የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ ባሳለፍነው ሳምንት 75ኛ ዓመቱን ፍሬ በተሞላውና ቁምነገር በታጨቀ መርሃ ግብር በድምቀት አክብሮታል። የሙዚቃ ድግስ እንጂ የቁምነገር መድረኮች ታዳሚያቸው በቁጥር ትንሽ ነው። ቢሆንም ለአንድ ሳምንት የዘለቀው ክዋኔ ተካፋዮችን አላጣም። በክዋኔውም የመጻሕፍት ሽያጭና አውደርዕይ፣ የልጆች ዝግጅቶች፣ የመጻሕፍት ላይ ውይይቶች፣ የግጥም ምሽቶችና የሙዚቃ ዝግጅቶች ቀርበዋል።
ከሳምንቱ ማብቂያ ቀናት ቀደም ብሎ ሚያዝያ 25 ቀን 2011ዓ.ም ማምሻውን «አልፎ ያላለፈ እና ሌሎች» የተሰኘውንና በሱለይ አደም የተጻፈው መጽሐፍ ለውይይት ቀርቦ ነበር። ለውይይቱም መነሻ ሃሳብ ያቀረበው መምህርና ታሪክ አዋቂው ሰለሞን ተሰማ ሲሆን፤ በመጽሐፉ ላይ ያደረገውን ዳሰሳና የግል አስተያየቱን አቅርቧል። «አልፎ ያላለፈ እና ሌሎች» የሱለይ አደም የበኩር ሥራ ነው። መጽሐፉ በ201 ገጾች ተቀንብቦ በ110 ብር ዋጋ ገበያውን ከተቀላቀለ ጥቂት ወራት ናቸው ያለፉት፤ ይሁንና በአጭር ጊዜ ውስጥ ተነባቢነትን ማግኘት እንደቻለም በተለያዩ ማኅበራዊ ድረገጾች የሚሰጡ አስተያየቶች ተመልክቶ መናገር ይቻላል።
መጽሐፉ ምን አዲስ ነገር ቢኖረው ነው ? የሚለውን በሰለሞን እይታ የተወሰነ ብንተነትነው ወድደናል። መጽሐፉ በቁጥር ሃያ አጫጭር ታሪኮችን የያዘ ነው። በብዛትም የመጀመሪያ ደረጃ የትረካ አንጻር በመጽሐፉ ይገኛል። ይህም «እኔ…» በሚል ተራኪ የቀረበ ሲሆን ደራሲው የጾታ ምጣኔን ተጠቅሟል። ለውይይት መነሻ ሃሳብ ባቀረበው ሰለሞን እይታ መሰረት፤ መጽሐፉ የተለየ ትኩረትን የሚስቡ አምስት ታሪኮችን የያዘ ሲሆን የተቀሩት አሥራ ሶስቱ በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ትችት የሚያቀርቡና ወንዶችን ገጸባህሪ ያደረጉ ናቸው። ከመጽሐፉ የፊት ገጽ ስንጀምር፤ «አልፎ ያላለፈ እና ሌሎች» የሚለው የመጽሐፉ ርዕስ ጎልቶ ሲጻፍ፤ ደራሲው በምስጋና ክፍል እንደገለጸው በሰዓሊ ዳንኤል ጌታሁን የተዘጋጀ ስዕል የሽፋን ስዕል እንዲሆን የተመረጠ ነው።
ባገኘችው ክፍተት መካከል አልያም የጋረዳትን «ግንብ» ሰብራና ለማስፋት በእጆቿ የክፍተቱን ጠርዞች ይዛ፤ በከፊል ገጿ እየታየ አሻግራ ያለፈውን የምታይ ሴት ትታያለች። እንግዲህ ስዕል እንደተርጓሚው አይደለ? የስዕሉ ነገር ይቆየንና ወደ መጽሐፉ ርዕስ ስንመለስ፤ ዳሰሳውን ያቀረበው መምህር ሰለሞን መጽሐፉ የአጭር ልብወለድ ስብስብ ከሚሆን ይልቅ ወጎችና ትርክቶች ስብስብ ቢሆን እመርጣለሁ የሚል ሃሳብ አቅርቦ ነበር። ይሁንና ግን በመጽሐፉ ሽፋን ላይም ሆነ ውስጥ ርዕሱ እንጂ በውስጥ ያሉት ሥራዎች ዘውግ ተጽፎ አይገኝም። ምን አልባትም አንባቢ በተሰማውና በተረዳው ልክ ዘውጉን ሊጠራው ይችላል ተብሎ የተተወ ይሆናል።
ከዚህ በተጓዳኝ ደራሲው፤ እንደ ሰለሞን ገለጻ «ስርቻ ውስጥ» ያሉ እውነቶችን በእነዚህ ታሪኮች ውስጥ አሳይቷል። ይህም ከታሪክ አንጻር ብቻ ሳይሆን በቋንቋ አጠቃቀም የተገለጸ ነው። ምንም እንኳን የሥነ ጽሑፍ መምህራን በቃላት ምርጫ ላይ ጥንቃቄ እንዲደረግና አማካይ የሆኑ፣ ተደራሲውን የማያስቸግሩ ቃላትን መጠቀምን ቢያበረታቱም፤ አዳዲስ የሚመስሉ ቃላት መኖራቸው የመጽሐፉ አንዱ ጥንካሬ መሆኑም ተገልጿል። በመጽሐፉ ሥራዎች ውስጥ ተደራሲን ሊያደናቅፉና ግራ ሊያጋቡ የሚችሉ ቃላትን ትርጓሜ ማካተት ጠቃሚነቱም በዚህ አጋጣሚ ተነስቷል።
«አልፎ ያላለፈ»ን በተመለከተ፤ በመጽሐፉ በተለይም ከእስልምና ጋር የሚገናኙና በሃይማኖቱ ውስጥ ለሚኖሩትና ለሚያውቁት የበለጠ ግልጽ የሆኑ ቃላት በጥቅም ላይ ውለዋል። ይህ በአንድ ወገን ከመጽሐፉ የሚገኝ አዲስ ነገር ሲሆን ቃሉቱን መጠቀምም የሚያስተምር እንደሆነ ነው ዳሰሳውን ያደረገው ሰለሞን የጠቀሰው። ከዚህም በተጓዳኝ በመጽሐፉ ዙሪያ ለውይይት የተለያዩ ሃሳቦች የቀረቡ ሲሆን የቋንቋ አጠቃቀምን በተመለከተ ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ ግን ለውይይት ተርፏል። በመጨረሻ «ሃያውን ታሪኮች በአራት መደብ ከፍያቸዋለሁ።» ያለው ሰለሞን፤ እነዚህንም በጭብጣቸው መሰረት አስቀምጧቸዋል።
የመጀመሪያው የሴትን ደግነትና በማይታወቁ ሰዎች ውስጥ ያለን ተስፋ የሚያሳዩ ታሪኮች ክፍል ነው። ሌላው የወንድን ልጅ ልፋትና ድካም፤ እንዲሁም በአንድ ትንሽ ችግር እንዴት የካቡት ነገር ሊናድ እንደሚችል የሚያመላክቱ ሲሆኑ የሴትን ልጅ እንዲሁም የእናትና የልጅን ነገር የሚነግሩ ታሪኮችም ይገኛሉ። በመጨረሻ የሰውን ልጅ ብቸኝነትና አስተዳደግ የሚገልጹ ታሪኮች አሉ። ከዚህ አጠር ያለ የመጽሐፍ ላይ ውይይት ቆይታ በኋላ ስለዚህ መጽሐፍ ሳስብ በተለይ ከሴቶች አንጻር የሰጠው ትኩረት ስቦኛል። በርካታ መጻሕፍት እንዲሁም አጫጭር ወጎች ተብለው በነጠላ የሚቀርቡ ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎች፤ በአብዛኛው «እኔ» በሚል የመጀመሪያ የተራኪ መደብ ሲሰፍሩ ራሱ በወንድ ጾታ የሚቀርቡ ናቸው። ይህ ጉዳይ ምንአልባት የበለጠ ጥናት የሚጠይቅ ሳይሆን አይቀርም።
ስለምን ብሎ በሴቶች የተሠሩ አንዳንድ ሥራዎች ሳይቀሩ በወንድ ድምጽ ወይም ተራኪ የሚቀርቡ ናቸው። ነገሩ ምንአልባት የሚጽፍ ሰው አንባቢ ነውና፤ ለንባብ የሚቀረቡን ሥራዎች ሁሉ በወንድ ተራኪ የሚቀርቡ በመሆናቸው በዛ ተጽእኖ ምክንያት ሊሆን ይችላል። በጥናትም ከዚህ የተሻለ ምክንያታዊ ምላሽ ሊገኝ ይችላል። ሱለይ አደም በዚህ የመጀመሪያ ሥራው ግን በሴት አንቀጽ የመጀመሪያ ደረጃ ተራኪ እየሆነ ያቀረባቸው ሥራዎች የሚያስመሰግኑትና በጉዳዩ ላይ ጥናት ለማድረግ ለሚወዱም አንድ ግብዓት ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ።
ከ«አልፎ ያላለፈ እና ሌሎች» መጽሐፍ ምን አዲስ አለ? የተባለ እንደሆነ አንዱ ይኸው ያልኳችሁ በአንደኛ መደብ ተራኪ ሴት ባለታሪክ መፍጠሩ ነው። ከዚህ በተጨማሪ መምህር ሰለሞን እንዳለው የቋንቋ አጠቃቀምና አዳዲስ ቃላትን የሚያሳውቅ መሆኑም፤ በተለይም ከእስልምና ሃይማኖትና አንዳንድ ስርዓቶች ጋር የተገናኙ ቃላት መሆናቸውም ብዙ የሚያቀብለን ይመ ስለኛል። ከዚህ ባለፈ ሱለይ አደም ይህን መጽሐፍ ስላስነበበን እያመሰገንን ሌሎች ሥራዎችም አሉኝ ብሏልና፤ እነርሱን የምንጠብቅ ይሆናል። ሰላም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2011
ሊድያ ተስፋዬ