6ኛው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ዛሬ ይጠናቀቃል

ባለፉት አስር ቀናት በጅማ ሲካሄድ የቆየው 6ኛው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ዛሬ ፍፃሜ ያገኛል። ሁሉንም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በ26 የስፖርት አይነት ሲያፎካክር የቆየው ይህ ትልቅ ሀገር አቀፍ የስፖርት መድረክ ባለፉት በርካታ ቀናት የፍፃሜ ፉክክሮችን አስተናግዷል። ትናንትና ከትናንት በስቲያም በተለያዩ ውድድሮች የፍፃሜ ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን ዛሬ በሚደረጉ ጥቂት የፍፃሜ ፍልሚያዎች የሚቋጭ ይሆናል።

ዛሬ ረፋድ 5:00 ሰዓት ላይ በወንዶች እግር ኳስ ፍፃሜ ደቡብ ኢትዮጵያ ከኦሮሚያ፣ በተመሳሳይ በሴቶች እግር ኳስ ፍፃሜም ሁለቱ ክልሎች 9:00 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል።

ከፍተኛ ፉክክር የታየበት እና ከፍተኛ የተመልካች ቁጥር የተመዘገበበት የ6ኛው መላው ኢትዮጵያ ጨዋታ የቦክስ ስፖርት ውድድር ትናንት ከተጠናቀቁት ዋነኛው ነው። በቦክስ ስፖርት አዲስ አበባ በሁለቱም ፆታ አጠቃላይ አሸናፊ የሆነበትን ውጤት አስመዝግቧል። አዲስ አበባ በወንዶች 4 ወርቅ፣ 1 ብር እና 4 የነሐስ ሜዳልያ በማግኘት በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ፣ ኦሮሚያ 3 ወርቅ፣ 2 ብር እና 2 ነሐስ በማግኘት 2ኛ ደረጃ ይዟል። አማራ 1 ወርቅ፣ 5 ብር እና 3 ነሐስ በማምጣት 3ኛ እንዲሁም ድሬዳዋ 1 ወርቅ፣ 1 ብር እና 5 ነሐሴ 4ኛ፤ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ 1 ወርቅ፣ 1 ብር 1 እና 1 ነሐስ በማስመዝገብ የደረጃ ሰንጠረዡ ላይ 5ኛ ሲቀመጥ ደቡብ ኢትዮጵያ በ2 ነሐስ 6ኛ ሆኗል። ጋምቤላ በ 1 ነሐስ፣ ቤኒሻንጉል 1 ነሐስ በወንዶች ቦክስ ስፖርት ሜዳሊያ ያገኙ ክልሎች ናቸው። በሴቶች ደግሞ አዲስ አበባ 3 ወርቅ፣ 2 ብር እና 1 ነሐስ በማስመዝገብ 1ኛ ሲሆን፣ ኦሮሚያ 3 ወርቅ እና 2 ብር በማምጣት 2ኛ ደረጃ ሲይዝ፣ አማራ በ 1 ብር በ4 ነሐስ ሶስተኛ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ በተመሳሳይ 1 ብር እና 4 ነሐስ እኩል ደረጃን ይዟል። ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ በ 2 ነሐስ ውድድሩን ጨርሷል።

ትናንት ፍፃሜ ካገኙት ስፖርቶች መካከል የቴኒስ ስፖርት ይገኝበታል። በጥንድ ድብልቅ ፆታ ውድድር አዲስ አበባ የወርቅና የነሐስ ተሸላሚ ሲሆን ኦሮሚያ የብር ሜዳሊያ አግኝቷል። በጥንድ ወንዶች ፉክክርም አዲስ አበባ የወርቅና የነሐስ ተሸላሚ ሲሆን አማራ የብር ሜዳሊያ አስመዝግቧል። በጥንድ ሴቶች አዲስ አበባ በተመሳሳይ የወርቅና የነሐስ፣ ኦሮሚያ የብር ሜዳሊያ አስመዝግቧል። በነጠላ ወንዶች አዲስ አበባ ወርቅ ፣ አማራ ብር ፣ አዲስ አበባ ነሐስ ሜዳሊያ ሲያገኙ በሴቶች ነጠላ በተመሳሳይ አዲስ አበባ ወርቅና ነሐስ ሲያገኝ ኦሮሚያ ብር ተሻላሚ ሆኗል።

መስማት የተሳናቸው ስፖርተኞች ውድድርም ብርቱ ፉክክር የታበት ጨዋታ ሆኖ ፍፃሜውን አግኝቷል። በዚህም መሠረት ኦሮሚያ ክልል በ10 ወርቅ፣ በ11 ብር እና በ6 የነሐስ ሜዳልያ ውድድሩን በበላይነት አጠናቋል።

የአማራ ክልል ጠንካራ ቡድን ይዞ የቀረበ ሲሆን 3 ወርቅ ፣ በ 3 የብር እና በ7 የነሐስ ሜዳልያ በማግኘት ውድድሩን ፈፅሟል። አዲስ አበባ ደግሞ በ 3 ወርቅ ፣ በ 3 ብር እና በ 2 የነሐስ ሜዳልያ 3ኛ በመሆን ያጠናቀቀ ሲሆን ሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ፣ ድሬዳዋ እና ቤኒሻንጉል ክልሎች በቅደም ተከተል ከ4ኛ እስከ 8ኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

የውድድሩን መገባደድ ተከትሎ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ፣ የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታ በስፖርታዊ ጨዋነት የተሞላ እና ዓላማውን እያሳካ መሆኑን ተናግረዋል። በየስፖርት አይነቱም በተወዳዳሪ ስፖርተኞች መካከል ጥሩ ጨዋታ ለማየት እንደቻሉም ገለፀዋል። በመላው ኢትዮጵያ ጨዋታ ከሁሉም አካባቢ የተውጣጡ ስፖርትኞች በዚህ ውድድር መታየታቸው ሀገር አቀፍ ፌዴሬሽኖች እስከታችኛው አደረጃጀት ድረስ ወርደው እንዲሠሩ ያሳየ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል።

ሀገር አቀፍ ፌዴሬሽኖች በስልጠናና የስፖርት ቁሶች ድጋፍ በማድረግ እስከታችኛው የስፖርት መዋቅር ማገዝ እንዳለባቸው ያሳሰቡት ሚኒስትር ዴኤታው ቅንጅታዊ አሠራርን ማዘመን እንደሚገባም አሳስበዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You