ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምትልካቸው ምርቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በግብርናው ዘርፍ የሚሸፈኑ ሲሆን፤ አገሪቱ በተፈለገው የምርት ጥራት ደረጃ ተወዳዳሪ ምርት ለዓለም ገበያ ባለማቅረቧ ከዘርፉ ማግኝት የሚገባትን ትርፍ እንዳታገኝ እንቅፋት ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ ከምታቀርባቸው ምርቶች መካከል በ13 የግል የቄራ ድርጅቶች አማካኝነት የምትልከው የሥጋ ምርት ተጠቃሽ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እነዚህ ድርጅቶች በተለያየ ምክንያት የሥጋ ምርታቸውን ለዓለም ገበያ እያቀረቡ ባለመሆናቸው ማግኝት የሚገባትን የውጭ ምንዛሬም እንዳታገኝ እንቅፋት ሆነዋል፡፡
የአበርገሌ ዓለም አቀፍ እንስሳት ሀብቶች ልማት ድርጅት የሥጋ ምርታቸውን ለዓለም ገበያ ማቅረብ ካቆሙ የቄራ ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ የድርጅቱ ማርኬቲንግ ኃላፊ አቶ አማኑኤል ግደይ ድርጅቱ ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ያልቻለበትን ምክንያት እንዳብራሩት፤ ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ምርቱን ወደ መካከለኛ ምሥራቅና ኮሞሮስ ሲልክ ነበር፤ የዱባይ መንግሥት የተበላሸ የሥጋ ምርት አስገብታችኋል በሚል በ2007 ዓ.ም ጠቅላላ የኢትዮጵያ የሥጋ ምርት ወደ አገሩ እንዳይገባ አግዶ እንደነበር፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም ጉዳዩን አጣርቶ አንዳንድ የቄራ ድርጅት ባለቤቶችና ኃላፊዎችን ተጠያቂ በማድረግ ዕርምጃ ወስዷል፡፡
ይህንን ተከትሎ በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ማረጋገጫ ያላገኝ የቄራ ድርጅት ወደ እነዚህ አገሮች ምርቱን ማስገባት አይችልም ተብሎ ድርጅቱ ምርቱን ወደ ውጭ መላኩን እንዳቆመ የጠቆሙት አቶ አማኑኤል፤ በ2008 ዓ.ም የእነዚህ አገራት ኦዲተሮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለውጭ ገበያ የሚልኩ ሁሉንም የቄራ ድርጅቶችን እንደፈተሹና በአንዳንድ መስኮች ማስተካከያ እንዲደረግባቸው ትዕዛዝ መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ በተሰጠው የማስተካከያ አስተያየት በ‹‹ቼክሊስቱ›› መሰረት ማስተካከያ አድርጎ ምርቱን ለውጭ ገበያ ለመላክ ዝግጁ ቢሆንም፤ ኦዲተሮቹ ‹‹እኛ መጥተን ማረጋገጥ አለብን›› በማለታቸውና፤ በእነርሱ በኩል ምርቱን ለመላክ የሚያስችል የምስክር ወረቀት ለማግኘት ‹‹ዛሬ ነገ›› በሚል ምክንያት በመዘግየቱ እስከአሁን ድረስ ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዳልቻለ አቶ አማኑኤል ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ አማኑኤል ገለጻ፤ ድርጅቱ ከሁለት ወር በፊት ባደረገው የገበያ ማፈላለግ ሥራ ከ60 እስከ 80 ሜትሪክ ቶን ሥጋ ከአሉላ አባነጋ ኤርፖርት በቀጥታ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ መውሰድ ከሚፈልጉ ባለሀብቶች ጋር ውል ቢፈጽምም፤ ‹‹ምርቱን ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ሳውዲ ዓረቢያ አልላካችሁም›› በሚል ምክንያት ምርት መላክ አልተቻለም፡፡
አቶ አማኤል፤‹‹የሥጋ ፍላጎት በዓለም ገበያ ከፍተኛ በመሆኑ መስተካከል አለባቸው የሚባሉ ክፍተቶች ካሉ አስተካክለን ወደ ሥራ ለመግባት ሙሉ ለሙሉ ፍላጎት አለን፡፡ የግብርና ሚኒስቴር ከእነዚህ አገራት ጋር አስፈላጊውን የዲፕሎማሲ ሥራ በማድረግ አስቸኳይ መፍትሔ በመስጠት ድርጅቱ ወደ ሥራ እንዲገባ ምቹ ሁኔታ መፍጠር አለበት›› ብለዋል፡፡ የጅግጅጋ ቄራዎች ድርጅት ከአራት ዓመት በፊት ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ማቆሙን የጠቆሙት የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ፋይሰል ጉሀድ፤የእንስሳት ዋጋ መናር፣ የሥጋ ኤክስፖርት ዋጋ ዝቅተኛ መሆን፣ ባለፉት ሁለት ዓመት በአካባቢው ድርቅ መከሰት፣ ጥራት ያለው እንስሳት በብዛት ገበያው ላይ አለማግኝት፣ የእንስሳት መኖ መወደድ፣ ህገወጥ የእንስሳት ዝውውር በአካባቢው መበራከቱና መሰል ምክንያቶች ድርጅቱ ሥጋን አምርቶ ለውጭ ገበያ እንዳያቀርብ እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡
ለችግሩ መፍትሔ ለማምጣት ህገወጥ የእንስሳት ዝውውርን ለማስቆም ከፍተኛ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ፤ የኤክስፖርት አሠራሩ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን የሚያበረታታ በመሆኑ መቀየር እንዳለበት፤ የእንስሳት መኖ ውድ በመሆኑ ዋጋው ላይ ማስተካከያ ማድረግ፤ የእንስሳት መኖ ማምረቻ ኢንዱስትሪውንና የእንስሳቶችን ዝርያ ማሻሻል ፤ እንዲሁም በበረሀና ድርቅ በሚበዛበት አካባቢ ባሉ የቄራ ድርጅቶች ላይ የእንስሳት መኖ የማምረት ሥራ ላይ የተለያዩ አካላት ማሰማራት እንደሚያስፈልግ ዶክተር ፋይሰል ጠቁመዋል፡፡
‹‹አክሸከር ኢትዮጵያ ኬዚንግ ፒ.ኤል.ሲ›› ሞጆ የሚገኘው የሥጋ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ግደይ ገብረመድህን በበኩላቸው፤ የማረጃ መስመሩ በሥራ ስዓት በተደጋጋሚ እየተበላሸ ሥራን በማስተጓጎሉ፤ አንዳንድ የመለዋወጫ ዕቃዎችን ከውጭ በማስገባትና በአገር ውስጥ በመግዛት መጠቀም ቢቻልም መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ በያዝነው ዓመት የካቲት ወር መጨረሻ ሥራ ማቆሙን ተናግረዋል፡፡ አቶ ግደይ የአገር ውስጥና የውጭ የቴክኒክ አማካሪዎች ችግሩን አጥንተው የማረጃ መስመሩ መቀየር እንዳለበት በማቅረባቸው የድርጅቱ አስተዳደር ማሽኑን ከውጭ ገበያ የመግዛቱን ሂደት ሲያጠናቅቅ ሥራ እንደሚጀምር ጠቁመዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የኤክስፖርት ቄራ ኢንስፔክሽን እና ሰርተፊኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ጌዲዮን ይልማ የአበርገሌ ቄራ ድርጅት ምርቱን ለውጭ ገበያ መላክ ያልቻለበትን ሲያብራሩ፤ ከሦስት ዓመት በፊት የውጭ ኦዲተሮች በድርጅቱ ተገኝተው ባደረጉት ግምገማ የፈለጉትን የጥራት ደረጃና መስፈርት ባለማሟላቱ ምርቱ ወደ አገራቸው እንዳይገባ አግደዋል፡፡ አገራቱ ድርጅቱን በድረ ገጻቸው የሥጋ ምርታቸውን እንዲያስገቡ ከተፈቀደላቸው የቄራ ድርጅቶች ስም ዝርዝር ውስጥ ባለማካተታቸው፤ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል የምርት ማረጋገጫ ተሰጥቶት ወደ ውጭ እንዲልክ ቢደረግም የመመዘኛ መስፈርቱን ባለማሟላቱ ወደ ውጭ የመላኩ ሥራ አልተሳካም፡፡
እንደ ዶክተር ጌዲዮን ማብራሪያ፤ የአበርገሌ ዓለም አቀፍ እንስሳት ሀብቶች ልማት ድርጅት ሲቋቋም ታሳቢ አድርጎ የነበረው በቀጥታ ከመቀሌ ኤርፖርት ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዲችል ነበር፡፡ ነገርግን ከአበርገሌ ወደ አዲስ አበባ ምርቱ በሚጓጓዝበት ወቅት ለከፍተኛ ወጪና ለምርት ጥራት መጓደል የሚያጋልጥ በመሆኑ፤ ድርጅቱ ከውድድር ውጪ እየሆነ መጥቷል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ያሉባቸውን ክፍተቶች ሞልተው ምርታቸውን ወደ ውጭ ለመላክ ጥረት ስላላደረጉ አሁን ላይ አገሮች ምርታቸውን ለመቀበል ፍቃደኛ አይደሉም፡፡
ድርጅቱ ዘንድሮም ደረጃውን የጠበቀ ምርት ባለማቅረቡ ሚኒስቴሩ ፈቃድ ከልክሏል፡፡ ዶክተር ጌዲዮን ሚኒስቴሩ በቀጣይ ኦዲተሮቹ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የቄራ ድርጅቱን እንዲጎበኙና መስፈርቱን አሟልተዋል ብለው ሲያረጋግጡ ፈቃድ የሚሰጧቸው ከሆነ ምርታቸውን ወደ ውጭ የሚልኩበት መንገድ እንደሚያመቻችላቸው ጠቁመው፤ ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ ድርጅቱ ክፍተቱን ለይቶ ጠንክሮ መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የቄራ ድርጅቱ የተንዛዛና ውስብስብ አሠራር ያለው መሆኑ፣ የአስተዳደሩ በየጊዜው መቀያየር፤ የድርጅቱ የአመራር ቦርድ ድርጅቱ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት የወሳኔ አሰጣጥ ክፍተት ያለበት መሆኑ፤ ችግሮችን በቶሎ ቀርፎ ወደ ገበያው ለመመለስ እንዳልቻለ ዶክተር ጌዲዮን ተናግረዋል፡፡ የቄራ ድርጅቶቹ ምርታቸውን ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ ሚኒስቴር መስራያ ቤቱ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ቢሆንም፤ በአንድ ወይም በሁለት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ድጋፍ ብቻ ችግሩ የሚቃለል ስላልሆነ የተለያዩ ተቋማት በመቀናጀት የተቃና ሥራ የሚሠራበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት ዶክተር ጌዲዮን አስታውቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2011
ሶሎሞን በየነ