ለኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት ተዘጋጅቷል

ከሦስት ወራት በኋላ በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ በሚካሄደው የ2024 ኦሊምፒክ ጨዋታ፣ የወርቅ ሜዳሊያ ለሚያጠልቁ አትሌቶች ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት እንደተዘጋጀ የዓለም አትሌቲክስ በድረገጹ አስታውቋል። ተቋሙ ባዋጣው መረጃም በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ የገንዘብ ሽልማትን የሚሰጥ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን እንደሚያደርገውም ገልጿል።

የዓለም አትሌቲክስ እንዳስታወቀው፣ በየአራት ዓመቱ ከዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በገቢ ድልድል ድርሻ የሚያገኘውን 2.4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በውድድሩ በአንደኝነት ለሚያጠናቅቁና የወርቅ ሜዳሊያ ለሚያሸንፉ አትሌቶች በሽልማት መልክ ያበረክታል። ይህም በፓሪስ በሚካሄደው ትልቁ የኦሊምፒክ ድግስ በ48 የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ወርቅ ለሚያጠልቁ አትሌቶች የሚሰጥ ይሆናል። በእነዚህ የአትሌቲክስ ውድድሮች የወርቅ ሜዳሊያን የሚያጠልቅ እያንዳንዱ አትሌት 50 ሺ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት እንደሚያገኝም ታውቋል።

በተጨማሪም በሪሌይ ውድድር የሚያሸንፉ አትሌቶች ተመሳሳይ መጠን ያለው ገንዘብ እንደሚሸለሙ ገልጿል። ሽልማቱ በኦሊምፒክ ውድድር ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጥ ሲሆን ከዚህ ቀደም አትሌቶች ሲያሸንፉ የሚያገኙት ሜዳሊያ ብቻ መሆኑም ተመላክቷል።

ይህ በዓለም አትሌቲክስ የተጀመረው የገንዘብ ሽልማት ሂደትን በደረጃ ለማሳደግ የታቀደ ሲሆን እአአ በ2028 በአሜሪካ ሎስአንጀለስ የክረምት ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የብር እና የነሐስ ሜዳሊያን ለሚያስመዘግቡ አትሌቶችን በሽልማቱ ለማካተት ቁርጠኛ እንደሆነ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንት ሴባስቲያን ኮ የውሳኔውን ዝርዝር ሁኔታ ሲያስረዱ በሰጡት አስተያየት “የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዎች ሽልማትን ማስተዋወቅ ለዓለም አትሌቲክስ እና በአጠቃላይ ለአትሌቲክስ ስፖርት ወሳኝ ወቅት ነው፣ ይህም አትሌቶችን ለማብቃት እና ለውድድሩ እውቅና ለመስጠት ያለንን ቁርጠኝነት አጉልቶ ያሳያል” በማለት ገልጸዋል። ሽልማቱ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ስኬት ውስጥ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አስረድተዋል።

የዓለም አትሌቲክስ ከዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሚያገኘውን ገንዘብ በሙሉ ለኦሊምፒክ ጨዋታ ስፖርቶች የሚሰጥበት ሂደት፤ እአአ በ2015 በተቀመጠ ውሳኔ መሠረት መሆኑንም ኮ ጨምረው ገልጸዋል።

ለአባል ፌዴሬሽኖቹ ከዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የትርፍ ክፍፍል ክፍያ የተጀመረው ለአትሌቲክስ ዕድገት ከሚደረጉት ድጎማዎች ላይ በዓመት ተጨማሪ 5 ሚሊዮን ዶላር መከፋፈሉም ተጠቅሷል። በ2028 የሎስአንጀለስ የክረምት ኦሊምፒክ ጨዋታዎች በሦስቱም ሜዳሊያዎች ገንዘብ ለመሸለምም ቃል ገብተዋል።

በኦሊምፒክ የሜዳሊያ አሸናፊ ለመሆን በገበያ ላይ የሚኖረውን ዋጋ ማስቀመጥ ባይቻልም፣ ወይም ሀገርን በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ለመወከል በሚሰጠው ቁርጠኝነት እና ትኩረት ላይ የሆነ ቦታ በመጀመር እና አንዳንድ ሽልማቶችን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

አትሌቶች በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ወደ ውድድር የሚመጡት ዓለም አቀፋዊ ትርኢትን በመላበስ እንደሆነም ተናግረዋል።

የሽልማት ገንዘብ ክፍያው በዓለም አትሌቲክስ የማፅደቂያ ሂደት ላይ የሚመረኮዝ ሲሆን፣ ይህም ስፖርተኞቹ የተለመደው ፀረ-አበረታች መድኃኒቶችን በመለየት መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል። በዚህም መሠረት እያንዳንዱ የኦሊምፒክ ሻምፒዮን 50 ሺ ዶላር እንደሚቀበል አረጋግጠዋል። የሪሌይ ቡድኖች ተመሳሳይ መጠን የገንዘብ ሽልማትን የሚቀበሉ ሲሆን 50 ሺ ዶላሩን በቡድን የሚከፋፈሉት ይሆናል። የ2028 ኦሊምፒክ የሽልማት እና የጉርሻዎች ቅርጽ እና አወቃቀሩ በቅርቡ ይፋ እንደሚሆንም ተነግሯል።

ፓሪስ ለዚህ ትልቅ የዓለም ድግስና ትልቅ ሽልማት ለሚያስገኘው ውድድር ዝግጅቷን እያደረገች ሲሆን አብዛኞቹን ውድድሮች በዋና ከተማዋ ይካሄዳሉ። በ32 ስፖርቶች 329 የስፖርት ሁነቶችን እንደሚያስተናግድ የሚጠበቀው ውድድሩ እአአ ከ1960 በኋላ የተወሰኑ የስፖርት አይነቶችን አካቶ የሚካሄድ ቢሆንም፤ አትሌቶቹ የ50 ሺ ዶላር ሽልማቱን ለመውሰድ የሚያደርጉት ፍልሚያ ተጠባቂ ነው። በእግድ ላይ የሚገኙትን ራሺያንና ቤላሩስን ሳይጨምር የተለያየ ሀገራትን በመወከል ከ10 ሺ በላይ አትሌቶች ለድሉ እንደሚፋለሙ ይጠበቃል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You