የዓለምን ዛፎች የሚያጠና አዲስ ሳተላይት ወደ ሕዋ ተላከ

የዓለምን 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ዛፎች የሚያጠና አዲስ ሳተላይት ወደ ሕዋ ተላከ:: ካርቦንን አምቀው የሚይዙ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸው። ይሁን እንጂ ከ1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን የሚበልጡት ዛፎች ምን ያህል ካርቦን አምቀው እንደያዙ ለመለካት እና ፈፅሞ ማወቅ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል። የአውሮፓ የጠፈር ኤጄንሲ ግን ይህ መጠበቅ እንዳበቃ ማክሰኞ ዕለት አስታውቋል። ኤጄንሲው በዓይነቱ የተለየ መንኮራኩር የማምጠቅ ሙከራው እንደተሳካም ገልጿል።

ልዩ የራዳር ሥርዓት የተገጠመለት ሳይተላይቱ ከደኖችን ጣራ ስር ምን እንዳለ ይፋ ያደርጋል ተብሏል። ተመራማሪዎች ካርቦንን አምቆ በመያዝ ደኖች ያላቸውን ጠቀሜታ እና የደን ጭፍጨፋ ተፅዕኖን በተሻለ መልኩ እንዲረዱት ያግዛል የሚል ተስፋም ተጥሎበታል። በደቡብ አሜሪካ የፈረንሳይ ግዛት አካል ፍሬንች ጎያና ከሚገኘው ኩሩ የጠፈር ማዕከል የተነሳው ሳተላይቱ ከሚያጠናቸው ደኖች አንዱ በሆነው አማዞን አናት ላይ መብረሩ ተነግሯል።

“የጠፈር ጃንጥላ” የሚል የቁልምጫ ስም የተሰጠው ሳተላይቱ መልዕክት የሚልክ 12 ሜትር የሚሸፍን ግዙፍ አንቴና ይዟል። አንቴናው ከደኖች አናት በታች የተደበቁ ቅርጫፎች እና ግንዶች ምን እንደያዙ በጥልቀት መመልከት እንደሚችል ተጠቁሟል። ሃሳቡን ወደ አውሮፓ ጠፈር ኤጄንሲ ያቀረቡት የምድር ምልከታ ብሔራዊ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ጆን ሬሜዲዎስ “እነዚህን ደኖች መጠየቅ እንፈልጋለን። ወደ ውስጥ በትክክል ማየት እንችላለን” ሲሉ ሳተላይቱ ከተላከ በኋላ ተናግረዋል።

ኃላፊው የአማዞን፣ የኮንጎ እና የኢንዶኔዥያ ደኖችን ለመጀመሪያ ጊዜ በትክክል ለማወቅ ትልቅ ስኬት ይሆናል ብለዋል።”በሕዋ ያሉ አብዛኞቹ ራዳሮች የበረዶ ግግሮችን ጥሩ ፎቶግራፎችን ማንሳት ይችላሉ። ነገር ግን ደኖችን ሲመለከቱ የደኑን የላይኛው ክፍል፣ ትናንሽ ቅርንጫፎችን፣ ቅጠሎችን ብቻ ያሳያሉ። ደኑ ውስጥ ዘልቀው አይገቡም” ሲሉ (ዶ/ር) ራልፍ ኮርዲ የተባሉ ተመራማሪ ገልፀዋል።

አንድ ነጥብ 2 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ሳተላይት እንደ ሲቲ ስካን የመሰለ ዘዴን በመጠቀም እየተመላለሰ ፎቶ በማዘጋጀት  ትንተና ይሰጣል። በአሁኑ ወቅት ተመራማሪዎች እንያንዳንዱን ዛፍ በመለካት እያቀራረቡ የሚሰጡት ትንተና “ትልቅ ችግር” እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሳተላይቱ በዩናይትድ ኪንግደም የተሠራ ሲሆን፤ ሮኬቱን ወደ ሕዋ ከመላክ ባለፈ ሳተላይቱን ማሰማራት ፈተናዎች ገጥመውት እንደነበር ተነግሯል።

ቡድኑ የመጀመሪያውን ካርታ በስድስት ወራት ውስጥ አዘጋጅቶ የመጨረስ ተስፋ የሰነቀ ሲሆን፤ እስከ ሚቀጥለው አምስት ዓመት ድረስ መረጃ እንደሚሰበስቡ ገልፀዋል። ካርታዎቹ ምን ያህል ካርቦን እንደታመቀ ከማሳየት ባለፈ በዛፎች መጨፍጨፍ ምክንያት ምን ያህል ካርቦን እንደሚጠፋም ያሳያሉ ተብሏል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You