ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ ተፈራ ተወልደው ያደኩት በአዲስ አበባ ከተማ ፈረንሳይ በሚባለው አካባቢ ነው። እስከ ስድስተኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውንም በዛው አካባቢ በሚገኘው መካነ ህይወት 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን 7ኛ እና 8ኛ ክፍል ደግሞ ህብረት ፍሬ በተባለ ትምህርት ቤት ተምረዋል።
የስምንተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በከፍተኛ ውጤት በማለፋቸው እሳቸውን ጨምሮ ስድስት ልጆች በቀድሞ ስሙ እቴጌ መነን አሁን ደግሞ የካቲት 12 እየተባለ በሚጠራው ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ወደ ከፍተኛ ትምህርት የሚያስገባ ውጤት ቢኖራቸውም ከአስተዳደጋቸው የተነሳ ለመንፈሳዊ ትምህርት ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው በቅድስት ስላሴ ኮሌጅ ገብተው በቲዮሎጂ መስክ ከፍተኛ ማዕረግ ይዘው ለመመረቅ ችለዋል።
ከዚያ በኋላም 2ኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፊዮሎሎጂ (በጥንታዊ ፅሁፍ ጥናት ዘርፍ) 1997ዓ.ም ወስደዋል፤ የዶክትሬት ዲግራቸውም ጣሊያን አገር በሚገኘው ፍሎረንስ ዩኒቨርሲቲ በጥንታዊ ቅርሶች ላይ ጥናት አድርገው በ2003ዓ.ም ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። በዚህም ሳያበቁ ሁለተኛው የዶክትሬት ዲግሪ እዛው በጣሊያኑ ፍሎረንስ ዩኒቨርሲቲ በግዕዝ ስነ ልሳን ዘርፍ ምርምር አድርገው ለመመረቅ ችለዋል።
ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ ተፈራ በቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በመምህርነት፤ ከዚያም በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተለየዩ ቦታዎች ላይ በኋላፊነት እንዲሁም ኮልፌ በሚገኝ ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ አካዳሚክ ዲን በመሆን አገልግለዋል።
በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል በመምህርነት እያገለገሉ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪም በቅርቡ ያሳተሙትን «ነቃዐ መፅሐፍት» የተባለውን መፅሃፋቸውን ጨምሮ አምስት ስራዎችን ለህትመት አብቅተዋል። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከቀሲስ ዶክተር አምሳሉ ተፈራ ጋር በጥናታዊ ቅርሶች፥ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርጓል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ወደ መንፈሳዊ ትምህርት እንዲያዘነብሉ መነሻ የሆኖት ምን ነበር?
ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ፡- አባቴ መምሬ ተፈራ ካህን በመሆናቸው መንፈሳዊውንም ሆነ ዘመናዊ ትምህርቱን ቀስሜ እንዳድግ አድርገውኛል። ሁለቱንም ትምህርት ጎን ለጎን አድርጌ እንድማር አባቴ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጉልኝ ነበር። እንዳውም ከዛም ይልቅ ብዙዎች የማያደርጉትን አባቴ የሰንበት ትምህርትም እንድከታተል እድሉን ፈጥረውልኛል።
ስለዚህ አስተዳደጌም ሆነ የተማርኩባቸው የትምህርት ተቋማት በስነምግባርና በስነመለኮት እንድታነፅ ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው አምናለሁ። በተጨማሪም የሰንበት ትምህርት በተከታተልኩበት የቀበና ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን ታላላቅ ሊቃውንት ያሉበት መሆኑ አሁን ላለኝ ማንነት የላቀ ድርሻ ነበራቸው።
ይህ የመንፈሳዊ ትምህርት ፍቅር በጥንታዊ ፅሁፎችና ቅርሶች ላይ ጥናት እንዳደርግ ግፊት አድርጎብኛል። በጥንታዊ ፅሁፎች ላይ ጥናትና ምርምር ሳደርግ እግረ መንገዴን ከግዕዝና ከአረብኛ በተጨማሪ በርካታ ቋንቋዎችን እንዳውቅ ረድቶኛል።
አዲስ ዘመን፡– በድምሩ ስንት ቋንቋ ዎችን ነው የሚናገሩት?
ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ፡– እውነት ለመናገር ቋንቋዎቹን የማውቃቸው በመናገር ደረጃ ሳይሆን ለማንበብና ለጥናት በሚረዳኝ መጠን ነው። ስለሆነም በንባብና ለመግባቢያ ያህል የማውቃቸው ማለትም የስራ ቋንቋዎቼ ከሆኑት ከግዕዝ፥ ከአማርኛና ከእንግሊዝኛ ውጪ እብራይስጥኛ፥ ግሪክኛ፥ አረብኛ፥ ጣሊያንኛ፥ ላቲንኛ እንዲሁም ለአጭር ጊዜ በወሰዱኩት ስልጠና አረማይክን ማወቅ ችያለሁ። በድምሩ ግን ወደ ዘጠኝ የሚደርሱ ይመስለኛል። ይሁንና አብዛኛቹን ተናጋሪዎቹ በሚናገሩበት ደረጃ ሳይሆን ለማንበብና ለጥናት ያህል ብቻ መሆኑን እንድትገነዘቢልኝ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ በርካታ ቋንቋዎ ችን ማወቅ መቻሎ ምን ፈየደሎ?
ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ፡- በርካታ ቋንቋዎችን ማወቄ በተለይ አሁን ላለሁበት ሙያና ጥናት ትልቅ እገዛ አድርጎልኛል ብዬ አምናለሁ። በተለይ ፊሎሎጂ ደግሞ ጥናቱ ፅሁፎች ላይ የሚያጠና ዘርፍ በመሆኑ ያንን ጥንታዊ የሆነ እውቀቶችና ንግግሮችን ለማወቅ ቋንቋዎቹን ማወቅ ወሳኝነት አለው።
በዋናነት የእኔ ስፔሻሊቲ የግዕዝ ቋንቋዎችና የብራና ፅሁፎችና ድርሳናትን ማጥናት ነው። በአጋጣሚ የግዕዝ ፅሁፎች የተፃፉትና የተተረጎሙት ከአረብኛ ስለሆነ ወደ ኋላ ሄዶ ምንጫቸውን ለማወቅ በተለያዩ ቋንቋዎች የተተረጎመበትን መንገድና የንፅፅር ስራ ለመስራት ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው።
ስለዚህ አሁን ላለሁበት ደረጃ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቶልኛል ብዬ አምናለሁ። በተጨማሪም ዘመናዊ የሚባሉትን እንደ እንግሊዝኛ፥ ጀርመንኛ ቋንቋዎችን ማወቄ ብዙ ምሁራን በኛ ስነፅሁፍ፥ የብራና ፅሁፎችና ድርሳናት የተተረጎሙትም ወደ እነዚህ የአውሮፓ ቋንቋዎች በመሆኑ ጥናቴን በተሳካ ሁኔታ እንዳካሄድ ረድቶኛል። ስለዚህበተለይም ወደ እዚህ አይነቱ ጥናትና ምርምር ተቋም የሚገባ ማንኛውም ሰው በርካታ ቋንቋዎችን ለመማር ራሱን ማዘጋጀት አለበት የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡– በአገሪቱ በፊሎሎጂ ዘርፍ በቂ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለው ያምናሉ?
ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ፡– እውነት ነው፤ እንደተባለው ኢትዮጵያ የጥንታዊ ፅሁፎችና ቅርሶች ቀዳሚዋ አገር ብትሆንም ቀዳሚነቷንና ጥንታዊነቷን የሚያሳዩ በእውነቱ ወደ ጎን ተትተዋል። ለዚያ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችና ጥናቶች እንደተርፍ ነገር እየታዩ መሆናቸው በጣም ያሳዝናል። ስለዚህ የሚጠበቀውን ያህል እንዳልተሰራ ነው የማምነው።
በአንፃሩ ግን ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኝ በተለይ ደግሞ በአውሮፓ ተመራማሪዎችና አጥኚዎች በኛ ጥናታዊ ፅሁፎች ላይ ጥናት ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ይጎርፋሉ። የሚፈልጉትን ያህል እየወሰዱ ያጠናሉ፤ ያስጠናሉ። እኔም ለጥናትና ምርምር በሄድኩባቸው አገራት ያየሁት ይህንን ነው። ትኩረት ሰጥተው ስራዬ ብለው እኛ የናቅናቸውንና ትኩረት የማንሰጣቸውን ቅርሶችን ሲያጡና ብራናዎቻችንን ሲያገላብጡ ታሪክ ሲቆፍሩ ስመለከት ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል እንደሚባለው ሆኖ ነው ያገኘሁት። በአገራችን ግን የተሰጠው ትኩረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
ይህም ቢሆን ግን ጅማሮዎች አሉ፤ ተስፋ ሰጪዎችም ናቸው። በዚህ ረገድ በመጀመሪያ ደረጃ እንደ ጥሩ ጎን የምናየው አባቶቻችን አስቀድመው ፅፈው፤ ሰንደው በማስቀመጣቸው ነው። ስለዚህም የቀደሙት አባቶቻችን ሊመሰገኑ ይገባል። ከዚህ ቀጥሎም እ.ኤ.አ በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ የነበረው መንግስት ለሃይማኖትና ለቅርስ ትኩረት ይሰጥ ስለነበር እንዲሁም በወቅቱ የነበሩት ጳጳስ አቡነ ቴዮፍሎስ ለጥንታዊ ፅሁፎች ፣ ለብራና እና ቅርሶች ከፍተኛ ጥበቃ ያደርጉ ስለነበር በርካታ ቅርሶቻችን እንዲጠበቁልን አድርገዋል።
በተለይም አቡነ ቴዮፍሎስ ለቅርሶች መጠበቅ ልዩ ትኩረት ይሰጡ ስለነበር ቢጠፉብን እንኳን እነዚህን ፅሁፎችና ቅርሶች ማይክሮ ፊልም እናስነሳ የሚል ሃሳብ ሲቀርብላቸው በሙሉ ልብ ነበር የተቀበሉት። እናም መመሪያ ሰጥተው 9ሺ200 በላይ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የብራና ፅሁፎች በፎቶ ወይም በማይክሮ ፊልም ተነስተው እንዲቀመጡ አድርገዋል። ይህም ዋናዎቹ ቅርሶች ቢጠፉ እንኳን ኮፒያቸውን ማግኘት እንድንችል እየረዳን ይገኛል። ከዚያም አልፎ ለጥናት ለምርምር ዋናዎቹን ቅርሶች ማስወጣት ሳይጠበቅብን በኮፖዎቹ እንድንስራ ከፍተኛ ተቀሜታ አበርክቶልናል።
በተጨማሪም በወቅት የነበሩት ታላላቆቹ የኢትዮጵያ ሊቃውንቶች እነ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት፥ ፕሮፌሰር ስርግባብ ገብረስላሴ፥ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ የራሳቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል። በተለይ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ እነዚህ ሃብቶችን በመተንተን ደረጃ ብዙ የሰሩና እየሰሩ ያሉ ምሁር ናቸው።
አሁን ወዳለው ወደ እኛ ትውልድ ስመጣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስቀድሜ እንዳልኩት በ1997ዓ.ም የጥናትና ምርምር መስኩ በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ እንዲሰጥ ማድረጉ ያስመሰግነዋል። ይሁንና ፈረንጆቹ በኛ ጥናታዊ ፅሁፎች ላይ ጥናት ማድረግ ከጀመሩ 300 እና 400 ዓመት ይሆናቸዋል። በተለይም የጀርመንና ፈረንሳይ አጥኚዎች በርካታ ጥናቶችን አድርገዋል። የሚገርመው እኛ የቅርሶቹ ባለቤት ሆነን ሳለን በሃብቶቻችን ላይ ጥናትና ምርምር ማድረግ የጀመርነው በጣም አርፍደን ነው። ግን ደግሞ መጀመሩ በራሱ ይበል የሚያሰኝ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በፊሎሎጂ የትምህርት መስክ ያሉት ዋና ዋና ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ፡- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያው ዙር በግዕዝ የሰለጠኑ ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ደግሞ በግዕዝም በአረብኛም በአጀሚም (በአረብኛ ፅሁፍ የተፃፈ ግን ቋንቋው ግን አረብኛ ያልሆነ የተፃፉ ፅሁፎች) ሁሉ ለተለየዩ አገልገሎት ይውሉ ዘንድ እንዲጠኑ እድሉ ተከፍቷል። በአሁኑ ውቅት ደግሞ ዶክትሬትም መስጠት ስለጀመርን ብዙዎች በማይታወቁ የፅሁፍ ሃብቶቻችን ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ በመስራት ላይ ናቸው። የክልል ዩኒቨርሲቲዎች በጥሩ ሁኔታ እየተነሳሱ ነው ያሉት።
አንዳንዶቹ በዲፓርትመንት ደረጃ ሌሎቹ ደግሞ በኮርስ ደረጃ የግዕዝ ስነፅሁፍን፥ የፊሎሎጂ ትምህርት እየሰጡ ለተማሪዎችና ቅርሱ ላለባቸው አካባቢዎች ሁሉ እያስተማሩ ይገኛሉ። ይህም ጥሩ የሚባል ቢሆንም ግን በቂ አይደለም። ሌላው ግን በሚዲያዎች በኩል የምናየው ትኩረት የሚፈለገውን ያህል ነው ብዬ አላምንም።
በነገራችን ላይ እስካሁን ድረስ የምንማርበትና የምናስተምርበት መፃሃፍት ከውጭ የመጡ ናቸው። በእኛ ሃብቶች ዙሪያ በእኛ ቋንቋ የተፃፋ መፃሃፍት እስካሁን አልነበረም። ከዚያ አንፃር በቅርቡ በጎንደር ያስመረቅሁት «ነቃዐ መፅሐፍት» የተሰኘው መጽሃፌ በኢትዮጵያ የሚገኙ ከ600 በላይ መፃሃፍት ዝርዝርን የሚያወሳ መፃሃፍ
ለተጠቃሚዎች አድርሺያለሁ። ይህ መፅሃፍ ለተማሪዎቻችን ለማህበረሰቡ ይጠቅማል ተብሎ የታሰቡ መፃሃፍት ተተንትነው የቀረቡበት ነው። በዚህ መፃሃፍ ትልቁ ስራ የጥንታዊ ፅሁፎቻችን ምን ምን ይዘት እንዳላቸው ብራናዎችና ገድላት ሁሉ ዘርዝሮ በማስቀመጥ ለተመራማሪዎች ወሳኝ መረጃ የሚሰጥ መሆኑ ነው።
ሌላውና ትልቁ የዚህ መጽሃፍ ጠቀሜታ በውጭ አገር የሚገኙ የብራና ፅሁፎቻችንን እነማን ናቸው? የትኛው ፅሁፍ በየትኛው አገር ይገኛል የሚለውን ነገር በዝርዝር ማካተቱ ነው። በዚህ መፅሃፍ ከተዘረዘሩት ጉዳዮች አንዱ ጥንታዊ የብራና ፅሁፎች አድራሻ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም በፈረንሳይ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው 1ሺ150 የብራና መጽሃፍት፥ በእንግሊዝ ከአፄ ቴዎድሮስ መማረክ ጋር ተያይዞ 929 ብራና መጽሃፍት መኖራቸውን ያስቀምጣል።
በጀርመንም የተወሰዱትና የተለያየ ጥናት ውስጥ ያሉት ከኢትዮጵያ የ931 የብራና መጽሃፍት ሲገኙ የተለያዩ ጥናቶች እየተሰሩባቸው ናቸው። ጣሊያንም በርካታ የብራና መጽሃፍትንና ቅርሶችን ያስቀመጠች አገር ስትሆን ባደረጉት ማጣራት 1292 በላይ መጽሃፍትን መያዟን አረጋግጫለሁ። እነዚህ ቅርሶች ውድና መተኪያ የሌላቸው በመሆናቸው ሁላችንንም የሚያስቆጩ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡– በእጃችን ናቸው የምንላ ቸውስ ቢሆኑ ከስጋት ነፃ ናቸው ተብሎ ይታመናል?
ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ፡– እንዳልሽው በእጃችን ያሉትም ቢሆኑ ከፍተኛ ስጋት ነው ያለባቸው። በዋናነት ከውጭ አገር የሚመጡ ለተለያየ የሚወሰዱበት ሁኔታ አለ። አንዳንዶቹ በቱሪስት መልክ፥ አንዳንዶቹ ለጉብኝት ፥ አንዳንዶቹ ደግሞ ደብዳቤ ሳይዙ የእኛ ሰዎች በየእቃ ቤቱ የሚጠብቁት ሁሉ በራቸውን ለዘራፊዎች የሚከፍቱበት ሁኔታ ሰፊ ነው። ጥቂት የማይባሉትም ቱሪስቶች ፎቶ አንስተው ይወስዳሉ፤ በነገራችን ላይ ይህ ተግባር አንዱ የሌብነት መስክ ነው።
ሌላው ደግሞ በእጃቸው አንጠልጥለው የሚወስዱበት አጋጣሚም አለ።አየር መንገድ ላይ የሚያዙትም በዚህ መልክ ከየቤተክነቱ የተዘረፉ ናቸው። ይህ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ማየት ይቻላል።
ይህም ሊገታ የሚቻለው የተባበረ ስራ መስራት ከቻልን ነው። በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፥ ህግ አስከባሪዎች፥ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ከአስጎብኚ ድርጅቶች ጋር ተባብሮ መስራትን ይጠይቃል። በተጨማሪም ያሉን ሃብቶች ለአገር ጥቅም ይውሉ ዘንዳ እንደዚህ አይነቱ የጥናትና ምርምር ስራዎች ሊበረታቱ ይገባል። ብዙውን ጊዜ የምናደርገው ያሉንን ሃብቶች ዘግተን ማስቀመጥ እንጂ ለጥናትና ምርምር ስናውለው አንታይም። ስለዚህ ሃብቶቻችንን ለጥቅም ልናውላቸው ይገባል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንፃር የወደፊቱ የፊሎሎጂ የትምህርት ዘርፍ በምን መልኩ መቃኘት አለበት ይላሉ?
ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ፡- የዚህን ትምህርት መስክና ይህንን ሙያ ለመታደግ ትልቁ ነገር ሁሉም ሰው በቁጭት መነሳት አለበት። ይሄ ጉዳይ እስላም ወይም ክርስቲያን መሆንን አይጠይቅም። በአረብኛ የተፃፉ ቅርሶች የሙስሊሞች ፣በግዕዝ የተፃፉት የክርስቲያኖች ጉዳይ ብቻ አይደሉም። የሃገር ሃብቶች ናቸው።
ይህንን ግንዛቤ በህብረተሰቡ ዘንድ ማስረፅ ያስፈልጋል። በሁለተኛ ደረጃ በየትምህርት መስክ ያሉ ምሁራን፥ በዚህ ዘርፍ ያሉ ተማሪዎች በሙሉ ሰፊ በሆኑ የፅሁፍ ቅርሶች ላይ ሰፊ ጥናት ማድረግ ይገባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ቁርጠኝነት ያስፈልጋቸዋል ባይ ነኝ። ምክንያቱም አብዛኞቹ ተማሪዎች በአቋራጭና በማያደክም መንገድ በመሄድ ጥናት የሚሰሩበት ሁኔታ አለ። ስለዚህም ከዚህ አስተሳሰብ መውጣትና ቅርሶቹ ባሉበት ስፋራ በመሄድ ጥልቀት ያለውና ለሃገር የሚበጁ ጥናቶች ማካሄድ ይጠበቅባቸዋል። እዚህ ቤተመጽሃፍት ተቀምጦ የሚሰራ ስራ ለአገር ቀርቶ ለራስም አይበጅ። እምብዛም ውጤት አያመጣም።
ሌላው የትምህርት ክፍሉን በማጠናከር ተማሪዎቹን ችግር ፈቺ ማድረግ ወሳኝ ስራ ነው ሊሆን የሚገባው። ተማሪዎቹ አዲስ እውቀትና ግኝት አፍልቀው ለጥሩ ምርምር ጥናት የሚጋብዝ እውቀት እንዲቀስሙ ማድረግ ይጠብቅብናል። በዚህ ዘርፍ ያለው ሌለኛው ተግዳሮት በመንግስት በኩል ስራ የመቅጠር ሁኔታ ያለመኖሩ ነው። በልማት ድርጅቶች በኩል ደግሞ ለጥናትና ለምርምር የሚወጡትን ተማሪዎች ያለመደገፍ ሁኔታ በዘርፉ ምሁራን እንዳይበራከቱ አድርጓል።
በተጨማሪም የጥናትና የምርምር ስራ በገንዘብ እጥረት ምክንያት የሚፈለገውን ያህል ከግቡ ሳይደርስ የሚቀርበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ ለጥናት ለምርምር የተቻለውን ያህል ድጋፍ መስጠት ያስፈልጋል። በዩኒቨርሲቲዎች በኩል ደግሞ ለጥናትና ምርምር የሚመድቡት በጀት ትልቅ መሆን ይገባዋል። ሚዲያዎቹም ትልቁን የማስተዋወቅ ስራ መስራት ይገባቸዋል ባይ ነኝ። ይህን የመሰለ አዲስ እውቀት የሚያመጣና ትላንትን እንደመስታወትየሚያሳይ ዘርፍ በመሆኑ በሁሉም በኩል ሊደገፍ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ዘርፍ የሚያጠኑ ተማሪዎች ሲጨርሱ ከመምህርነት ውጭ በምን ሙያ ላይ ሊሰሩ ይችላሉ?
ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ፡– በፊሎሎጂ ዘርፍ የሰለጠኑ ተማሪዎች በብዙ መልኩ ስራ ሊፈጥሩ ይችላሉ። ስራው በአብዛኛው በጥናትና በምርምር የሚሰራ ስለሆነ ከተቀጣሪነት አልፎ ተመራማሪ ሆኖ መስራት ይቻላል። በዋናነት ደግሞ በባህል ሚኒስቴር ስር ባሉት ልዩ ልዩ ክፍሎች ሁሉ ቢገቡ የተሟላ ባለሙያ የሚያደርጋቸውን ዕውቀት ይዘው ነው የሚመጡት።
ሌላውም በቱሪስት አስጎብኚነት፣ በቅርስ ጥበቃና በታሪክ ጥበቃ በኩልና በተለያየ ማህበረሰብ አቀፍ እና የባህልና ታሪክ ጉዳዮችን ሊሰሩ አዲስ ነገር ይዘው ሊወጡ የሚችሉበት ሁኔታ አለ። ግን ደግሞ መነሻ ገንዘብ፣ ስራ መቀጠሪያ በተወሰነ መልኩ ተስፋ ካልተገኘ ተነሳስተው ይመጣሉ ማለት አይቻልም።
እስካሁን ከተማሪዎቻችን ውስጥ አብዛኞቹ መምህራን ናቸው። አንዳንዶቹ በዮኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያስተምራሉ፣ በባህልና ቱሪዝም በቅርስና ባህል ሚኒስቴር፣ በቱሪስት አስጎብኚነት በኩል፣ በማንኛውም የጥናትና ምርምር ደረጃ የተሻለ አጥኚ ሊሆኑ ይችላሉ። ከታሪክ፣ ከቋንቋና ከባህል አንጻር የተገናኘ ስራ መስራት የሚያስችል በመሆኑ ወደ ዘርፉ መግባት የሚፈልጉ ሰዎች ሊገደቡ እንደማይገባ መምከር እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡– በሌላ በኩል ጥቅም ስለማያስገኝና ብዙ ዋጋም ስለሚያስከፍል በእዚህም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ሌሎች ባለሙያዎች ደፍረው ለመጻፍ ይቸገራሉ። አብዛኞቹም ዕውቀታቸውንም የጋን ውስጥ መብራት ያደረጉበት ሁኔታ አለ። በዚህ ላይ የሚያነሱት ሃሳብ ይኖር ይሆን?
ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ፡- በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው ያመጣሽው። እንዳልሽው እንዲህ አይነት የጥናትና ምርምር ስራዎች የያዙ መፅሐፍትን ማዘጋጀት ከገንዘብ አንጻር ሆነ ከጊዜ ዋጋ ያስከፍላል። በትርፍ በኩል እንዳውም ባይታሰብ ይሻላል። በእኔ እምነት ግን ሌላ ትልቅ ትርፍ አለው።
ይኸውም ቅርሶችቻችን ሰንዶ ማስቀመጥ መቻላችን በራሱ ለአገራችን ትልቅ ውለታ ነው የምናስቀምጠው። ከዚህ አንፃር የብራና ጽሁፍ የጻፉ አባቶቻችን ጽናት አስተምረውናል። ያለምንም ማበረታቻ፣ ጥቅምና ፍላጎት ታሪክን ለአገር ብለው አስቀምጠዋል። እኔ የነቅዐ መፅሃፍትን ስፅፍ መታሰቢያ ያደረግኩት ለእነርሱ ነው። ፈጣሪያቸውን በመፍራት ኖረው ለአገራቸውና ለህዝባቸው ዕድሜ ዘመናቸውን ለደከሙ፣ ታሪክ ሰርተው ቅርስ ጠብቀው ላስረከቡ ሊሂቃን ነው።
ስለሆነም ለእዚህ መጻፍ ያለብን ሰዎች ሙያችን በሚፈቅደውና ጥናትና ምርምር ባደረግንበት የምንችለውን ያክል ርቀት ከሄደን በኋላ ማሳተሙ፣ ገንዘብ ማውጣቱ፣ ጥቅም ማግኘቱ ጊዜ የሚወስድ ነው። እኔ ግን መጀመሪያ አዕምሯችን ያለው ነገር ይቀመጥ ነው የምለው። እኔ ይህንን መጽሃፍ ከጀመርኩት 11 ዓመት በላይ ሆኖኛል። ከእነዚህ ጎን ለጎን እግዚያብሄር ረድቶኝ ነው ሌሎች ስራዎች የሰራሁት።
እንደተባለው ስራው አድካሚ ነው፤ ብዙ ሰዓት መጠቀምንም ይጠይቃል፤ ከቀደመው አባቶቻችን ጽናት ወስደን መስራት ይጠበቅብናል። ሁሉም ሰው በእዚህ ትጋት መነሻነት መስራትም መጻፍም አለበት። ገንዘብ ሳያስብ ትውልድ የመቅረጽ ርካታ፣ የአዕምሮ ዕርካታ ለማግኘት በማሰብ ለመጻፍ መነሳት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ትውልድ በመቅረጽ በኩል ምሁራን ከአሁኑ ትውልድ ጋር ለመግባባት ይቸገራሉ። ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው? አያይዘውም የእርሶን ተሞክሮ ቢነግሩን?
ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ፡– ይሄ አንድ ምላሽ የለውም። የተደራረበና የአንዱ ለሌላው ተመጋጋቢ ምላሽ ነው የሚሆነው። እኔ እንዳልኩሽ ያደግኩበት ባህሉን ጠንቅቆ ከሚያውቅ፥ ሃይማኖተኛና በስነምግባር በታነፃ ቤተሰብ ውስጥ ነው። እኔ ልጆቼን የማሳድገውና ተማሪዎቼም በዚህ መልክ ታንፀው እንዲጎለብቱ ነው የምፈልገው።
ለምሳሌ መብራት ክፍል ውስጥ ካልጠፋ ማጥፋት፣ ውሃ ሲንጠባጠብ እንዳይባክን ማቆም ከአንድ አገሩን ከሚወድና ሃላፊነት የሚሰማው ዜጋ የሚጠበቅ ስለመሆኑ በተግባር አይተው እንዲኖሩት የበኩሌን ሚና እወጣለሁ። ነገር ግን እንደዚህ አይነት ስሜት ተገንብቶ ያደገ ማንነት ያስፈልገናል። ማህበረሰቡም በእዚህ መልኩ ከራሱ በላይ ማየት፣ ማሰብና ተቆርቋሪ መሆን አለበት። ሃይማኖተኛ ከሆነ እንደ ሃይማኖት ካልሆነም ጥሩ ሰው ሆኖ እንዲቀረጽና ለሌላው መድረስ እንዲችል ማድረግ ያስፈልጋል።
የአስተዳደጋችን ሁኔታም የነገ ማንነታችንን ይገልጽልናል። በተቻለን መጠን ከልጅነት ጀምሮ ልጆችን በስነ ምግባር ማሳደግ፣ ወደ ንባብና ወደ ትምህርት እንዲያዘነብሉ መምራት ይገባል። ወደ ጥፋት መንገድ እንዳይሄዱ መጠበቅ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የልጅነት አስተዳደጌ ጠቅሞኛል ብዬ አስባለሁ።
ትልቁ ነገር ግን አሁን ያለው ወጣት ችኩል ነው፣ ይሰለቻል። ቅርስ፣ ታሪክ፣ ባህል የሚባለው ነገር ሁሉ መስማት ይደክመዋል። ከዚያ ይልቅም በአጭር መክበር፣ ቶሎ ገንዘብ ማግኘት ነው የሚፈልገው። ይህንን መቀየር ከባድ ነገር ነው። ሆኖም ትግል በማድረግ፣ ተጨባጭ ነገርን በማሳየት ወጣቱን መመለስ ይገባል ብዬ አስባለሁ።
እንደተባለው ከወጣቶች ጋር ወጣት መሆን፣ ከትልልቆች ሽማግሌ ከምንላቸው ጋር ዕውቀት፣ ጥበብና ልምድ አለኝ። አገር ሰርተው፣ ቤተሰብ መስርተው ባልኖርንበት ዕድሜ 70 እና 80 ዓመት ኖረው አሁንም ወጣት መስለው የሚንቀሳቀሱ አሉ። እነርሱ ጠጋ ብሎ መስማት ያስፈልጋል። ብዙ የሚጠቅም ነገር አለ። የወጣትነት ዘመናቸውን እነርሱ እንዴት እንዳሳለፉት ሲነግሩን ያስተምረናል።
ከነባር ምሁራኖችም ስንረዳ ከእነርሱ የሚጠቅም ነገር እናገኛለን። በተመሳሳይም በጎልማሳ ዕድሜ ካሉ ምሁራንና ነዋሪዎች ማዳመጥም ወጣቱና አዳጊው ማህበረሰብ ጥሩ ትምህርት ያገኝበታል ብዬ አስባለሁ። ነባር ምሁራኖችና ህብረተሰቡም አዳጊውን ማህበረሰብ ቦታ አይሰጡትም አያዳምጡትም። ይህም ሌላ ክፍተት ነው። አሁን ጊዜው ሌላ ነው። እነርሱንም ማዳመጥና ያላቸውን ነገር መስማት ያስፈልጋል። ከላይ ያሉት የበታቾቹን፣ ከታች ያሉትም የበላዮቹን ሳይንቁ የተመጋገበ ኑሮ ስንኖር ኑሯችን፣ ስራችንና ህይወታችን ይስተካከላል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡– የቋንቋ ምሁር እንደመሆንዎት በተለይ ቋንቋ አጥንተናል የሚሉ አንዳንድ ምሁራን የጻፉት መጽሀፍ በህብረተሰቡ መካከል መከፋፈልን፣ አለመግባባትን እየፈጠሩ እናያለን። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ፡- ይሄ እውነት ለመናገር ብዙዎቹን ምሁራንን የሚባሉትን የሚያሳዝን ነው።ኢትዮጵያ የብዙ ቋንቋ ተናጋሪ፣ ብሄር፣ ባህል ያላት አገር ናት። ይህ ሃብት ነው ደስ ሊያሰኝ የሚገባ እንጂ፡ የልዩነት መነሻ መሆን የለበትም። አንደኛው ቋንቋ ከአንደኛው በፍጹም የሚበልጥበት ነገር የለም።
ምክንያቱም ለእዛኛው ቋንቋው ይበልጣል ለሚባልለት ሰው የሱን ያህል ያረጋል የተባለው ቋንቋ ለሌላውም ይገልጽለታል፣ ትዳሩን ይገልጽበታል፣ ኑሮውን ይገፋበታል፣ እርሻውን ያርስበታል፥ ማህበራዊ ኑሮውን ያሳልጥበታል። ምንም ሳይጎድልለት ይግባባበታል። በእኔ እምነት በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየታየ ያለው ችግር ልዩነቶቻችን ሲናፍቁ በነበሩ የውጭ ሰዎች ጫና የተፈጠረ ነው።
የአለም መጽሃፍት እንደሚያስረዱት ቋንቋ ሁሉ ክቡር ነው። ያልተማሩ፣ ደሀ፣ ራቁታቸውን የሚሄዱ፣ ዝቅተኛ ናቸው የሚባሉ ሰዎች እንኳን ቢሆን እንደ ቋንቋ አጥኚ ስናየው ሰዋሰዋቸው፣ ህጋዊ ንድፉ፣ ስነአመክንዮ የሚያስደቅና አንዱን ከአንዱ የሚያበላልጡ ምሁራን ብዙ የሚያስተምሩ ናቸው።
ይህንን ማሽን አይሰራውም። አእምሯቸው ፈጣሪ በሰጣቸው ዕውቀትና ችሎታ ያንን ቋንቋ ባደጉበት ባህል ይዘውት ያድጋሉ፣ ለአገርም አንድ ቋንቋ ያበረክታሉ። ደግሞም ሁሉም ቋንቋ በራሱ አውድ ሙሉ ኑሮውን ሳይቸገር እየሄደበት ይታያል።
አደጉ በሚባሉት እንደ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛና ጀርመንኛ አገራት ጭምር ሳይቀሩ ቋንቋ የውጭ ቋንቋ የቴክኖሎጂ ነገር አዲስ ነው። ግን እንደ አገር፣ እንደ መንግስትም እንደ ምሁርም የሚሰሩት ነገር አለ። አደጉ በሚባሉት እንደ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛና ጀርመንኛ አገራት በቴክኖሎጂ ምክንያት አዲስ ቋንቋ ሲመጣባቸው በተቀመጠው አሰራርና የህግ አግባብ መሰረት በራሳቸው ቋንቋ ፍቺ ይሰጡትና ይጠቀሙበታል እንጂ አይምጣብን ብለው አይገፉት። ቋንቋ በዚህ መልኩ ያድጋል።
የተለያዩ ቋንቋዎች ማወቃችን ለግንኙነታችንና ለአብሮነታችን ዋነኛ መሰረት ነው። ይሁንና በአሁኑ ወቅት በአገራችን የምናየው ቋንቋ ከመሰረታዊ እሳቤው ውጪ እየዋለ መሆኑን ነው። በጣም የሚያሳዝንም ጉዳይ ነው። ቋንቋ የመለያያ እና መበደያ ሲሆን ያሳዝናል። ቋንቋ ሊሆን የሚገባው መግባቢያና ተቻችሎ መኖሪያ ነው። እንዳውም አንዱ የሌላውን ለማወቅ ነው መጓጓት የሚገባው ባይ ነኝ።
በተለይም ደግሞ አብረን እንደመኖራችን መጠን አንዳችን የሌላውን ቋንቋ ብናውቅና እንዲያድግም ብንፈቅድ እርስ በርስ መተዋወቂያና የበለጠ በሰላም ለመኖር ያግዘናል። ራሳችንን የምናበለፅገበት መንገድ ነው ሊሆን የሚገባው። ስለዚህ ቋንቋ ለፖለቲካ አላማ ማዋል አንድም ሰው መሆንን መርሳት ነው፤ ሁለትም ቋንቋ የተፈጠረበትን መሰረታዊ እሳቤ ካለማወቅ የሚመነጭ ነው።
ሶስተኛውና መሰረታዊው ሃሳብ ለነገ መኖር እንዳንችል የሚያደርግ የተዳፈነ ረመጥ ነው የምናስቀምጠው። ከዚያ አንፃር እኔ የፖለቲካ ሰዎችም ቢሆኑ፥ ምሁራንና አክቲቪስቶች የሚሰጡት ሃሳብ አግባብነት የለውም ብዬ ነው የማምነው። ደግሞም የሌላውን ቋንቋ ማንኳስ የራስን ቋንቋ ለማሳደግ ምንም አስተዋፅኦ አይኖረውም። እውነት ለመናገር በየትኛውም የአለም አገራት ቋንቋ በይገባኛል ባይነት አድጎ በልፅጎ አያውቅም። በአጠቃላይ ቋንቋን ተገን አድርጎ የሚፈጠሩ አምቧጓሮዎች በተገኘው መልኩ መወገዝ ያለበት እኩይ ተግባር ነው።
አዲስዘመን፡- እግረ መንገድዎን እስቲ ስለወቅታዊው የአገራችን ፖለቲካ ሁኔታ ያሎትን ምልከታ ይግለፁልን?
ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ፡– እንደ አንድ ዜጋ የአገራችን ጉዳይ ይመለከተኛል ብዬ አምናለሁ። ይህ አገር በሰላማዊነቷ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ሃይማኖቶችና አስተሳሰቦች ያላቸው ህብረተሰቦች በጋራ የሚኖርባት ድንቅዬ አገር ናት። ይህንን የመሰለ አንፀባራቂ እሴት ለማጥፋት የሚሯሯጡ አካላት እንዳሉ አምናለሁ።
ይህም አለመታደል ነው ብዬ ነው የማስበው። በዚህ ደረጃ በማንነታቸው ምክንያት የዜጎች መፈናቀልና መንገላታት ማየት ከዚህ የበለጠ አሳሳቢ ነገር የለም። መወገዝም ያለበት ጉዳይ ነው። ስለዚህ እንደ ድሮው አቃፊ ሆነን ፥ ተቻችለን፥ መኖር ይገባናል። አንዱ ዛሬ ጊዜ ሰጥቶ በሌላው ላይ እንደዚህ አደርጋለሁ ሲል መርሳት የሌለበት ነገር ነገ ደግሞ ፋንታን መቀበሉ የማይቀር መሆኑን ነው።
ቁምነገሩ ፈረቃ አይደለም። በፈረቃ አንዱ አንዱን እየበደለ የሚቀጥል ከሆነ መቼም የማያቋርጥ ጥቁር ደም ስንቀባባ ነው የምንኖረው። ይሄ ግን አይጠቅምም። የፖለቲካ መሪዎች የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር እየሮጡ ያሉትን ሩጫ ገትተው ህዝቡን አቅጣጫ ማስያዝ ይጠበቅባቸዋል። ህዝቡ ተቻችሎ የመኖር እሴትን የማያስቀጥሉ የፖለቲካ መሪዎችን ፊት መንሳት አለበት ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመስግናለሁ።
ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ፡- እኔም እድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 3/2011
በማህሌት አብዱል