
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ኮርኔይ ሀገራቸው ከአሜሪካ ተገቢው አክብሮት እንደሚገባት ገልፀው በንግድ እና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ወደ ውይይት የሚገቡት “በራሳችን ፍላጎት መሠረት ነው” ብለዋል። ካርኔይ ዋሽንግተን ለጉብኝት የሚሄዱት የካናዳን ሉዓላዊነት ያከበረ “ኮስተር ያለ ንግግር የሚኖር ከሆነ” ብቻ እንደሆነ አስታውቀዋል።
እንደ ካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ ከሆነ ካርኔይ እና ትራምፕ በስልክ የተነጋገሩ ሲሆን በቅርቡ ተገናኝቶ ለመወያየት ተስማምተዋል። የጽሕፈት ቤቱ መግለጫ “ሁለቱ መሪዎች በካናዳ አስፈላጊነት ላይ እንዲሁም እንደ ነጻ እና ሉዓላዊ ሀገር ከዩኤስ ጋር በሁለቱ ሀገራት የጋራ ጥቅም ላይ አብሮ ለመሥራት ተስማምተዋል” ብሏል።
ትራምፕ የካናዳን ምርጫ ያሸነፉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ካርኔይን እንኳን ደስ አለዎት ማለታቸውም ተሰምቷል። ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ከተመረጡ በኋላ በተደጋጋሚ ካናዳን “51ኛዋ የአሜሪካ ግዛት” ስለማድረግ ሲናገሩ ተደምጠዋል። ማክሰኞ ዕለትም ከዋይት ሐውስ ተመሳሳይ አቋም ተንፀባርቋል። የዋይት ሐውስ ምክትል ቃል አቀባይ አና ኬሊ “ምርጫው ዶናልድ ትራምፕ ካናዳን የአሜሪካ 51ኛ የተወደደች ግዛት ማድረግ ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ የለም” ብለዋል።
ሰኞ ዕለት ካርኔይ እና ሊብራል ፓርቲያቸው የካናዳን ምርጫ በድል ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር የዶናልድ ትራምፕ ሃሳብ “ፈጽሞ በጭራሽ የሚሆን አይደለም” ብለዋል። “እውነቱን ለመናገር፣ ማንኛውም ሀገር እንኳ ቢሆን . . . ፓናማ ወይንም ግሪን ላንድ አልያም ሌላ ሀገር ቢሆን የሚሆን አይመስለኝም” ሲሉ ገልጸዋል።
ይሁን አንጂ ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ የምንደርስ ከሆነ እና ከአውሮፓ ኅብረት እና ዩኬ ጋር የንግድ አጋርነታችንን የምናጠናክር ከሆነ “ሁለታችንም የምናሸንፍበት መንገድ ይኖራል” ሲሉ ተናግረዋል። አሜሪካ ለካናዳ የንግድ ድርጅቶች ትልቋ ገበያቸው ናት። የካናዳ ምርቶች 75 በመቶ ማረፊያቸው የአሜሪካ ገበያ ሲሆን ካናዳ የአሜሪካ ከፍተኛ የድፍድፍ ነዳጅ አቅራቢ ሀገር ናት። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2024 አሜሪካ ከካናዳ ጋር ያላት የንግድ ጉድለት 45 ቢሊዮን ዶላር ተገምቷል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም