የሞራል ትጥቅ

“ ‹ያላነበበ ሰው አንድ ጊዜ ብቻ እንደኖረ ይቆጠራል፤ ባንጻሩ ያነበበ ሰው አንድ ሺህ ጊዜ እንደኖረ ይቆጠራል› የሚለውን ብሂል በውል ሕይወቴ ላይ አለመተግበሬ ዛሬ ለደረሰብኝ አደጋ በቂ የሥነልቦና ዝግጅት ለማድረግ የዘገየሁ አልሆንም ነበር” ይላል እንግዳዬ ደምሴ አሰፋ። በተለምዶ አጠራሩ ጃንሜዳ ሰፈር ከአባቱ አቶ አሰፋ ሃይሉና ከእናቱ ከወይዘሮ ተዋበች ከበደ በወርሃ ሃምሌ 1973 ዓ.ም ተወለደ። ወላጅ እናቱ እንደቀበሌ ባሕር ዛፍ የተመዘዘው ሎጋ ቁመቱ አስግቷቸው የአብዮቱ እሳት ልጃቸውን እንዳይነጥቃቸው በመፍራት ፈጣሪያቸውን አብዝተው ይማጸኑ ነበር። እሱም ለአፈሳ ከሚያጋልጥ ቦታና ከአጓጉል ድርጊቶች ራሱን ይጠብቅ ነበር። በዚህም ሁኔታው ከሰቀቀን ቢድንም መሠረተ ትምህርት ማስተማሩ እንዳለ ሆኖ የማትሪክ ውጤት መቅረት ትዝታውን ሙሉ እንዳላደረገለት አጫወተኝ።

በቀበና አንደኛ ደረጃና በኮከበ ጽባህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው ደምሴ ሁለተኛ ደረጃ ማጠቃለያ ትምህርቱን ማለፍ ባለመቻሉ ቴክኒክና ሙያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ሰልጥኖ ለቤቱ የመጀመሪያ ልጅ በመሆኑ የእናቱን ማጄት ጎዶሎ ለመሙላት ከኑሮ ጋር ግብግብ ተያያዘ። ይህም አቢሲኒያ ባንክ እስከገባበት ድረስ ባቋራጭ ቶሎ ለመክበር የድብብቆሽ ንግድ ጋር አገጣጠመውና በጸጸት የሚያወሳቸው ጥቂት የማይባሉ የእድሜ ዘለላዎችና የጠለሹ የሕይወት ምዕራፎችን ፈጠረበት። ከቡና ንግድ ወደጣውላ ሥራ እንደተሻገረ መነሻው ፈር የጨበጠ አልነበረምና በመክሰሩ ከሄደበት ሚዛን ቴፒ ጓዙን ጠቅልሎ አዲስ አበባ ከተመ። ይሁን እንጂ ሕይወት አማራጭ መንገዷ እልፍ ነውና ከኩዮቹ ኋላ መቅረቱ በጸጸት ሲንጠው አቢሲኒያ ባንክ በአርካይቭ ባለሙያነት ቀጠረው።

ባንኩ ለሠራተኞቹ የሚሰጠውን የትምህርት እድል ተጠቅሞ ዲፕሎማውን ለመማር ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀለ። ሁን ያለው ሲሰምር እንደዚህ ነውና ውሎ ሳያድር እናት ባንክ ተወዳድሮ አለፈና በአካውንቲንግ የነበረውን ዲፕሎማ ወደ ዲግሪ አሳደገው።

የሥልጣን እርከኖችን በብቃት እየተሻገረ የተሻለ ደረጃ ላይ መቀመጥ ቢችልም በስኳር ህመም አማካኝነት የተሰናከለው ጤናው ከፍቶ ብርሃኑን ነጠቀውና ለአይነስውርነት ዳረገው። “የቀን ጨለማ ውጦ ከህልሜም ከእንጀራዬም ሲለየኝ ምድር የከዳችኝ ሰማይ የተደፋብኝ መሰለኝ” አለ የዛሬ እንግዳዬ ደምሴ ። በዚያን ጊዜ የነበረውን ሁነት አስታውሶ ሲያወጋኝ አይኖቹ እንባ አቅርረው አካሉ ሽምቅቅ እያለበት።

በመጥፎ ቅዠት ሰረገላነት ከሲኦል ከተማ ገብታ በዱር ገደሉ እየተንከራተተች፣ በረዶ በሠራ ውሃ እየተነከረች፣ በዕሳት እየተጠበሰች እንደምትሰቃይ ነፍስ ባለቤቱ መስከረም አዱኛም ያ ወቅት ሲነሳ ከሃሞት በመረረ ትዝታ ለማውሳት ይቅርና ምራቅ እንኳን መዋጥ ቸግሯት እየተናነቃት እንደ ዓባይ ወንዝ ዙሪያ ጥምጥም ስትሾር ቆይታ ከነገሬ ነጥብ ደረሰች።

“እንዴት ያለ ነገር እንዴት ያለው ጉድ፣

ባምጠው ባምጠው የማይወለድ።”

እንዲል አዝማሪው አንጀቷን አስራ የማምሻ ህመሟን አካፈለችኝ። “የምኞቴ ሰፈፍ የህልሜ መፍቻ ቁልፍ የሆነው ባለቤቴ ከኑሮ ተላምደን ከሕይወት ጋር ተፈቃቅደን ፍቅር የነገሰበት ሳቅ የሞላበት ጎጆ ማቆም በጀመርንበት ጊዜ ባላው ተዛንፎ ጣሪያው አዘነበለና ምሰሶው ወደቀ፤ ይሁን እንጂ ሞቷል ሲሉት እየኖረ ታሟል ሲሉት እየሻረ አሁን ላይ ከኮተቤ ዩኒቨርሲቲ በልዩ ፍላጎት (ስፔሻል ኒድ) ትምህርት ሁለተኛ ዲግሪውን ተምሮ ለማጠናቀቅ የመመረቂያ ጽሁፉን እየሠራ ይገኛል” አለች ጣምራ ጣምራ ይወርድ የነበረው እንባዋ የመከራ ሰንበሩን ሽሮ በፈገግታ ብሩህ ጸዳሏን እያቀለመ።

ደምሴ የትምህርት ዝግጅቱና የሥራ ዘርፉ ፋይናንስ ጋር እጅጉን የተቆራኘ ሆኖ እናት ባንክ ምንም እንኳን በሥራ ገበታው ላይ ሊያቆየው ባይችልም የሃዘኑ ማበሻ የስሙ ማስታወሻ እንዲሆነው በማሰብ ችግሩ ሲፈጠር በብድር የገዛውን ቤት ቀሪውን እዳ በመሰረዝ አጽናኑት። ይህ እንዳለ ይሁን እንጂ በአንድ ጀንበር የሕይወት አጋጣሚ ለትዳሩና ለቤተሰቦቹ መቅረዝ የነበረው ባለሥራ የዘመን ትግሉ፣ የኑሮ ፍትሉ ብሎም የሕይወት ማስጌጫው ህብር ቀለሙ ደበዘዘና ውሻ በቁልቁለት በማይጎትተው እንጀራ የተቀማጠለው ምሰሷቸው ርቦት ሲያዛጋ አጎቷ በረዷት ገንዘብ ላይ በብድር ጨመረችበትና መኪና ከገዛች በኋላ መንጃ ፍቃድ አውጥታ የሜትር ታክሲ ሥራ በመጀመር የዘመመ ጎጇቸውን ቀጥ አደረገችው። በማስከተል አዲስ ሕይወት የዓይነስውራን ማእከል በመውሰድ የተሰበረ ሞራሉን በማከም የባለቤቷን ሥነልቦና ዳግም ወለደችው፤ “ሴትን ያማከረ ቤቱን በሾህ አጠረ” ይሉት ብሂል ሃቅ ነውና።

ሁኔታውን ሰምቼ ለቃለመጠይቅ ቤታቸው በተገኘሁ ጊዜ ልጃቸው ዳናዊት ደምሴ የስምንተኛ ክፍል ተማሪና የ 13 ዓመት ልጅ ብትሆንም ስታነብለትና ከቴክኖሎጂ ጋር ልታላምደው ስትጥር አይቼ እድሜዋን የቀደመች የልጅ አዋቂ ስል ለማድነቅ ተገደድኩ። ችግሩ በተፈጠረበት አጋጣሚ የነበራትን ስሜት እንድታጋራኝ በጠየኳት ሰአት እንዲህ ነበር ያለችኝ።

“እኔ ከአባቴ ፈተና የተማርኩት በማንኛውም ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ አካል ጉዳተኝነት ሊፈጠር እንደሚችል ነው። በሁለቱም የተሳላችሁ ሰይፎች ሁኑ እንዲል ሃዋሪያው ጳውሎስ ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ ሳይሆን አስቀድመን ብርቱ የሥነልቦና ስንቅ ጠንካራ የሞራል ትጥቅ መያዝ እንደሚገባን ነው።”

አስከትዬ በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክስ በምክትል ፕሬዚዳንትና በልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑትን ተባባሪ ፕሮፌሰር (ዶ/ር) መስፍን ደጀኔን ስለደምሴ አዲሱ ማንነቱና ትምህርት አቀባበሉ ሃሳብ እንዲሰጡኝ ጠየኳቸው። ባጭር ጊዜ ሁኔታዎችን ተላምዶ ራሱን ለመቀየር ሲታትር እጅግ በጣም ደስ ተሰኝተው በዩኒቨርሲቲው ቀና ትብብር በክፍያ የጀመረውን ትምህርት ነጻ እንዳደረጉለት አጫወቱኝ።

“እያንዳንዱ ፈተና የሕይወት ሽግግር በመሆኑ ከዕዳው ይልቅ ምንዳውን እናስተውል” እንዲል ሶቅራጠስ ስንቸገር መላ እንፍጠር በማለት ጽሁፌን ቋጨሁ።

ሀብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You