በደጋፊዎች ደም የቆመ ክለብ

ደጋፊዎች ያላቸውን ሁሉ ሰጥተው የክለባቸውን ህልውና ማስቀጠላቸው የተለመደ ነው።በእርግጥም የየትኛውም ክለብ የደም ስሮች ናቸው ደጋፊዎች፤ ነገር ግን ከገንዘብ፣ ጊዜ እና ጉልበት ድጋፍ ባለፈ ደም እና ወዛቸውን ከፍለው ማቆማቸው እንግዳ ነገር ነው።ይህንን ያህል መስዋዕትነት ተከፍሎለት በህይወት ሊቆይ የቻለው ይህ የእግር ኳስ ክለብ ደግሞ የጀርመኑ ዩኒየን በርሊን ይሰኛል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ተወዳጅ ስፖርት ለሆነው እግር ኳስ በርካቶች መስዋዕትነት መክፈላቸው የተለመደ ነው።ነገር ግን ደጋፊዎች በዚህ ልክ አንድ ሆነው ለክለባቸው በመቆም ምስራቅ ጀርመናዊያኑን የሚስተካከላቸው የለም።‹‹ብረቶቹ›› የሚል ቅጽል ስም ያላቸው እነዚህ ደጋፊዎች ስለክለባቸው ፍቅር ሲሉ ሁሉን ሰጥተው ቀስ በቀስ እየሞተ የነበረውን ክለባቸውን ታድገው በትንሳኤ ከትልልቆቹ የአውሮፓ ክለቦች እኩል እንዲጠራ አድርገዋል።

እአአ በ1906 ምስራቃዊ በርሊን ላይ የተመሰረተው ይህ ክለብ በወቅቱ ስመጥር የነበረ ሲሆን፤ የቀዝቃዛውን ጦርነት ወቅት ጨምሮ በጀርመን ሊግ ቆይታው ቻምፒዮንም ነበር።የጀርመንና የዋና ከተማዋ በርሊንን ውህደት ተከትሎም በቡንደስሊጋው ሁለተኛው ዲቪዚዮን ሲጫወት የቆየ ክለብ ነው።የክለቡ መገልገያ የሆነው አልተን ፎርስትሪ ስታዲየምም በሀገሪቷ ታዋቂ ከሆኑት መካከል አንዱ በመሆኑ ከእግር ኳስ ያለፉ ሌሎች ሁነቶችንም ያስተናግዳል።በዚህ ሁኔታ የቆየው ክለቡ እአአ በ2004 የገጠመው የገንዘብ ኪሳራ እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ለዓመታዊ የውድድር መመዝገቢያ ክፍያ እስከማጣት አድርሶት ነበር።በወቅቱ የጀርመን እግር ኳስ ማህበር ለሚያደርገው ምዝገባ ክፍያውን ፈጽሞ በእንቅስቃሴ ላይ ለመቆየትም 1ነጥብ5 ሚሊዮን ፓውንድ ያስፈልገው ነበር።

ታዲያ በዚህ ወቅት ደጋፊዎች ከሚወዱት ክለባቸው ፊታቸውን ከመመለስ ይልቅ ምን ማድረግ እንዳለባቸው መከሩ።እናም ይህንን የገንዘብ ችግር ቀርፎ የክለቡን አቅም ለማጠናከር ያስችላል ላሉት መላ ጊዜ ሳይፈጁ ተሰለፉ።በቀይ ማሊያ ለባሾች የተደረገው ይህ ረጅምና ቀልብ ሳቢ ሰልፍም ደም የመለገስ ነበር።በሀገረ ጀርመን ደም መለገስ ገንዘብ የሚያስገኝ ተግባር በመሆኑ ደጋፊዎች ለክለባቸው ያላቸውን ፍቅር ሳይሰስቱ በማበርከት ገንዘቡን በቀጥታ ትግል ላይ ለሚገኘው ክለባቸው ገቢ አደረጉ።‹‹ለክለባችን እንድማ›› የሚለው ይህ መፈክርም ለአንዴ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ በተግባር ላይ እየዋለ ክለቡን በገንዘብ እጦት ከመፍረስ ታድጎታል።

በዚህ ሁኔታ የሚገጥሙትን አስቸጋሪ አካሄዶች ያለፈው ክለቡ እአአ በ2007/8 የውድድር ዘመን ደግሞ ሌላ ዱብ እዳ ደረሰበት።ይኸውም እአአ ከ1920 አንስቶ ግልጋሎት ሲሰጥ የቆየው ስታዲየማቸው አልተን ፎርስትሪ የመናድ አደጋ ማስተናገድ ጀመረ።ዘመናዊውን ዓለም የማይመጥነውና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ደረጃንም በማያሟላው የስታዲየሙ ወቅታዊ ሁኔታም ክለቡ ፈቃዱን ሊነጠቅና ከነበረበት ደረጃም ዝቅ ሊል እንደሚችልም በደጋፊዎቹ ዘንድ ስጋት አሳደረ።ሁሌም ለክለባቸው ቀድመው የሚሰለፉት ደጋፊዎች ከኪሳቸው የገንዘብ መዋጮ ቢያደርጉም ለደረሰበት ጉዳት በቂ ሆኖ አልተገኘም።አስገራሚዎቹ ደጋፊዎች ስለ ዩኒየን በርሊን የማይሆኑት የለምና ሌላ ዘዴ አፈለቁ፤ 2ሺ የሚሆኑትም በበጎ ፈቃደኝነት መዶሻና ሚስማር ጨብጠው ወደ ግንባታ ገቡ።

ምናልባትም ሃሳቡ ቀልድ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን ቸልተኝነት የማያውቃቸው ደጋፊዎች ያሰቡትን እውን በማድረግ ለዓመታት ላባቸውን በማፍሰስ ለመደርመስ ጥቂት የቀረውን ስታዲየም አንጸው ዳግሞ ከእነግርማ ሞገሱ አቆሙት።አሁን ላይ በዋና ከተማዋ በርሊን በግዝፈቱ ሁለተኛ ደረጃን የያዘው ስታዲየሙ የሙዚቃ ድግስን ጨምሮ ታላላቅ መርሀ ግብሮችም ይስተናገዱበታል።ስታዲየሙ በዘመናዊ ሁኔታ ደረጃውን ጠብቆ ከመገንባቱ ባለፈ ሜዳውም ወቅቱን በዋጀ ሁኔታ ተሰርቶ መጠናቀቁን ተከትሎ ክለቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨዋታውን ከሊፕዚንግ ጋር ሲያደርግ በስፍራው የነበረው ድባብ እጅግ አስደማሚ ነበር።በደጋፊው ጥንካሬ ከወደቀበት የተነሳው ክለቡ በውድድሩ አስደናቂ ተሳትፎ በማድረግ ውለታውን በተግባር በመመለስ ላይም ይገኛል።

ከ45ሺ በላይ የተመዘገቡ ደጋፊዎች ያሉት ዩኒየን በርሊን እአአ በ2019 ቡንደስሊጋውን የመቀላቀል እድል ሲያገኝ፤ በ2021 ደግሞ በአውሮፓ ኮንፍረንስ ሊግ ሰባተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል።በቀጣዩ ዓመት በዩሮፓ ሊግ አምስተኛ ደረጃን ሲይዝ፤ በቡንደስሊጋው አራተኛ ሆኖ ማጠናቀቁን ተከትሎ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ እስከመሳተፍ የደረሰ ብቃቱን ማሳየት ችሏል።ታሪኩን የሚያውቁ የእግር ኳስ አፍቃሪያንም ‹‹ክለቦች ያለ ደጋፊ ሊቆሙ አይችሉም፤ የዩኒየን በርሊን ደጋፊዎች ግን ለሌሎች ምሳሌ ናቸው›› ሲሉ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You