መንግሥት ከሰሞኑ የቀጣይ አመት የሆነውን የ2016 በጀት አመት በጀት እና የሚከውነውን እቅድ ሲገልፅ በጦርነቱ እና በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸውን መሠረት ልማት ወደነበረበት ለመመለስ እና ከዚሁ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን እንደሚከውን አሳውቋል:: በመሆኑም ይህን የተሻለ አቅም ዘላቂ ውጤት እንዲኖረው መንግሥት ከሚከውነው ተግባር በተጨማሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አስፈላጊ ነው የሚል ሃሳብ (እምነት) አለኝ::
እንደአጠቃላይ በመማር ማስተማር ሂደት ያለውን ክፍተት ለመሙላት ከፍ ያለ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ያስፈልጋል:: ቀደም ሲል በጦርነቱ ትልቅ የሆነ መዛባት የተፈጠረባቸው ሦስት ክልሎች አፋር፣ አማራ እና ትግራይ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸውን ላቋረጡ ተማሪዎች እና በዚሁ ምክንያት ለሥነ ልቦና ጉዳት ተዳርገው ውጤታቸው ለተበላሸ ወይም በተገቢው ልክ ላልሆነ ተማሪዎች ከአቻ ጓደኞቻቸው ወይም የዕድሜ እኩያዎቻቸው ጋር እንዳይራራቁ እና በተቻለ መጠን ተቀራርበው መጓዝ እንዲችሉ ከመደበኛ የመማር ማስተማር ሂደት በተጨማሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው::
ሂደቱን በተመለከተ በያዝነው ዓመት የክረምቱ ሁለት ወራት የመምህራን የእረፍት ጊዜ መሆን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሀገር አቀፍ ጥሪ በማድረግ መምህራንና ሌሎች በጎ ፍቃደኞችን (ለምሳሌ እንደ ሥነ ልቦና ባለሙያዎች) በማካተት እንደ መግባቢያ ቋንቋ ያሉ ክፍተቶች በትርጉም በሄድ ፎን (headphone system) በመጠቀም እንዲሁም ሁኔታዎች ሊፈቅዱ ከቻለ online ሂደቶችን በመጠቀም እና የሥነ ልቦና ጉዳቶችን በማከም ተማሪዎች ወድ ቀድሞ እና ጤናማ ወደሆነው የመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ እንዲመለሱ ማድረግ ይቻላል:: ከዚህም ባለፈ በዚህ ሂደት ውስጥ እውነተኛ የሆነ ወንድማማችነትን እና አብሮነትን በተግባር በመከወን ዘላቂ ለሆነው ኢትዮጵያዊነት እሳቤ ድርሻን መወጣት ያስችላል::
ሌላው የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች ነጥቦችን በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ቢካተቱ ዘላቂ በሆነ ትውልድን በመሥራት ሀገርን በመገንባት ሥራ ላይ ከፍ ያለ አዎንታዊ ውጤት ማምጣት ይቻላል:: ትምህርት ለአንድ ሀገር እድገት መሠረት በመሆን ቁልፍ ሚና የሚጫወት ነው:: ስለሆነም እያንዳንዱ ዜጋ የራሱን አበርክቶ መወጣት እንዲችል ትምህርት የመማር ዕድል ሊያገኝ ይገባል:: ይህ ተግባር ለአንድ ተቋም ወይም ትምህርት ሚኒስቴር ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ተሳትፎና አስተዋፅኦ ይፈልጋል::
1. የተማሪዎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት
2. የስፖርትና የሀገርን ዕወቅ ክበባት
3. የትምህርት ተቋማትን በተመለከተ (በተለይም የግሉን ተቋማት ማጠናከር)
4. ክበባት በአዲስ አስተሳሰቦች (idea share) የአስተሳሰብ ግንባታን ማድረግ ቀጣይ ዲፕሎማቶች የምንሠራበት ሂደት ነው::
5. የመምህራን ጊዜውን የዋጀ እና ሙያውን የሚመጥን አቅም ይመለከታል::
1. የተማሪዎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት
– በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን በቀጣይነት አንድ መስፈርት ማድረግ:: ይህ የሚሆነው ለመምህራንና ለተማሪዎችም ነው::
– ተማሪዎች በዕውቀት ችሎታቸው በሚመዘኑበት ሥርዓት ውስጥ (የብሐራዊ ፈተና መመዘኛ ሥርዓት ውስጥ) በማካተት የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን በሰዓትና በአገልግሎት ዓይነቱ መለኪያ በማድረግ በተማሪዎች ዘንድ አገልጋይነትና (nationalism) አስተሳሰብ እንዲሰርፅ ማድረግ::
ምሳሌ
ተማሪዎች በት/ቤታቸው ውስጥ የጨርቅ ከረጢት በማምረት የፕላስቲክ ከረጢቶችን (ፌስታል)
በመተካት የአካባቢ ተፈጥሮ ሥነ ምህዳርን ከአደጋና ስጋት በመጠበቅ ማስተላለፍ ይቻላል::
2. በዓመቱ መጨረሻ ላይ ወይም በትምህርት ዘመኑ ማብቂያ ለአንድ ወር ወይም ለሁለት ሳምንታት ተማሪዎች የፓርኮች ስካውት በመሆን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡበት፤
3. የምርት መሰብሰቢያ ወቅት ላይ የምርት ማሰባሰብ የበጎ ፍቃድ በመስጠት የሀገርን እና የወገንን አቅምና ድካም በመደገፍ የራስን አስተዋፅኦ የሚያደርጉበት፤
በጎ ፍቃደኝነትን ቋሚ ተግባር በማድረግ አገልጋይ የሆነ ትውልድ መፍጠር ነው::
2. የስፖርትና የሀገርን ዕወቅ ክበባት
ስፖርት፡- ትምህርት ቤት ትልቁና ዋናው ትውልድ መቅረጫ ተቋም ነው:: ዛሬ ላይ ነገ ኢትዮጵያን የሚወክሉና የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚቻለው በት/ቤት ውስጥ ነው::
ለዚህ እንደመነሻ እንዲሆን አረንጓዴ የተማሪ መታወቂያ ለሁሉም የኢትዮጵያ ተማሪዎች በሚል መርሐ ግብር ማለትም
ከ12 ዓመት የትምህርት ቤት ቆይታ ውስጥ በአማካይ አምስቱን በመውሰድና አስሩን የትምህርት ወራት በ100 ብር መዋጮ በማሰብ 10×10=100 ብር 100×5=500 ብር ማዋጣትና ቀጥታ በአካል የቀድሞ ትምህርት ቤታችን በመገኘት የምንተገብረው መርሐ ግብር ነው::
ዓላማው፡- የመጀመሪያው ጤናማና ዲሲፕሊን ያለው ትውልድ መሥራት ነው:: ዲሲፕሊን ሲባል ስፖርት መርህ ወይም የወንድማማችነት የመሰሉ መርህዎችን በተማሪዎች አስተሳሰብ ውስጥ ማስረፅ
– ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት
– የራስን የስፖርት ትጥቅና የመሳሰሉ ግብዓቶች የማምረትና የመጠቀም አቅምን መፍጠር ነው:: ባሉን የኢንዱስትሪ ዞኖች ውስጥ ያለንን የጥሬ ዕቃና የሰው ሀብት በሚገባ በመጠቀም ኢትዮጵያዊ የሆኑ የስፖርት ትጥቆችን ማምረት በጊዜ ሂደት ደግሞ ራስን እያሳደጉ በዓለም ገበያ ተፎካካሪ በመሆን የኢትዮጵያን ብራድ መፍጠር ነው::
– በዘላቂነት ሕዝባዊ የሆኑ ስፖርታዊ ተቋማትን በመገንባት ስፖርቱን ከመንግሥት ጠባቂነት ማላቀቅ ነው:: አንድ የስፖርት ክለብ ለአንድ ከተማ ጌጥ እንጂ ሸክም አይሆንም::
– ሁለተኛው ለዚህ ላበቁን እና መነሻችን ለሆኑት ት/ቤት፣ መምህራን፣ እንዲሁም ማኅበረሰብ አሁን ላይ ያለበትን የሕይወት እውነታ መረዳት ነው:: በዚህም ዛሬ ላይ ታናናሾቻችን የሚማሩበት ት/ቤት የጎደለውን አቅም መሠረተ ልማት እና ግብዓት በመረዳት ለማሟላት የሚያስችለንን ዕድል መፍጠር ነው::
ክበባት፡- የሀገርን ዕወቅ (ኢትዮጵያን እንወቅ) ክበባት
አንደኛው ተማሪዎች ትምህርታዊ ጉዞ የሚያደርጉበት ጉዞ ሲሆን፣ ሁለተኛው በዓመት መደበኛ የሆነ ሁለት ጊዜ የሚያደርጉት የጉብኝት መርሃ ግብር ነው:: ይኼኛው መርሃ ግብር እንደየ ዕድሜያቸው በመለየት በቅርብ ርቀት ሀገራቸውን የሚጎበኙበት ራስን የማወቅና እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ ሀብትን ማፍራት የምንችልበት ሂደት ነው::
3. የትምህርት ተቋማትን በተመለከተ (በተለይም የግሉን ተቋማት ማጠናከር)
በሀገራችን በአብዛኛው አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት የመንግሥት ተቋማት ቢሆኑ ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ የግል ተቋማት ቀላል የማይባል አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ::
የግል የትምህርት ተቋማት በአብዛኛው ማለት ይቻላል ከግለሰቦች ላይ ቤት በመከራየት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ናቸው:: ተቋማቱ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስለማይችሉ ይህ ሁኔታ መስተካከል አለበት:: ስለሆነም በጋራ በዚህ ሙያ ወይም ሥራ ውስጥ ያሉትን እና ቀደም ሲልም የሠሩትን በጋራ በማድረግ ወይም በጋራ ሆነው ተቋም የሚገነቡበት (share company) የሚመሠርቱበት ሂደት ያስፈልጋል:: በዚህም ሁኔታ የተበታተነውን አቅም በማሰባሰብና አንድ በማድረግ እንደ ተቋም የተሻለ አገልግሎት፣ ከፍ ያለ የሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም የተሻለ ተጠቃሚ ወይም ተገልጋይን መፍጠር ይቻላል::
በዚህ ሥራ (ተቋም ውስጥ) social share የሚባል ከ10%-15% የሼር ድርሻ ይኖራል:: ይህ ድርሻ (social share) ሙሉ በሙሉ የሚውለው በተለያዩ ምክንያቶች ልጆች መማር፣ መመገብ እንዲሁም አንድ ተማሪ እንደ ተማሪ የሚያስፈልጉትን ነገሮችን ማሟላት ለማይችሉ ተማሪዎች ለማሟላት የሚውል ድርሻ ወይም ሀብት ነው::
ምንም ይፈጠር ምንም ልጆች መማር በሚገባቸው ዕድሜ በችግር ምክንያት ከአቻ ጓደኞቻቸው ከትምህርት ገበታ መነጠል የለባቸውም::
ሼር ሆልደርስ ሲባል ከመነሻው ወይም ከመጀመሪያው ገንዘብን ብቻ ወይንም ሀብትን ብቻ ሳይሆን ትውልድን የመሥራት ኃላፊነትን ሼር ማድረግ አለባቸው::
4. ክበባት በአዲስ አስተሳሰቦች /idea share/ የአስተሳሰብ ግንባታን ማድረግ ቀጣይ ዲፕሎማቶች የምንሠራበት ሂደት ነው::
በሁሉም ትምህርት ቤቶች ክበባት እንዳሉ የሚታወቅ ነው:: በተጨማሪ ከጊዜው ጋር አብሮ ለመሄድ ቢካተቱ ያልኳቸው ክበባት ወይም የአስተሳሰብ ግንባታ ልምምድ የሚካሄድባቸው ክበባት፡-
1ኛ የኢትዮጵያ ልጆች ኢትዮጵያዊነታቸውን ወይም ራሳቸውን የሚገልፁት እንዴት ነው? ታሪካቸውንስ እንዴት ነው የሚረዱት? እንዴትስ ነው የሚያስረዱት?
2ኛ ቴክኖሎጂን ጨምሮ በሌላው ዓለም ያለውን አዳዲስ ሁነቶች የሚያዩበት የሚረዱበት የሚቀበሉበት እንዲሁም ከራሳቸው ጋር አስማምተው የሚሄዱበትን ሂደት ይመለከታል::
3ኛ የተፈጥሮ ሀብት (resource)፡- እንደ አጠቃላይ ሀገራችን ኢትየጵያ ያላት ሀብት ምንድነው? የተፈጥሮ ሀብትስ ሲባል ምን ምንን ያካትታል? አላቂ የማይተካ ሀብት ነው? ወይንስ? በሀገር ቤት ያለውን ብቻ ነው? ወይንስ ድንበር ተሻጋሪ ነው? እንዴት እየተጠቀምን እና እየጠበቅን ነው? የሚል አሁናዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ቀጣዩ ትውልድ ምን ማድረግ ይፈልጋል? እንዴት የበለጠ እሴት መጨመር ያስችለዋል? እንዴት መጠበቅና ማስተላለፍ አለበት?
ለምሳሌ፡- የመሬት ሀብትን ብናይ፡- የመሬት ሀብት አጠቃቀማችን እንዴት ነው? አዲስ አበባን ጨምሮ ትልልቅ ከተሞቻችን ላይ የመሬት ሀብትን እንዴት ነው የምንጠቀመው? አንድ ከተማ ለመሥራት ወይም ለመገንባት የሚያስፈልገውና ያለው የመሬት ሀብት ምን ያህል ነው? ምን ያህል ጥናት ይደረጋል? አስቀድሞ የሚደረግ ጥናት ነው? ወይንስ በክለሳ መልኩ የሚደረግ ነው?
ከተሞችን ሀብት አድርጎ በረጅም ዕቅድ መሥራት አይቻልም?
የመሬት አጠቃቀም፡- የመኖሪያ ቤት ቦታዎች የትኞቹ ናቸው? የኢንዱስትሪ ከተማ? የቱሪዝም መዳረሻ ከተማ? የትምህርት ተቋማት ከተማ? እነዚህና ይህንን የመሳሰሉ ዝርዝር መስፈርቶች ለይቶ ማወቅ አይቻልም?
ከተሞቻችን ማንን ይገልፃሉ? በርግጥም እኛን ይገልፃሉ? ከተማ ሲሠራ ለማነው የሚሠራው? የትኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ያማከለ ነው? ሁሉንም ያማከለ ነው?
አፍሪካ እጅግ ብዙ የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት ናት:: እነዚህ ሀብቶቿ የዜጎቿ ሕይወትና ጌጥ እንጂ የግጭትና ሞት ምክንያት መሆን የለባቸውም:: በአጠቃላይ በዚህ ሂደት ችግሮችን ማለፍና ማሸነፍ የሚችል በራሱ የሚተማመን ትውልድ የምንሠራበት ሂደት ነው::
4ኛ. ስፖርትና ኪነ ጥበብ፡- የስዕል፣ የግጥም እንዲሁም የስፖርት ክህሎትን በማዳበር ውድድሮች በት/ቤት ደረጃ ከዚያም ከፍ ሲል በሀገር አቀፍ ደረጃ የምናካሂድበት መርሃ ግብር ነው::
5. የመምህራን ጊዜውን የዋጀ እና ሙያውን የሚመጥን አቅም ይመለከታል
መምህራን ተከታታይና ቀጣይነት ያለው ትምህርት እንዲሁም አቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ተጠቃሚ የሚሆኑበት መርሃ ግብር ነው::
መምህራን ሁሌም በዕወቀት ተፎካክረው አሸናፊ ትውልድ የሚፈጥሩ መሆን አለባቸው::
መምህሩ ራሱ የሚታደስበት እና በተለያየ ምክንያት ከተስፋ መቁረጥና አቅም ማጣት ወጥቶ ወደ ሙሉና ብቁ ማንነት እንዲመለስ ማድረግ ነው::
መምህርነት በርግጥም የሙያዎች ሁሉ አባት መሆኑን በተግባር ማረጋገጥ::
ምሳሌ፡- አንድ የስፖርት መምህር የኒውትሪሽን ትምህርት ቢማር አሊያም አፕግሬድ ቢያደርግ ከመምህርነቱ ባሻገር በስፖርት ከለብ የአሰልጣኝነት ሙያ አክሎ መሥራት ይችላል:: በተሻለ የሥራ ባህል እና በበለጠ የማገልገል ስሜት ዕድሜውንና እውቀቱን ያለገደብ በመጠቀም መጥቀም ይችላል::
- ሰፊና ተደራሽነት ያለው የመገናኛ ብዙኃን ጣቢያዎች ላይ የተወሰነ የአየር ሰዓት በመጠቀም መምህራን በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ያጋጠማቸውን አዳዲስ ሃሳቦች የሚለዋወጡበትና የሚነጋገሩበት ዕድል መፍጠር ያስፈልጋል:: በዚህም የመረጃና የተግባር ሂደት ክፍተቶችን መቀነስ ያስችላል:: ለዛሬ አበቃሁ አመሰግናለሁ::
ሳባ ከአዲስ አበባ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ.ም