የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ ህገመንግስቱ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። ህገመንግስቱን ማክበርና ማስከበር ደግሞ ከእያንዳንዱ ዜጋ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከመንግስት የሚጠበቅ ነው። ይሁን እንጂ አሁን ባለው ሁኔታ ህገመንግስቱ ሙሉ ለሙሉ እየተከበረ፣ የዜጎችም ህገ መንግስታዊ መብት እየተረጋገጠ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ ከጥያቄ ያለፈ ምላሽ አላገኘም።
በአንዳንድ አካባቢዎች በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀያቸው፣ ከቤት ንብረታቸው እየተፈናቀሉ ለእንግልትና ስቃይ ተዳርገዋል። አንዳንዶችም ከአካል ጉዳት እስከ ህይወት መጥፋት የደረሰ አደጋ አስተናግደዋል። ቤትንብረታቸው ተቃጥሎባቸው ተሰደዋል። ይሄ እና ሌሎች ወቅታዊ ነገሮች ሲታዩ ህገ መንግስቱ በሚባለው ልክ እየተከበረ መሆኑ ያጠራጥራል። የህግ የበላይነትም በትክክል ተተግብሯል ብሎ ደፍሮ ለመናገርም ያስቸግራል።
የህግ የበላይነት ሙሉ ለሙሉ እየተከበረ አይደለም ለማለት የሚያስደፍረውም በተለይ ካለፈው አንድ ዓመት ጀምሮ በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ አረመኔያዊ ድርጊቶችን ተከትሎ በእኩይ ተግባር የተሰማሩ ግለሰቦች፣ የእነሱም ተባባሪዎች እና ለችግሩ ፈጣሪዎች ከለላ የሚሰጡ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ለፍርድ ቀርበው የእጃቸውን አለማግኘታቸው ነው። ይሄ በእውነትም የህግ የበላይነት አልተከበረም ለማለት ያስችላል። ለዚህም ነው በየመድረኮቹ የህግ የበላይነት ይከበር የሚል ተደጋጋሚ አስተያየቶች የሚነሱት ። መንግስትም የዜጎቹን ደህንነት እና ሰብአዊ መብት የመጠበቅ እና የማስጠበቅ ሀላፊነት እና ግዴታ አለበት።
ይሁን እንጂ አሁን ባለው ሁኔታ መንግስት ይሄንን ግዴታውን በሚገባ ተወጥቷል ለማለት አይቻልም። በመንግስት በኩል አብዝቶ የሚታየውና የሚሰማው በትግስት ፣በማስተማርና በመገሰፅ ላይ ያተኮረ እርምጃ ነው። ለዘመናት ከመጣንበት በዱላ የማመን አባዜ ተወጥቶ በትዕግሰትና በማስተማር ማመኑ ይበል የሚሰኝ ነው። ይሁንና አመርቂ ውጤት እያመጣ አይደለም። አጥፊዎችም በድርጊታቸው ቀጠሉ እንጂ የጥፋት እጃቸውን አልሰበሰቡም። ህዝብን በህዝብ ከማነሳሳት አንዱን ብሄር በሌላው ብሄር፤ አንዱን ሀይማኖት በሌላው ላይ ለማነሳሳት ከሚያደርጉት የጥፋት እንቅስቃሴ አልተቆጠቡም።
ስለዚህ መንግስት እስካሁን የሄደበትን ህግን የማስከበር ፣ የዜጎችን መብቶች የማስጠበቅ መንገድ መቀየር ይገባል፤ ትግስቱንም መቀነስና የህግ የበላይነትን አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት።መንግሥት ቅቡልነት የሚኖረው ሕግና ሥርዓትን ማስከበር ሲችል ነውና! መብቱ ሊከበርለት የሚገባ ቀድሞ ግዴታውን መወጣ ለቻለ ዜጋ ነውና እኩይ እጆች አንዲሰበስቡ የህግ የበላይነትን ማስከበሩ ላይ መንግስት ከእስከ አሁኑ ሂደት በተሻለና ጠንከር ባለ መልኩ መስራት ይጠበቅበታል። ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ በዲሞክራሲ የሽግግር ሂደት የህግ የበላይነትን በሚመለከት መንግሥት ሕጋዊ ሕግ አስከባሪ መሆኑን ዜጎችና የፖለቲካ ምሁራን መገንዘብና ማወቅ ይኖርባቸዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ሰሞኑን ያስገነዘቡትም ይሄንኑ ነው። መንግሥት ሕግን በሚያስከብርበት የሕግ አውድና ሕግን በሚያስፈጽምበት ተቋማዊ ሥራ አማካኝነት ሕጋዊ ሕግ አስከባሪ መሆኑን ዜጎችም ሆኑ የፖለቲካ ልሂቃን ማወቅ፣ ማሰብ፣ መናገርና ማስተማር አለባቸው ብለዋል። መንግሥት ሕግን የሚያስከብርበት የሕግ አውድና የሚያስፈፅምባቸው ጠንካራ ተቋማት መኖራቸው የአመራሩን የሕግ የበላይነትን ማክበር ወይም በሕግ የመገዛት አዝማሚያ ማሳያዎች በመሆናቸው መንግሥት የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ አቅም እንዳለውም አስረድተዋል።
መንግሥት ሕግ የሚያስከብርበት የሕግ አውድ ሲባል በወጣው ሕግ መሠረት ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ሲሆን፤ የተመጣጠነ የኃይል እርምጃ ማለትም ከሕግ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ መሆኑን ልሂቃኑም ይህንን መገንዘብ አለባቸው፤መንግሥት ሕጋዊ ሕግ አስከባሪ የሚሆነው፤ ተሰንዶና ታስቦ በተቀመጠ መልኩ ሕጎችን በማሻሻል የትኛው ሕግ የሕግ የበላይነትን ያስከብራል ብሎ በመለየትና የማሻሻል ሥራ በመስራት ነው። ዜጎችን ያሳተፈ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን በመናገር፤ የተቋማት ሥነ ልቡናዊ አወቃቀር የተቀረጸበት መንገድ አንደኛውን ጽንፍ የተከተለ መሆኑን፤ በኅብረተሰቡና በጸጥታ አስከባሪዎች መካከል በጥርጣሬ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ይህንን መቀየር ትልቅ ሥራና ጊዜ እንደሚፈልግ አንስተዋል።
መንግስት አሁን የጀመረውን ትዕግስተኝነት ቀንሶ የዜጎችን ህገመንግስታዊ መብት ለማስከበር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለህግ የበላይነትን ጠንክሮ መስራት አለበት። ኅብረተሰቡም የህግ የበላይነት የሚከበረውና ሰላም የሚረጋገጠው መንግስት በሚወሰደው እርምጃ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ የአጥፊዎችን ሴራ ሲያከሽፍና ህግ ተላፊዎችን አጋልጦ ሲሰጥ እንደመሆኑ በዚህ ዙሪያ የሚጠበቅብትን ሁሉ መወጣት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2011