ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በነገው ለንደን ዳይመንድ ሊግ ለድል ይጠበቃሉ

እአአ በ2012 ለንደን ኦሊምፒክ የተካሄደበት ንግስት ኤልሳቤት ስታዲየም ነገ የዳይመንድ ሊግ 10ኛው መዳረሻ የሆነውን ውድድር ያስተናግዳል። በዚህ ውድድር ላይም የሩጫ፣ የሜዳ ተግባራት እንዲሁም የፓራሊምፒክ አትሌቶች ተሳታፊ ይሆናሉ። ከውድድሩ ተሳታፊ አትሌቶች መካከልም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች የሚካፈሉ ሲሆን፤ የተለመደውን የአሸናፊነት ቅድመ ግምትም አግኝተዋል።

የዳይመንድ ሊጉ አዘጋጆች በድረ ገጻቸው ባስቀመጡት የተሳታፊ አትሌቶች ዝርዝር መሰረት በ5ሺ ሜትር፤ በቅርቡ በሃንጋሪ የሚካሄደውን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተጠባቂ የሆኑ እና በርቀቱ ምርጥ የተባሉ አትሌቶች ተካፋይ ይሆናሉ። በዚህም ጠንካራ የአሸናፊነት ፉክክር ይታያል በሚል በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ይጠበቃል።

በውድድሩ ከሚካፈሉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል አስደናቂ ብቃት ላይ የምትገኘው የዓለም የአምስት ሺ ሜትር ቻምፒዮና አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ የአሸናፊነት ግምት አግኝታለች።

ጠንካራዋ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ አምና በአሜሪካዋ ኦሪጎን በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በ5ሺ ሜትር የወርቅ በ1ሺ500 ሜትር ደግሞ የብር ሜዳሊያ ማግኘቷ የሚታወስ ነው። በመካከለኛ ርቀት ሩጫዎች ስኬታማ የሆነችው ጉዳፍ በዚህ ወቅት በ5ሺ ሜትር ስማቸው ከሚጠቀሱ አትሌቶች ቀዳሚዋ ስትሆን፤ በቶኪዮ ኦሊምፒክም የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤት ነበረች። በኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል በቅርቡ በስፔን በተካሄደው የሰዓት ማሟያ ውድድር ርቀቱን 14:13.32 በሆነ ሰዓት በመግባት የግሏን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገቧ ይታወቃል። ይኸውም በለንደን ዳይመንድ ሊግ ከሚሳተፉ አትሌቶች የተሻለ ሰዓት ባለቤት የሚያደርጋት በመሆኑ በቡዳፔስቱ የዓለም ቻምፒዮና ላይ ሃገሯን ከመወከሏ አስቀድሞ የምታጣጥመው ድል ይኖራታል ተብሎ እንዲጠበቅ አድርጓል።

ፈጣን ሰዓት ያላት ሌላኛዋ አትሌት መዲና ኢሳ ደግሞ 14:40.02 ባለቤት ስትሆን፣ ይህም አትሌቷን በኢትዮጵያውያን በኩል ጠንካራ ተፎካካሪ ያደርጋታል ተብሎ እንዲጠበቅ አድርጓል። በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀቶች የምትታወቀው ግርማዊት ገብረእግዚአብሄርም 14:46.12 የሆነ ፈጣን ሰዓት ያላት አትሌት እንደመሆኗ የነገውን ፉክክር ጠንካራ እንዲሆን ያደርገዋል። እአአ በ2021 የዓለም ወጣቶች ቻምፒዮና ላይ በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤትና ተስፋ ከሚጣልባቸው ወጣት አትሌቶች መካከል ሚዛን ዓለም አንዷ መሆና የሚታወስ ሲሆን፣ አትሌቷ በዚያው ዓመት ሄንግሎ ላይ በተካሄደው የሰዓት ማሟያ ውድድር ርቀቱን 14:46.20 በሆነ ሰዓት በመሸፈን ምርጥ ሰዓቷን ልታስመዘግብ ችላለች። ናይሮቢ ላይ በተካሄደው የዓለም ወጣቶች ቻምፒዮና ለሃገሯ በ5ሺ እና 3ሺ ሜትር የብር እና ነሃስ ሜዳሊያዎችን ያገኘችው ሌላኛዋ ወጣት አትሌት መልክናት ውዱ ደግሞ 14:47.48 የሆነ ሰዓት ያላት የነገው ውድድር ተካፋይ ናት።

በ1ሺ500 ሜትር ስኬታማ እየሆኑ ከሚገኙ አትሌቶች መካከል የምትጠቀሰው ብርቄ ሃየሎም በነገው ለንደን ዳይመንድ ሊግ ትሮጣለች። በርቀቱ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል አንዷ ኔዘርላንዳዊቷ ሲፈን ሃሰን ናት። አትሌቷ የኦሊምፒክ ቻምፒዮን ስትሆን 14:22.12 ፈጣን ሰዓቷ ነው። ይኸውም ከጉዳፍ ቀጥሎ የምትቀመጥ ፈጣን ሰዓት ያላት አትሌት ያደርጋታል። በተጨማሪም ኬንያዊቷ ማርጋሬት አኪዶርም በውድድሩ ጠንካራ ፉክክር ታደርጋለች ተብላ ትጠበቃለች።

በ800 ሜትር ርቀት በሚካሄደው ፉክክር ወጣቷ አትሌት ድርቤ ወልተጂ በለንደን ንግስት ኤልሳቤት ስቴዲየም ይደምቃሉ ተብለው ከሚጠበቁ አትሌቶች አንዳ ነች። እአአ በ2018 ፊንላንድ ቴምፖራሬ ላይ በተካሄደ የዓለም ወጣቶች ቻምፒዮና በርቀቱ ለሃገሯ የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገብ የቻለችው ይህች አትሌት፣ በአምናው የኦሪጎን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን በዚሁ ርቀት የወከለች ሲሆን፤ ሜዳሊያ ለጥቂት ማጥለቅ አልቻለችም። ነገር ግን 4ኛ ደረጃን ይዛ ውድድሩን በማጠናቀቋ የዲፕሎማ ተሸላሚ ልትሆን ችላለች። በወቅቱ ርቀቱን የሸፈነችበት 1:57.02 የሆነ ሰዓትም የግሏ ምርጥ ሆኖ ተመዝግቦላታል። በሰዓቷ መሰረትም በውድድሩ ላይ ጠንካራ ፉክክር ከሚያደርጉና ለአሸናፊነትም ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል አንዷ ልትሆን ችላለች።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 15 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *