ሀገራችን በለውጥ ላይ መሆኗ በተደጋጋሚ የምንሰማውና እየኖርንበት ያለ እውነታ ነው። ይህ የለውጥ ወቅት ደግሞ በብዙ ፈተናዎችና ተስፋዎች የታጀበ ነው። የፈተናዎቹ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ቆሻሻ ነው። ቆሻሻን በሁለት ከፍለን ልናይ እንችላለን። አንደኛው ቆሻሻ ከአካላችን ጀምሮ በቤታችንና በአካባቢያችን የምናገኘውና በአብዛኛው ለጤናችን መቃወስ መንስኤ የሚሆነው የፅዳት መጓደል ሲሆን ይህ በገሃድ የሚታይ በመሆኑ በቀላሉ ሊፀዳ ይችላል። ሁለተኛውና አደገኛው ቆሻሻ የማይዳሰሰውና የማይታየው ነገር ግን አእምሮአችንን ቀይዶ የሚይዘው የአእምሮ ቆሻሻ ነው። ይህ ቆሻሻ ከአመለካከትና ከአስተሳሰብ እንዲሁም ከስሜት የሚመነጭ በመሆኑ በመጥረጊያ ወይም በውሃና ሳሙና ሊፀዳ አይችልም።
ይህ ቆሻሻ ሊፀዳ የሚችለው አእምሮን በአግባቡ በማሰራት ብቻ ነው። በአሁኑ ወቅት ይህ የቆሸሸ አእምሮ በሚፈጥራቸው የጥላቻና የመለያየት አጀንዳዎች በርካታ ችግሮች እየተከሰቱ ነው። በዚህም የተነሳ ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ብቻ በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለዓመታት ከኖሩበትና ሃብትና ንብረት ካፈሩበት ቀዬአቸው እየተፈናቀሉ ለችግርና ለእንግልት ተዳርገዋል። ከዚህም በላይ ደግሞ ለቀጣዩ ትውልድም አሳፋሪ ታሪክ ትቶ ለማለፍ የሚደረገው ሩጫ በተለያዩ መንገዶች ቀጥሏል። በተለይ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ የጥላቻ ዘገባዎችና እዚህም እዚያም የሚሰሙ የግጭት አጀንዳዎች የቆሸሸ አእምሮ የፈጠራቸው ሊወገዱ የሚገባቸው ናቸው።
በርግጥ የጥላቻ ንግግሮችና ሃሳቦች የራሳቸው መንስኤ እንዳላቸው ምሁራን ይገልጻሉ። ከነዚህም ውስጥ የግለኝነትና ራስ ወዳድነት ባህል እያደገ መምጣት፣ ኃላፊነት የሚሰማው ማህበረሰብ አለመፈጠር፣ በአቋራጭ ስልጣን ወይም ሃብት የመፈለግ ስግብግብነት መንገስ፣ በልብ የሰረፀ ጥላቻና ቂም በቀል እንዲሁም የተሳሳቱ የኋላ ትርክቶች ይጠቀሳሉ። እነዚህ የጥላቻ መንስኤዎች ደግሞ አሁን አሁን በተለያዩ የክልልና የግል ሚዲያዎችም ጭምር የሚንፀባረቁበት አዝማሚያ ይታያል። በራሳችን ቋንቋ ከውጭ የሚሰራጩ አንዳንድ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችም እንደፈሪ ዱላ ሩቅ ሆነው የሚማቱ፤ ከማስተማር ይልቅ በተሳሳተ መንገድ መስበክን የመረጡ ናቸው።
“የሚዲያ ነጻነት” የሚለውን አጠቃላይ የዴሞክራሲ ትልቅ አውድ ሽፋን በማድረግም በተሳሳተ መንገድ ላልተገባ የጥላቻ ሃሳብ ማራመጃነት ሲውሉ ይስተዋላል። ይህ የጥፋት መንገድ ስለሆነ መታረም አለበት። በህብረተሰቡም ያለው የሚዲያ አጠቃቀም ገና ኋላ ቀር እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። በተለይ ህብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለቀቁ መረጃዎችን የሚወስድበትና የሚመልስበት መንገድ መስተካከል አለበት። ለምሳሌ በፌስ ቡክ የሚለቀቁ መረጃዎችን ስንመለከት አብዛኛውን ጊዜ በጥላቻና ስድብ ላይ ያተኮሩ እና ስሜታዊነትን የሚያንፀባርቁ የሃሰት መረጃዎች ከጠቃሚ መረጃዎች በበለጠ ሲነበቡና ለሌላው አካልም ሲጋሩ (ሼር) ሲደረጉ ይስተዋላል።
ይህ ደግሞ መረጃዎቹ በስፋት እንዲሰራጩ እድል ይፈጥራል። በቆሸሸ አእምሮ ተፈጥረው የሚሰራጩ መረጃዎች የግጭት ፈንጂዎች በመሆናቸው ሊመክኑ ይገባል። ለዚህ ደግሞ መረጃ ተጠቃሚ ህብረተሰብ መልካሙን ከመጥፎ እየለየ መጠቀም መቻል አለበት። ይህን ማድረግ ሲችል የጥላቻ ፈንጂን ማምከን ይችላል። ጥቂት አካላት በተመቻቸ ቦታ ላይ ተቀምጠው በሚነዙት የጥላቻ ንግግር ለጉዳት የሚዳረገው በጉዳዩ ላይ ምንም አስተዋፅኦ የሌለውና ደሃው ማህበረሰብ ነው። በቅርቡ እንኳን ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ተፈናቅለው በስራ የዳበረ እጃቸው ስራ ፈትቶ ለእርዳታ የተዳረጉበትን ሁኔታ ስንመለከት ጥላቻ የሚያስከትለው አደጋ ምን ያህል የከፋ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም።
ባለፈው አንድ ዓመት በተለይ የቆሸሸውን አእምሮ ለማፅዳት ቂምና በደልን ይቅር በማለት እርስ በርስ ያለንን ማህበራዊ መስተጋብር እንድናጠናክርና በአንድነት፣ በፍቅርና በመተሳሰብ ሀገራችንን ለማሳደግ ሁላችንም ጥረት እንድናደርግ የሚያበረታቱ እርምጃዎች በመንግሥት ተወስደዋል። ከዚህ ቀደም በተለያዩ የፖለቲካ አመለካቶች እርስ በርስ ተበታትነው የነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ተሰባስበው በሀገራቸው ጉዳይ በጋራ እንዲመክሩና እንዲሰሩ ለማድረግ ተሞክሯል። በተለያዩ ጊዜያዊ ምክንያቶች ለእስር የተዳረጉ ዜጎች ምህረትና ይቅርታ ተደርጎላቸው ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለዋል።
የእርቀ-ሰላም ኮሚሽንም ተዋቅሮ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠሩ ቁርሾዎችን ለማከም ጥረት እየተደረገ ነው። አካባቢያችንንና አእምሯችንን የማጽዳቱ ዘመቻም ትላንት በመላ ሀገራችን ተካሂዷል። ይህ የፅዳት መርሀ ግብር የቆሸሹ አካባቢዎችን በእጃችን እያፀዳን በጥላቻ፣በቂም በቀል እና በቁርሾ የቆሸሹ ጭንቅላቶቻችንን በሰላም፣በይቅርታ እና በፍቅር ለማፅዳት አዲስ ምዕራፍ የምንከፍትበት ከአካባቢ ፅዳት የዘለለ ሀገር የመለወጥ እና ህብረተሰብ የመገንባት ዘመን ተሻጋሪ ዓላማ ያነገበ ነው።
ስለሆነም የቆሸሸ አካባቢ በመጥረጊያ በማጽዳት ለኑሮ ምቹ የሆነ ከባቢ መፍጠር አለብን። የቆሸሸ አእምሮ ደግሞ በሰላም፣በይቅርታና በፍቅር በማጽዳት የጥላቻና የግጭት ፈንጂ እንዳይሆን ማምከን ይገባል፡ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በድህነት ውስጥ የኖረን ህዝቦች ነን። ከዚህ በኋላ የሚከሰት ተጨማሪ ድህነት ደግሞ አጥፊያችን መሆኑን መረዳት ይኖርብናል።
የጥላቻ፣ ቂምና በቀልም ምንም አይነት ፋይዳ እንደማይኖረው ተረድተን ለሰላምና ለፍቅር ዘብ ልንቆም ይገባል። በቅርቡ በአንዳንድ የአፍሪካ እና የአረብ ሀገራት ከተከሰቱት የርስ በርስ ግጭቶችም ትምህርት ወስደን ከግጭት መንስኤዎች በብዙ እጥፍ ልንርቅ ይገባል። የቆሸሹ እጆቻችንን በሳሙና፣ የቆሸሸ አካቢያችንን በመጥረጊያ እንዲሁም የቆሸሸ አእምሮአችንን በንፁህ ህሊናና በይቅርታ አፅድተን ሀገራችንን ወደሰላምና ብልጽግና ለመውሰድ መረባረብ ይኖርብናል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2011