
አቶ ታገስ ሙሉጌታ – በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ንግድ ትስስር መሪ ሥራ አስፈፃሚ
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የአፍሪካ ሀገራት ወደ ሀገራቸው በሚያስገቧቸው ምርቶች ላይ የሚጣለውን ቀረጥና ሌሎች ከቀረጥ ውጭ ያሉ ተግዳሮቶችን በሂደት በመቀነስ የእርስ በርስ የንግድ ትስስር ለማሳለጥ ታልሞ የተቋቋመ ነው:: ከ16 በመቶ በታች የሆነው የአፍሪካ ሀገራት የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ እ.ኤ.አ በ2040 ከ15 እስከ 25 በመቶ እንደሚያሳድገው የመንግሥታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መረጃ ያሳያል::
በዚህ ረገድ ትስስሩ እውን ማድረግ ያስችላቸው ዘንድ አባል ሀገራቱ በተናጠልም ሆነ በጋራ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ይገኛሉ:: ኢትዮጵያም ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ የሚያስችላትን የብሔራዊ የንግድ ቀጣና መተግበሪያ ስትራቴጂ አዘጋጅታለች:: በዚህና እንደ አህጉር እየተደረጉ ባሉ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ትስስር መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ታገስ ሙሉጌታ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገናል:: እንደሚከተለው ይቀርባል::
አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ ሚኒስቴሩ የአፍሪካ ቀጣናዊ ትስስርን በማሳለጥ ረገድ እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴ ያብራሩልንና ውይይታችንን ብንጀምር?
አቶ ታገስ፡- ሚኒስቴሩ በአዋጅ ከተሰጡት ኃላፊነቶች አንዱ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ንግድ ሥርዓት ትስስር ረገድ የምታደርጋቸውን የንግድ ግንኙነቶችን በማስተባበር ሁሉንም የንግድ ሂደቶች በበላይነት ይመራል:: በዋናነትም የእኛ የሥራ ክፍል ይህንን የሥራ ሂደት የሚከታተለው ይሆናል:: ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድርን መከታተል፤ ማስተባበርና ድርድሩ ወደ ላቀ ደረጃ አድጎ እንዲጠናቀቅ ማድረግ ትልቁ ኃላፊነቱ ነው::
በሁለተኛ ደረጃ በቀጣናዊ የንግድ ትስስር ረገድ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችውን ድርድሮች የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባበር ይመራል:: ሶስተኛው ደግሞ በሁለትዮሽ ረገድ ኢትዮጵያ የምታደርጋቸው ድርድሮች የንግድ ድርድሮችን ያስተባብራል፤ ይፈርማል፤ ያስፈፅማል::
ስለዚህ ኢትዮጵያ አሁን ባላት ነባራዊ ሁኔታ በሁለትዮሽ ደረጃ ከ20 ያላነሱ ሀገራት ጋር ድርድር በማድረግ ተፈራርማለች:: እነዚህ የሁለትዮሽ ትስስሮች በዓለም አቀፍና በሌሎችም ትስስሮች ባለን ደካማ ልምምዶች እነዚህ የሁለትዮሽ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነቶች በትብብር ማሕቀፍ ደረጃ ያሉና የነፃ ገበያ መልክ የሌላቸው ናቸው:: ነገር ግን ከሱዳንና ከደቡብ ሱዳን ጋር ብቻ የሁለትዮሽ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት አላት:: ስለዚህ በተለይ የእኛ የሥራ ክፍል እነዚህን ሰፋፊ ጉዳዮች የሚመራ ነው::
አዲስ ዘመን፡- የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ሃሳብ ከጥንስሱ ጀምሮ የአፍሪካውያንን ተጠቃሚነት ለማሳደግና አህጉራዊ ብልፅግና ለማምጣት የታለመ እንደሆነ ይታመናል:: ትስስሩን በማሳለጥ ረገድ እንደ አህጉር እየተሠራ ያለው ሥራ ምን ይመስላል?
አቶ ታገስ፡– የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ስምምነት ምንም እንኳን ድርድሩ በመሪዎች ይሁንታ አግኝቶ ወደ ውይይት ከተገባ አጭር ጊዜ ቢሆንም ፍሬው ግን የተጠነሰሰው ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ አፍሪካ ሕብረት መመሥረት ጋር ተያይዞ ነው:: ከዚያ በኋላ ሃሳቡ እየጎለበተ መጥቶ የአፍሪካን ኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የታቀዱ መርሃ-ግብሮችን መሠረት አድርጎ ነው:: እንደሚታወሰው የአፍሪካ መሪዎች በ1980ዎቹ አካባቢ የሌጎስ የድርጊት መርሃ ግብርን ያዘጋጁ ሲሆን አፍሪካን እንዴት በኢኮኖሚ፣ በመሠረተ ልማት እናስተሳስራለን የሚል ሃሳብ የያዘ ነበር:: ይሁንና ይህ የድርጊት መርሃ ግብር በተሳካ ሁኔታ አልሄደም:: በመሆኑም ወደ ስምምነት አሳደጉትና በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የአቡጃ ትሪቲ (ስምምነት) በሚል በውል ደረጃ አደገ::
በእዚያ መሃል ሌሎች እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፤ ሆኖም ተጨባጭና ወሳኝ የነበረው ጉዳይ ይህ የውል ሂደትን እውን ማድረጉ ነው:: ሌሎች ውሎችም በውስጡ እንዲካተቱ ተደርገው፤ በሂደት የሚያድግ እና በምዕራፍ የሚከፋፈሉ ተግባራት አሉበት:: ለአብነት ያህል መጥቀስ ካስፈለገ እርስ በርስ ያለውን ንግድ ለማስተሳሰር መጀመሪያ እንደ ኮሜሳ፣ ኢኮዋስ ያሉ አካባቢያዊ የኢኮኖሚ ትስስሮች የላቀ የንግድ ሥርዓትና ቅርፅ እንዲኖራቸው የማድረግ፤ በመቀጠልም አንዱ ከሌላው ጋር መጠርነፍ፤ ከዚያ በኋላ ደግም አህጉር አቀፍ የሆነውን ምስል ማምጣት ነው:: ይህም ደግሞ በ34 ዓመታት ውስጥ አንድ የኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ መፍጠር ነበር እቅዱ::
ይህንን ለማሳካት የተሠሩ ሥራዎች አሉ፤ ለምሳሌ የኮሜሳን ውህደት ብንመለከት ነፃ የንግድ ስምምነት ወደ ከስተምስ ዩኒየን እንዲያድግ፤ እርስበርስ ያላቸው ግንኙነት እንዲጠናከር ተደርጓል:: ግን በሚታሰበው ልክ መሄድ አልቻለም:: ስለዚህ እ.ኤ.አ በ2012 ላይ መሪዎቹ በታሰበው ልክ እንዲሄድ ለማድረግ አህጉራዊ የንግድ ስምምነት መፍጠር አለበት የሚል ውሳኔ አስተላለፉ:: በመሆኑም በዚያው ዓመት በመሪዎች ይሁንታ ተጀምሮ ለረጅምና ለተከታታይ ጊዜያት ሲወያይበት ቆይተው በእ.ኤ.አ 2016 ተጀመረ:: ይህም ስምምነት ትልሙ አንቺም እንዳልሽው አህጉራዊ ብልፅግናን ማምጣት ነው:: ግን ደግሞ የጋራ የሆነ ልማት፤ እቅድ፣ ገበያ በመፍጠር የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠርም ዋነኛ ትኩረቱ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ይህንን እቅድ በተጨባጭ መሬት ላይ በማውረድ ረገድ የትኞቹ ሀገራት እንደ ምሳሌ ሊጠቀሱ ይችላሉ? በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ሚና እንዴት ይገለፃል?
አቶ ታገስ፡– ይሄ እንቅስቃሴ በአፍሪካ መሪዎች ደረጃ የሚመራ ነው:: ምንም እንኳን አንዳንድ ሀገራት የራሳቸው ፍላጎት ቢኖራቸውም፤ በተወሰነ መልኩ መጓተቱ ሊኖር ይችላል:: ሆኖም እንደ አህጉር አስቀድሜ የገለፅኩት ጥረቶች የሚናቁ አይደሉም:: ግን ደግም እቅዱ የተለጠጠ ጉጉት የነበረው ሆኖ ሊሆን ይችላል፤ አልያም እዚህም እዚያም የሚፈጠሩ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች ጉዳዩ በታቀደለት ፍጥነት እንዳይሄድ አድርጓል::
ዘግይቶም ቢሆን በአቡጃ ስምምነት መሠረት አሁን ላይ ከስተምስ ዩኒየን ለማቋቋም ድርድሩን ጨርሰናል፤ ግን ወደ ተግባራ ለመግባት ብዙ ተግዳሮቶች አሉት:: አሁንም ድረስ ነፃ የንግድ ቀጣናን ራሱ እውን ማድረግ አልቻልንም:: ተደራድረናል፤ ድርድሩን ጨርሰናል፤ ግን ወደ ትግበራ ሲመጣ ብዙ ችግሮች አሉበት:: በጥቅሉ እንደ አህጉር በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይሄድ ውጪያውም ሆነ ውስጣዊ ተግዳሮቶች አሉ::
ከእነዚህ ተግዳሮቶች መካከል መጥቀስ የሚቻለው ውጪያዊ የምንላቸው አፍሪካን የጥሬ እቃ ምንጭ አድርገው የሚያስቡ የምዕራቡ ሀገራት አሉ፤ ስለዚህ እርስ በርስ ያለው ኢኮኖሚ ባደገ ቁጥር ጥሬ እቃ ከሌላው ዓለም እንደማያገኙ ግልፅ ነው:: ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ፈተና ወደ ኋላ ሊጎትተን እንደሚችል እሙን ነው:: እንደ አህጉር ደግሞ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት በተመሳሳይ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ያለ መሆናቸው፤ በተመሳሳይ የፖለቲካ መረጋጋት ያለመኖሩ፣ በተመሳሳይ የመሠረተ ልማት እድገት ላይ ያለ መድረሳቸው፤ ትስስሩን እየጎተተው መሆኑን ነው አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳየው:: ርግጥ በአንድ ጊዜ የሚመጣ ነገር አይደለም፤ ትግል ይፈልጋል፤ መመካከር በየጊዜው አቅጣጫዎች ማስቀመጥ፣ በውሳኔው መሠረት እየገመገሙ መሄድ ይፈልጋል:: ያም ሆነ ይህ ግን አሁን በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት የሚታዩ መሻሻሎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው:: ለምሳሌ ድርድሩ በከፊል ተጠናቋል::
አዲስ ዘመን፡- በከፊል ተጠናቋል ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አቶ ታገስ፡- በከፊል ተጠናቋል ሲባል ለምሳሌ ድርድር የሚደረግባቸው ሰነዶች ወደ ስምንት የሚሆኑ ፕሮቶኮሎች ተጠናቀዋል:: ከእነዚህም የጥሬ እቃ፣ የአገልግሎት፣ የግጭት ፕሮቶኮል ተጠቃሽ ናቸው:: በመቀጠልም በምዕራፍ ሁለት ደግሞ ኢንቨስትመንት ፕሮቶኮል፣ የውድድር ፖሊሲ፣ የዲጂታል ግብይት ፖሊሲ፣ የወጣቶችና ሴቶች የንግድ ፖሊሲ ያካተቱ ስምንት ፕሮቶኮሎች ተጠናቀዋል:: ግን ደግሞ በውስጣቸው ብዙ ማስፈፀሚያ የሚሆኑ የአሠራር ሥርዓቶችን ይፈልጋሉ::
ለምሳሌ ፖሊሲ ከተዘጋጀ በኋላ መመሪያ እንደሚዘጋጀው ማለት ነው:: ስለዚህ የጥሬ እቃውን (ጉድስ) ፕሮቶኮል ሙሉ ለሙሉ ለማስፈፀም ከዘጠኝ በላይ አባሪዎች፤ በርካታ ተቀፅላዎች አሉት:: ለምሳሌ የጥሬ እቃ ንግድ ወደ መሬት ለማውረድ ሁሉም አባል ሀገራት በታሪፍ ቅነሳ ላይ መስማማት መቻል አለባቸው:: የታሪፍ ቅነሳው በተስማሙበት መሠረት ወደ ተግባር መግባት ይጠበቅባቸዋል:: የአገልግሎት ዘርፉም በተመሳሳይ ሊሆን ይገባል:: እነዚህ በተጨባጭ ወደ መሬት የሚወርዱ በመሆናቸው ትልቁ ጥላ ላይ ከመወያየት የባለድርሻ አካላትን ቁርጠኝነትና ተሳትፎ ይፈልጋሉ:: ይህ ሲሆን ደግሞ ባለድርሻ አካላት ጋር መጓተቱ ይኖራል::
ለምሳሌ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የጥሬ እቃ ታሪፍ ቅነሳ ሰነድ ስታዘጋጅ በሶስት ምዕራፍ ነው የተስማማነው፤ አንደኛው በአስር ዓመት ውስጥ ታሪፉ ዜሮ እንዲሆን ነው:: ይህም ማለት እ.ኤ.አ ከ2021 እስከ 2031 ነው የሚተገበረው:: ሁለተኛውና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልገውን ዘርፍ ደግሞ የተወሰነ የሽግግር ጊዜ ሰጥተን ከ2026 እስከ 2034 ለስምንት ዓመታት የሚቀንስ ነው:: ሶስተኛው ደግሞ ምንም ታሪፍ የማይቀንስበት በማድረግ ነው የተስማማነው:: በዚህ መሠረት የትኛው ምርት በየትኛው ምዕራፍ ይቀነሱ የሚለው ብዙ መመከር ይፈልጋል:: የፖሊሲ አቅጣጫንና የባለድርሻ አካላትን ድጋፍ ይሻል:: እሱ ላይ በተለያየ ፍጥነት ነው መግባባት መፍጠር የሚቻለው:: ለእኛም እንደ ሀገር ጊዜ ወስዶብን የነበረው እሱ ነው:: በመጨረሻ ግን እኛ አጠናቀን ለሴክሬታሪያቱም አስገብተን፣ አባል ሀገራቱም ተቀብለውት አሁን እኛ ጥሩ መስመር ላይ ነው ያለነው:: እንዲህ ዓይነት በተለያየ ምዕራፍ ላይ መሆናችን ሙሉ ለሙሉ እንደ አህጉር ጉዳዩን ወደ ተግባር ላለማስገባት በምክንያትነት ይጠቀሳል::
በከፍተኛ አመራሩ ዘንድ ቀና የሆነ ምላሽ አለ፤ ከፖለቲካ ቁርጠኝነት አኳያ አብዛኞቹ የአፍሪካ መሪዎች ይህንን ውህደት ይፈልጉታል:: በየጊዜው አጀንዳ አድርገው እየመከሩበት ነው:: ግን ደግሞ ወደ መሬት ሲወርድ ነው ተግዳሮቱ የሚበዛው:: እንደ አጠቃላይ በየሀገራቱ የተቋማት ያለመጠናከራቸው፣ ልምድ አለመኖሩ፤ ከዚያም ባሻገር የፖለቲካው አለመረጋጋት ወደ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ እንዳንገባ እንቅፋት ሆኗል ማለት ይቻላል::
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ እስከ አሁን ምን ያህል ሀገራት ስምምነቱን ፈርመዋል?
አቶ ታገስ፡- አስቀድሜ እንዳልኩሽ በከፍተኛ መሪዎች ደረጃ መልካም የሆነ አመለካከት አለ፤ ይህም በመሆኑ ከኤርትራ ውጭ 54ቱም አባል ሀገራት ስምምነቱን ፈርመዋል:: ይሄ የሚያሳየው በመሪዎች ደረጃ ምን ያህል ቁርጠኝነቱ እንዳለ ነው:: የታሪፍ ቅነሳ ሰነዱን ያዘጋጁ 49 ሀገራት ናቸው:: ስለዚህ በመፈረም ረገድ ችግር አልገጠመውም፤ ሙሉ ለሙሉ ወደ ተግባር ማስገባቱ ግን አንድም ትኩረት መስጠት አለባቸው:: ሁለተኛው ደግሞ የምርት ስሪት ምንጭ ነው:: ይህም ምርቱ አፍሪካ ውስጥ የተመረተ መሆኑን የምናረጋገጥበት ነው:: ይሄ በጣም ወሳኝ ጉዳይ ሲሆን ምርቱ አፍሪካ ውስጥ የተመረተ መሆኑን የምናረጋግጥበት ደንብ ነው:: ስለዚህ እሱን በሚፈለገው ፍጥነት ተደራድሮ አለመጨረስ ሙሉ ለሙሉ ትግበራው እውን እንዳይሆን አድርጎታል:: ይሄ ወሳኝ ጉዳይ ነው::
ስለዚህ በሚፈለገው ፍጥነት ተደራድሮ አለመጨረስ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዳይሆን አድርጎታል:: ግን ሌላው ምን ያህል በከፍተኛ መሪዎች ደረጃ ትኩረት እንደተሰጠው የሚታየው ዘርፉ ጋይድድ ትሬድ ኢኒሼቲቭ ፍሬም ወርክ አዘጋጅቶ በፓይለት ደረጃ ንግድ እንዲጀመር አድርጓል:: ይህም ከ2002 ጀምሮ ነው ይፋ የተደረገው፤ በወቅቱ ሰባት ሀገራት ነበሩ ወደ እዚያ ኢኒሼቲቭ ለመግባት ፍቃደኛ የሆኑት፤ አሁን ወደ 14 የሚጠጉ በእዚያ ማሕቀፍ ውስጥ ንግድ ጀምረዋል:: ስለዚህ እነዚህ ልምምዶች ዋናውን የትብብር ማሕቀፍን ለመተግበር እንደአስቻይና የመለማመጃ መድረክ ይሆናል ተብሎ ይታመናል::
አዲስ ዘመን፡- ለቀጣናዊ ትስስሩ እውን መሆን የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ዋነኛ መሳሪያ እንደሆኑ ይታወቃል፤ ከዚህ አንፃር የየሀገራቱ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
አቶ ታገስ፡- አሁን ላይ አፍሪካ ውስጥ የእርስ በርስ ንግዱን ማነቆ የሆኑትን፤ እስከ አሁን የሆኑትን አሁንም ያስቸግራሉ ተብሎ የሚታሰበው የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ነው:: ብዙ ጸሐፍት እንዳሰፈረቱም አንድን ምርት ከምሥራቅ አፍሪካ ወደ ምዕራብ አፍሪካ ከመላክ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት መላክ ይቀላል:: በመሆኑም መሠረተ ልማት በሚፈለገው ደረጃ ያለመዘርጋቱ የንግድ ወጪውን ይጨምረዋል:: ስለዚህ ምንም እንኳን ተቋሙ የሎጅስቲክስ ተቋም ባይሆንም፤ ወይም ወደቦችን ለመገንባት የተቋቋመ ባይሆንም ግን ለንግዱ መሳለጥ እነዚህ ነገሮች ያስፈልጉታል:: ደግሞም በአህጉርም ደረጃ እንደ አንድ የንግድ ማነቆዎች ተለይተዋል:: ስለዚህ አባል ሀገራቱ እነዚህን ተግዳሮቶች በተቻለ መጠን መቀነስ የሚቻልበትን ሁኔታ ውይይቶች ተጀምረዋል:: ስለዚህ በእያንዳንዱ ኮሪደር ላይ ምን ዓይነት መሠረተ ልማት አለ፤ ምን ይቀራል የሚለው ተለይቷል::
ከዚህ አንፃር እኛ የምንጠቀመው ወደብ የጅቡቲን ነው፤ ስለዚህ ጅቡቲን ኮሪደር አድርጎ የሚሄደውን ተሽከርካሪ ሁሉ የዳሰሳ ጥናት አድርገናል:: ይህ ማለት በአንድ ጀምበር መሠረተ ልማት ይዘረጋል ማለት አይደለም፤ ግን ችግሮችን ለመለየት ያስችላሉ:: ወደፊት በተለያዩ ፕሮጀክቶችና ድጋፎች ለማሟላት የጀመሩት ነገር አለ:: የተሻሉ አሁን ላይ ንግዱን ለማሳለጥ የሚያስችል የተለያዩ አማራጮች ላይ ውይይት እያደረግን ነው:: ምክንያቱም አሁን ባልኩሽ ጋይድድ ትሬድ ኢኒሼቲቭ የንግዱ ዘርፍ አንዱ የገጠመው ተግዳሮት የሚላከው በመጠን አነስተኛ የሆነ ምርት ነው፤ ለምሳሌ ከኬንያ የተነሳ እቃ ወደ ሴኔጋል ወይም ጋና በመኪና ሊሄድ ይችላል፤ ሲመለስ ግን እቃ ካላገኘ ኪሳራ ነው:: ስለዚህ ሴክሬታራይቱ ካርታ ነድፈው እቃ ይዞ የሚሄደው ተሽከርካሪ ሲመለስ ከተለያየ ሀገር እየሰበሰበ መምጣት እንዲችል ለማድረግ ነው:: ይህንን ደግሞ የሚያስተባብር አካል መኖር አለበት፤ በአሁኑ ወቅት ከሀገራቱ ጋር ያንን የግንኙነት አግባብ (መስመር) ለመፍጠር እየተሞከረ ነው::
ሌላው ትልቁ እንደ እድል የሚታየውና እኛም እንደ ሀገር መሥራት ያለብን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ነው፤ በ32 ሀገራት ከ50 በላይ መዳረሻዎች አሉት:: ለምሳሌ ኬንያ፣ ናይሮቢና ሞምባሳ ያርፋሉ:: ስለዚህ የኢትዮጵያ የካርጎ ፕሮሰሱን የሚጀምር ከሆነ እኛም የምናስተዋውቀው እሱን ነው:: ይህንን መሠረት በማድረግ ካርታው የሚሠራለት ከሆነ ለእኛ ጥሩ እድል ነው:: እኛ የንግድ ልውውጡን ስንጀምር በስፋት ይህንን አቅም ለመጠቀም የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴርም በዚህ ጉዳይ ላይ ፍላጎት ስላለው ውይይት ጀምረናል፤ በከፍተኛ አመራር ደረጃ ምክክር እየተደረገ ነው::
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሲናገሩ እንደሚደመጡት በቀጣና ደረጃ ትስስሩ ያለመጠናከሩ ትልቁና አህጉራዊን ትስስር እንዳይፈጠር ምክንያት ሆኗል ባይ ናቸው:: እርስዎ በዚህ ላይ የአልዎት እምነት ምንድን ነው?
አቶ ታገስ፡- ይህንን ጉዳይ በሁለት መንገድ ነው ማየት አለብን::፤ ርግጥ ነው አስቀድሜ ባልኩሽ መንገድ እያንዳንዱ ቀጣና በ1994 የሌጎስ ስምምነት ሲፈረም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስምንት ቀጣናዊ ብሎኮችን ለይቷል:: ከእነዚህም መካከል ኢጋድ፣ ኮሜሳ፣ ሳድቅ ተጠቃሽ ናቸው:: እነሱ እንዲጠናከሩ ነው ድጋፍ እያደረጋቸው ያለው:: ግን ሁሉም በሚፈለገው ደረጃ አልመጡም፤ የተወሰኑት ጥሩ ሄደዋል:: ለምሳሌ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ተጠቃሽ ነው:: ይህም ቢሆን ከዚህም ቀጣና ውስጥ ሁሉም አባል ሀገራት እኩል ስላልመጡ ሌላ ትስስር የተፈጠረበት ሁኔታ አለ:: ለምሳሌ ሁሉም የኢኮዎስ አባል ሀገራት እኩል መምጣት ስላልቻሉ የተወሰኑት ከፍ ብለዋል:: ስለዚህ እንደተባለው እያንዳንዱ ቀጣና በእኩል መንገድ ማደግ ቢችል መልካም ቢሆንም ትልቁን ትስስር ለመፍጠር ጥረት መደረጉ እንደ ችግር አላየውም:: ምናልባትም ወደ አንድ የሚገፋቸው ማሕቀፍ ይሆናል ብዬ ነው የማስበው::
ሁለተኛው ጥሩ እድል ወይም ጠቀሜታ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ስምምነት በተሻለ ደረጃ ያሉትን ወደኋላ አልመለሳቸውም፣ ትስስራቸውን ባሉበት እንዲቀጥሉ ነው የፈቀደው:: የሚዳኙትም ሆነ የንግድ ልውውጡን የሚያደርጉት በራሳቸው ማሕቀፍ ነው:: ግን እንደ አንድ ጥላ ደግሞ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ይኖራል:: ለምሳሌ የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ከአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ደረጃው ከፍ ይላል:: የተለያየ ቦታ አባል መሆን በራሱ ውጤታማ ለመሆን አዳጋች ነው የሚሆነው:: ምክንያቱም ከአንዱ ስብስብ ሌላኛው ጋር የአሠራር መጠላለፍ ሊከሰት ይችላል:: ስለዚህ አህጉራዊው የንግድ ቀጣና ትስስር መጠላለፍንም እያስተካከለው ይመጣል:: የነበረውን መፋዘዝ ሊያፋጥን የሚችል ነው የሚል እምነት አለኝ::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በተለይ በኢኮኖሚያቸው ከተሻሉ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ለመወዳደር ምን ምን ሥራዎች ልትሠራ ይገባል ይላሉ?
አቶ ታገስ፡– የመወዳደር አቅምን በተለያየ መልኩ ነው ማየት ያለብን:: ለምሳሌ ስለ እቃዎች ንግድ ውድድር የምናስብ ከሆነ የኢትዮጵያ የንግድ እቃዎች ዝርዝር ከ6 ሺ 400 በላይ ነው:: ስለዚህ በየትኛው ዘርፍ ነው የበለጠ ተወዳዳሪ መሆን የምንችለው የሚለውን ነገር መለየትና እዚያ ላይ አተኩሮ መሥራት ይገባል:: በመጀመሪያ ደረጃ አቅርቦቱ ሰፊ የሆነውን መምረጥ እና በሂደት ተወዳዳሪ የሚሆኑ ምርቶችን በውድድር ውስጥ በማስገባት አቅም ማሳደግ ይገባል:: በሁሉም ግን አንችልም የሚለው አያሳምነኝም:: እንደ ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የሆንባቸው ምርቶች አሉ፤ እዚያ ላይ እንዴት አድርገን ምርታማነታችንን አሳድገን እንሥራ የሚለውንና ካለን የመሬት አቅርቦት፣ የአየር ሁኔታ፣ የማምረት ሂደት ላይ ተመስርቶ ምርታማነት መጨመር ላይ ነው ትኩረት ማድረግ ነው የሚጠበቅብን::
ከዚህ ባሻገር በምናቀርባቸው ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር የበለጠ ተወዳዳሪነታችንን ማጎልበት ይኖርብናል:: በተለይ እንደ ቆዳ፤ ሥጋና መሰል በግብርና ውጤቶች ላይ እሴት በመጨመርና በመላክ የገበያውን ፍላጎት ማርካት መቻል አለብን:: በዚህ ረገድ አሁን እየተሠሩ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን ዓላማቸውን ስናይ እንደ ሀገር ምን እየተሠራ እንደሆነ ያሳያል:: በግልም ሆነ በመንግሥት የሚሠሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዋና ግብ እሴት መጨመር ነው:: የአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ፓርኮች አሉ:: እነዚህ ፓርኮቸ መስፋት ወደ ገበያ ለመግባት ትልቅ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው::
በነገራችን ላይ ነፃ የንግድ ቀጣና ትስስር ዋነኛ ዓላማው ቢሆንም ቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለትን ማሳደግም ግብ አለው:: አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ ዓላማው የእርስ በርስ ንግድን ማሻሻል በመሆኑ ከኢትዮጵያ የሄደ አንድ ምርት እንደ አፍሪካ ምርት ነው የሚታየው፤ ሌላ ሀገር ሄዶ ደግሞ እሴት ተጨምሮበት ሊመጣ ይችላል:: ለምሳሌ እኛ ቆዳ ዝም ብለን ከምንልክ አንድ ሌላ ሀገር ኬሚካል ካመረተ ኬሚካሉን ተጠቅመን በቆዳው ላይ እሴት ጨምረን መላክ እንችላለን:: በአህጉርም ደረጃ እሴት የመጨመር ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶታል:: ሆኖም አሁንም ካልተሠራ፤ ራስን ካላበቁና ካላዘጋጁ ተወዳዳሪ መሆን አይቻልም:: ለዚህም አዋጭ አማራጮችን መቃኘት፤ ስትራቴጂ መንደፍ ይኖርብናል:: በተጨማሪም የግሉ ዘርፍ እሴት ጨምሮ እንዲልክ መደገፍና ማበረታት ይጠበቃል:: በመሠረቱ አንድ የግሉ ዘርፍ ተዋናይ እሴት የተጨመረበትን የኢትዮጵያ ምርት መላኩ በራሱ ሊያኮራው ይገባል:: እዚህ ላይ ያለው ምልከታ እንደ ሀገር መቀየር አለበት የሚል እምነት ነው ያለኝ::
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ የሀገራቱ የንግድ ትስስር ምን ላይ ደርሷል?
አቶ ታገስ፡- አፍሪካ አሁን ላይ ያለው የእርስ በርስ የንግድ ልውውጧ ከ15 እስከ 16 በመቶ ነው የሚገመተው:: ይሄ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትንም ይህንን ያሻሽለዋል የሚል እምነት ነው ያለው:: የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የሚያወጣቸው መረጃዎች የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት በስምምነቱ ማሕቀፍና በታለመለት መልኩ መተግበር ሲጀምር በቀጣይ 20 ዓመታት አሁን ያለውን በ50 በመቶ ከፍ ያደርገዋል:: በአውሮፓ 60 በመቶ ያህል እርስ በርስ ይነግዳሉ:: ኤዤያ እስከ 46 በመቶ አሜሪካ 70 በመቶ በላይ እርስ በርስ የንግድ ልውውጥ ያደርጋሉ:: ለዓለም ያለው አስተዋፅኦ በዚሁ ልክ ነው:: እኛ እንደ አህጉር አሁን ላይ ለዓለም ንግድ እድገት የምናውጣው ከሶስት በመቶ አይበልጥም:: በመሆኑም ትስስሩ ሲጠናከር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖረንም አስተዋጽኦ ወደ ሁለት ዲጂት እናስገባዋለን ተብሎ ነው የሚጠበቀው:: ስለዚህ አሁን ላይ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም ግን ማደግ የሚችል ነው::
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ሀገራችን ወደ አፍሪካ የምትልከው ከ17 እስከ 20 በመቶ አይበልጥም:: እነሱም ቢሆኑ 98 በመቶ የሚሆነው እዚሁ ጎረቤት ያሉ እነሱማሌ፣ ጅቢቲ፣ ሱዳን የመሳሰሉት ሀገራት ውስጥ ነው:: ወደ ሀገር ውስጥ የምናስገባውም ቢሆን አምስት በመቶ ብቻ ነው፤ ይኸውም ሞሮኮ ማዳበሪያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ አፍሪካ የተወሰነ ተሽከርካሪዎች ስለሚመጣ ነው፤ ስለዚህ የኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የምታደርገው የንግድ ልውውጥ ጥቂት የሚባል ነው:: በመሆኑም የወጪና ገቢ ምርት መዳረሻቸውን ማስፋት ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን፡- የፋይናንስ ተቋማት ያለ መዘመናቸው ለትስስሩ አለመጠናከር እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል:: በዚህ ረገድስ ምን ሊሠራ ይገባል ይላሉ?
አቶ ታገስ፡– ልክ ነው፤ እንደ አንድ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፤ በተለይ ለግብይት የምንለዋወጠው ገንዘብ የሰለጠኑት ሀገራትን ገንዘብ ነው:: ምንም እንኳን የውጭ ምንዛሬን ትመና የመሥራት ኃላፊነት የሴክሬያቱ ቢሆንም፤ አሁን ያለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመፍታትና ወጥነት እንዲኖረው እርስ በርስ ለመነገድ እንቅፋት እንዳይሆን ለማድረግ እየሠሩ ነው::
አፍሮኤግዚም ባንክ የተወሰነ በጀት ተቀማጭ አድርጎ የወጪ ምንዛሬ እጥረት ሲጋጥማቸው ከባንኩ ቋት እየተጠቀሙ የንግድ ልውውጥ የሚያደርጉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል:: በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይገመታል:: ይህም በተወሰነ ደረጃ ችግሩን ይቀርፋል ተብሎ ይታመናል:: ይሁንና በምዕራብውያን ገንዘብ እስከ ተጠቀምን ድረስ ተግዳሮት ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም::
አዲስ ዘመን፡- የአሜሪካ መንግሥት አሁን ላይ እያስተላለፈ ያለው ውሳኔ በዚህ ስምምነት ላይ የሚኖረው አሉታዊ ሚና ይኖረው ይሆን? የሚያመጣውን ተፅዕኖ በመከላከል ደረጃስ ምን ሊሠራ ይገባል?
አቶ ታገስ፡– ርግጥ አሜሪካም ሆነ ከሌሎች ሀገራት የሚያገኘውን ድጋፍ ጠብቆ በጀት የሚይዝ ሀገራት ይኖራሉ:: እዚያ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ሚና ይኖረዋል:: ግን ከቀጣናዊ ነፃ የንግድ ትስስሩ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ይኖረዋል ብዬ አላስብም:: እስከ አሁን ባለኝ ደረጃ ሴክሬታሪይቱን የሚያግዙ ፕሮጀክቶች እንዳሉ አውቃለሁ፤ ግን የአሜሪካ የልማት ድርጅት ቀጥተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል ብዬ አላምንም:: ይሁንና ከውጭ የሚደረግ ድጋፍ አንድ ቀን ሊቆም እንደሚችል አውቀን ራሳችንን ችለን እንድንቆም ይሄ እንደ ማንቂያ ደውል ነው:: እንደ ሀገርም ቢሆን የልማት ድጋፎች ለመስፈንጠሪያ እንጂ ለመኖሪያ አልመን መንቀሳቀስ የለብንም::
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ ከአባል ሀገራቱ ምን ይጠበቃል ይላሉ?
አቶ ታገስ፡- በነገራችን ላይ በአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ከ2020 ጀምሮ ነፃ የንግድ ቀጣና ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ነው ለውይይት ሲቀርብ ነበር:: ይህ የሆነበት ምክንያት ብዙ ድርድርና የመሪዎችን ውሳኔ የሚፈልጉ በመሆናቸው ነው:: በየስብሰባው ውሳኔዎች ሲተላለፉ ነበር:: አስቀድሜ እንዳልኩሽ ግን አብዛኛው በከፍተኛ አመራር ሊወሰኑ የሚገባቸው ጉዳዮች ተጠናቀዋል:: ሁሉም ሀገራት ወደ ትግበራ እንዲገቡ መሪዎች ጠንካራ አቅጣጫ መስጠት ይጠበቅባቸዋል::
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና እንደ ሀገር ለመጠቀም የንግዱ ማኅበረሰብ በእነዚህ ጉዳዮች ግንዛቤውን ማሳደግ ይጠበቃል:: ተወዳዳሪነቱን ሊያሳድግ በሚያስችል ዝግጁነት ሊኖረው ይገባል የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እወዳለሁ::
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ::
አቶ ታገስ፡- እኔም አመሰግናለሁ
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን 2017 ዓ.ም