በኢትዮጵያ በቀን ሦስት ጊዜ በልቶ ለማደር ዕቅድ ከተነደፈበት ወቅት አንስቶ እስካሁን ድረስ ሦስቴ ለመብላት ያለመብቃታችን ምክንያቱ ዘርፈ ብዙ ሆኗል፡፡ የኑሮ ውድነትና የሸቀጦች ዋጋ መናር ፈታኝ በመሆኑ አነስተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል የሚጐርሰው አጥቶ ሲሰቃይ፣ መካከለኛ ገቢ ያለው ደግሞ መሠረታዊ ፍላጐቶቹን እንኳ ማሟላት የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
ለመሰረተ ልማትና ለግንባታ አገልግሎት ግብዓት በሆኑ እንደ ብረታ ብረት ባሉ ምርቶች ላይ ይታይ የነበረው የዋጋ ንረት በከፋ ደረጃ ወደ ምግብ ሸቀጦች ተሸጋግሮ ጤፍ በኪሎ ከ35 ብር በላይ፣ የሽሮ እህል ከ40 ብር በላይ፣ የኑግ ዘይት በሊትር ከ80 ብር በላይ፣ ድፍን ምሥር ከ40 ብር በላይ፣ አንድ ላስቲክ ወተት 17 ብር ሲሸጥ፤ የስኳርና የስንዴ ዱቄት አቅርቦት እጥረትም እንዲሁ ፈታኝ ሁኔታ ላይ በመሆናቸው ‹‹አኗኗራችን ከሞቱት በላይ፤ በሕይወት ካሉትም በታች ሆኗል! ›› የሚሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ቁጥራቸው የትዬለሌ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በአገሪቱ የዋጋ ግሽበት በቀናት ውስጥ እጅግ እየናረ መሄዱና ምርቱ ምንም ቢትረፈረፍ አንዴ ከወጣበት ተመልሶ ሲወርድ ያለመታየቱ ፈወስ የታጣለት የረጅም ጊዜ ልምዳችን ሆኖ ቆይቷል፡፡
በኢትዮጵያ በምግብ ምርቶችና ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት መከሰቱን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በየጊዜው የሚያካሂደው ጥናት ማሳያ ሲሆን፤ ለአብነትም ባለፉት ዓመታት የዋጋ ማሻቀቡን ለመቆጣጠር መሠረታዊ የምግብ ሰብል ምርቶች ከውጭ ገበያ እንዲቀርቡ በማድረግና የአገር ውስጥ አቅርቦትን በማሳደግ ዋጋን የማረጋጋት እርምጃ ተወስዶ ነበር፡፡ ይህ ዋጋን የማረጋጋት እርምጃ በወቅቱ ለጊዜያዊ መረጋጋቱ አስተዋፅኦ እንደነበረው ባይካድም፤ ዘላቂ ሊሆን ባለመቻሉ በተለይ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ ቆይቷል፡፡
የዋጋ ማሻቀቡ ምክንያቶች ኢኮኖሚያዊ ብቻ ባለመሆናቸው የአገር ውስጥ የሰብል ገበያ ሥርዓቱን ያዛቡ፤ ምርቶችን ከገበያ ዝውውር ውጭ በማድረግ ሰው ሠራሽ እጥረት የፈጠሩ፣ ምርትን በሕገወጥ መንገድ ወደውጭ የላኩ፣ በገበያ ዝውውር ውስጥ ለዋጋ መጨመር አስተዋፅኦ ያላቸውን አቀባባዮች ከመስመር የማስወጣት ተግባርና ቁጥጥር መደረጉ ተጠቃሽ እርምጃ ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት መንግሥት በወሰደው የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ እንዲሁም ሕዝባዊ ተቃውሞዎችና አለመረጋጋቶች ምክንያት የምርቶች ዝውውር በገበያ ውስጥ በመስተጓጎሉ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተከስቷል።
መንግሥት «በሀገሪቱ የተከሰተው አለመረጋጋት የከፋ ችግር አላስከተለም፤ ከቁጥጥራችን ውጭ አይደለም» ይበል እንጂ በሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት፣ በንግድ ተቋማት እንቅስቃሴና በማህበረሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ከባድ ጫና እያሳደረ መምጣቱ በግልፅ ታይቷል:: የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ችግሩን ለመቅረፍ ባለፉት ጊዜያት ያለምክንያት ዋጋ የጨመሩ ከ 4 ሺህ በላይ ነጋዴዎችን ሱቅ የማሸግ፤ ሰባት ሺህ ለሚሆኑት የጽሑፍና ለ8ሺ250 ነጋዴዎችም የቃል ማስጠንቀቂያ መስጠቱ በወቅቱ መገለፁ ይታወሳል።
ከዚህ የቁጥጥር ሥርዓት ባሻገር በጥቂት ወራቶች ልዩነት የሚያገረሸውን የዋጋ ንረት ለመግታት በየቀበሌው የሸማቾች የህብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅተው በተመጣጣኝ ዋጋ ሸቀጦችን በማቅረብ ለገበያ መረጋጋቱ አስተዋጽኦ ቢያበረክቱም ዋጋ ለመጨመር ምክንያት የሌላቸው የአገር ውስጥ ምርቶች የንረቱ አካል መሆናቸው ኅብረተሰቡን አንገት አስደፍተውታል፡፡ በዚህም የተነሳ እርስ በርስ ከመረዳዳት ይልቅ ራስ ወዳድ መሆን ሚዛን ደፍቷል፡፡ ዛሬ ኑ ቡና ጠጡ መባባል ጎጂ ባህል ሊሆን አፋፍ ደርሷል፡፡ ሁሉም ቤቱን ዘግቶ መቀመጥና የኑሮ ውድነት ያስከተለውን ችግር እንደ አመጣጡ መቀበል ግድ ሆኖበታል፡፡
በደርግ የአገዛዝ ወቅት በርበሬ በመጋዘኖቻቸው የደበቁ ነጋዴዎች፤ አሻጥረኛ ተብለው እርምጃ ተወስዶባቸው እንደተገደሉ የታሪክ ማህደር ያስረዳል። ዛሬ እየተፈፀመ እንዳለው የጄሶ እንጀራ የመሸጥ ተግባር ይህን መሰሉ ነጋዴ በደርግ ዘመን ተገኝቶ ቢሆን ኖሮ ምን ሊገጥመው እንደሚችል መገመት አይከብድም። ደርግ የወሰደውን አይነት ርምጃ ዛሬም መውሰድ አስፈላጊ ባይሆንም ሕገወጥ ነጋዴዎች ደሀውን ወገናቸውን የሚጎዱበትን ያልተስተካከለ አካሄድ የሚያርሙበት ሕጋዊ ርምጃ ግን ሊወሰድባቸው ይገባል፡፡
ዛሬ ወገኖቻችን ተፈናቅለው ሜዳላይ ፈሰው የእርዳታ ያለህ ብለው በሚማፀኑበት ወቅት ፣ አገሪቱ በለውጥ ማዕበል ውስጥ መሆኗ እየታወቀ ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያስከተለው ጫና እየታየ፤ ሕገወጥ ነጋዴዎች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆናቸው በቸልታ ሊታይ አይገባም፡፡ የንግድ ሚኒስቴር ለረጅም ዓመት ለዋጋ ግሽበቱ ላልተገባ የዋጋ ንረቱ ምክንያቶች ናቸው እያለ በርካታ ጉዳዮች ሲዘረዝር ቢደመጥም የንግድ ሥርዓቱን ሲያሻሽል ግን አልታየም። በህገወጥ ደላሎች መዳፍ ስር ያለውን የአገሪቱን የንግድ ሥርዓት ከእነዚህ ሥርዓት አልበኞች ማላቀቅም አልተቻለም።
ይህንን ለነገ የማይባል ፣የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ህይወት የሚነካ ፣ በተለይም መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች የመኖር ሕልውናን የሚፈታተንን የህገወጦች ጉዳይ መስመር ከማስያዝ ባሻገር፤ በአገሪቱ አሉ የሚባሉ የምጣኔ ሃብት ምሁራንን በማማከር ለተፈጠረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝና የዋጋ ግሽበት አፋጣኝና ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት ማድረግ ጊዜው አሁን ሊሆን ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2011