ቅራኔ የልዩነት ውጤት ነው፤ ነገር ግን ልዩነት ሁሉ ቅራኔን ይወልዳል ማለት አይደለም፡፡ በልዩነት ተከባብሮና ተቻችሎ አብሮ መኖር ይቻላል። በተፈጥሮ ሕግ መሰረት በአንድ አካል ውስጥ የተለያዩ ንዑስ አካላት ይኖራሉ። እነዚህ የተለያዩ ንዑስ አካላት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ ፍትጊያ ለለውጥ ወይም ለአዲስ ግኝት ምክንያት ይሆናል። የምንኖርባት ዓለምና ሌሎቹም ፕላኔቶች በግጭትና በመቀላቀል ሂደት እንደተፈጠሩ ሳይንስ ያረጋግጣል። የእኛም አፈጣጠር ቢሆን በሁለት የተለያዩ ጾታዎች ግንኙነትና ቅብብሎሽ ውጤት ነው።
ልዩነት በሚተዋወቁና በማይተዋወቁ በቅርብ ወይም በሩቅ በሚኖሩ ሰዎች መካከል በእምነት፣ በአስተሳሰብ፣ በጥቅም ዙሪያ ሊከሰት ይችላል። በአገራትም መካከል እንዲሁ ልዩነት ይኖራል። የሰው ልጅ በቅራኔ ሳቢያ አላስፈላጊ ግጭትና ውድመት እንዳይከሰት በተለያየ መልክ ጥረትና ትግል ያደርጋል። ማንም ቢሆን መሞትና መግደልን የሚወድ የለም። ሁሉም የሚያስፈልገውን አግኝቶ፣ ተከባብሮ በሰላም መኖርን ይሻልና።
ይህ አጠቃላይ የሰዎች ፍላጎት ሲሆን በመካከሉ አንዳንድ በግለኝነት መንፈስ የተበከሉ አልጠግብ ባዮች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ሌላውን ሲያጠቁና ህብረተሰቡን እርስ በእርስ እንዲጋጩ ማድረግ አሁን አሁን በገሀድ የሚታይ ተግባር ሆኗል፡፡ ይህ በመሆኑም በዚህ ልክ የሚፈጠሩ ግጭቶች ቂምና በቀል አዝለው ሰላም እንዳይደፈርስ መሰራት የሚገባው ቁልፍ ስራ ደግሞ አብሮ አለ፤ የእርቅ ስርዓት፡፡
ባህላዊ የእርቅ ስርዓት በየአካባቢው የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችና ግጭቶችን ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ለአገር በቀል የሕግ፣ ፍትህና አስተደዳደር ስርዓቶች ዕውቅና መስጠትና ተሃድሶ የማድረግ የረጅም ዘመን ታሪክ አለው፡፡ በኢትዮጵያ የአገር በቀል የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ስርዓቶች በጥናት ጭምር ተደግፈው የበርካታ ብሔረሰቦችን ባህላዊ አስተዳደርና ፍትህ ስርዓቶችን ከመደበኛው የፍትህ ስርዓት ጋር ጭምር የተቆራኙባቸው አካባቢዎች በርከት ይላሉ፡፡
በአገራችን ከ70 እስከ 80 በመቶ በላይ የሚሆኑ የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችና ግጭቶች የሚፈቱት በአገር በቀል የሕግ፣ ፍትህና አስተዳደር ስርዓቶች እንደሆኑ የጥናት ግኝቶች ያመለክታሉ፡፡ ባሕላዊ ወይም አገር በቀል የፍትህ፣ ሕግና የአስተዳደር ዕውቀቶች ህዝብና አገር ከተመሰረተ ጀምሮ በጥንታዊ ማህበረሰቦች ዘንድ ለግጭት አፈታትና ዳኝነት ተግባር ሲውሉ የነበሩ የእርቅ ስርዓቶችና ለስልጣኔም መሰረት የነበሩ እሴቶች ናቸው፡፡
በመሆኑም መንግሥት በፍትህ ስርዓቱ የማይዳኙ ነገር ግን ቂምና በቀልን በዘላቂነት ሊያስቀሩ የሚችሉ ዘዴዎችን መጠቀም ወቅቱ ያስገድደዋል፡፡ እዚህ ላይ በተለይ በታችኛው የአመራር እርከን ላይ ያሉ አመራሮች ግጭትን በመፍታት ረገድ እነዚህን ዘዴዎች ምን ያህል ተጠቅመውበታል ብሎ መጠየቅ የሚያስገድድ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ከ130 በላይ አገር በቀል የሕግ፣ ፍትህና አስተዳደር ስርዓቶች እንዳሉ በጥናት ቢረጋገጥም በዘመናችን ያለው የዛሬው አስተዳደር ከ60 ዓመታት በፊት ከወጣው የፍትሐ ብሔር ሕግ ጀምሮ ለአገር በቀል ዕውቀቶች ብዙም ዕውቅና አለመስጠቱ የግጭት አፈታት ስርዓቱን በሚገባ አለመጠቀማችን ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
እንደ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት ያሉ ሀገረሰባዊ ህጎች በኢትዮጵያ በተለይም የመንግሥት ሕግና ፍትሕ ስርዓት በስፋት ባልተዳረሰባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ከማህበራዊ ህይወት ጋር ተያያዞ ዛሬም ድረስ ተግባር ላይ እየዋሉ ያሉ በመሆኑ ዛሬ ዛሬ የሚታየውን መልከ ብዙ ግጭቶችን ለመፍታት መንግሥት በልዩ ትኩረት ሊጠቀም ይገባል፡፡
ለአብነትም በኦሮሞ ጃርሱማ፣ በአማራ ሸንጎ፣ በሃድያ አራረዎ፣ በማረቆ ጉዳ እና በሌሎች ብሔረሰቦች ዘንድ የሚገኙ የሽምግልና፣ የእርቅና የግልግል አገረሰባዊ የዳኝነት ተቋማት በህዝብ ውስጥ ለሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች በዘላቂ መፍትሔነት የሚጠቀሱ አደረጃጀቶች በመሆናቸው እንጠቀምባቸው:: በየማህበረሰቡ መካከል ለሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶችን በማብረድና በማስታረቅ ረገድ እነዚህ ባህላዊ ተቋማት ሚናቸው የጎላ ነው።
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት፣ ወደፊትም ችግሮች እንዳያጋጥሙ ለማድረግ በየአካባቢው ያሉ ባህላዊ መዋቅሮችን ዕውቅና መስጠት፣ ማጠናከርና ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቃል፤ ለዚህ የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ ያለበት መንግሥት ነው፡፡ ለዚህ መጠናከር ደግሞ ምሁራን ጥናትና ምርምር በማድረግ አገር በቀል መልካም እሴቶች በስርዓተ ትምህርት እንዲካተቱ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2011