አንዳንዶች ታላላቅ ታሪኮችን ይሠራሉ፤ ታሪክ ግን አፉን ሲለጉምባቸው ይታያል:: ታዲያ ከእነዚህ መሀከል አንደኛው ይኸው ባለዋሽንቱ ፕሮፌሰር መሆኑ ሀቅ ነው:: የዚህ ታላቅ ሰው ሥራና ታሪክ በምንም ሚዛን የሚጣጣሙ አይደሉም:: የረቂቅ ሙዚቃው መካኒክ፣ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ እንደሥራው ተነገረለት የሚል ካለ፤ ከበሬ ወለደ ታሪክ የሚተናነስ አይደለም:: ምናልባት ታሪኩን ስናደምጥ፤ አሊያም ስናነብ መገረማችን አይቀርም:: ግርምቱ ግን፤ በሠራው ሥራ ብቻ ሳይሆን እርሱን ባለማወቃችንም ጭምር ነው:: የእርሱ እውነተኛው የታላቅነትና የክብር ምስሉ የተደበቀው ከማህበረሰቡና ከሀገራዊው የልብ መስታየት ውስጥ ብቻ አይደለም:: አሳዛኙ ነገር፤ በሙዚቃው አዳራሽ ውለው የሚያድሩ አብዛኛዎቹም እንኳን፤ በቅጡ ያማያውቁትና ያልተረዱት መሆኑ ነው:: በሙዚቃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ መምህሩ ስሙን በሚያነሳበት ቅጽበት፤ በተማሪው ዘንድ “አሸናፊ ከበደ ማነው?” የሚል መደናገርና የእንግዳነት ፊት የሚስተዋል መሆኑ ነው:: አንዳንዶች በትንሽ ሥራ፤ በትንሽ ድካም የታሪክ ማማ ላይ ወጥተው ቁንጮ ሲሆኑ፤ በታላላቅ ሥራዎቻቸው ሠገነት ላይ የቆምንባቸውን ስንዘነጋ የልብ ስብራትና የአንጀት ቁስል የሚፈጥር ነው::
ስለ እረቂቅ ሙዚቃ አንስቶ፤ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደን መዘንጋት ማለት፤ ያጎረሰን ጣት እንደመንከስ ነው:: አልነከስንም ለማለትም አይቻልም:: ነገሩን በግራ ቀኝ ለመመልከት ስንሞክር፤ ይህ መረሳት እጣ ክፍሉ የሆነው ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ለመላው የረቂቅ ሙዚቃ ቀማሪዎች ይመስላል:: ምናልባት የዚህ ዓይነቱን የሙዚቃ ጣዕም ለማጣጣም የሚሆን ጆሮ አሊያም ደግሞ ልብ የሚል ልብ አጥተናል፤ እንጂማ በሰላሙ እንዴት እንዲህ…የአሸናፊ ከበደ ታላቅነት ግን ከሙዚቃውም ያለፈ ነበር:: “ሙዚቀኛ ለሙዚቃ ኖታ እንጂ፤ ለብዕር ቀለም ጊዜ አልባ ነው” የሚመስል የደመና እሳቤ አለና፤ እርሱ የደመናውን ጥቁር መጋረጃ ገልጦ ብዙ ነገሮችን ያሳየን ሰው ነበረ:: በዚያ ላይ ለችሎታው ልክ ቃላቶች የሚገኙለት አልነበረም:: በሄደበት ሁሉ ሀገሩን ይዞ የሚዞር የሀገር ልጅ ነበር:: አይኖቻቸውን ገልጠው ይህን ለመመልከት የቻሉ ግን ጥቂቶች ናቸው:: እርሱ በሚያልፍባቸው ረቂቅ ሙዚቃዎቹ ውስጥ ሁሉ ሌላ የመጠሪያ ስሞችን ይጎናጸፋል:: “ባለ ዋሽንቱ እረኛ” እና “ጥቁሩ ኮዳሊ” ከዋና ስሙ ቀጥለው የሚጠራባቸው ናቸው::
ባለዋሽንቱ እረኛ፤ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ግንቦት 8 ቀን 1930 ዓ.ም ከዘጠኝ ወራት የእናት ሆድ ቆይታ በኋላ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ እራሱን ችሎ የምድርን አየር በሳንባው የማገበት ዕለት ነበር:: በዚህ ቀን አዲስ አበባ፤ ይህን ታላቅ ሰው ተቀበለች:: እረቂቁን ህጻን፤ ለእረቂቅ ሙዚቃ ንጉሥ አድርጋ ልትሾም ያሰበችው ምናልባትም በዚያው የተወለደባት ዕለት ላይ ነው:: የአሸናፊ ወላጅ አባት ከበደ አድነው የግራዝማችነት ማዕረግ ያላቸው ወታደር ናቸው:: የወታደር ልጅ ወታደር አሊያም ቀለሜ ቢሆን እንጂ፤ ሙዚቀኛ ለመባል ከተአምር ያልተናነሰ ተአምር ያሻው ይሆናል:: ይሄ ተአምርም ወላጅ እናቱ ወይዘሮ ፋንታዬ ነከሬ ሳይሆኑ አይቀሩም:: እኚህ ሴት ለሙዚቃ ባይፈጠሩም፤ ከማህጸናቸው ልጅ ብቻ ሳይሆን ሙዚቀኛ ልጅ እንዲፈጠር ይወዱ ነበር:: ለዚህም ይመስላል፤ አሸናፊ ከበደ ገና ጨቅላ ልጅ ሳለ ጀምሮ፤ ሙዚቃዊ ስሜትን በውስጡ ለመዝራት ይቆፍሩ ነበር:: ልጅ ከተወለደ ወዲያ አብዛኛው ወላጅ፤ በልጁ የነገ ዓለም የምኞት ልብ ውስጥ ቆፍሮ የሚተክለው፤ የሚታየውን የራሱን የዛፍ ችግኝ ነው:: አቮካዶው የአቮካዶን፤ ማንጎም የማንጎውን ፍሬ ብቻ ለማየት ይወዳል:: እንዲህ መሆኑ ክፋት ባይኖረውም፤ ደግነትን ሊያጎድል ግን ይችላል:: አሸናፊን ሙዚቃ እንዲያሸንፈው ያደረጉት እናቱ፤ ከእናትነት ባለፈ ታሪካዊ ተምሳሌትነትን አኑረዋል::
አሸናፊ ከበደ ደማቁን የቀለም ጉዞውን ሲጀምር፤ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ገብቶ፤ የማይሞላውን የዕውቀት ስልቻ አዝሎ ጉዞውን ጀመረ:: አንደኛውን አጠናቆ ሁለተኛው ማረፊያው ኮከበ ጽባሕ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሆነ:: ከዚህ በኋላ ግን ጓዙን ሸክፎ፤ አዲስ አበባን ተሰናብቶ ሐረር ገባ:: ወደ ሐረር መምህራን ኮሌጅ አቅንቶም፤ በመምህርነት ሙያ ቆቡን ደፋ፤ ተመረቀ:: ጉዞው አሁንም አልተገታም፤ የተወሰነ ካገለገለ ኋላ፤ የዕውቀት ረሃቡን የተመለከቱት ጃንሆይ፤ እስቲ ከዚያ ሄዶ እንኳን የዕውቀት ስልቻው ቢሞላለት፤ የሙዚቃ ጥሙንም ቢቆርጥለት ብለው፤ በትምህርት ወደ ውጭ ሀገር ሰደዱት:: አሜሪካን ሀገር ደርሶም፤ በ1961 ዓ.ም በኢስትማን ዩኒቨርሲቲ በሙዚቃ የማስትሬት ዲግሪውን ጫነ:: ነገር ግን፤ የጭንቅላት ስልቻ እንደ ሆድ አይደለምና በቃኝን፤ ጠገብኩን ጥንቱን አልፈጠረበትም:: የሰጡትን የማስተርስ ወረቀት ይዞ፤ “ሸኙኝ“ ወደ ሀገሬ ልግባ ከመንደሬ ሳይል፤ ዳግም ለሦስተኛ ዲግሪ ተዘረጋ:: በ1963 ዓ.ም በዌስሌይ ዩኒቨርሲቲ፤ ሦስተኛውን ዲግሪ ከዶክተርነት ማዕረግ ጋር ተረከበ:: አሁን ግን ሀገር ይናፍቃል:: “ሀገሬን ሀገሬን” ያስብላል::
1959 ዓ.ም እና ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ፤ እንደ አባይ ድልድይ በገዘፈ፤ እንደ እግዜር ድልድይ ከላይ በተንሳፈፈ፤ እንደ አስታራቂው መንገድም ለፍቅር ባፈጠጠ ልዩና ታሪካዊ ቦታ ላይ ተገናኙ:: ሥራና ሠሪ፤ ታሪክና ታሪከኛውን ያገነኛው ድልድይ፤ በቅዱስ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ምሥረታ ላይ መሠረቱን ጥሎ እዚህ ጋር ጀመረ:: ብዙ ያልተነበበው አንደኛው ገድሉም፤ በቅዱስ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ቆይታው ወቅት የሠራቸውንና ያለመለማቸው አበቦችን ነው:: በወቅቱ ጃንሆይ፤ አንድ ዘመናዊ የሙዚቃ ትምህርት ቤት እንዲቋቋም ጽኑ ፍላጎት ነበራቸው:: ይህን ተከትሎም፤ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተቋቋመ:: እናም፤ ይህን ባለግዙፍ ራዕይ የሆነው የሙዚቃ ትምህርት ቤት ሲቋቋም ግንባር ቀደም ከሆኑት መሀከል አንዱ አሸናፊ ከበደ ነበር:: ለትምህርት ቤቱም (ዳይሬክተር) ርዕሰ መምህርም ተደረገ:: ለዚህ ቦታም በታሪክ የመጀመሪያው ሰው ለመሆን በቃ:: እዚህ ሳለ፤ ሥራው ትምህርት ቤቱን መምራት ብቻ አልነበረም:: ጎን ለጎን የሙዚቃ ሥራዎችን አድማስ በማስፋት በረዥሙ ያሳልጠው ጀመረ:: ከዚህ ቅጥር ጊቤ ሌላ፤ ወደ ሁለት የተለያዩ አቅጣጫዎች እጁን ዘረጋ:: የመጀመሪያው እዚሁ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሲሆን በዋናነት ሁለት ተቋማት ይገኙበታል:: የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወወክማ) እና የቀዳማዊ ኃይለ ሥልሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት፤ መርሓ-ዕውራን ትምህርት ቤት ናቸው:: ከያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የተረፈችውን ጊዜና ጉልበት፤ ከዕውቀቱ ጋር አጣምሮ ተማሪዎችን በሙዚቃ ያሠለጥናል::
በሌላ በኩል ደግሞ ፊቱን ወደ ባህርማዶ አሻግሮ ይመለከት ነበር:: ትምህርቱን ለመከታተል በወጣበት ጊዜ፤ የተመለከታቸው በርካታ ነገሮች አሉና ሀገሩና የሀገሩም ሙዚቀኞች ልክ እንደዚያው እንዲሆን ምኞቱ ነበር:: ከውጭ ሀገራት ሙዚቀኞች ጋር ትስስር በመፍጠርም አብረው በጋራ መሥራት ጀመሩ:: የግንኙነት ሰንሰለቱ የተዘረጋው፤ ሀገርና ትምህርት ቤቱን በሚጠቅም መልኩ እንጂ ለራስና በራስ ብቻ አልነበረም:: ተማሪውን በዕውቀት ለማሻገር፤ ከራሱ የጭንቅላት ስልቻ እያወጡ ማዘገኑ ብቻ በቂ መስሎ አልታየው ነበር:: በስሩ የነበረውን ባንድ እያስከተለም እውቀት ሸመታና የልምድ ልውውጥ ተጀምሮ ቀጠለ:: ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደና ትምህርት ቤቱ ለአምስት ዓመታት ያህል መልካም በሆነ መልኩ አብረው ተጓዙ:: ታላቁ ሰው ሌላ ታላላቆችንም አፈራ:: መቼም፤ ጃንሆይ እንደሆኑ በዚህ ሙዚቀኛ ያላቸው እምነትና የሚታያቸው ተስፋ ቀላልና የሚገመት አይመስልም:: በወቆይታው ወቅት ላሳየው ድንቅ ተግባርም የኋላ ላይ ሁለት ሽልማቶችን ተጎናጽፏል:: በመጀመሪያም፤ በንጉሠ ነገሠቱ “ብሔራዊ የሙዚቃ አቀናባሪ” የሚል ማዕረግ ተሰጠው:: ቀጥሎም፤ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴዎቹ ውስጥ፤ የሀገሩን ባህል በዓለም በማስተዋወቅ ለተጫወተው ከፍተኛ ሚና ደግሞ፤ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሌላ ሽልማት አበረከተለት::
(በነገራችን ላይ፣ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የሥነጽሑፍ ሃያሲ ስለመሆኑ የምናውቅ ስንቶቻችን ነን? አዎ፣ ፕሮፌሰር አሸናፊ የሥነጽሑፍ ሃያሲ ነበር። ለዛውም ስለ ሀገራችን ሥነጽሑፍ በዓለም መድረክ ላይ በብእሩ የተከራከረና የወቅቱን የሥነጽሑፋችንን ይዞታ አገላብጦ በመመርመር እስከ ዛሬም ተጠቃሽ የሆነ ጥናትን ለትውልድ ያሻገረ ምሁር እንደ ነበር ቢያንስ በቅንፍ አስቀምጠንለት ልናልፍ ይገባል።)
1959 ዓ.ም ለአሸናፊ ከበደ መልካም ተስፋን የሰነቀች ዓመት ነበረችና በአንድ ደረጃ ታላቅነቱን ከፍ የምታደርግ ሌላ የእድል በር ተከፈተች:: ከወደ ቡዳፔስት፤ ከሀንጋሪ መንግሥት የግብዣ ጥሪ ደረሰው:: በዚያም ሁለት ታላላቅ ድርሰቶቹን ለትርኢት አሰናዳቸው:: “ባለ ዋሽንቱ እረኛ” እና “የኢትዮጵያ ሲንፎኒያ” የተሠኙትን ነበር:: በሁለቱም ላይ የኦርኬስትራው መሪ ከመሆኑም በላይ እርሱ እራሱ አቀናባሪ በመሆን በሸክላ አሳትሞ አወጣቸው:: በሁሉም ቦታ፣ በየትኛውም መንገድ ውስጥ ከድንቅ ችሎታው ጋር ለሙዚቃ የተፈጠረ መሆኑን አስመሰከረ:: ከእርሱ ጋር አብረው በጋራ የሠሩት ሀንጋሪያውያኑ የሙዚቃ ባለሙያዎችም፤ ባለዋሽንቱን እንዲህ ሲሉ ስም ሰየሙለት፤ “ጥቁሩ ኮዳሊ” አሉት:: በቆይታው፤ ጥምር ኦርኬስትራውን በመሪነት ሲያስከትላቸው፤ በድንቅ ብቃቱ ተማርከው ልባቸውንም ሳይቀር ሰጥተውት ነበርና ባወጡለት ስም እያቆላመጡ ይጠሩት ነበር:: በቡዳፔስት ሆኖ ካሳተማቸው የሸክላ ሥራዎች የተገኘውን ገቢ ለኪሱ አላስመኘውም:: በቀጥታ ወስዶ ለመርሓ-ዕውራን የበጎ አድራጎት ድርጅት ሰጠ::
ሙዚቃ የታላላቆች፤ የሕይወት ዘመን መተንፈሻ ሳንባ ነው:: ለዚህ ታላቅ ሰው ግን ይህ ብቻውን በቂ አልነበረም:: የሙዚቀኛነቱን ባህር አቋርጦ ጸሀፊም ሆነ:: ዳርቻው ላይ ተቀምጦ እንደገና ለመጻፍ ብዕር አነሳ:: በ1956 ዓ.ም “ንሰሐ” የተሰኘውን ሁሉን አሳሽ መጽሀፍ ጽፎ ለመጻሕፍት ዓለም እንካችሁ አለ:: በመቀጠልም፤ ልቡን ላላወሰው ሙዚቃ “የሙዚቃ ሰዋሰው”ን ጻፈና እድሜ ዘመኑን፤ ከሀገር ውስጥና ከባህር ማዶ እየሰበሰበ ከሞላው ስልቻ ላይ፤ ዕውቀትና ጥበብን ከቋቱ እየመዘዘ አደለ:: ሙዚቃ የዓለም ሕዝብ ሁሉ ቋንቋ ቢሆንም፤ የራሱ ብቻ የሆነ ቋንቋም አለውና “የሙዚቃ ሰዋሰው” የተሰኘው መጽሀፉም፤ ለዚህ ትልቁ የቃላት መፍቻ ሊሆን የሚችልም ነው:: የፕሮፌሰርነት ማዕረጉም ቢሆን፤ እንዲሁ የመጣና እንዲሁ ዝም ብሎ የተቀመጠ አይደለም:: በሙዚቃ መንገድ ውስጥ ያገኘውን ዕውቀትና ልምድም፤ እጅግ በርከት ያሉ የጥናትና የምርምር ሥራዎችን ለመሥራት ተጠቅሞበታል:: በዚህ ሁሉ፤ የተሰጠው አነሰው እንጂ፤ ከተሰጠው ነገር አንዱንም አላባከነም::
ባለዋሽንቱ ከሀገር ውስጥ ሙዚቀኛነት ከፍ ብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝናና ተወዳጅነትን አትርፎ የነበረ ቢሆንም፤ ነቢይ በሀገሩ … ሆነና ታሪክን ነፈግነው:: ዛሬም ድረስ የምናደምጣቸው፤ እጅግ ማራኪ የሆኑ ረቂቅ ሙዚቃዎቹ ቢኖሩም፤ እንደ ሌላው ድምጻዊ ሁሉ ማነው? የማነው? ስለማንል፤ ባለቤቱን በቅጡ እንዳናውቀው አድርጎናል:: ከሀገሩ የሙዚቃ ክምር ሳር ምሶ በዓለም አቀፍ መድረክ ከነሰነሳቸው ሥራዎቹ መሀከል፤ “እረኛው ባለ ዋሽንት” ትልቁና ዋነኛው እንጂ ብቸኛው አይደለም:: “ሰላም ለኢትዮጵያ”፤ “የተማሪ ፍቅር”፤ “የሀገራችን ሕይወት”፤ “እሳት እራት” ከሚሉት ሥራዎቹ ላይ ወጣ ብሎ የመዘዛቸውን፤ “ኒርቫኒክ ፋንታሲ” እና “ኮቱሬዢያ”ን ጨምሮ በርካታ ሥራዎቹ ለዓለም መድረክ ድምቀት ለመሆን በቅተዋል::
ባለዋሽንቱ፤ በሀገር ውስጥ ሆኖ እጅግ በርካታ ታሪኮችን ከሠራ በኋላ፤ ፊቱን ወደ ሀገረ አሜሪካ አዙሮ ነበር:: የሙዚቃን ጥበብ ከዕውቀት ጋር አድሎታልና እጁን ስሞ የማይቀበለው ማንስ ይኖርና… እናም፤ በፍሎሪዳ ግዛት ውስጥ በምትገኝ የሙዚቃ ኮሌጅ ውስጥ በመምህርነት መሥራት ጀመረ:: በዚያ ቆይታ ውስጥ ይህ ብቻ አልነበረም፤ ተቀማጭነቱ ከዚያው የሆነውንና ታዋቂውን የ “ኢትዮጵያ ምርምር ካውንስል” ን በዳይሬክተርነት ይመራም ነበር:: ከግላዊ ሕይወቱ አንጻርም፤ ሽግግር የተደረገባቸው ነገሮች ነበሩ:: አስቀድሞ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረባቸው ጊዜያት፤ ወይዘሮ እሌኔ ገ/መስቀል ውሃ አጣጭ የትዳር አጋሩ ስትሆን ልጆችንም አፍርተዋል:: ሁለተኛውን የትዳር ጎጆም፤ ከአንዲት አሜሪካዊ ዜግነት ካላት ሴት ጋር ቀልሰው፤ እዚያም ልጆች ተወልደዋል:: በድምሩም፤ የሦስት ሴቶች ልጆችና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ሆነ::
ጊዜው፤ 1990 ዓ.ም ቦታው ደግሞ አሜሪካ፤ ፍሎሪዳ ግዛት ውስጥ… መጀመሪያ አልባው መጨረሻ፤ እጅግ አስቀያሚና አወዛጋቢ የሕይወት መቋጫ ሆኖ ተከሰተ:: ባለዋሽንቱ፤ የሕይወት ዘመኑን የመጨረሻ ኑሮ በባህር ማዶ ካደረገ ጥቂት የማይባሉ ዓመታት አልፈዋል:: ከእለታት በዚያች ቀን፤ የተወለደባት ግንቦት 8፤ የ60ኛውን ዓመት የልደት በዓሉ ታቅፋ ደረሰች:: የዚያኔ፤ የባለዋሽንቱ ሰማይ ላይ ሁለት የተለያዩ መልኮች ታዩ:: ጸሐይና ዝናብ አብረው ወደ ሕይወቱ ወረዱ:: ቀደም ሲል ጸሐይ ማልዳ፤ የደመናውን ጭጋግ ገፋ፤ ከብሩህ ተስፋ ጋር ፈንጥቃ ነበር:: ብዙም ሳይቆይ፤ ዝናቡም የጸሐይዋን መውጣት ከቁብ ሳይቆጥረው፤ ዶፉን ከበረዶ ቀላቅሎ የሕይወቱን ጣራና ግርግዳ አንኮታኮተው:: የእነዚህን ሁለት ነገሮች ግጥምጥሞሽ የሀገሬ ሰው ሲመለከት፤ “ጅብ ወለደች” አይደል የሚለው? እርግጥ ነው አልተሳሳተም:: የዚያን ዕለት ያልታወቁ ነብሰ በላ ጅቦች ተወልደው ነበር:: በዕለቱ መጀመሪያ ሁሉም ነገር ሰላም ነበር:: ከፈነጠቀችው ብሩህ ሰማይ ላይ ቁልቁል ከሚምዘገዘገው ጨረር ውስጥ አጨንቁሮ የሚመለከተው ነገርም፤ በተስፋ የተሰነቀውን የ60ኛ ዓመት የልደት በዓሉን በሰማዩ ላይ ከተለኮሰች ሻማ ጋር ነበር:: የሚያየው የመልካም ምኞት መግለጫ ቃላትን ነበር:: ግን “ነበር” እንጂ አይደለም:: የበራችው ሻማ መልሳ ድርግም!፤ እልም አለች:: ምን ይሁን ምን ሳይታወቅ፤ በልደቱ ቀን ከገዛ ቤቱ ውስጥ ሞቶ፤ በድን ሆኖ ተገኘ:: ነብሱን የበላው ጅብም፤ ማን ይሁን ማን፤ እምጥ ይግባ ስምጥ የሚታወቅ ነገር የለውም:: ብቻ ግን፤ ባለዋሽንቱ እረኛ ባለዋሽንቱ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ፤ ሞቶ ተገኘ አሉ:: እኛም ሞቶ ተገኘ ብለን ተቀበልን:: እርሱና የእርሱ መጨረሻም፤ ይኼው ነው::
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም