እንደ መንደርደሪያ…
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ- መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) ከንጉሠ ነገሥቱ ስደት መመለስ ከሦስት ዓመታት በኋላ የተመሠረተ ተቋም ነው። በወቅቱ ለዘመናዊት ኢትዮጵያ ይጠቅማሉ ተብለው ከተተለሙ ተቋማት ከቀዳሚዎቹ ተርታም ይመደባል። ይህ የሰባ አምስተኛ ዓመት ምስረታ በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ያከበረው ተቋም ሥራውን የጀመረው «የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት ወመዘክር» በሚል መጠሪያ ንጉሡ ባበረከቷቸው መጻሕፍት፤ ተጠሪነቱ ለትምህርት ሚኒስቴር ሆኖ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ምንም እንኳን አንዳንድ ምኁራን በኢትዮጵያ የዘመናዊ አብያተ-መጻሕፍትና መዘክር ጅማሮን ወደ ቀዳማዊ ምኒልክ ዘመን ቢወስዱትም “የጽሕፈት ሚኒስቴር” መቋቋምና ለሚኒስቴሩም የሌሎች ተቋማትን የጽሑፍ ቅጂዎች የመሰብሰብ ስልጣን መሰጠቱ ከወመዘክር ጋር ይስተካከላል ማለት አይቻልም። በእርግጥ እንደ ጥንተ – ስልጡንና የፊደል ባለቤትነታችን ጉዳዩ ከንባብና ጽሑፍ ስልጣኔ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ የነበረ ነው ቢባል ያስማማኛል።
በዘመናዊ መልክ ለመቋቋም ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ ቀዳሚው ሲሆን ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሤም ባለውለታው ናቸው። በምስረታው ወቅትም «የሕዝባችንን ድልና የሀገራችንን ነፃነት በምናከብርበት በዚህ ዕለት እነሆ አዕምሮውን ነፃ ማውጫ ይሆነው ዘንድ መሰረቱን ጥለናል።» በማለት ተናግረው እንደነበር መዛግብት አስፍረው አኑረውታል። የዚህ መንደርደሪያ ዓላማ የተቋሙን አገልግሎት በማሻሻል ረገድ ጥንካሬዎቹን መግለፅ አይደለም። ይህ የሚታወቅ ነውና ጥንካሬዎቹን ይዘንለት አፋጣኝ ለውጥና መታደስን ከሚሹት ጉዳዮች ብሎም በብርሃኑ ላይ የሚያጠሉትን ጥቂት ነጥቦች ብቻ በመጠቆም ይህ ብርቅዬ ተቋም ድክመቶቹን አርሞ እንዲቀጥል ለማስታወስ ነው።
ለተቋሙ በዋና ዳይሬክተርነት ከተሰየሙ በኋላ በርካታ ለውጦችን እያስመዘገቡ የሚገኙት አቶ ይኩኖ አምላክ መዝገቡ ለቤቱ እንግዳ ባይሆኑም ወደ ተቋሙ በኃላፊነት ሲመጡ በኤጀንሲው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከተቋሙ ተገልጋዮች ጋር ውይይት አድርገዋል። በዚያም ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል በብዛት የተነሳው ከዚያ ጊዜ ቀደም ብሎም በተደጋጋሚ በተቋሙ ችግሮች ላይ ውይይት መደረጉ አንዱ ነው። በተመሳሳይ በውይይቶች የመፍትሄ ሃሳቦች ቢቀርቡም የተለወጠ ነገር ባለመኖሩ ተገልጋዩ መሰላቸቱና «የተውነውን ነገር ዳግም የምናነሳው በሀገሪቱ ላይ በሚታየው የለውጥ ጅማሮ ሳቢያ ነው።» የሚሉ አስተያየቶችም ቀርበዋል።
ከተለያዩ ውይይቶች፣ የናሙና መጠይቆች እንዲሁም የቃል አስተያየቶች በተጨማሪ በተቋሙ የአገልግሎት ክፍሎች ውስጥ የተዘጋጁትን “የአስተያየት መስጫ መዝገብ” ላገላበጠ ሰው ለዓመታት ተመሳሳይ ችግርና ቅሬታዎች እየተነሱ መቆየታቸውን መረዳት አይከብደውም። አስተ ያየቶቹ አሁንም መቀጠላቸው ደግሞ ለችግሮቹ አለመቀረፍ ህያው ምስክሮች ናቸው። ዘመኑን ያልዋጀ አገልግሎት የኢትዮጵያ የመዛግብት ቅርስን፣ ሥነ- ቃልና ጥበብን እንዲሁም መሰል ትውፊቶችን እንዲጠብቁና እንዲያለሙ ከተተለሙ ተቋማት አንዱ ይኸው በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ስር በአዋጅ ቁጥር-179/1991 መሰረት የተቋቋመው «የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ- መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ» አንዱ ነው።
በተለያየ ስያሜ ሲታወቅና ተጠሪነትና መዋቅሩን ሲቀ ያይር የኖረው ይህ የሀገሪቱ ማዕከላዊ ተቋም አገልግሎቱም የበረከተ ነው። ተቋሙ የጋዜጣና መጽሔት ንባብ ክፍልን ቢያዘጋጅም አለመታደል ሆኖ ከሁለትና ሦስት ህትመቶች በቀር ሌሎቹን ላለማስገባት የበጀት አለመኖርን ምክንያት አድርጎ ኖሯል። መንግሥትም ለዚህ ትልቅ ሀገር አከል ተቋም ትኩረት ነፍጎታልና ይህንን ጽሑፍ እስከማሰናዳበት ወቅትም በዚህ ረገድ ምንም የተቀየረ ነገር የለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ኃላፊነት መምጣት በኋላ መስተካከል ጀምሮ የነበረው በርካታ ህትመቶችን የማቅረብ ጅማሮም አንድ ወር ሳይዘልቅ ወደ ነበረበት ተመለሰ።
ይህ ጉዳይ አሁን ላይ ከሚታተሙ የጋዜጣና መጽሔቶች ቁጥርና ከአንባቢው ፍላጎት አንፃር ታይቶ ሊቃኝና ማስተካከያ ሊደረግለት ይገባል። በተለይ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በሰፊው የሚዳስሱ ህትመቶች በተለያዩ ዘዴዎች ለአንባቢው እንዳይቀርቡ የማድረጉ ነገር ከዚህ በፊት በነበረው ሥርዓት ለረጅም ጊዜ ተኪዶበት አዋጭ እንዳልሆነ ተረጋግጧል። የወመዘክር ብርሃን እና ጥላ በቅርቡ በሐዋሳ ከተማ ለ26ኛ ጊዜ የተከበረው ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን መሪ ቃሉ አድርጎት የነበረው «አካል ጉዳተኞችን በማብቃት አካታችነትንና እኩልነትን እናረጋግጥ» የሚለውን ሃሳብ ነበር።
ይህ መሪ ቃል የአካል ጉዳት ያለባቸውን ወገኖች ሁሉዓቀፍ ተሳታፊነትና አካታችነት ያለመ ልማትና ዕድገት ዕውን እንዲሆንና ለሁሉም የተመቸ አገልግሎት እንዲኖር ያስጠብቃል። የብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲን ለመጠቀም የሚመጡ አካል ጉዳተኞች በመወጣጫና በመግቢያ ደረጃው ሳቢያ በጣም ሲቸገሩ ይታያል። በተቋሙ ለመታደም የሚፈልግ አንድ የተሽከርካሪ ወንበር አልያም ምርኩዝ ተጠቃሚ ተገልጋይም ይሁን ለተቋሙ ሠራተኛ የተመቻቸ ነገር የለም። ለዚህ መፍትሄ ይሆናል ተብሎ ከአሜሪካን ኤምባሲ ጋር በጋራ ተጀምሮ የነበረው የአሳንሰር (Lift) ግንባታ አለመጠናቀቁና ለዓመታት ያለምንም እንቅስቃሴ መጓተቱ አንዱ የቸልታችን ማሳያ ነው፡፡
ከሰሞኑ ከኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አካባቢ የተሰማው ነገር ደግሞ አሁንም ቢሆን በሀገሪቱ እየተገነቡ ያሉትም ሆኑ እንደ አዲስ የሚሻሻሉ ግንባታዎች አካል ጉዳተኛ ወገኖችን ታሳቢ እያደረጉ እንዳልሆነ ገላጭ ነው። ይህ የራሱ ሕንፃ እንኳ የሌለው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አዋጅ ቁጥር 624/2001ን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንዲያስፈፅም ኃላፊነት ቢሰጠውም የአዋጁ የተለያዩ ድንጋጌዎች ፈፃሚና አስፈፃሚ አጥተዋል። ሰባ አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን «ቃል ያዛልቃል» በሚል ፍካሬ ለመዘከር የደረሰውና የጋራ የዕውቀት ቤታችን የሆነው ወመዘክር ማየት ለተሳናቸው ወገኖቻችን የብሬይል መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፤ በቂ የሚባል ግን አይደለም።
ወሳኝ የሚባሉ ተጨማሪ መጻሕፍትን ወደ ድምፅ መጽሐፍነት የሚቀይሩና ሌላ ዓይነት የአካል ጉዳት ያለባቸውን ወገኖች አካታችነትም መተለምና ይህንን አካታች ያለመሆን ችግሩንም በአጭር ጊዜ ውስጥ መቅረፍ ይኖርበታል። የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገል ግሎቱን ለሕዝብ አመቻችቻለሁ ብለው ጥሪ ካቀረቡ በኋላ አገልግሎቱን ፍለጋ የሚመጣውን ሰው ሕንፃው እንዲገለገል የማይፈቅደለት ከሆነ የአገልግሎቱ መኖር ካለመኖሩ እኩል ይሆናል፡ ፡ በጓደኞቹ እየታገዘ ከነተሽከርካሪ ወንበሩ እየገባ የንባብ ቤቱን የሚጠቀም ደንበኛ ስመለከት ሁሉ የትልቅ ሕንጻን ያህል የተጓተተው የመወጣጫ አሳንሰሩ ተሰርቶ ማለቂያን ጊዜ እናፍቅ ነበር፡፡ ይህንን እንድል ምክንያት የሆኑኝ የሁለት መጻሕፍት ደራሲያን ገጠመኞች ናቸው።
ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ለዓመታት በኢምፔሪያል ሆቴልና አምስት ኪሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም አዳራሽ ውስጥ መጻሕፍትና ንባብ ነክ ሥራዎችን ሲሠሰራ ቆይቷል፡፡ ላለፉት ስድስት ያህል ዓመታት ደግሞ ከአንጋፋው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ጋር በትብብር በመስራት ወርሃዊ የመጻሕፍት ውይይት መሰናዶውን በኤጀንሲው አዳራሽ እያከናወነ ይገኛል። በየካቲት 03 ቀን 2011ዓ.ም የወሩ ተረኛ አወያይ የነበረው መጽሐፍም የወጣቱ ሰዓሊና ደራሲ ብሩክ የሺጥላ የበኩር ሥራ የሆነው «የኔ ስጦታ» የተሰኘው መጽሐፍ ነበር።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀ ንሲ ከጀርመን የባህል ማዕከል (ጎቴ ኢንስቲትዩት) ጋር እንዲሁ በትብብር ወርሃዊ የመጽሐፍ ውይይት ላይ ዘለግ ላለ ጊዜ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በመጋቢት 29 ቀን 2011ዓ.ም የወጣቱ የሕግ ባለሙያ ዳግማዊ አሰፋ «አዲስ ሕይወት» የተሰኘ መጽሐፍ በጎቴ ኢንስቲትዩት፣ በእናት ማስታወቂያና በወመዘክር ትግግዝ በተሰናዳው መርሃ ግብር ላይ የወሩ መወያያ ሆኖ ነበር፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው ሁለቱም ጸሐፍት ወጣት ናቸው፡፡ ሁለቱም ለብዙ የሀገሬ ወጣቶች ተምሳሌት ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው። ሁለቱም ጸሐፍት በተለያየ ምክንያት አካል ጉዳተኛ ሆነዋል። ሁለቱም ወጣቶች መጽሐፋቸው ለውይይት በቀረበበት ቀን በወመዘክር አዳራሽ ተገኝተዋል፡፡
ሁለቱም ደራሲያን ወደ ተቋሙ አዳራሽ ለመግባት እጅግ በጣም ተቸግረው ነበር፤ በመጻሕፍቶቹ ውይይት ላይ የተገኙ አካል ጉዳተኛ ወገኖችም ይህንኑ ታዝበዋል፡፡ ሰዓሊና ደራሲ ብሩክ የሺጥላ የአካል ጉዳተኛው ቀጥተኛ ተሳትፎና ጠያቂነት ከሌለበት የማህበረሰቡ አባላት በራሳቸው ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የሚያደርጉት ብቸኛ ጥረት የተሳካ ውጤት እንደማያመጣ ነግሮን:- «አንዳንዴ አዲስ በሚሰሩ ሕንፃዎች ላይ የሚሰሩ የዊልቸር መወጣጫዎች በጣም የሚያንሸራትቱ፣ በጣም ቁልቁለት ወይም ዳገት የሆኑ፣ ስፋታቸው የተሽከርካሪ ወንበሩን የጎን ስፋት የማይመጥን… ብቻ የአካል ጉዳተኛውን ለመጥቀም ከማሰብ ሳይሆን ከላይ የተቀመጠላቸውን መመሪያ ለመፈፀም ብቻ ተብለው የተሰሩ የሚመስሉና መሠረታዊ የምህንድስና ጉድለት ያለባቸው ነው የሚሆኑት።» በማለት የታዘበውን ችግር አስታውሶናል።
ብሩክ ይህንኑ ጉዳይ ሲቀጥለውም፡ -“ታዲያ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ላይ አካል ጉዳተኛው በቀጥታ የሚሳተፍበት መድረክ ካልተመቻቸ እነዚህ ችግሮች የሚፈቱበት ሁኔታ ይመናመናል። በውስጣቸው ትልልቅ ለውጥን ለሀገራቸውም ለዓለምም ይዘው የተፈጠሩት አካል ጉዳተኞችም ይህን ችሎታቸውን ለሕዝብ የሚያቀርቡበት ቦታ ካልተመቻቸላቸው ወደ ውጪ ወጥተው ሕይወታቸውን ለመምራት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። የተመቻቸ ሁኔታ ባይኖርም አሁንም ጠያቂ መሆን ያለበት የችግሩ ሰለባ የሆነው አካል ራሱ ነው።” በማለት የየግልና የህብረት እንቅስቃሴን ይጠራል፡፡
አለመታደል ሆኖ መጻሕፍት ሰፈር አካባቢ ባለው የስም እና ገበያ ተኮር እንዲሁም በሚዲያው አካባቢ በሚገኙ የምልከታ ቀራፂዎቻችን አተያይ ሁለቱም መድረኮች፣ መጻሕፍትና ጸሐፍቱ ሊያገኙ የሚገባውን የሚዲያ ሽፋንም ሆነ ሽያጭም አላገኙም ብዬ አምናለሁ። የሆነው ሆኖ የኤጀንሲው አመራርና ሠራተኞች ከተገልጋዩ ጋር በመተባበር አፈር ይመስል የነበረውን ምድረ ግቢ ውበት ፈጥረውለት ለንባብና ውይይትም የተመቸ እንዲሆን መሥራታቸው በእጅጉ ያስመሰግናቸዋል። በተለይም ሸሚዛቸውን ሰብስበው በጉልበት ሥራው ሳይቀር የሚሳተፉትና የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሆነው በቅርቡ የተሾሙት የምስጋናውን የጎላ ድርሻ ይወስዳሉ።
የብዙ መንግሥት መሥሪያ ቤት ችግር የሆነ የግቢ መዝረክረክ ዜጎችም ለንፅህና ትኩረት እንዳንሰጥ ያደረገ ነውና። በበርካታ የሀገሬ ወጣቶች በትኩረት የሚነበበው ኢዮብ ማሞ (ዶ/ር) «እይታ» በተሰኘው መጽሐፉ ላይ መሥሪያ ቤቶቻ ችንን የጎበኘ ዜጋ ስለመሥሪያ ቤቶቹ ሰራተኞችና ስለመሪዎቻቸው ሊደርስበት የሚችለውን ድምዳሜ ሲነግረን ነው መሰል፡ – «ሰው ቤታችን ሲመጣ የሚያየው ነገር የሚያሳየው የቤታችንን ሁኔታ አይደለም፣ የአመለካከታችንን ሁኔታ እንጂ። ምክንያቱም የቤታችንን ሁኔታ የፈጠረው አመለካከታችን ስለሆነ ነው። ምናልባት የአንድ መሥሪያ ቤት አስተዳዳሪ ከሆንክ በመሥሪያ ቤቱ ቢሮዎችም ሆነ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚታየው ሁኔታ ሁሉ ያንተው አመለካከት ነፀብራቅ ነው።” ብሏል።
ሪያድ አብዱል ወኪል(የሕግ ባለሙያ) ibnalhabeshi@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2011