እንደአገርና ሕዝብ በርካታ ችግሮች አሉብን። ያልተግባባንባቸውና የሚያጨቃጭቁን ብዙ ነገሮች መኖራቸውም አይካድም። በሰለጠነና በዴሞክራሲያዊ አግባብ ይፈታ እንጂ አለመግባባትም ሆነ ልዩነት ተፈጥሯዊ ነውና መኖሩ የሚደንቅ አይደለም።
ማህበራዊ ሳይንስ እንደሚለውም በአግባቡ ይስተናገዱ እንጂ ግጭትም ሆነ የሃሳብ ፍጭት የለውጥና የዕድገት መሠረቶች ናቸው። ሰው ማህበራዊ ፍጡር እንደመሆኑ በዕለት ተዕለት የኑሮ መስተጋብሩ ግጭቶች ይፈጠራሉ። በሀሳብ ውዝግብ ሰው ከራሱ ጋር የሚጋጭበት ጊዜም በርካታ ነው። በአጠቃላይ ሰውና ግጭት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ማለት ይቻላል።
ግጭት መጥፎ መልክ የሚይዘውና አላስፈላጊ የሚሆነው ጦርና ዱላ ሲያማዝዝ፣ ድንጋይ ሲያስነሳና የአካል የንብረትና የሕይወት ውድመትን ሲያስከትል ነው። ይህ ዓይነቱ ግጭት ያልሰለጠናና ፋይዳ ቢስ ነው። ልዩነቶችን በጥላቻ ማየትና መፈረጅ ይህንንም ተከትሎ ጉዳት ማድረስም በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም፤ አይኖረውምም። ከጥፋትና ከጸጸት በቀር የሚያስገኘው አንዳችም ፋይዳ የለምና።
አሁን አሁን በአገራችን የሚስተዋለው ግጭት አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። የሁለት ሰዎች ድንገተኛጸብ ዘርና ሃይማኖት እየተቆጠረለት ለብዙዎች ሕይወት መጥፋትና መፈናቀል ምክንያት እየሆነ ነው። ግጭት ተፈጥሮ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ሲያልፍ በሰብአዊነት ከመቆረቆር ይልቅ የሟቹ ብሔርና ሃይማኖት ምንድነው ብሎ ለብቀላና ለመጠፋፋት የሚነሳሳው በርክቷል።
ኃላፊነትን ባላገናዘበ መልኩ በግጭት ወቅት የተጎጂዎችን ብሔርና ሃይማኖት እየጠቀሱ የሚዘግቡ መገናኛ ብዙሃንም እየተስተዋሉ ነው። ጥፋትን በጥፋት ለመመለስ የሚደረገው ሩጫም ቀላል አይደለም። ከግጭት ያተረፈ እንደሌለ እየታወቀ አንዱ ጋር ሲበርድ ሌላ ቦታ እያገረሸ የንጹህ ወገኖቻችን ሕይወት ያለምክንያት ሲቀጠፍ መስማት የሰርክ ተግባር እየሆነ ነው። ጭር ሲል አልወድም በሚል ብሂል እሳት ከማብረድ ይልቅ ቤንዚን በማርከፍከፍ ከዜጎች ሰቆቃና ሞት ለማትረፍ የሚሰራ ኃይል እንዳለም የሰላም ሚኒስትሯ ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል የመስሪያ ቤታቸውን የዘጠኝ ወር ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ገልጸዋል።
ይሁንና በምንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብንሆን ተስፋ እንዳንቆርጥ የሚያደርገን ነገር ግን አልጠፋም። ባህር ማዶ ሳንሻገር ልዩነትን አቻችሎ ፍቅርን አጽንቶና መተባበርን አሰፍኖ በአንድነት ለመኖር የሚያስችለን ታላቅ እሴት በሕዝባችን ውስጥ አለ። ትኩረት ሰጥተን በአግባቡ ከተጠቀምንበት አንተም ተው አንተም በማለት ቂምን አሽሮ ግጭትን የሚያበርድ ኢትዮጵያዊ እሴት በእጃችን ይገኛል። ይህ እሴት ኢትዮጵያውያን ለብዙ ሺህ ዓመታት በፍቅርና በሰላም እንዲኖሩ ያደረገና አብሮነታችንን ያጸና ነው።
በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦቻችን ዘንድ ያሉ አገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች ከእኛ አልፎ ለሌላውም ዓለም የሚተርፉ ናቸው። የኢትዮጵያን ሕዝቦች ባህል ያጠኑ ምሁራን በጣም ከሚገረሙበት ነገር አንዱ በሕዝባችን ውስጥ ባለው የግጭት አፈታት ዘዴ መሆኑም ተደጋግሞ የተገለጸ ጉዳይ ነው። እነዚህ ባህላዊ የግጭት አፈታት መንገዶች የተፈጠረውን ችግር ከመፍታት አልፈው ቂም እንዳይቋጠርና ግጭቱ በድጋሚ እንዳይመለስ እስከማድረግ የደረሰ አቅምም አላቸው።
ይህን መሰል አኩሪ እሴት እያለንና ብዙ ሕዝባችን የዕውቀትን ማዕድ ተቃምሷል በሚባልበት በዚህ ወቅት ነገሮችን ከማብረድ ይልቅ እያጋጋሉ ዜጎችን ለሰቆቃ ለመዳረግ የሚንቀሳቀሱ አካላትን መመልከቱ ኧረ ምን ነክቶን ነው ያስብላል። በየትኛውም ቦታ አንዱ ሕዝብ ለሌላው ሕዝብ ጠላት ሆኖ አያውቅም።
በተለያዩ ቦታዎች በተደረጉ የሕዝብ ለሕዝብ መድረኮች ከሕዝብ የሚደመጠው ድምጽ እንደ ሕዝብ እርስ በእርስ ችግር የለብንም የችግሩ ምንጭ ጥቂት ፖለቲከኞችና የሕዝብ በሰላም መኖር ዕረፍት የማይሰጣቸው አካላት ናቸው የሚል ነው። በእኛ መካከል ጊዜያዊ ችር ቢፈጠር እንኳን ማንም ጣልቃ ካልገባብን ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ፈትትን እንዴት አብረን እንደምንኖር እናሳያችኋለን ነው የሚለው የሕዝቡ ድምጽ።
እውነት ነው! በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉትና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚቻለው ሕዝብን በማድመጥና ነገሩን ለሕዝቦች በመተው ነው። ፖለቲከኞችም ሆነ አክቲቪስቶች ዋነኛ ሥራቸው መሆን ያለበት ለአገርና ለሕዝብ ይበጃል የሚሉትን የፖለቲካ ፕሮግራም ነድፎ ለሕዝብ ማቅረብ ነው። ከዚህ ውጪ ለጊዜያዊና ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ሲባል ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨትና ጥላቻን በአጀንዳነት ማቅረብ ረብ የለሽ ከመሆኑም በላይ የህሊና ሰላምንም ይነሳል።
ስለሆነም የሕግ የበላይነትን የማስከበሩና ሰላምን የማረጋገጡ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ችግሮች እንዳይከሰቱም ሆነ ከተከሰቱ በኋላ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲፈቱ ሕዝብን በመፍትሄነት መጠቀሙ ትኩረት ይሰጠው እንላለን!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 3/2011