የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ2017 ጠቅላላ ጉባኤው ሜይ 16/ግንቦት 08 ዓለም አቀፍ በሰላም አብሮ የመኖር ቀን ተብሎ እንዲከበር ወስኗል። ድርጅቱ ውሳኔውን ያሳለፈው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሰላምን፤ መቻቻልን፤ አብሮነትን፤ አካታችነትንና መግባባትን ለማስፈን የሚያደርጋቸውን ጥረቶች ለማገዝና እነዚህ እሴቶች የኅብረተሰቡ ገዢ መርሆች ሆነው እንዲጎለብቱ ለማድረግ ነው። ቀኑ ሰላምና ወንድማማችነት የነገሰባትን ዓለም ለመገንባት በአብሮነት መቆምንና በልዩነት ውስጥ ኅብረት መፍጠርን ዓላማው አድርጎ ይከበራል።
እኛ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻችንን ይዘን በብዝሀነት የመኖር አኩሪ ታሪክ ያለን ህዝቦች ነን። እነዚህ ልዩነቶቻችንና ብዝሀነታችን ደግሞ በየትኛውም ማህበራዊ መስተጋብራችን ውስጥ የሚታዩ ነባር እሴቶቻችን ናቸው። እነዚህ እሴቶቻችንም በማህበራዊ ምግባር የሚያንጹን፤ የሚገዙን፤ የሚቆጣጠሩንና አከባብረው በጋራ የሚያኖሩን መንፈሳዊ ህጎቻችን ናቸው።
እኛ ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ ህይወታችን ሀይማኖት የማይገድበው፤ የዘር ልዩነት የማይወስነው ሰው መሆንና የአብሮነትን ፍላጎት ብቻ የሚያጠይቅ የእድር፤ የሰርግ፤ የሀዘንና የሰርግ ማህበራዊ መስተጋብሮች ባለቤቶች ነን። እነዚህ ማህበራዊ እሴቶቻችን ሰዋዊ ግንኙነታችን የተገመደባቸው፤ መነሻቸውም መድረሻቸውም ኢትዮጵያዊነት የሆነ የግንኙነት አውዶቻችን ናቸው።
በሰላም አብሮ መኖር ማለት ልዩነትን መቀበልና ማክበር ማለት ነው። ይህ ደግሞ አንዱ ሌላውን የማድመጡን፤ የመቀበሉን፤ የማክበሩንና የማድነቁን አቅምና ፈቃደኝነት ይይዛል። ከላይ የገለጽናቸው ማህበራዊ መስተጋብሮች ደግሞ እነዚህን ሁሉ የሚያሳዩ መድረኮች ናቸው። እነዚህ እሴቶች በአንድ ወቅት የሚታዩ፤ በአንድ ትውልድ የሚገለጹ ብቻ ሳይሆኑ፤ ዘመን የሚሻገሩ፤ በትውልድ ሰንሰለት ለቀጣዩ የሚተላለፉ፤ ነባሪውን የሚገልጹ ብቻ ሳይሆኑ መጻኢውንም ትውልድ የሚያንጹ ናቸው። እናም ልዩነትን አውቆና ችሎ አብሮ መኖር በራሱ ሰላምን መስበክ ነው።
የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፤ የሳይንስና የባህል ድርጅት እንደሚለው፤ ጦርነት የሚጸነሰው በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ነው። በአንጻሩ ለሰላም የመቆም እሳቤም መገንባት ካለበት በዚያው በሰው አዕምሮ ውስጥ ነው። እናም አሁን በሰፊው ስናየው በዓለም ዙሪያ፤ አጥብበን ስንመለከተው ደግሞ በአፍሪካና በአገራችን ኢትዮጵያ የሚታየው ግጭት፤ የርስ በርስ መናቆርና መገፋፋት በውጤቱ የሰላም መጥፋት ቢኖረውም፤ መነሻና መንስዔው ግን ግን አብሮ የመኖር እሴቶች መሸርሸር ነው።
ይህ መሸርሸርም ከምንም አይመነጭም ከሰዎች አዕምሮ በሚጠነሰስ ራስን ብቻ አግንኖ የመውደድና የመቀበል፤ ይህንንም በሌሎች ጥቃትና ጉዳት ላይ የመመስረት ፍላጎት ውጤት ነው። እንዲህ ያለው ፍላጎት አብሮ መኖርን፤ ሰላምንና ተስፋንም ይሸረሽራል። መጪወን ዓለምም ያጨልማል።
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በአገራችን እየታየ ያለው እውነታ ከዚህ አይርቅም። በተለያየ መንገድ ለዘመናት የተገነባው አብሮነታችን ተሸርሽሯል። ውበትና መገለጫ ሆኖ በዓለም ሲያሳውቀን የነበረው ልዩነታችን አሁን አሁን ላይ መገፋፊያ ሲሆንም እየታየ ነው። ሁሉም በማንነቱ መከበርና መኩራት እንዳለበት ግልጽ ቢሆንም ይህንን ጉዳይ አገራዊ አንድነትን በማይሸረሽር መልኩ ማስኬድ ላይ ችግር ስለነበር ትንንሽ ምክንያቶች እየተፈለጉ ለየብቻ ሊያቆመን ጫፍ ላይ ደርሷል። እንዲያም ሆኖ ግን እኛ ኢትዮጵያውያን የተገመድንበት የአብሮነት እሴት ገመዱ ከሀር የተዋበ፤ ከስር የጠነከረ ነውና አሁንም አብረን ነን።
እርግጥ ነው፤ አልፎ አልፎ በተከሰቱ ችግሮችና ግጭቶች የተዋለዱ፤ የተዛመዱ፤ የተጋቡና ጡት የተጣቡ ወገኖች በመካከላቸው ያልነበረ ጊዜያዊ መገፋፋት ተስተውሏል። እርግጥ ነው፤ በተከሰቱ ችግሮች ለዘመናት ታስቦ የማይታወቅ የዘር ክር ተመዝዞ አንዱ ጥቃት አድራሽ አንዱ ተጠቂ ሆነን ከቀያችን ተፈናቅለናል።
የተፈጠረው ጊዜያዊ ክስተት ግን የመጪውን ዘመን ተስፋ የሚያጨልም አይደለም። የነበረውን የረጅም ዘመን ታሪክ የሚያስረሳ ቢመስልም ይህ ሁሉ ግን ጊዜያዊ ነው። አዎን ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት የፈጠረው፤ ወቅታዊ የጥቂቶች አዕምሮ የጸነሰው እኩይ ሀሳብና መጥፎ ምግባር ነውና አጭር ነው።
አሁን ከዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ልንወጣ ይገባል። የህግ አንቀጽ ሳንጠቅስባቸው፤ ዳኛና ችሎት ሳንሰይምባቸው ችግሮቻችንን የምንፈታባቸው፤ አጥፊን ገስጸን ተበዳይን የምንክስባቸው በርካታ ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶች ስለላሉን ለነርሱ ቦታ እንስጥ።
ግጭቶች ሲፈጠሩ ሰላም አስከባሪ ኃይል እየላኩ ማረጋጋት ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም። ይልቁንም፤ በሰላም አብሮ የመኖርን ጥቅም በማስተማርና ይህንን ባለማድረጋችን የደረሱብንን መከራዎች ማስተማሪያ በማድረግ፤ ለዘመናት የዘለቁ የአብሮነት እሴት ትሩፋቶችን አጉልተን በማሳየት ግጭቶችን ከምንጫቸው ማድረቅ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን የባህልና የስነምግባር ሀብታሞች ነን።
ይህም ብቻ አይደለም፤ ስርዓት አውቀው በወጉ የሚተገብሩ፤ አስተምረው ለትውልድ የሚያስተላልፉ አባቶችና እናቶች አሉን። እናም እነርሱን እንስማ፤ እሴቶቻችንንም እንጠቀምባቸው። ከአሁኑ በላይ የሚያስፈልጉን ጊዜና ወቅት የለምና!
በተለይም በጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች ዘዋሪነት የሚቀሰቅሱና የዘር መልክ ይዘው አድማሳቸውን የሚያሰፉ ግጭቶች የማኅበረሰቦችን በሰላም አብሮ የመኖር የቆየ መልካም ታሪክ ላይ አስከፊ ጠባሳ ጥለው ያልፋሉ። የተደረገውም ይህ ነው። አሁን ግን ይህንን ቅሬታና ቁርሾ ልንሻገረው ይገባል። ለዚህ ደግሞ ወደመንፈሳዊ ሀብቶቻችን፤ ወደአገራዊና ባህላዊ የአብሮ መኖር እሴቶቻችን ልንመለስ ይገባል።
በመሆኑም፤ የሃይማኖት መሪዎች፤ የማኅበረሰብ ተወካዮችና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የመቻቻልን መርህ ሊዘክሩን፤ የአብሮነትን እሴት ሊያስተምሩን የግድ ነው። እኛም ወደራሳችን ተመልሰን ሰላማችንን በአብሮ የመኖር እሴታችን አቅፈን ልናስጠብቅ ይገባናል። የዘንድሮው የዓለም በሰላም አብሮ የመኖር ቀን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የተለየ ትርጉም የሚሰጠው ነውና አብሮ የመኖር ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶቻችንን ከመቼውም በላይ ልንጠቀምባቸውና ልንጠብቃቸው ይገባል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2011