አዲስ አበባ፡- የአብዛኛዎቹ የአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ትርፍ ከሚጠበቀው በታች መሆኑ እንዳሳሰበው የአማራ ክልል የልማት ድርጅቶች ድጋፍና ክትትል ባለስልጣን አስታወቀ።
የአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ድጋፍና ክትትል ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መጋቢው ጣሰው ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለጹት፤ በክልሉ የልማት ድርጅቶች በአብዛኞቹ የሚጠበቀው ትርፍ ማግኘት አልተቻለም።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፣በ2009 በጀት ዓመት የውጭ ኦዲት ሪፖርት መሰረት የተጣራ ትርፍ ከባለፈው 2008 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 159 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ቅናሽ ያሳያል።
እንደ አቶ መጋቢው ገለጻ፤የ2009 በጀት ዓመት የተጣራ ትርፍ ምጣኔ ከግብር በኋላ 199 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ነው። ነገር ግን የ2008 በጀት ዓመት ትርፍ ሲታይ 359 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ይደርሳል። ይህም ከቀድሞው ጋር ሲነጻጸር የ159 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ቅናሽ እንዳለው ያሳያል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፣የጣና ኃይቅ ትራንስፖርት ድርጅት አምስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አቅዶ ያገኘው ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ብቻ ነው። ኮምቦልቻ ዶሮ ሀብት ልማት በበኩሉ 11 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አቅዶ የአገኘው ግን ከእቅዱ በታች ስድስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር ብቻ ነው።
የተሻለ አፈጻጸም ከነበራቸው መካከል ደግሞ የአማራ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ድርጅት 160 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ለማትረፍ አቅዶ ያተረፈው ግን 83 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው። በሌላ በኩል አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ግንባታና ቁጥጥር ሥራ ድርጅት 19 ሚሊዮን ብር አቅዶ ያልተጣራ ዘጠኝ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ነው ያገኘው። አማራ ቤቶች ልማት ድርጅት በበኩሉ 25 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር አቅዶ 17 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ብቻ ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱንም አመልክተዋል።
ከልማት ድርጅቶቹ መካከል ከፍተኛ ውን ያልተጣራ ትርፍ 159 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ያገኘው አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ነው። ነገር ግን ከእቅዱ አንጻር ሲታይ ማሳካት የቻለው 26 ነጥብ ስድስት በመቶውን ብቻ ነው። ምንም እንኳን ተቋሙ ኢንቨስትመንት ላይ ያለ ቢሆንም አማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ 49 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ያልተጣራ ትርፍ ለማግኘት አቅዶ ያገኘው 541 ሺ ብር መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ከ13 የአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የገቢ ሪፖርት እንደሚ ያሳየው አብዛኛዎቹ ከሚጠ በቅባቸው ገቢ በታች ማግኘታቸው አሳሳቢ መሆኑን አቶ መጋቢው ተናግረዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ተቋማት በእቅድ መርቶ ገቢን እና ወጪን ባለመሰባሰቡ የሚጠበቀው ትርፍ አልተገኘም። በዚህም ምክንያት የድርጅቶቹን ትርፍ በሚፈለገው መጠን አላደገም። ካለፉት ዓመታት ጀምሮ አብዛኞቹ የልማት ድርጅቶች ለውድቀት የዳረጋቸው የአመራሩና ሠራተኛው በእቅድ ተመርቶ በተደራጀ ሁኔታ የማስፈጸም አቅም እያሽቆለቆለ መምጣቱ ነው።
የልማት ድርጅቶች የተጣራ ትርፍና ኪሳራ መግለጫን በተመለከተ የ2009 የኦዲት ምርመራ ተደርጎ ሂሳባቸው ከፀደቀላቸው የ14 ልማት ድርጅቶች በተሰበሰበ መረጃ መሰረት፤ አጠቃላይ የተጣራ የሃብት መጠን 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ደርሷል። የአንዳንድ ልማት ድርጅቶች ቋሚ ሃብት በትክክል ተተምኖ የተያዘ ባለመሆን ግን ሰፊ ክፍተት እንዳለ አቶ መጋቢው ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2011
በጌትነት ተስፋማርያም