የሥራ ባሕላችንን

አንድ ርምጃ ለማሻገር

 ባደጉት ሀገራት በቀን ለ24 ሰዓት በሳምንት ሰባቱንም ቀናት ይሠራል፡፡ የደከመው ሊያርፍ ወደ ቤቱ ሲሄድ ያረፈው እየተካው እድገታቸው ቀጥሏል፡፡ እኛ ጋ የሥራ ሰዓት ስምንት ሰዓት ነው ለሚለው አባባል አጽንኦት መስጠትን መርጠናል፡፡ ያችው የሥራ ሰዓት ተብላ የተበየነችውን ስምንት ሰዓትም በተገቢው ቢሠራበት መልካም ነበር፡፡

እኔን ጨምሮ መሰሎቼ ገና ወደ ሥራ ቦታችን ከመድረሳችን ለሻይ ቡና አለፍ ሲል ለቁርስ ከመከረኛው ስምንት ሰዓት ላይ እናነሳለን፡፡ ምንም እንኳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለውጥ ቢኖርም በሀገራችን አብዛኛውን የሰው ኃይል የሚያሠራው ግብርናም በዋናነት የሚከናወነው በክረምት የዝናብ መኖርን ተከትሎ ነው፡፡

በከተማም በአብዛኛው የግልም ሆነ የመንግሥት ተቋማት የሥራ መግቢያ ጠዋት ከሁለት እስከ ሦስት ሰዓት ነው፡፡ ይህን ተከትሎ ጠዋትና ማታ የትራፊክ ጭንቅንቁ የእግረኛ ግፊያው የጉድ ነው፡፡ ምዕራባውያን «ረሽ ሀወር» የሚሉት ማለት ነው፡፡

ሁሉም እኩል ከቤቱ ወደ ሥራው ማታም በተመሳሳይ ከሥራ ወደ ቤት ስለሚሄድ መንገዱ ተቆላልፎ ቁጭ ይላል፡፡ በየቦታው ያለው የትራፊክ መጨናነቅ ደረስኩ አልደረስኩ ትርፉ ጭንቀት ብቻ ነው፡፡ ይሄ ሰዓት ተማሪዎችም እውቀት ለመሸመት በማሰብ መንገድ ላይ የሚሆኑበት በመሆኑ ችግሩን ያብሰዋል፡፡ ሁሉም በተመሳሳይ ሰዓት መውጣቱ የትራንስፖርት እጥረት ስለሚያስከትል፤ ትራንስፖርት ጥበቃ ረዥም ደቂቃ ባስ ሲልም ሰዓታትን መጠበቅ የግድ ይላል፡፡

ይሄ የመንገድ መዘጋጋቱም ሆነ መጨናነቅ ተመልሶ አስራ አንድ ሰዓት ላይም ይከሰታል፡፡ ሁሉም ባይባልም አብዛኛው የሥራ ቦታ የሻይ ሰዓትም ሆነ የምሳ መመገቢያው ተመሳሳይ ነው፡፡ በዚህም መከረኛው ሰልፍ በመመገቢያ ቦታዎች ላይም ይስተዋላል፡፡ አብዛኛው ቦታ የሥራ ሰዓቱና የእረፍት ሰዓቱ ተመሳሳይ በመሆኑ ጉዳይ የገጠመው የአንድ ተቋም ባልደረባ በእረፍት ሰዓቱ በተመሳሳይ ጉዳይ የሚያስፈጽምበት ቦታም የእረፍት ሰዓት ስለሚሆን ጉዳዩን ለመከወን ይቸገራል፡፡ በዚህ ረገድ ባንኮች መደበኛ የእረፍት ሰዓት ተብለው የተለዩ ሰዓታት ላይ የሚያስተናግዱ ባለሙያዎች አነስተኛ ስለሚሆኑ ጭንቅንቅ ቢኖርም አገልግሎት መስጠታቸው በራሱ ጥሩ ነው፡፡

በአብዛኛው ቢሮ ያለውን የሰው ኃይል ቁጥር ከግምት ውስጥ በማስገባት የእረፍት ሰዓታቸውን በፈረቃ ከማድረግ ይልቅ ሁሉም እኩል የምሳ ብሎም የሻይ ሰዓቱ ይሆናል፡፡ በዚህም ጉዳይ ገጥሞት ከምሳ በፊት ወደ አንድ ተቋም የደረሰ ባለጉዳይ የምሳ ሰዓት አልቆ ሠራተኞች እስኪመለሱ ለመጠበቅ ይገደዳል፡፡

ጠዋት ለሥራ ግር ብሎ የወጣው ሰው በየሥራ ቦታው ስለሚውል መንገዱ ነፃ ይሆናል፡፡ ጠዋት ሲለመኑ የነበሩ ትራንስፖርት ሰጪዎች በተራቸው ትራንስፖርት ተጠቃሚን ሲለምኑ ይውላሉ፡፡ የመዲናችን የትራንስፖርት ኡደት ይህ ነው፤ ጠዋትና ማታ ትራንስፖርት ፈላጊው ትራንስፖርት ሰጪዎችን ይለምናል፤ ቀን እነሱ በተራቸው ይለምናሉ፡፡

ይህን የትራንስፖርት ጭንቅንቁን ሽሽት ማምሸትን የመረጠ፣ አምሽቶ የሚሠራ፣ እንዲሁም በማታ የተለያዩ ጉዳዮች የገጠመው ሰው ቢንቀሳቀስ ከተሞቻችን ጭር ያሉ ናቸው፡፡ በርካታ የትራንስፖርት ተጠቃሚ ስለሌለ አገልግሎት ሰጪውም እምብዛም ነው፡፡ ይህን ለማካካስ ይመስላል፤ በማታ ሰላማዊ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች የሚጠይቁት ክፍያ ከቀኑ የአገልግሎት ክፍያቸው በላይ ነው፡፡

እኛ ጋር ኑሮ ተወደደ፣ ቤት ኪራይ ጨመረ ብለን ማልቀስ ባናቆምም አሁንም አብዛኛው ሥራችን በቀን እንደተገደበ ቀጥሏል፡፡ በፎርብስ እ.አ.አ በ2023 የቢሊየነሮች ዝርዝር የዓለማችን ሁለተኛው ሀብታም በሚል የተቀመጠው ኤለን መስክ መታወቂያው የግሉ ባደረገው የቲውተር አካውንቱ ላይ ከሚሰነዝረው አነጋጋሪ ሀሳብ በተጓዳኝ በቀን 16 ሰዓት መሥራቱ ሌላኛው መለያው ነው፡፡

በሳምንት ሰባቱንም ቀናት ለ16 ሰዓታት ይሠራል፡፡ የኤለን መስክንና የመሰሎቹን ልምድ የወሰዱ የተወሰኑ

 የሀገራችን ሥራ ፈጣሪዎች ሊተገብሩት ቢጥሩም ለብቻቸው ለመሥራትና ለማሰላሰል ካልሆነ በስተቀር አብዛኛው ሠራተኛ በማታ ለመሥራት ፈቃደኛ አይደለም፤ ወይም ለሚሰጠው አገልግሎት ከፍተኛ ክፍያን ይሻል፡፡

የዚህ ምክንያቱ የሥራ ባሕሉ ካለመለመዱም በተጓዳኝ ለመሥራት የሚያስቡትም ትራንስፖርት አያገኙም፤ ቢያገኙም የሚጠየቀው ክፍያም ተመጣጣኝ አይደለም፡፡ በተጨማሪም የአብዛኛው ሰው ዕረፍት ስለሆነ አገልግሎት ፈላጊው ቁጥር አነስተኛ ሲሆን፤ ሀገር ምድሩ ጭር ያለ ስለሚሆን በመንገድ ላይ ለመንቀሳቀስም ሆነ የአገልግሎት መስጫ ቦታቸውን ክፍት አድርጎ አገልግሎት ለመስጠት ደህንነት አይሰማም፡፡

የስምንት ሰዓትን አዙሪት የተሻገሩ አየር መንገድና መሰል ድርጅቶቻችን ከአህጉርም አልፈው በዓለም በሚሰጡት የላቀ አገልግሎት አኩርተውናል፡፡ ይህም ካሰብንበት እንደምንችል ማሳያ ነው፡፡ በቀን ስምንት ሰዓት ሠርተን ለመድረስ ካሰብንበት መድረስ እንደማንችል ከተገነዘብን ከርመናል፡፡ በዚህም ለሀገሪቱ መጻኢ ዕድል ዋና ተብለው በተለዩ እንደ ህዳሴ ግድብና መሰል ፕሮጀክቶችና አምራች ኢንዱስትሪዎች የ24 ሰዓት ሥራ ተጀምሯል፡፡ ችግሩ እስካሁን የ24 ሰዓት ሩጫው በተወሰኑ ፕሮጀክቶች ተገድቦ መቆየቱ ነው፡፡

ይህ ታሪክ ሊቀየር ዝግጅት ተጀምሯል፡፡ በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ለአገልግሎት ፈላጊዎች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በማሰብ በፈረቃ ሥራ ሊጀመር መሆኑ ተሰምቷል፡፡ የመንግሥት የበላይ አካላት ካመኑበት ማሳካት እንደሚቻል በቅርቡ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታስቦ 566 ችግኝ መተከሉ ማሳያ ነው፡፡

የፈረቃ ሥራው በከተማ አስተዳደሩ ሲጀመር ሌሎች የግልም ሆኑ የመንግሥት ድርጅቶች ፈለጉን እንደሚከተሉ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ያኔ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ይሳለጣል፤ ከተማ አስተዳደሩ ለኪራይ የሚያወጣውን ብር በመቀነስ በተወሰነ ቦታ በርካታ አገልግሎት መስጠት ይቻላል፡፡

ያኔ ማታ ጭር የሚለው መንገድ በሰዎችና በተሽከርካሪዎች መሞላት ይጀምራል፡፡ እኛም እንደሌላው ብር አይበቃንም ብለን ከማማረር ተላቀን ተጨማሪ ገቢ እንዴት እናግኝ ለሚለው ዓይን ያበራል፡፡ ከስምንት ሰዓት የተሻገረ ለመሥራት ከአንድ ሥራ በላይ ተጨማሪ ሥራ ለመሥራት የግድ ከሀገራችን መውጣት አይጠበቅብንምና ትንሽ ሠርተን ብዙ የማረፍ የሥራ ባሕላችንን በቅርቡ እንደሚቀየር ተስፋ አለኝ፡፡

 ከትዝታ ማስታወሻ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *