
የዛሬን አያድርገውና በዓለማችን ሠራተኞች በፋብሪካ ውስጥ በነበረ ለጤና አስጊ በሆነ ምቹ ያልሆነ አካባቢ ውስጥ በቀን ከ10 እስከ 20 ሰዓታት ያለ እረፍት ለመሥራት ይገደዱ ነበር :: ዓለማችን የመሥራት መብትም ቢሆን የተከበረባት አልነበረችም:: ሠራተኞች ለሚሠሩት ሥራ ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያም አያገኙም::
በአጠቃላይ በየዓመቱ ሚያዝያ 23፣ ወይም በፈረንጆቹ ግንቦት አንድ የሚከበረው ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ቀንም መነሻው ይሄው የሠራተኞች የሥራ ጫና ጥያቄ የወለደው ነው:: ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ136ኛ እንዲሁም በሀገራችን ለ 50ኛ ጊዜ እያከበርን ያለነው ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ቀን (ሜይዴይ) ታሪካዊ አመጣጥም ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው መሰረታዊ የዓለም ሠራተኞች ጥያቄ ጋር ይሰናሰላል::
የጥያቄው ጅማሬ እአአ 1886 ነው:: ያኔ ሜይ 1/1886 ይሄን እና ሌሎች ጥያቄዎችን አንግበው በቺካጎ የሥራ ማቆም ርምጃ በማድረግ የተነሱበት የወቅቱ ሠራተኞች ምሬት ነው:: እነዚህም ናቸው ለእኛ ለዛሬዎቹ ሠራተኞች ብዙ ዋጋ ከፍለው የማያልፍ ታሪክ አኑረው ያለፉት::
የዓለም አቀፍ የሠራተኞች መብት ትግል በተጀመረባት እና አሁን ድረስ ለዓለም አቀፍ ሠራተኞች መብት እውቅና እንዳልሰጠች በሚነገርላት አሜሪካ፣ እንዲሁም ካናዳ የሚገኙ የሠራተኞች ማሕበራት፤ እ.ኤ.አ በ1884 የሥራ ማቆም አድማ ለማድረግ መወሰንን ተከትሎ በተደረገ እንቅስቃሴ በርካታ ሠራተኞች ላይ ከፍተኛ ግድያ ተፈጽሟል:: የአድማው መሪ ናቸው የተባሉትም በስቅላት እንዲቀጡ ተደርጓል::
የዓለም አቀፉ ሶሻሊስት ፓርቲ ምክር ቤት በ1889 በፓሪስ ባደረገው ስብሰባው፣የሥራ ሰዓት 8 ሰዓት ብቻ እንዲሆን የቀረበውን ሃሳብ ለመደገፍ ግንቦት 1 ቀን 1890 በመላው ዓለም ሰልፍ እንዲደረግ ዓወጀ:: ለዚህ ደግሞ የቀረቡ የሠራተኛውን ጥቅም የሚያስከብሩ ሃሳቦች ከአሠሪውና ከመንግሥትም ሳይቀር ተቃውሞ ማስከተላቸው በምክንያትነት ይጠቀሳሉ::
በችካጎ እ.ኤ.አ የሜይ 1/1886 የሥራ ማቆም ርምጃ በርካታ ሠራተኞች በፖሊሶች በመገደላቸውና “የዓድማ አነሳሽ” የተባሉ መሪዎች በስቅላት በመቀጣታቸው፣ ለተቃውሞ በወጡ ሰልፈኞች ላይ የደረሰው ጥቃት በመላው ዓለም ቁጣንና እንቢተኝነትን ቀሰቀሰ::
እ.ኤ.አ በ1889 ፓሪስ ላይ የተጠራው ሁለተኛው የሠራተኞች ኅብረት መሥራች ጉባዔ ሜይ 1 እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ1890 ጀምሮ የሠራተኞች ቀን “ሜይዴይ” በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ውሳኔ አስተላለፈ:: በትግል የጸናው የሠራተኛው የመብትና የጥቅም ጥያቄ ተቀባይነትን አግኝቶ የሥራ ሰዓት 8 ሰዓት እንዲሆን አድርጓል። ቅዳሜም የረፍት ቀን ሆኗል። ለሠራተኞች ምቹ የሥራ ሁኔታን መፍጠርን የተመለከቱ አስገዳጅ ሕጎች እንዲወጡም አስችሏል። ከግንቦት 1886 ጀምሮም ሠራተኞች በቀን እስከ 8 ስዓት ብቻ እንዲሰሩ ታወጀ::
የከፋውን የግፍ ግድያ ተከትሎ እ.ኤ.አ በ 1889 በፓሪስ በተካሄደው የሠራተኞች ሕብረት መሥራች ጉባኤ ሜይ 1 ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሠራተኞች ቀን ሆኖ እንዲከበር ውሳኔ የተላለፈበት ግንቦት አንድን፤ የትግሉ መጠናከር ያሰጋው የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ግሮቨር ክሊቭላንድ የሠራተኞች ቀን ተብሎ እንዲከበር ፈርሞ በሕግ አፅድቆታል:: በዚህና ሌሎችም ምክንያቶች በዓሉ የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ታሪካዊ መነሻም ነው::
ምክንያቱም ይሄንኑ ቀን መነሻ በማድረግ እ.ኤ.አ 1908 በሴቶች ላይ የሚደርስ ጭቆናና ግፍ ያንገሸገሻቸው 15 ሺህ የሚሆኑ ሴቶች፤ ከፍተኛ ጫና የነበረውን የሥራ ሰዓት ተቀንሶ ይሻሻልልን፤ የተሻለ ክፍያ እናግኝ፤ በምርጫ እንሳተፍ በሚል በኒዮርክ ከተማ ሰልፍ ወጥተው እንደነበር የተለያዩ የታሪክ ፀሐፊዎች ይናገራሉ::
የሴቶች ቀን ሃሳብ ያመነጨችው ክላራ ቴትኪን በዴንማርኳ ኮፐንሃገን እ.ኤ.አ በ1910 የሴት ሠራተኞች ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ነበር ሃሳቧን ያነሳችው:: በወቅቱ ከ17 ሀገራት የተውጣጡ 100 ሴቶች ተሳትፈውበት የነበረ ሲሆን፤ ሃሳቧም በጉባኤው ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት አግኝቷል:: እነዚህንና ሌሎች ምክንያቶችን አብነት በማድረግም ቀኑ በትክክልም የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ታሪካዊ መነሻ ስለመሆኑ ለመናገር የደፈርኩት::
ለዚህ ቀን ሴቶችም ወንዶችም ሠራተኞች ውድ የሆነውን ሕይወታቸውን እስከ መስጠት የዘለቀ ዋጋ ከፍለውበት ነው ያለፉት:: ዛሬ በማክበር ላይ የምንገኘው በዓሉ መከበር በጀመረበት ጊዜ በየዓለማቱ የሚገኙ ሠራተኞች በተለይም የፋብሪካ ሠራተኞች በወቅቱ በአሠሪዎቻቸው ይደርስባቸው የነበረውን ግፍና በደል እንዲሁም ጭቆና በመፋለም መብታቸውን ለማስከበር ያደርጉ የነበሩትን ይሄን እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የዘለቀ ትግል ወደኋላ መለስ ብለን የምናስታውስበትም ታሪካዊ በዓል ነው::
ያኔ በነዚያ በክንደ ብርቱ ሠራተኞች የተደረገው ይሄ ትግልና የተከፈለው መስዋዕትነት ለዛሬው የዓለም ሠራተኞች በዓል እና ለሴቶች ቀን መከበር ማይነጥፍ ጽኑ መሰረት ከመጣል ባሻገር ለሠራተኛው ማሕበረሰብ ብዙ ተጨባጭ ውጤቶች አስገኝቷል:: በርካታ ለውጦችንም ማምጣት ችሏል:: ሩቅ ሳንሄድ እዚሁ በሀገራችን ትግሉና የሕይወት መስዋዕትነቱ ለሴቷ ሠራተኛ በወሊድ ሰዓት በኩል ያመጣውን ለውጥ እና ተጨባጭ ውጤት ብናይ ከአንድም ሦስቴ የተሻሻለበትን መጥቀስ እንችላለን:: በንጉሰ ነገሥቱ አፄ ኃይለስላሴ እና በደርግ ዘመን ጊዜ ለሴቷ ሠራተኛ ይሰጣት የነበረው የወሊድ ፈቃድ አርባ ቀናት ነበር:: በኢሕአዴግ ወደ ሦስት ወር ወይም በቀናት ወደ ዘጠና ቀን፤ በዚህ ለውጥ ዓመታት ደግሞ ወደ አራት ወር ወይም ወደ 120 ቀን አድጎ ልናየው በቅተናል::
ሩቅ ሳንሄድ በለውጡ ማግስት በዓሉ በመዲናችን አዲስ አበባ ብቻ ሥራ ማግኘት የሰው ልጆች ሰብአዊ መብት ተደርጎ በመያዝ እየተሠራበት ይገኛል:: ይሄም የዓለም የሠራተኞች ቀን በብርቱ ከሚታገልለት አጀንዳ አንዱ እንደመሆኑ መጠን፤ በተለይም ለሴት ሠራተኞች በተለያየ መንገድ ሥራ እንዲፈጠር ያስገኘው ተጨባጭ ውጤት እጅግ ከፍተኛ ነው:: ለዚህም ነው አሁን ላይ በመዲናችን የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ፤ መብት በማስከበር ረገድ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበውም፤ እየመዘገበም ያለው::
ለአብነትም በተለያዩ ምክንያቶች ለከፍተኛ ማሕበራዊ ችግር ተጋልጠው ሕይወትን ለማስቀጠል ሲሉ በወሲብ ንግድ ለሚተዳደሩና ለጎዳና ኑሮ የተጋለጡ ሴቶችን ለመታደግ ”ለነገዋ የሴቶች ተሀድሶና ክሕሎት ማበልፀጊያ ማዕከል” ለአገልግሎት መብቃቱ ማሳያ ነው:: የመሥራት አቅም ኑሯቸው በኢኮኖሚ እጥረት ብቻ ሥራ ሠርተው ገቢ ማግኘት ላልቻሉ ሴቶች የተስማሚ ቴክኖሎጂ ድጋፍ በማድረግ የራሳቸው ሥራ ሠርተው ራሳቸውን ብሎም ቤተሰቦቻቸውን ማስተዳደር የሚችሉበት አቅም መፍጠር መቻሉም የዚሁም ከሰብዓዊነት ባሻገር ያለው የመሥራት መብትን የማክበር አንድ ርምጃ ነው::
በከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ሆነው ልጅ በመውለዳቸው ብቻ ዕለታዊ ሥራ ሠርተው ለመኖር የተቸገሩ እናቶች ልጆቻቸውን የሚያቆዩበት፤ ሙሉ ወጪያቸው በከተማ አስተዳደሩ የሚሸፈኑ፤ የሕፃናት የቀን ማቆያ ማዕከላት በማቋቋም ልጆቻቸው ያለምንም ስጋት በነፃ ተመግበው እንዲሁም የተሟላ ክብካቤ አግኝተው የሚውሉበት ዕድል መፈጠሩም ከዚሁ ቀን ጋር ተያይዞ፣ የሴት ሠራተኞችን መብትና ጥቅም የማስከበር ትግል ጋር ተያይዞ በሀገራችን የመጣ ውጤት ነው::
ከቀኑ መከበር ጋር በማያያዝ ያኔ ሜይ 1/1886 የተደረገው እና ከዚህም በኋላ ትግሉ ቀጥሎ ቀኑ ለሴቶች ቀን መነሻም በመሆኑ ከሴት ሠራተኞች ጋር ተያይዞ በሀገራችን ዛሬ ላይ በተለይ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ያመጣውን ውጤታማ ለውጥ ጠቃቅሰን እንጂ፤ እንደ ሀገርም እንደ ዓለምም ለሠራተኛው በርካታ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል:: ምክንያቱም፣ ከሠራተኛው ጥያቄና አብዮት በኋላ የቀጠለውና በተለይ በአውስትራሊያ ሠራተኞች ”ስምንት ሰዓት ለሥራ፤ ስምንት ሰዓት ለዕረፍት፤ ስምንት ሰዓት ለመኝታ‘ በሚል መፈክር የተቀጣጠለው የሠራተኛው ትግል ፍሬ አፍርቶ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ 1919 ጀምሮ ዕውቅና በማግኘት የተለያዩ የሠራተኞችን መብት እና ጥቅም የሚያስከብር ስምምነት እና ሕጎች እንዲፀድቁም የሚያደርግ ውጤት አስመዝግቧል::
የመሥራት መብት ሰብዓዊ መብት መሆኑም ተረጋግጦበታል:: ይሄው ጉዳይ በሀገራችን ሕገ መንግሥትም ሆነ፤ ኢትዮጵያ ተቀብላ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች በስፋት የሚገኝ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል:: ከዚሁ ጋር ተያይዞም መንግሥት አስፈላጊውን የሕግ እና መዋቅር በማዘጋጀት ሁኔታዎችን ምቹ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል:: ይሄ በሠራተኞች መብትና ጥቅም መከበር ረገድ እየታዩ ላሉ ዘርፈ ብዙ ውጤቶች መገኘትም ትልቅ አቅም ሆኗል::
በተለይ ደግሞ ለሴት ሠራተኞች (ለአብነት፣ ለመዲናችን ሴት ሠራተኖች) የመሥራት መብትን መሰረት በማድረግ መንግሥት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሊሆኑ የቻሉበት ምክንያትም ከዚሁ ጋር ይያያዛል:: በኢትዮጵያ ይህ ታሪካዊ ቀን የሠራተኞችን መብት ከማስከበርም በላይ የአሠሪና ሠራተኛን ጤናማ ግንኙነት ከማጠንከር አንፃር ጉልህ አስተዋጾ አድርጓል:: በመላ ሀገራችን በተለይም በፋብሪካዎች ምቹ የሥራ ሁኔታ በመፍጠር፤ በሥራ ላይ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ዕድገት በማፋጠንም ድርሻው ከፍተኛ ነው::
በዓሉን በመላው ዓለም የሚገኙ ቁጥራቸው የበዛ ሠራተኞች መሠረታዊ መብቶቻቸውን አስከብረውበታል:: የመብት ጥያቄዎቻቸው ምላሽ እንዲያገኙ አድርገውበታል:: ብዙ ድሎችንም ተጎናጽፈውበታል:: ከነዚህም መካከል በበዓላት እና በሕመም ለቀሩበት ክፍያ የማግኘት መብት በዋናነት ይጠቀሳል:: የተሻለ የሥራ ሰዓት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ደንብ መሻሻል፣ የተሻሻለ እና ጤናማ የሥራ ከባቢ መኖር፣ የሚሉት ደግሞ ከብዙዎቹ መካከል የሚጠቀሱ ጥቂት ማሳያዎች ናቸው::
በአሁኑ ወቅት ይሄን ቀን ከ160 በላይ የዓለም ሀገራት በተለያየ መልክ የሚያከብሩት ሲሆን ለአብነት በግሪክ፣ ፈረንሳይ፣ ጃፓን፣ ፓኪስታን፣ አሜሪካ እና እንግሊዝ በዓሉ የሠራተኞችን መብቶች መሻሻል በሚጠይቁ ሰላማዊ ሰልፎች ታጅቦ ይታሰባል:: ደቡብ አፍሪካ፣ ቻይና፣ ቱኒዚያ፣ ዚምባብዌ፣ ታንዛኒያ እና ሌሎች ሀገራት ደግሞ በሕዝባዊ በዓልነት ታስቦ ይውላል:: ኢትዮጵያም በዓሉን ከሚያከብሩ ሀገራት አንዷ ሆና ሃምሳ ዓመታትን ዘልቃለች::
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም