
ሸገር ከተማ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን ለውጥ ለማምጣት እየሠራች ነው። በሥራ ፈጠራ፣ በአዳዲስ ንግዶች እና በልዩ ልዩ ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች። ከተማዋ ወጣቶች እና ሴቶች ሥራ እንዲያገኙ የሚያስችል የኢንቨስትመንት አማራጮችንም እያገኘች ነው። ይሁንና አሁንም ድረስ በትኩረት ሊሠራባቸው የሚገቡ የውሃ እጥረት፣ መኖሪያ ቤት እና መንገድ የመሳሰሉ አንዳንድ ተግዳሮቶች እንዳሉባት መካድ አይቻልም።
የከተማዋ አስተዳደር እና አመራሮች እነዚህን ተግዳሮቶች ለማስተካከል እና አሁን እየተመዘገበ ካለው በተሻለ ውጤት ለማምጣት ስትራቴጂ ቀይሰው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ‹‹ሁሉም በትጋት ከቀጠለ ሸገር በኢትዮጵያ ጠንካራና ውብ ከተማ መሆን ትችላለች›› የሚሉት የሸገር ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ነብዩ ራጋ ናቸው።
ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ ነብዩ፤ የኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማና አስተዳደር አዲስ የተመሰረተች መሆኗን እና ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ብቻ ማሳለፏን አስታውሰው፤ ምስረታዋ እና ያስቆጠረችው እድሜ ትንሽ ቢሆንም፤ ከተማዋ ትልቅ እድገት እያስመዘገበች መሆኗን ተናግረዋል። ከተማዋ እያስመዘገበች ባለው ዕድገትም ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እየሆነ ሲሆን፤ ይህን የተጠቃሚነት ጉዞ በዓላማ ለማስቀጠል ቁርጠኞች እንደሆኑ አስረድተዋል።
በከተማዋ ካሉ ህብረተሰቡን ሊጠቅሙ ከሚችሉ ዋነኛ ዘርፎች መካከል አንዱ ኢንቨስትመንት ነው። በዚህ ዘርፍ ብዙ ፈተናዎች በመጋፈጥ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ሥራዎች ተጀምረዋል ይላሉ።
እንደእሳቸው ገለፃ፤ የሸገር ከተማ ከመቋቋሟ በፊት፣ ብዙ ከኢንቨስትመንት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ግልጽ ያልሆኑ ወይም በደንብ በቅንጀት የሚሠሩ አልነበሩም። ለምሳሌ በከተማዋ ውስጥ እንዲሁም በአካባቢው የሚገኙ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ምን ያህል አስተማማኝ እንደነበሩ አይታወቅም ነበር። የፕሮጀክቶቹን ወቅታዊ ሁኔታም ማረጋገጥ አይቻልም ነበር። በተለይ የአካባቢው ኢንቨስትመንት ተብለው ሥራ ላይ የዋሉ፣ በግንባታ ላይ ያሉ ወይም ሙሉ በሙሉ ያልተተገበሩ ነበሩ።
በሌላ በኩል በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ደካማ እና ወጥነት የጎደለው ነበር። ይህን ተከትሎ መዋለንዋያቸውን ለማፍሰስ ወደ ከተማዋ የሚመጡ ባለሀብቶች እና ሥራ ፈጣሪዎች በቢሮክራሲያዊ መጓተት እና ደካማ የዘርፍ ቅንጅት የኢንቨስትመንት ሥራን አስቸጋሪ አድርጎት ቆይቷል።
ይህንን የተገነዘበው የሸገር ከተማ ኢንቨስትመንት ቢሮ እርምጃ ለመውሰድ ወስኖ ወደ ተግባር ገብቷል። ችግሮቹን ከመሠረቱ እንዴት መፍታት እንደሚቻል የጋራ ውይይት በማካሔድ፤ የኢንቨስትመንት ዘርፉን በልህቀትና በቅልጥፍና ለመምራት አስፈላጊ የሚባሉ አስቻይ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ያስረዳሉ።
እንድ አቶ ነብዩ ገለጻ፣ ሰነዶችን በማዘጋጀት ወደ ትግበራ ለመግባት ሙከራ ተደርጓል። በዚህም በተለይ የኢንቨስትመንት ደረጃዎችን መለየት፣ ለኢንቨስትመንት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ቦታዎችን ማወቅ፣ ኢንቨስተሮችን እና መዋለ ንዋይ የሚያፈሱ ድርጅቶች የሚመረጡበትን የምርጫ መስፈርት ማዘጋጀት ተችሏል። ለአሰራር ምቹ ሁኔታዎችን እና ግልፅነቶችን የሚፈጥሩ መመሪያዎች ማውጣት እና የዲጂታል ስርዓቶችን እና የቴክኖሎጂ ውህደት መፍጠር ይገኙበታል።
ሰነዶቹ ከተማዋን ለኢንቨስትመንት ሥራ ምቹ ከማድረጋቸውም ባሻገር፣ ተጠያቂነት ያለው የኢንቨስትመንት ሥርዓት ለመዘርጋት መሠረት የሆኑ ግልጽነት፣ ቅልጥፍና እና የአገልግሎት ጥራት ላይ በልዩ ሁኔታ ትኩረት እንዲደረግ አስችሏል። የሚሉት አቶ ነብዩ፤ የሸገር ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት ከላይ የተነሱትን አስቻይ ሁኔታዎች በቅድሚያ በመዘርጋት በቀጣይ ሊተገበሩ የሚገቡ ዋና ዋና አላማዎችን ማስቀመጥ ችሏል ሲሉ ይናገራሉ።
አቶ ነብዩ እንዳሉት፤ እነዚህን ተግባራት ተግባራዊ ማድረግ በመቻላቸው በርካታ ቁልፍ ግቦችን በማሳካት ወደፊት እንዲጓዙ አግዟቸዋል። በዚህም በመጀመሪያ በከተማዋ ሥራ ፈጣሪነትን ማበረታታት እና ወደ ኢንቨስትመንት እንዲቀየር የሚያስችሉ ማበረታቻዎች እየተደረጉ ይገኛሉ። ይህንን ተከትሎ በርካታ ስራ ፈጣሪዎች በልዩ ልዩ መስኮች ወደ ዘርፉ መግባት እንዲችሉ ቀዳሚ አላማ ተደርጎ እየተሰራ ነው ይላሉ።
በሌላ መልኩ በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ቅልጥፍናን እና ምርታማነትን ማረጋገጥ እንዲቻል የተለያዩ ሥራዎች ተሰርተዋል። ለአብነትም በስራ ሂደት ላይ ኢንቨስተሮች ጥያቄ ሲያቀርቡ አስፈላጊውን ሰነድ ከማጣራት ጀምሮ በሚደረግ ሂደት ውስጥ መዘግየቶችን እና የሰዎችን ስህተት ለመቀነስ የኢንቨስትመንት ጥያቄና ሌሎች ሂደቶችን ዲጂታላይዝድ የማድረግ አላማ ተቀምጦ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። በተጨማሪ የኢንቨስትመንት ዘርፉ መስፋፋትን ተከትሎ በከተማዋ ለሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ለወጣቶች የስራ እድል የመፍጠር ዓላማ ተይዞ ወደ ስራ ተገብቷል ይላሉ።
‹‹በአጭር ጊዜ ውስጥ ዓላማችንን ግብ ከመምታት ባሻገር የጥረታችንን ፍሬ እያየን በመሆኑ ኩራት ይሰማኛል›› የሚሉት ምክትል የጽህፈት ቤት ሃላፊው፤ ከስኬቶቹ መካከል በሸገር ከተማ የኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት እየተከናወኑ የሚገኙ አፈፃፀሞችን ያብራራሉ።
እንደ አቶ ነብዩ ማብራሪያ፤ እየተጠናቀቀ ባለው የበጀት ዓመት ከ200 በላይ ስራ ፈጣሪዎች እና ከ30 በላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ተመዝግበው ወደ ትግበራ ገብተዋል። በተጨማሪ በዓመቱ ከ500 በላይ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮችም የኢንቨስትመንት ውጥኑን ተቀላቅለዋል። እነዚህ ባለሀብቶች ተደምረው ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል አስመዝግበዋል።
የኢንቨስትመንት ዋናው ግብ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን፤ ለስራ እድል ፈጠራ ትልቅ አቅም መፍጠርም ነው የሚሉት ምክትል ኃላፊው፣ ከ90 ሺ በላይ ሥራ እድል በእነዚህ አዳዲስ በተፈጠሩ የኢንቨስትመንት ንዑስ ዘርፎች ተመቻችቷል። ስራ አጥነትን ከመቀነስ አንፃር በአንድ ዓመት ውስጥ ትልቅ ስኬት ሊመዘገበ ችሏል። በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ከ200 በላይ ተጨማሪ ስራ ፈጣሪዎች እና 400 ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ኢንቨስትመንት ለመጀመር የሚፈለገውን መስፈርት በማሟላት ወደ ትግበራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ናቸው። ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስራ በመፍጠር፣ በዓመቱ ግዙፍ ካፒታል በማስመዝገብ የተገኘው ስኬት በጥቅሉ አመርቂ ነው ብለዋል።
“ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከተገኘው ስኬት ጎን ለጎን የፕሮጀክት ክትትል እና የዘርፍ አፈፃፀም ግምገማዎች በከተማዋ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት እየተሰራ ይገኛል” የሚሉት ምክትል ሃላፊው አቶ ነብዩ፤ በአሁኑ ጊዜ ከአምስት ሺህ 97 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በሸገር ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ስር ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው። ይህ ቁጥር በዙሪያው ካሉ ዋና ከተሞች ጋር ሲነፃፀር በጣም ከፍተኛው ነው።
ፕሮጀክቶቹ በንዑስ ዘርፍ ሲታዩ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና እንዲሁም በአገልግሎት ዘርፍ ላይ ውጤታማ የኢንቨስትመንት ክንውን ታይቷል ይላሉ። በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚካተቱ ከ2 ሺህ 600 በላይ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በአገልግሎት ዘርፍ ላይ የሚገኙት ደግሞ ከ1 ሺህ 900 በላይ ናቸው። 430 የሚሆኑት ደግሞ በግብርና ዘርፍ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው ብለዋል። ከእነዚህ መካከል በርካታ ፕሮጀክቶች በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ ወደ ሥራ መግባት ችለዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በከተማ አስተዳደሩ ስር አሁንም ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ የሚገኙ የኢንቨስትምንት ዘርፎች መኖራቸውን አስታውሰው፤ 364 የሚሆኑ ፕሮጀክቶች ግንባታቸውን አጠናቀው ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ጠቅሰዋል። 913 ፕሮጀክቶች ደግሞ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገው በአሁን ወቅት በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ። እነዚህን እና በቀጣይ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እያደረጉ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ሲታዩ፤ በአጠቃላይ ከአንድ ሺህ 500 በላይ ፕሮጀክቶች ንቁ ሆነው ወደ ኢንቨስትመንት ሥራ ለመግባት በሂደት ላይ መሆናቸውን መረዳት እንደሚቻል ያብራራሉ።
ይህን ውጤት ማስመዝገብ የተቻለው የሸገር ከተማ በኢንቨስተሮች እና መዋዕለ ንዋያቸውን ፈሰስ ማድረግ ለሚሹ ባለሀብቶች በተሰጠው ትኩረትና በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ነው። የሸገር ከተማ ለቱሪዝም ኢንቨስትመንት ምቹ ነው ያሉት ምክትል ሃላፊው፣ በርካታ ሆቴሎች እና ሎጆችን ጨምሮ ለመስህብነት የሚውሉ ቦታዎች በባለሀብቶች እንዲሁም በተናጥልና በጥምረት እየለሙ ይገኛሉ። ለምሳሌ በመልካ ናኖ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ኩሪፍቱ፣ ቤለማ ሪዞርት እና በሌሎች ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የቱሪስት አገልግሎት ስፍራዎች ተጠቃሽ ናቸው ይላሉ። ይሁን እንጂ በከተማዋ አሁንም በዘርፉ አያሌ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ይገልፃሉ።
እንደምክትል ሃላፊው ገለፃ፤ እነዚህ ተግዳሮቶች በተለይ ከከተማዋ ምስረታ በፊት ሲንከባለሉ የቆዩ እና አሁንም ድረስ የሚታዩ አንዳንድ ክፍተቶች ናቸው። ከባለፈው አስተዳደር የተወረሱ እና አሁንም የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታትም የሚከተሉትን እርምጃዎች ለመውሰድ ጥረት እየተደረገ ነው። ከተግዳሮቶቹ መካከል የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ቃል በገቡ ባለሀብቶች በተገቢው ጊዜ እና መስፈርታቸውን ጠብቀው በመፈፀም ላይ የታዩ ክፍተቶች አሉ። በዚህም አሁን ያለው አስተዳደር እና የኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ግልጽነት የሚያጎላቸው፣ በተሳሳተ መረጃና ማስረጃ የሚተገበሩትን፣ የፕሮጀክቶች መጓተት እና የአገልግሎት ክፍተቶች የሚታይባቸውን በመለየት እንዲሰረዙ ተወስኗል። ይህንን ተከትሎ ከ600 በላይ ፕሮጀክቶች ታግደዋል።
ሌላው የዘርፉ ተግዳሮት በተለይ ነባር በሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ ከመሬት አጠቃቀም፤ ከአሰራር ሰርዓት እና ግልፅ ከሆነ መረጃ ጋር በተያያዘ ክፍተቶች ታይተዋል። ከዚህ ባሻገር ኢንቨስተሮች አገልግሎት ፈልገው በሚመጡበት ወቅት የቢሮክራሲ ብቃት ማነስ እና ቅልጥፍና ክፍተት ታይቷል። እነዚህ ተግዳሮቶች በመሰረታዊነት ለመፍታት እና እልባት ለመስጠት በከተማው አጠቃላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ የሚሆኑባቸውን ቦታዎች በመለየት ከ100 በላይ በሆኑ ቦታዎች ላይ ግምገማ ተካሂዷል። አሁን ግልጽ መረጃ፣ የተሻለ ቅንጅት እና የተሻሻሉ የህግ፤ የአገልግሎት እና የአሰራር ሥርዓቶች እየተዘረጉ ይገኛሉ።
በሸገር ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ዘርፍ እድገትን ለማሳለጥ ተግዳሮት ከሆኑ ምክንያቶች ውስጥ የመሠረተ ልማት ውስንነቶች (በተለይም በመንገድ፣ በውሃ ተደራሽነት እና በሀይል አቅርቦት) አንዳንድ ፕሮጀክቶች ወደ ስራ እንዳይገቡ እንቅፋት እየሆኑ ነው። እነዚህን ለማስተካከል አስተዳደሩ በንቃት እየሠራ ይገኛል ይላሉ።
የሸገር ከተማ አመሰራረቱ ወጣት የሚያስብለው ቢሆንም ትልቅ ውጤት እያሳየ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል። ብዙ ባለሀብቶች ወደ ከተማዋ እየመጡ ነው። በተለይም በኢንቨስትመንት ዘርፍ ከተማዋ ወደ ፊት እየገሰገሰች ትገኛለች። ነገር ግን ሸገር ከተማ አሁን ካላት መሰረተ ልማት የተሻለ መንገድ፣ ውሃ እና መኖሪያ ያስፈልጋታል። የከተማው አስተዳደር እና አመራሮች እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ማቀዳቸውን ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በነበራቸው ቆይታ መረዳት ተችሏል። በዚህ ከቀጠለ እና ሁሉም ሰው ለሸገር ማደግ አስተዋጽኦ ካደረገ ሸገር ከተማ ወደፊት ትልቅ ከተማ እንደሚሆን የሚያጠያይቅ አይደለም።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም