የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ዘርፍ ለአጠቃላይ ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ የላቀ አበርክቶ እንዳለው ይታወቃል። ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ያለውን አበርክቶ ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ እንዲቻል በየክልሉ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆች የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል በሲዳማ ክልል የሚገኘው የአለታ ወንዶ ቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ አንዱ ነው።
ኮሌጁ በየዓመቱ በተለያየ የሙያ መስክ በርካታ ተማሪዎችን ያሰለጥናል። በቴክኖሎጂ ዘርፍ እየሰለጠኑ ካሉ ሰልጣኞች መካከል ሰልጣኝ አስቻለው ተስፋዬ አንዱ ነው። አስቻለው የሻማ ማምረቻ ማሽን (candle making machine) የፈጠራ ሥራ ሰርቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ካደረጉ ሰልጣኞች መካከል አንዱ ነው።
ሻማን በሀገሪቱ ማምረት የሚያስችል አዲሱ የሻማ ማምረቻ ማሽን ሻማን ብቻ ሳይሆን ጧፍንም ጭምር የሚያመርት ማሽን ነው። የሻማ ማምረቻ ማሽኑ ትልልቅና ትንንሽ ሻማዎችን እንዲሁም ጧፍን በአንድ ጊዜ ማምረት ያስችላል። ማሽኑ በ20 ደቂቃ ውስጥ ትላልቁ መጠን ያላቸውን 100 ሻማዎች እና 34 ትንንሽ ሻማዎች እንዲሁም 50 ያህል ጧፎችን በአንድ ጊዜ ያመርታል። በአንድ ሰዓት ውስጥ ከ400 በላይ ተመሳሳይ ምርቶችን ማምረት የሚያስችል ሲሆን፤ ይህም ሲባል 300 ትላልቅ ሻማ፤ 102 ትንንሽ ሻማና 150 ጧፍ ያመርታል ማለት ነው።
በአለታ ወንዶ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ለመግባቱ ዋንኛው ምክንያት ለፈጠራ ሥራ ያለው ውስጣዊ ፍላጎት እንደሆነ የሚናገረው አሰልጣኝ አስቻለው፤ ይህንን የፈጠራ ሥራ ለመሥራት የቻለው በአካባቢው ከተመለከተው የማህበረሰቡ ችግር በመነሳት ነው። በአካባቢ ላይ መብራት እንደልብ የማይገኝ በመሆኑን ህብረተሰቡ የሚጠቀመው አዲስ አበባ አካባቢ ተመርቶ የሚመጣው የሻማ ምርት መሆኑ ለፈጠራ ሥራው ተጨማሪ መነሻ ሀሳብ እንደሆነለት ይናገራል።
‹‹የሻማ ማምረቻ ማሽን አካባቢያችን ላይ ስለሌለ እኛ አካባቢ የሻማ ዋጋ ውድ ነው። አሁን ባለው የገበያ ዋጋ የአንድ ሻማ ዋጋ 16 ብር የሚሸጥ ሲሆን፤ ህብረተሰቡም ይህንን ብር አውጥቶ ለመግዛት በእጅጉ ይቸገራል። ይህ ማሽን ደግሞ ይህንን ችግር መቅረፍ ያስችላል›› የሚለው አስቻለው ፤ ማሽን ተሰርቶ ካለቀ በኋላ ተባዝቶ እንዲከፋፈል በመደረጉ የማህበረሰቡን የመግዛት አቅም ከግንዛቤ ውስጥ ባገናዘበ መልኩ አሁን ላይ በአካባቢ ላይ ያለውን የሻማ ዋጋን ወደ 10 ብር ዝቅ ማድረግ መቻሉንና ቀደም ሲል ከነበረው ዋጋ አንጻር ሲታይ የስድስት ብር ልዩነት እንዲኖረው ሆኗል።
አስቻለው እንደሚለው፤ ይህ ማሽን አገልግሎት ላይ ከዋለ በኋላ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል። በተለይ በገጠሪቱ አካባቢዎች ያሉ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የማያገኙ ማህበረሰቦች እንዲሁም በኃይል መቆራረጥ ምክንያት የሚቸገሩ ሰዎች ችግር በእጅጉ የፈታ ነው። በተለይ ዝናብ ሲኖር መብራት በመቋረጥ ወይም ከነአካቴው ባለመኖሩ የተነሳ ህብረተሰቡ ከሦስት ወራት በላይ ለዘለቁ ጊዜያት መብራት የማያገኝበት ሁኔታ እንደሚኖር ጠቁሞ፤ በዚህ ሰዓት ለህብረተሰቡ አማራጭ የሚሆነው ሻማ መጠቀም ስለሆነ የሻማ መግዛት ፍላጎቱ ይጨምራል። ለዚህም ህብረተሰቡ ሻማን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማድረግ የሚያስችል ነው።
በከተማ አካባቢዎችም ቢሆን አብዛኛውን ጊዜ ለቤተክርስቲያን፣ ለልደት፣ ለሠርግ ፣ ለሀዘን ጊዜ እና ለመሰል ፕሮግራሞች ሻማና ጧፍ ተፈላጊነታቸው ይጨምራል። በዚህ ጊዜ ታዲያ ማህበረሰቡ ሻማና ጧፍን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት ያስችለዋል። በተለይ ሻማ በአብዛኛው ጊዜ ለብዙ ነገሮች ተፈላጊ በመሆኑ በጣም ዘመናዊ የሚባሉ አሠራሮችን በመከተል የተለያዩ የሻማ አይነቶችን ማዘጋጀት እንደሚቻል አስቻለው ይናገራል።
አስቻለው፤ ‹‹አሁን ላይ በተለይ ለልደት የባለልደቱን ስም በመጻፍ፣ ፎቶውን በሻማ ላይ የማተምና ሌሎች ሥራዎችም ይሠራሉ። ማሽኑ ከማምረት በተጨማሪ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሻማ ዲዛይኖችን በማዘመን በሻማ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት የሚያስችል በመሆኑ፤ በማሽኑ ከመሥራት በተጨማሪ ሻማዎችን በማምረት በኩል የተጠቀምናቸው የፈጠራ ሥራዎች ጥበቦች ከፍተኛ የሚባሉ ናቸው›› ይላል።
የሻማ ማምረቻ ማሽኑ በአውቶማቲክና በማንዋል በሆነ መልኩ መጠቀም እንዲቻል ተደርጎ የተሰራ ነው። መብራት ባለበት አውቶማቲኩን መጠቀም የሚቻል ሲሆን፤ መብራት በሌለባቸው አካባቢዎች ደግሞ በማንዋል ተጠቅሞ ሻማን ማምረት እንደሚቻል ነው የሚናገረው። መብራት በሌለበት ማሽኑን ለሚገዙ ሰዎች ልክ በከሰል ማንደጃ እንዲሰራ ተደርጎ የተሰራ ነው የሚለው አስቻለው፤ መብራት ባለባቸው አካባቢዎች ማሽኑን ለሚገዙ ሰዎች ደግሞ መቆጣጠሪያ፣ ሰዓት እና እያንዳንዱ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ተገጥሞለት አውቶማይዝድ ሆነውን እንደሚሸጡ ይናገራል።
ማሽኑ መብራት በሌለበት አካባቢ በጣም በዝቅተኛ ዋጋ የሚሸጥ ሲሆን፤ መብራት ባለበት አካባቢ የሚገጠምለት የእቃ ዋጋ ስለሚጨምር ዋጋው ጭማሪ አለው። ማሽኑ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ሀገር ከሚገባው ሻማ ማምረቻ ማሽን ጋር ሲነጻጸር ዋጋው ቅናሽ መሆኑን ጠቅሶ፤ ውጭ ላይ ካለው ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ሰፊ ልዩነት አለው። ከውጭ ሀገር የሚገባው ማቀዝቀዣ ያልተገጠመለት፣ ኤሌክትሪክ መስመር የሌለው እና በአንድ ጊዜ 50 ሻማዎች ብቻ የሚያመርተው ማሽን ዋጋ እስከ 120ሺ ብር እንደሆነም ይናገራል።
ማሽኑን ሰርቶ ለማጠናቀቅ 82 ሺ ብር ብቻ ወጪ የጠየቀ መሆኑን ያነሳው አስቻለው፤ እንደ ሀገር የውጭ ምንዛሪን ከማስቀረት አንጻር ብቻ ሳይሆን ያለንን የፈጠራ ክህሎት (ችሎታ) ተጠቅሞ ከውጭ ሀገር የሚገባን ማሽን በሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶች መተካት መቻሉ በራሱ ትልቅ አቅም እንደሆነ ነው የገለጸው። ይህም ማሽኑን ብዙዎች እንዲጠቀሙ ሥራ እንዲሰሩበት ከማድረግ በተጨማሪ ለበርካቶች የሥራ እድል የሚፈጥር እንደሆነም ተናግሯል።
የሻማ ማምረቻ ማሽኖች ከውጭ ሀገር የሚመጡ ብቻ ሳይሆኑ በሀገር ውስጥም ተሰርተው ገበያ ላይ የዋሉ ማሽኖች መኖራቸውን ጠቁሞ፤ ‹‹እነዚህን ማሽኖች በጥንቃቄ አይተን ካጠናን በኋላ ማሽኖቹ ላይ የሚጨመሩ ማለትም ማሽኖቹ የጎደላቸው ነገር ግን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በመጨመር የተሠራ አዲስ የፈጠራ ሥራ ውጤት ነው›› ይላል። ለአብነት ቀደም ሲል የነበሩት የሻማ ማምረቻ ማሽኖች ብንመለከት አንድ ዙር አምርቶና አቀዝቅዞ ለማውጣት ከአንድ ሰዓት በላይ የሚፈጁ ሲሆን፤ ይህ ማሽን ግን ፍጥነቱን ጨምሮ በ20 ደቂቃ ብቻ አምርቶና አቀዝቅዞ ማውጣት የሚችል ከመሆኑም በላይ፤ በአንድ ሰዓት 100 ያመርት የነበረው ወደ 400 መቶ ከፍ እንዲል በማድረግ ምርታማነትን እንዲጨምር ያደረገ ማሽን እንደሆነም አስረድቷል።
ከውጭ ሀገር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው ሌላው ማሽን ማቀዘቀዣና የኤሌክትሪክ መስመር የሌለውና ሲሽጥም ተነጣጥሎ የሚሸጥ ሲሆን፤ ሁሉንም ማቴሪያሎች አሟልቶ የያዘ ባለመሆኑ ለሥራ ምቹ አይደለም የሚለው አስቻለው፤ ማሽኑን በሀገር ውስጥ ግብዓት ከመሥራት ባሻገር በፈጠራ የጨመሯቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉም ተናግሯል። አያይዞም የሻማ አሠራሩ ስፋትና መጠን ለሥራ በሚመች መልኩ ዲዛይን የተደረገ ስለመሆኑ አስረድቷል።
ከውጭ ሀገር በሚመጡት የሻማ ማምረቻ ማሽኖች ሻማን ለማምረት የሚጠቀሙት ግብይቶች የጎንዮሽ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ናቸው የሚለው አስቻለው፤ የሻማ ምርቶችን ለማምረት የሚጠቀሙት ‹‹ዋክስ›› ከተሰኘ ኬሚካል እንደሆነና የሚገኘውም ከይርጋለም አግሮ ኢንዱስትሪ ፕሮሰሲንግ ‹‹ቶኒዋክስን›› ከሚያመርት የማርና ሰም ኢንዱስትሪ ተፈጥሯዊ (ኦርጋኒክ) ከሆኑ ምርቶች መሆኑን ጠቅሷል።
ከውጭ የሚመጣው የሻማ ማምረቻ ግብዓት ግን ከነዳጅ ተረፈ ምርት የተሰራ መሆኑን ጠቅሶ፤ ‹‹ከዚህ አንጻር እኛ የምንጠቀመው ተፈጥሮዊ ወይም ኦርጋኒክ የሆነ ግብዓት በመሆኑ የሚያመጣው የጎንዮሽ ጉዳት የለም ማለት ይቻላል፤ ከውጭ እንደሚመጣው ለጎንዮሽ ጉዳት አሳልፎ የሚሰጥ አይደለም። ይህ ደግሞ በሁለቱ ማሽኖች መካከል ያለው ልዩነት ትልቅ እንደሆነ ማሳያ ነው›› ይላል።
‹‹ሻማውን ለመስራት የሚጠቀሙበት ግብዓት ተፈጥሯዊ (ኦርጋኒክ) መሆኑ ብቻ ሳይሆን የሚጨመርበት ጣዕም (ፍሌበር) የተለየ ነው›› የሚለው አስቻለው፤ የማሩን ሰም በቀጥታ መጠቀም በመቻላቸው የተሻላ ጣዕም (ፍሌበር) እንዲኖረው ማስቻሉ ለየት የሚያደርገው እንደሆነ አመላክቶ ነገር ግን የነዳጅ ተረፈ ምርትን መጠቀም የጎንዮሽ ጉዳት ሊያመጣ እንደሚችል ነው የጠቆመው።
በአሁን ወቅት አምስት ለሚደርሱ ሀገር በቀል ኢንተርፕራይዞች ስልጠና በመስጠት እነሱ እያመረቱና ማሽኑን እያባዙ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተዳረሰ እንደሆነ ያነሳው አስቻለው፤ ለአብነትም በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን፣ ሀዋሳ እና ሌሎችም በርካታ ቦታዎች ላይ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቁሟል።
እንደ አለታ ወንዶ ቴክኒክና ሙያ የተሰራው የሻማ ማሽን አንድ መሆኑን ጠቅሶ፤ ይህ ግዮን በመባል የሚታወቀው የሻማ ማምረቻ አሁን ላይ የሻማ ምርቶችን በስፋት እያመረተ መሆኑን ይናገራል። በተለይ አሁን ላይ ቀደም ሲል ከነበረው በተሻለ ሁኔታ የሚያመርት በመሆኑ የሚያመርታቸው የሻማ ምርቶችን ከአለታ ወንዶ አልፎ ሀዋሳ ድረስ እያቀረበ እንደሚገኝ ጠቁሟል።
‹‹ማሽኑ ለአጠቃቀም ምቹና ቀላል ነው። መቆጣጠሪያውን(ኮንትሮል ፓናሉን) በመጠቀም የፈለገን ቦታ ላይ ሆነን መቆጣጠር እንችላለን። ማሽኑ ማንኛውም ሰው ሊጠቀምበት የሚችል ምቹ ተደርጎ የተሰራ ነው። አንድ ሰው በማሽኑ ለመጠቀም የአንድ ሳምንት ስልጠና ካገኘ ብቁ መሆን ይችላል›› ብሏል።
ማሽኑ የሚሰጠውን አገልግሎትና ተጠቃሚው ያገኘውን ጥቅም በተመለከተ የተለያዩ ዘዴዎች ተጠቅመው መረጃ መሰብሰባቸውን የሚናገረው አስቻለው፤ ማሽኑን ኢንተርፕራይዞች አብዝተው ለህብረተሰቡ በሸጡበት አካባቢዎችና የሻማ ምርቶችን ገዝተው ከሚጠቀሙት የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የዳሰሰ ጥናት ተካሂዶ ግብረ መልስ መሰብሰቡን አስታወሰዋል። ለኢንተርፕራይዞቹ ማሽኑን የሚመለከቱ ጉዳዮች ህብረተሰቡ ደግሞ የሻማውን አቅምና ጥራት ሻማው በርቶ የሚቆይበት የጊዜ ቆይታ እና መስል ጥያቄዎች ለሁለቱም አካላት በማቅረብ መረጃ ለመሰብሰብ ተችሏል።
ማሽኑ የተሰራው 2013 ዓ.ም ሲሆን አሁን ላይ ከኢንተርፕራይዞች እና ከህብረተሰቡ ይህንን ብታሻሽሉ በሚል የሚሰጡትን አስተያየቶች በመሰብሰብ የተሰጡ አስተያየቶችን መነሻ በማድረግ ጥናት በማካሄድ በየጊዜው በማሽኑ ላይ ማሻሻያዎች እያደረጉ እንደሆነ አስቻለው ተናግሯል። በአሁን ወቅትም ማሽኑ ያለበትን ክፍተት በመለየት የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን፤ አሁን ላይ ተፈላጊው ደረጃና ጥራት ያለው ሻማ ማምረት የሚችልበት ደረጃ ላይ መደረሱን አስረድቷል።
ማሽኑን ለማስተዋወቅም በተለያዩ አውደ ርዕዮች ላይ በመሳተፍ ምርቶችን በመሸጥና በማስተዋወቅ ላይ እንገኛለን የሚለው አስቻለው፤ ህብረተሰቡም እንደዚህ አይነት የሻማ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመመረታቸው ሲመለከቱ በመገረምና በማድነቅ የሚያበረታታ ሞራልና አስተያየት እንደሚሰጡ ይናገራል። ህብረተሰቡ ከሚሰጣቸው አስተያየት በሀገር ውስጥ የሚመረተው ሻማም ሆነ ጧፍ በገበያ ላይ ካለውም የተሻለ ጥራትና የቆይታ ጊዜም ያለው ሻማ እያመረቱ እንደሆነ ነው መረዳት የቻሉት።
‹‹በየትኛውም የሀገሪቷ አካባቢዎች የሚገኙ ሕዝቦች ይህንን የሀገር ውስጥ ምርት በመጠቀም በሀገራቸው ምርት ሊኮሩ ይገባል። ምርቶቹ በሀገር ውስጥ ተምርተው ህብረተሰቡ የማይገዛ ከሆነ ዋጋ የለውም። ስለዚህ ህብረተሰቡ ገዝቶ ሲጠቀም የፈጠራ ሥራው ይበረታታል፤ ለሌላ ሥራም ሞራል ያገኛል›› የሚለው አስቻለው፤ በቀጣይ የዚህን ማሽን አቅም በማሳደግ ያለውን አቅም ተጠቅሞ ከፍ ባለ ሁኔታ ምርት አምርቶ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ተርፎ ወደ ውጭ መላክ የሚችልበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ሀሳብ እንዳለውም ተናግሯል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9/2015