዛሬ ያለው ሱፊ ትክክለኛ አልሆን ብሎ ነው እንጂ ሱፊ ማለት ንፁህ ሰው ማለት ነው። ቅድም እንዳልኩት ከራሱ ይልቅ ሰው የሚያስበልጥ ለሰው መኖርን የሚያስተምር ነው።
ሰው የሚወድ የሚረዳ ማለት ነው። ፈጣሪውን የሚፈራ ትክክለኛ ሰው ማለት ነው። አሁን በዛ ደረጃ አለ ለማለት አያስደፍርም። ሆኖም ከዚያ በኋላ ስለ ሱፊ የሚባል አንዳንድ አመለካከቶች መጡ። እኔ በወቅቱ ሙስሊሙን ህብረተሰብ አንድ ለማድረግ በመላው ኢትዮጵያ ዞሪያለሁ። ነገር ግን ያንን አንድነት ደግሞ የተወሰነው አካል አልፈቀደውምና «ተወው» አሉኝ አስተውኝና ከእርምጃዬ አስቀሩኝ። ከዚያ በኋላ በነበሩት 11 ዓመታት የሙስሊሙ አንድነት ደፍረሶ ልዩነቶም ጎልቶ ወደ የማይገባ አቅጣጫ አምርቷል።
እናም ያን ጊዜ አንድነቱ ተፈጥሮ ቢሆን እዚህ አይደርስም፣ ሙስሊሙም አይለያይም ነበር የሚል ቁጭት አለኝ። ከዚያ በኋላማ እንዳልኩሽ ልዩነቱ እየሰፋ መጣ። ችግሩ እየባሰ፥ ከፊሉም ሰው እየታሰረ፥ እየተገረፈ፥ ከፊሉም ከአገር እየተሰደደና እየተባረረ ብዙ መከራዎች ደረሱ። አሁን ያንን መሰዳደቡ፥ መደማማቱ፥ መወጋገዙ፥ መጣላቱ ቀርቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቋቋማቸው ዘጠኝ ኮሚቴዎች አማካኝነት ልዩነቶቻችን ትተን ወደ አንድነት መጥተናል። ወደፊትም ሁላችንም ተከባብረን ተቻችለን እንኖራለን የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በእርስዎ እምነት ይህንን ስር የሰደደ የብሔርተኝነት ችግር እንዴት መፍታት ይቻላል?
ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር፡- በእውነቱ በአገራችን ብሔርተኝነት ችግር እየጎላ የመጣው ከንጉሡ መውረድን ተከትሎ ነው የሚል እምነት አለኝ። ይህን ችግር አንቺም እንዳልሽው ከሃይማኖት ጋር እያያዙት ይገኛል። ነገር ግን ከሃይማኖት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ይልቁንም ገንዘብና ስልጣን ናፋቂዎች የሚሸርቡት ሴራ እንጂ። ይህ የልዩነት በሽታ በሙስሊሙ ማህበረሰብም እንዲሁ እንደወረርሽኝ ለማስ ተላለፍ ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ። ቀደም ብዬ እንዳልኩት እስልምና እምነት ህዝብን እኩል ማየት ይጠይቃል፤ ለህዝብ ማዘንን ይፈልጋል።
በዚህ መርህ መሰረት ሁሉ መሪ ምዕመኑን በእኩል ማየት ከቻለና ይህንን የስልጣን ናፋቂዎች አስተሳሰብ ነቅሎ ከጣለ እንደ ቀድሞ አንድነታችን መመለሱ አይቀርም ባይ ነኝ። በመመካከር የጎበጠውን በማቅናት የከፋውን በመመለስ በእኩልነት በማየት ይስተካከላል የሚል እምነት አለኝ። በእኛ በኩል ብዙ ጥረቶች እያደረግን ነው የምንገኘው። ለዚህ ደግሞ ከወላጆችና መምህራን ጀምሮ ለአገር አንድነትና ቀጣይነት መታገል ይገባቸዋል። በተለይ ትውልዱን በመቅረፅ ረገድ ሃላፊነታቸውን መወጣት ይገባቸዋል። መንግሥትም ቢሆን ዜጎቹን በእኩልነት ማየትና ማስተዳደር ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን በእርስዎ የሥልጣን ዘመን ወጣቱ የሚጠይቀውን ጥያቄ መልሶ ከመሄድ አኳያ ምን እሠራለሁ ብለው አቅደዋል?
ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር፡- ጥያቄው የወጣቶች ብቻ ሳይሆን አዛውንቶችም አሉበት። ከዚህ ቀደም ያለው መጅሊስ ሱፊ በሚለው በኩል ብቻ የተቋቋመ ነበር። ሌላም ሌላም ልንናገራቸው የማንችላቸው ችግሮች ነበሩ። እኔ ደግሞ አቋሜ ከዚህ የተለየ አይደለም፤ ከትክክለኛው መስመር የወጣን አካል መምከር ይገባል ብዬ አምናለሁ። ከሱፊውም ቢሆን በጣም የወጣ አለ። ከሰልፍያውም በጣም የወጣ ስላለ ያንን መመለስ እንዳለብኝ ነው የሚሰማኝ። ሲያጣላ የነበረውም በአንድ ወገን ስለነበር ነው። አሁን ኡላማውም ሆነ ቦርዱም የተቋቋመው ከሁለቱም ነው።
አሁን ያ ችግር ይፈታል የሚል ሙሉ ተስፋ አለኝ። እኔም እዚህ ቦታ ላይ እስካለሁ ድረስ ሁለቱንም በእኩል መንገድ ለማስተናገድ ነው የማስበው። የማስተናግደውም በጎባጣ አካሄድ አይደለም። ሰባራ ተጠግኖ ጎባጣው ተጠግኖ ትክክል ሆኖ ለአገር በሚበጅ መንገድ ሊሆን ነው የሚገባው። ሃይማኖቱ ባዘዘው መንግሥት በሚፈልገው መንገድ የምናየውና የምንሳተፍበት ነው የሚሆነው። ሁሉም እንደፈለገው ሆኖ አንድነት አይገኝም።
አብዛኛው ሰው አንድ መሆናችን አስደስቶታል። ሃይማኖታችን የሰው ልጅ የሰው ልጅን አይደለም ሊገድለው ሊያሳድደው የበታች አድርጎ ሊያየው እንደማይገባ ነው የሚያስገነዝበው። ስለዚህ ስምምነታችን በተጨባጭ ተግባራዊ እንደሚሆን ኢሻላህ እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ሌላው በመጅሊሱ አካባቢ ስር ሰዶ ቆይቷል የሚባለው ችግር መልካም አስተዳደርና ሙስና ነው። ከዚህ አኳያስ ምን ለመሥራት ነው ያቀዱት?
ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር፡- ሙስና በማንም ሃይማኖት የተወገዘ ነው። ሙስሊሙም ሆነ ክርስቲያኑ መሪም ሆነ ተመሪ ሊሠራው የማይገባ ነው። እኔ 40 ዓመት መጅሊስ ስቀመጥ አንድም ቀን ስለገንዘብ ጉዳይ አንስቼ አላውቅም። አሁንም እዚህ እስካለሁ ድረስ ምንአልባት እኔ በማላውቀው መንገድ እስካልሆነ ድረስ ሙስና ይፈፀማል ብዬ አላስብም። ሙስና ሲፈፅም ያገኘሁትም ቢሆን አላቀውም። የተወገዘ የተጠላ ነው የሚሆነው። ግን ሙስናን ከመሰረቱ ለማጥፋት መድሃኒቱ የመሪ ደህና መሆን ነው። አመራሩ መሪው ደህና ከሆነ ከታች ያለው በግዱ ደህና ይሆናል።
መሪው ያረገረገ ከሆነ የታቹ ሊስተካከል አይችልም። ይህ ጉዳይ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም የተስፋፋ ነገር ነው። እኔ በመጅሊስ ውስጥ የክልል 14 መሪ ሆኜ ለዘጠኝ ዓመት ተቀምጫለሁ በእነዚህ ዓመታት ሙሉ ደመወዜ ከሁለት ሺህ ብር አንድ መቶ ብር አልጨመረችም። ጓደኞቼም ቢሆን በልተዋል ብዬ የምምሰክርበት የለኝም። ዘጠኝ ዓመት ስንቀመጥ ያለንን በፍቅር ተካፍለን ነው የኖርነው አሁንም ወንድማማች ነን። ስለዚህ ለዚህ ዋናው መድሃኒት የመሪው ደህና መሆን ነው። ከበላይ ያለው ደህና ከሆነ ከበታች ያለው ይስተካከላል ብለን እናምናለን።
አዲስ ዘመን፡- ከአገር ሠላም አኳያ የሚቀርና ሊሠራ ይገባል የሚሉት ሥራ ካለ ቢነግሩን?
ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር፡- የአገር ሠላም ከማስፈን አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እየሠሩ ያሉት ሥራ መልካምና ይበል የሚያሰኝ ነው ባይ ነኝ። በእርሳቸው ላይም ሙሉ እምነት አለኝ። ይልቁኑም ህዝቡ የጠቅላይ ሚስትሩን መንገድ በመከተል ለራሱና ለአገሩ ሰላም በፍቅር ተሳስቦ መኖር ይገባል። ለዚህ ደግሞ ከልብ የሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ አለበት። እርግጥ ነው ችግሩ ስር የሰደደ እንደመሆኑ በአንድ ጊዜ አንድነት ሰላም ይመጣል ማለት አስቸጋሪ ነው። ግን ሁሉም በቁርጠኝነት ከተነሳ ሰላማችን እንደሚመለስ አንድነታችን እንደሚጠናከር ሙሉ እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በጣም በተደጋጋሚ ስለዶክተር አብይ መልካም ነገሮችን አንስተው ልኛልና እስቲ በዚህ አገጣሚ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉትን አመለካከት ይንገሩኝ?
ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር፡- እኔ መቼም አዲስ አበባ ከመጣው ከ50 ዓመት በላይ ሆኖኛል። በዚህ እድሜ እስከምደርስ ድርስ ብዙ መሪዎችና ባለስልጣናት አውቃለሁ ግን እንደሳቸው አይነት ሁሉን አሟልቶ ፈጣሪ የሰጠው ሰው አላየሁም። እርግጥነው ከዚህ ቀደም በእሳቸው ጉዳይ ላይ ተጠይቄ ሥራ ላይ መልስ አልሰጥም የሚል ምላሽ ሰጥቼ ነበር። ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ የሠሩት ሥራ በአራትና በአምስት ዓመት የማይሠራ ሥራ ሆኖ ነው ያገኘሁት።
እንደእሳቸው በአንድነት የሚያምን ክርስቲያኑን እስላሙን እኩል የሚያይ፥ ህዝብን በጉልበት በፍቅር የሚገዛ መሪ በኢትዮጵያ እስካሁንም አልተፈጠረም ወደፊትም ይፈጠራል የሚል እምነት የለኝም። ለሰላምና ለፍቅር ካላቸው ልባዊ መሻት የተነሳ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተከስቶ የነበረውን ልዩነት ወደ አንድ እንዲመጣና እርቅ እንዲፈፀም ያደረጉት አስተዋፅኦ በታሪክ የሚዘነጋ ጉዳይ አይደለም።
በተመሳሳይ እኛ ሙስሊሞች ለዓመታት ተራርቀን ስንኖር እስካሁን አንድም የኢትዮጵያ መሪ ልዩነታችንን አጥፍተን ወደ አንድ እንድንምጣ ያደረገ የለም። እርሳቸው ግን ምንም ሳይገድባቸው ዳግም ህዝበ ሙስሊሙን አንድ አድርገዋል። በዚህም በእውነት ላመሰግናቸው ነው የምወደው። በሌላ በኩል አገሪቱ ከገባችበት ኢኮኖሚያዊ ችግር ለማውጣትና በዓለም ያላትን ገፅታ ለመቀየር እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴም ይበል የሚያሰኘው ነው።
በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ በአገኘኋቸው አጋጣሚ ሁሉ ትህትና እንጂ የባለስልጣንነት ስሜት አላይባቸውም። ከሁሉም ጋር ወንድማማች ሆነው ነው የሚወያዩት። የሚከተሏቸው ሰዎች እንኳ ሰው ለመጨበት ወደኋላ ሲሉ እሳቸው ግን ልክ በቅርብ እንደሚያውቅ ወዳጅና ቤተሰብ ነው አቅፈው የሚቀበሉት። ይህም ዶክተር አብይን ለየት ያደርጋቸዋል የምለው ባህሪያቸው ነው። ስለዚህ የማስተላልፈው መልዕክት ሁሉም ዜጋ የዶክተር አብይን አላማ ተገንዝቦ ከጎናቸው ሊሆን ይገባል የሚል ነው።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ የረመዳን ፆም ወቅት ውድ ጊዜዎትን ሰውተው ከእኛ ጋር ቆይታ በማድረገዎ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር፡- እኔም በመላው የሙስሊም ህዝብ ስም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 17/2011
ማህሌት አብዱል