ሙያና ሙያተኞችን ያከበረ ሽልማት

ማንም ሰው ወደዚች ምድር የሚመጣው የሆነ ተልእኮ ለመፈፀም ነው:: ሁሉም ሰው ይህችን ዓለም የሚቀላቀለው በምክንያት ነው:: ይመስለናል እንጂ ማንም ሰው ያለ በቂ ምክንያት ወደ ምድር አይመጣም:: አንድ የተፈጠረበት አላማ ይኖረዋል:: የተፈጠረለትን አላማ ሊያሳካ ነው ወደዚች ምድር የመጣው:: ታዲያ የሰው ልጅ አንዴ ወደ ምድር ከመጣ ወዲህ ሰርቶ ለመኖርና በልቶ ለማደር በህይወት ጎዳና ይወጣል ይወርዳል፤ ይወድቃል ይነሳል::

ይህ ሁሉ ውጣ ውረድና ወድቆ መነሳት ታዲያ አንድም ሕይወትን ለማቆየት ሁለትም የተሻለ አግኝቶ ሕይወትን ለመቀየር እንደሆነ እሙን ነው:: በዚህ የሕይወት ውጣ ውረድ ጥቂት ትጉሃን ልፋት ድካማቸው ሰምሮ ጥረት ሙከራቸው አምሮ፤ የዘሩት ላብና እውቀት ፍሬ ሰጥቶ ለስኬት ይበቃሉ:: ከነዚህ ስኬታማ ትጉሃን ውስጥ የተወሰኑት የላባቸውን ፍሬ አፍሰው ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሚኖሩበት ማኅበረሰብ የሚያቋድሱ፣ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም መኖር ቤዛ የሚሆኑ፣ ለማኅበረሰባቸውና ለወገኖቻቸው ዋስና መከታ ብሎም ለብዙዎች ሕይወት መደላደል ምሳሌ ሆነው ይገኛሉ::

የስነ ልቦና ምሁሩ አብርሃም ማስሎው ለሰው ልጅ መሻትና ፍላጎት አምስት ደረጃዎች እንዳሉ ይገልፃል:: በአብረሃም ማስሎው need hierarchy ከስረኛው የመሰላሉ ደረጃ ስር ያሉ ሰዎች መድከም መልፋታቸው የራሳቸውን ስጋዊ ወይም ፊዚዮሎጂካል ፍላጎት ለማሟት ብቻ ነው:: ሁለተኛ፣ ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ያሉት ይታለፉና በአምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሰዎች አብርሃም ማስሎው ሰልፍ አክችዋላይዜሽን ወይም ከራስ ፍላጎት በላይ የደረሱ ሲል ይገልፃቸዋል::

እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎች እውቀታቸውን፣ ሀሳባቸውንና ጉልበታቸውን ከራሳቸው አሳልፈው ለማኅበረሰባቸው፣ ለወገኖቻቸውና ለሰው ልጅ ሁሉ አሳልፈው የሚሰጡ የሰው ልጅ ስብእና የመጨረሻ ጥግ ላይ የደረሱ የማኅበረሰብ ጌጥ የሰውነት አርማና ግርማ ናቸው:: ከሰፊው ማኅበረሰብ ተፈጥረው፣ ጥረውና ግረው፣ ለፍተውና ደክመው ለሚኖሩበት ማኅበረሰብ የሚበጅና የሚጠቅም ተግባር ለሚፈፅሙ በተለያዩ የሙያ መስኮች ውስጥ ለሚገኙ ጥቂት ስኬታማ ሰዎች ክብርና ምስጋና፣ ሽልማትና እውቅና መስጠት ደግሞ ከአንድ ማኅበራዊ ኃላፊነት ከሚሰማው ዜጋ የሚጠበቅ ሰብአዊ ግዴታ እንደሆነ ይታመናል::

በርግጥ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያውያን እንደሙያዊ አብርክቷቸው ባመጡት ስኬት ልክ ከመንግሥት፣ ከማኅበራት፣ ከሕዝብና ከተለያዩ ድርጅቶች እውቅናና ሽልማት ሲሰጣቸው ማየት የተለመደ ነገር ነው:: ከንጉሱ ሥርዓት ጀምሮ በሳይንሱ፣ በስፖርቱ፣ በኪነ ጥበቡ፣ በውትድርናው… ወዘተ በሌሎችም ዘርፎች ለሀገራቸው ትልቅ ሥራ የሠሩና ባለውለታ ለሆኑ ጀግኖች በተለያዩ ግዚያት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷል:: ይኼው የሀገር ባለውለታዎችንና ጀግኖችን የመሸለሙና እውቅና የመስጠቱ ተግባር አሁንም ቀጥሏል::

በኪነ ጥበቡ እንደነ ጉማ፣ በቢዝነሱ እንደ የጥራት ሽልማት ድርጅትና ሌሎችም በተለያዩ መስኮች በሙያቸው አበርክቶ ላላቸው ዜጎች ሽልማትና እውቅና የሚሰጡ የሽልማት ዝግጅቶችና ድርጅቶች ተቋቁመዋል:: በዚሁ ማኅበራዊ ኃላፊነት በመነሳሳት በኢትዮጵያ ተወልደው፤ ጥረውና ግረው ስኬታማ በመሆን ለሚኖሩበት ማኅበረሰብ ብሎም ለሕዝባቸው በጎ ተግባር ለፈፀሙ አርአያ ግለሰቦች እውቅናና ሽልማት ለመስጠት የስታር ዋይድ አዋርድ ሽልማት መስጠት ተጀምሯል::

ምንም እንኳን ከዚህ በፊት በተለያዩ ዘርፎች ለሀገር ባበረከቱት አስተዋፅኦ ልክ ሰዎች ይሸለሙ የነበረ ቢሆንም እውቅናና ሽልማቱ ሁሉንም የሙያ ዘርፎች ያማከለ ነበር ለማለት አያስደፍርም:: አብዛኞቹ የእውቅናና ሽልማት መርሃ ግብሮችም ትኩረታቸው በኪነ-ጥበብና ስፖርቱ ላይ ብቻ ያተኮሩ ነበሩ:: ይሁንና አሁን ላይ የዚህ ሽልማት መጀመር ከሞላ ጎደል በሁሉም ሙያ መስኮች ለሀገራቸው በልዩ ልዩ ሁኔታ አስተዋፅኦ ያበረከቱና ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም መትረፍ የቻሉ ሰዎችን ለመሸለምና እውቅና ለመሥጠት እድል የሚሰጥ እንደሆነ ተነግሮለታል::

ካለፈው ዓመት ጀምሮ መካሄድ የጀመረው ይህ የሽልማት መርሃ ግብር በተለያዩ የሙያ መስኮች ተሰማርተው ስኬታማ የሆኑና ከስኬታቸው ትሩፋት ለማኅበረሰባቸውና ለሕዝባቸው በጎ ነገር ላጎናፀፉ አሸናፊ ግለሰቦች የዕውቅናና የክብር ሽልማት ሰጥቷል:: ባለፈው ዓመት በወርሃ ሰኔ 2016 ዓ.ም መጨረሻ ላይ በተዘጋጀው የስታር ዋይድ አዋርድ ሽልማት መርሃ ግብር በርካታ ኢትዮጵያውያን ስኬታማ ግለሰቦች ሊመሰገኑና ሊወደሱበት የሚገባቸውን ይህን የእውቅናና የክብር ሽልማት አግኝተዋል::

የዚህ ሽልማት መርሃ ግብር ዋነኛ አላማ በተሰማሩበት የተለያዩ የሙያ መስኮች ስኬታማ በመሆን ከራሳቸው አልፈው ለማኅበረሰባቸውና ለመላው ሕዝባቸው ትሩፋት ያበረከቱ ግለሰቦችን ላደረጉት መልካም ተግባር ምስጋናና ክብር እንዲሁም እውቅና መስጠት ሲሆን፣ ከዚህ በተጓዳኝ ሌላው የማኅበረሰብ አካል በተለይ ህፃናትና ወጣቶች ከነዚህ ስኬታማ አውራዎች የሕይወት ተሞክሮ ቀስመው ስኬታማዎቹን አርአያና ምሳሌ አድርገው እነርሱም ለስኬትና ለጋራ ውጤት እንዲተጉና እንዲጥሩ ለማነሳሳት መሆኑ ተጠቁሟል::

ከስኬታማዎቹ አሸናፊዎች ትምህርት ወስዶ ለከፍተኛ ውጤትና ስኬት የሚጥር አምራች ትውልድን መፍጠር ደግሞ ለኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ እድገትና ብልፅግና የማያወላዳ መሰረት እንደሆነ ይታመናል:: በዚህ መነሻነት ዘንድሮም ከአምናው በተለየ ሁኔታና ሰፊ የሙያ መስኮችን ባካተተ መልኩ ሁለተኛውን የእውቅናና ሽልማት መርሃ ግብር በመጪው ግንቦት ወር እንደሚዘጋጅ ታውቋል:: በዚህ የእውቅናና ሽልማት መርሃ ግብር ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ታዋቂና ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ተገልጿል::

ይህ ሁለተኛው የስታር ዋይድ አዋርድ መርሃ ግብር በሁሉም መስኩ የተዋጣለት እንዲሆን ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝም የተጠቆመ ሲሆን፤ ተሸላሚዎችን ለመምረጥ ከተለያዩ የሙያ መስክ የተሰባሰቡ የዳኞች ኮሚቴ ተዋቅሮ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል። ለሽልማቱ የሚበቁት አሸናፊዎች ከዳኞቹ ኮሚቴ የውጤት አሰጣጥ በተጨማሪ ሰፊው ሕዝብ በሚሰጣቸው ድምፅ የሚወሰን እንደሆነም ተጠቅሷል::

ሰፊው ሕዝብ ለእጩዎች ድምፅ እንዲሰጥም ‹‹ስታር ዋይድ አዋርድ›› የሚል ድረ-ገፅ የተከፈተ ሲሆን በዚህ ድረ-ገፅ የእጩዎቹ ግለ ታሪክ ካከናወኑት ተግባር ጋር የሚቀርብ መሆኑም ተገልጿል:: መላው ሕዝብ በዚህ ድረ-ገፅና በሌሎች በሚከፈቱ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ለሚመርጣቸው እጩዎች ድምፅ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተነግሯል::

የሕዝብ የምርጫ ድምፅና የዳኞች ምርጫ ተደምሮ በሚገኘው ውጤት የ2017 ዓ.ም ስታር ዋይድ አዋርድ አሸናፊዎች ተለይተው በመጪው ግንቦት ወር ይህን የክብርና የእውቅና ሽልማት በደማቅ ሁኔታ በክብር እንደሚቀበሉ አዘጋጆቹ ተናግረዋል::

ለውድድር ቀርበው እውቅናና ሽልማት የሚያስገኙ አስራ ዘጠኝ የሙያ ዘርፎች መመረጣቸውንም አዘጋጆቹ ተናግረው፤ በነዚህ ሙያ ዘርፎች ከራሳቸው አልፈው ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው በሙያቸው ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረጉ ሰዎች እውቅናና ሽልማት የሚበረከትላቸው መሆኑን ጠቁመዋል:: ይህ የሽልማት መርሃግብር ከሚመለከተው የመንግሥት አካል እውቅና ያለውና ከአእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ማረጋገጫ ያለው መሆኑንም ገልፀዋል::

ከነዚህ የሙያ ውድድር መስኮች ውስጥ በአስመጪና ላኪነት፣ በባንክና ኢንሹራንስ፣ በአምራች፣ በሆቴልና ሪዞርት፣ በሪል እስቴት፣ በግንባታ፣ በትምህርት፣ በሥራ ፈጠራ/በሴት፣ በወንድና ወጣት/፣ በአገልግሎት ሰጪ ዘርፍ፣ በእድሜ ዘመን ጋዜጠኝነት፣ በበጎ አድራጎት፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ተፅእኖ ፈጣሪነት፣ በግብርና፣ ፋሽንና ዲዛይን፣ በመልካም ሥራ አመራርና በንግድ አመራር ዘርፎች ይገኙበታል::

ለአብነት በነጋዴዎች፣ ሥራ ፈጣሪዎችና በኢንቨስትመንት የሙያ ዘርፎች ስኬታማ የሆኑት የሚሸለሙት ሌሎችም ከእነርሱ ተምረው የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጥሩ ለማበረታታትና ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ ጠቀሜታ ስላለው ነው:: በባንክና ኢንሹራንስ ሙያ ዘርፍ ውጤታማ ሰዎች የሚሸለሙት ደግሞ በዋናነት የተጠቃሚዎችን የእርካታ ከፍታ ማሟላት በመቻላቸው ነው:: በዚህ ምድብ ውስጥ ሁሉም የግልና መንግሥት ባንኮችንና ኢንሹራንስ ተቋማትን ያካትታል::

በማኅበራዊ ሚዲያ ተፅእኖ ፈጣሪ ዘርፍ በዚህ ዘመን ለበርካቶች ተደራሽ የሆኑት ማኅበራዊ ሚዲያዎች ከማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ በጎም፤ በጎ ያልሆነም ይጫወታሉ:: ኃላፊነት ተሰምቷቸው ለማኅበራዊ ዋስትና በጎ ሚና የሚጫወቱ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን መሸለም ማለት ሁሉም ወገኖችና የአኗኗር ዘይቤያቸውን ለበጎ እንዲያውሉት ለማበረታታት ነው::

በኮንስትራክሽንና በግንባታ ዘርፍ ላይ ላሉት ደግሞ እንደገዢ ሃሳብ አንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚቀነቀን ዘመናዊ አስተሳሰብ አለ:: ግንባታ ከሌለ እድገት የለም:: ግንባታ ጨረስን ብለው የሚያወሩ የደጉ ሀገራት እንኳን ሁሌም ግንባታ ላይ ናቸው:: የሚገነቡት ቢያጡ የገነቡትን አፍርሰው አሻሽለው ይገነባሉ:: በዚያው ውስጥ የሰው ኃይል ለውጥ ስላለ ግንባታ ወሳኝ ነገር ተብሎ ነው የሚታሰበው:: ስለዚህ በኮንስትራክሽንና ግንባታ ዘርፍ ተሰማርተው ስኬታማ የሆኑ ሰዎች ሲሸለሙ ለሀገሪቱ ግንባታ፣ ለከተማና ለአካባቢው ለገጠሩም ውበት ያበረከቱትን መልካም ተግባርም ለማድነቅና እድገትንም ለማበረታታት ነው::

በቀልጣፋ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሙያ ዘርፍ በኢትዮጵያ ለሚከናወነው የመልካም አስተዳደርና የፀረ ሙስና ዘመቻ የተዋጣለት እንዲሆን ለማገዝና ሕዝቡ ከተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚደርስበት እንግልት ለመቀነስ ይህን ዘርፍ በሽልማት ማጉላት ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ እንዲካተት ተደርጓል::

በሆቴልና ሪዞርት ዘርፍ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ገቢ ስለሚያሳድግ፣ የመልካም ገፅታ ግንባታንም ስለሚያፋጥን ታስቦ ነው ይህ ዘርፍ በዚህ ውድድር መርሃ ግብር እንዲካተት የተደረገው:: በተመሳሳይ በትምህርትም ዘርፍ በማያጠራጥር ሁኔታ ሀገር የሚገነባው በትውልድ እንደመሆኑና ትውልድ የሚታነፀው ደግሞ በትምህርት በመሆኑ ይህ ዘርፍ በዚህ የሽልማት መርሃ ግብር በመካተቱ ትውልድን ለመገንባት የሚለፉ ስኬታማ ትምህርት ተቋማት እውቅናና ሽልማት ይሰጣቸዋል::

በሪል እስቴት ዘርፍም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚኖርበት ቤት ለኑሮና ለሕይወት አመቺ አይደለም:: ምቾት በሌለበት ቤት ውስጥ የሚኖረውን ሕዝብ ከዚህ ተላቆ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት እንዲኖረው በርካታ ሪል እስቴቶች እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ:: ከነዚህ ውስጥም ስኬታማዎቹን አወዳድረው እንደሚሸልሙ አዘጋጆቹ አሳውቀዋል::

በተመሳሳይ በበጎ አድራጊ ግለሰቦች ዘርፍም በሰብአዊ አድራጎታቸው ሊከበሩና ሊሸለሙ ይገባል ተብሏል:: በውድድር የተመረጡትም እውቅናና ሽልማት ይሰጣቸዋል:: በተቀሩት ዘርፎችም እንዲሁ በመካከላቸው ውድድር ተደርጎ ለሽልማት የሚበቁ ይሆናል::

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You