በእስካሁኑ መንገዳችን፤ ምናልባትም ጥቂት የወደፊቱን ጊዜ ጨምሮ የአገራችን የእድገቷ መሰረት ግብርና ነው። ግብርና የአብዛኛው ህዝባችን ኑሮውም ህይወቱም ነው። ላለፉት ዓመታት ስንመኘው ለኖርነውና ለምንናፍቀው የኢንዱስትሪ መር የኢኮኖሚ ስርዓትም መነሻ አድርገን የሰየምነው ግብርናን ነው። በአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገታችን መነሻ የሚያደርገው ግብርናን ነው። ዛሬም ስለግብርና መናገር አለብን።
አዎን ስለግብርና እንናገር፤ ይህ አገር ይለውጣል፤ ለኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ መንገድ ይጠርጋል የምንለው ዘርፍ በርግጥ ራሱን ለውጧል ወይ? ራሱንስ አዘምኗል ወይ? ብንል፤ ምላሹ እረ የለም! ሆኖ እናገኘዋለን።
ዘርፉ በአገራችን ዘመናዊ የመንግስት አስተዳደር ከተጀመረበት የአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ጀምሮ በስርዓተ መንግስቱ ውስጥ ተካትቶ ሀላፊና አስተናባሪ ተመድቦለት እንደሚሰራ ድርሳናት ይመሰክራሉ።
ያኔ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን “የእርሻና የመስሪያ ቤት ሚኒስቴር” ይባል የነበረው ከአንድ ምዕተ ዓመት በኋላም “የግብርና ሚኒስቴር” ተብሎ በመንግስታዊ መዋቅር ውስጥ አለ። ይሁን እንጂ፤ ዘመኑን የዋጀ ለውጥና ይዘት በግብርና ስራችን ውስጥ እጅግም አይስተዋልም።
ባለፉት አንድ መቶ ዓመታት የአገራችንን ግብርና ለማዘመንም ሆነ ምርትና ምርታማነትን አሳድገን ከፍጆታ የተላቀቀ፤ በገበያ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ አሰራር ለማስፈን የተተለመው ሁሉ ከፍላጎት አላለፈም። ግን ለምን?
በቅርቡ የግብርና ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ “ግብርና ለተመዘገበው የአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ትልቁን ድርሻ ቢያበረክትም …እድገቱን ማፋጠን አልቻለም። ለዚህም በምክንያትነት ከሚነሱት ነጥቦች መካከል በዝናብ ላይ ጥገኛ መሆን፤ የግብርና ሜካናይዜሽን ትኩረት ማነስ፤ የምርምር ውጤቶች ሚና አናሳ መሆን፤ የመልካም አስተዳደር ችግር… በዋናነት ይጠቀሳሉ።” ይላል። እነዚህ ሁሉ አሁንም “ለምን? “ ያሰኛሉ።
አገራችን የበርካታ ወንዞችና ተፋሰሶች ባለቤት ናት እያልን ለምንድን ነው ዘመናዊ መስኖ ተጠቅመን የማናመርተው? የአስተራረሳችንም ሆነ የምርት አሰባሰባችን ወደዘመናዊ ሜካናይዜሽን ማሻገር ለምን ያቃተን? ለምንስ ነው ደግሞ እድሜ ጠገብ የምርምር ማዕከላት አሉ እያልን ስለምርምር ውጤት ማነስ የምንናገረው ? ይህ ባለመሆኑ የምንሻው ለውጥና ዘመናዊነት ሁሉ ፍላጎት ብቻ ሆኖ ቀርቷል።
የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽዖ ዘርፉንም ብንመለከት በችግሮች የተተበተበ ነው። የእንስሳት ሀብታችን ከጥራት ይልቅ በቁጥር ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን ይዘን መቅረብ አልቻልንም። ያለውንም ቢሆን እሴት ጨምረንና ተዋጽኦውን በአይነትም በመጠንም አብዝተን ከመላክ ይልቅ እንስሳትን በቁማቸው እየላክን ማግኘት የሚገባንን ያህል አላመጣንም።
ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብቷ በተለይም በዳልጋ ከብት መጠን ከአፍሪካ አገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ ብትሰለፍም የህዝቦቿን ፍላጎት የሚመጥን ወተት አምርቶ ማቅረብ አልተቻላትም። በአቅም ደረጃ አሁንም የአገር ውስጥ ፍጆታን አሟልቶ በዓመት እስከ ሃያ ሚሊዮን ሊትር ወተት አምርቶ ወደውጭ የመላክ አቅም ቢኖርም እኛ ግን ወተት በዶላር ገዝተን ከውጭ እናስገባለን። በ2010 ዓ.ም ብቻ እንኳን የአስር ሚሊዮን ዶላር ወተት በግዥ ወደአገር ውስጥ አስገብተናል። ግን ለምን?
ከዚህ በኋላ ግን ቆም ተብሎ ሊታሰብ ይገባል። እናም በየመስኩ ያሉትን ችግሮችና ማነቆዎች ነቅሶ በማውጣት ሊያሻግረንና ከድህነት ሊያወጣን የሚችል መንገድ መተለም፤ እሱንም ይዘን በ”ጊዜ የለንም” ፍጥነት መተግበር የግድ ይለናል። በዚህ ረገድ ለዘመናት በቤተ-መጻሕፍትና በቢሮ መደርደሪያ ላይ የተሰደሩ የጥናትና የምርምር ውጤቶች ወደ መሬት ወርደው እንደወቅቱና አካባቢው ወደስራ ሊተረጎሙ ይገባል።
“የበርካታ ወንዞች ባለቤት፤ የአፍሪካ የውሀ ማማ ነን” የሚለው ትርክት ቆሞ ከዝናብ ጥገኝነት የምንላቀቅበትን የመስኖ ተጠቃሚነት መላ መሻትና ማጥበቅ ይኖርብናል። በተለይ፤ የተቀናጀ የግብርና መስኖ ቴክኖሎጂ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል። ምክንያቱም፤ ቴክኖሎጂው በአነስተኛ ጓሮ ላይ የተለያዩና ተመጋጋቢ የእንስሳትና የሰብል ምርቶችን በማምረት ድርብ ተጠቃሚ ስለሚያደርግ ነው። ይህ ደግሞ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ያረጋግጣል፤ የስርዓተ ምግብን ችግርም በማስወገድ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጸኦ አለው።
አዎን ባልተሻሻለና ባልዘመነ ግብርና አሁን ያለውንም ሆነ ወደፊት እየጨመረ የሚሄደውን ህዝብ ለመመገብ አይቻልም። እናም ግብርናው ሊዘምን ይገባል። በዚህ ረገድ ግብርና ሚኒስቴር በአሁኑ ወቅት በእቅዴ ውስጥ ነው የሚለውን የመስኖ እርሻ ተደራሽ የማድረግ ተግባር ሳይውል ሳያድር በስፋት ሊቀጥልበት ይገባል።
የቴክኖሎጂ አቅርቦትንና አጠቃቀምንም በተመለከተ የኢኮኖሚና አዕምሯዊ አቅምን ማዕከል ያደረጉ፤ ከኋላ ቀር አሰራር የሚያላቅቁ ውጤቶችን በማቅረብና ለአርሶና ለአርብቶ አደሩ በማስተዋወቅ፤ ባለመሰልቸት በማስገንዘብ የአስተሳሰብም የአሰራርም ለውጥ እንዲመጣ መስራት ይኖርበታል።
በጥራት ላይ ሳይሆን በቁጥር ላይ የተመሰረተውን የአገራችንን የእንስሳት ሀብት ግንዛቤም አንደኛው የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን ይገባዋል። በዚህም ምርታማነታቸው የተረጋገጠላቸው የአገር ውስጥና የውጭ የእንስሳት ዝርያዎችን ለይቶ በማስተዋወቅና የክህሎት ስልጠና በመስጠት አርሶ አደሩንም ሆነ አርብቶ አደሩን ከሀብቱ ተጠቃሚ የሚሆንበትን፤ አገርም የምታድግበትን አሰራር መንደፍና ተግባራዊ ማድረግ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም።
በአሁኑ ወቅት በየክልሉ እየተቋቋሙ ያሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች አብዛኞቹ ከግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ሌላውና ቀጣዩ ትኩረት ለነዚሀ ኢንዱስትሪዎች ግብዐት የሚሆኑ የግብርና ምርቶችን በማምረትና በማቅረብ ላይ መሆን አለበት። ይህንን ስናደርግ የውጭ ምንዛሬ ብክነት ይቀራል፤ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ መንገዱም ይሰፋል።
ከዚህ በኋላ ስንዴም ሆነ ወተት ከውጭ አገር የምናስመጣበት ምክንያት አይኖርም። ይልቁንም ሁሉንም በአገራችንና በአቅማችን ልናመርት፤ የተመረተውንም በጠንካራ የገበያ ትስስር ለሸማቹ በማቅረብ አምራቹንም ሸማቹንም ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል።
በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን የሚታዩ የአስተሳሰብና የአሰራር ችግሮችና ማነቆዎች እንደየአግባባቸው መፍትሄ ሊሰጣቸው ይገባል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የዛሬውን የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ፤ የነገውን ፍላጎታችንንና መዳረሻችንን፤ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊውን እውነታ መሰረት ያደረገ አገርን ለብልጽግና፤ ህዝብን ለልዕልና የሚያበቃ የግብርና ፖሊሲና ስትራቴጂ ሊኖረን ይገባል። ይህ ደግሞ ያለውንም ቢሆን በአግባቡ ፈትሾ ወቅታዊ እስከማድረግ ሊያስጉዘን ይችላል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2011