የጁዶ ስፖርትን የዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን አባል ለማድረግ እየተሠራ ነው

የኢትዮጵያ ጁዶ ስፖርት ፌዴሬሽን በዓለም አቀፉ የጁዶ ፌዴሬሽን ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በቅርቡ ምስረታውን ያካሄደው የኢትዮጵያ ጁዶ ፌዴሬሽን፣ እስከ አሁን ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያልተመዘገበ ሲሆን፤ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሚሰጠውን የማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንደሚጠብቅ ታውቋል።

የጁዶ ስፖርት በኢትዮጵያ በስፋት መዘውተር የጀመረው ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በኢንትግሬትድ ማርሻል አርት ስር ተመዝግቦ ይገኛል። በአዲስ አበባ ደረጃ በ2005 ዓ.ም ፍቃድ አግኝቶ እንቅስቃሴ ማድረግም ጀምሯል። ስፖርቱ ከሀገራችን የባህል ስፖርት ከሆነው ትግል ጋር የሚመሳሰልና በሁሉም አህጉራት ማህበራት ያሉት ሲሆን ከ200 በላይ ሀገራት በዓለም አቀፉ ጁዶ ፌዴሬሽን ተመዝግበው ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ጁዶ ፌዴሬሽንም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ለማግኘት እንቅስቃሴ ላይ መሆኑንና ሌሎች የፌዴሬሽኑን የስራ እንቅስቃሴዎችን አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። መጋቢት 2015 ዓ.ም አደራጅ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ጥቅምት 4/2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጁዶ ፌዴሬሽን መመስረቱን በማስታወስም የጁዶ ስፖርት ታሪካዊ ዳራን፣ አደራጅ ኮሚቴውን፣ ስፖርቱና የውጪ ግንኙነት ከተመሰረተ ጀምሮ ያለበት ደረጃ፣ ተሳታፊዎች፣ስልጣንና ኃላፊነት ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ተነስተዋል።

በዋናነት የተነሳው ጉዳይ፣ ፌዴሬሽኑን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመመዝገብ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የማረጋገጫ ሰርተፍኬት ለማግኘት እየጠበቀ እንደሆነና በቀጣይ በሚደረገው የኦሊምፒክ ኮሚቴው ጠቅላላ ጉባኤ ይሁንታ ካገኘ ፌዴሬሽኑ ዓለም አቀፍ ምዝገባውን እንደሚያከናውን አስታውቋል።

ስፖርቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባይመዘገብም በአፍሪካ ደረጃ ግንኙነቶች እንዳሉትና እነሱን ለማስቀጥልና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመመዝገብ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴን እውቅና ማግኘት እንደሚኖርበት ተገልጿል። ለዚህም በስራ አስፈጻሚው አማካኝነት አስፈላጊ ሰነዶች ተሟልተው ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና አለማቀፉ የጁዶ ፌዴሬሽን ጥያቄ ሊቀርብ ችሏል።

ስፖርቱ ከዚህ ቀደም በሲቪክ ማህበራት ስር ‹‹የኢትዮጵያ ጁዶና ጁጂሱ አሶሴሽን›› በሚል ማህበር ምዝገባ በማካሄዱና በዓለም አቀፉ ማህበር እንደ ፌዴሬሽን በመመዝገቡ ለፌዴሬሽኑ ምስረታና ዓለም አቀፍ ምዝገባ እንቅፋት ፈጥሯል። ማህበሩ ሲመሰረት ባለሙያዎችን ያማከለና ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅ ሆኖ እያለ በዓለም አቀፉ ማህበር እንደ ፌዴሬሽን በመመዝገቡ ችግሮች እንደተፈጠሩና ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይህንን ችግር ይፈታል ብሎ እንደሚጠብቁ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ማስተር ወንድሙ ደሳለኝ ጠቁመዋል። በዚህም ከሲቪክ ማህበራት ባለስልጣን ጋር ማህበሩ ከቆመለት አላማ ውጪ መንቀሳቀስ እንደሌለበት መግባባት ላይ መድረሳቸውን አክለዋል።

የሲቪክ ማህበራት ተቋም አንድ ወጥ የሆነ ተቋም እንዲኖርና ስፖርቱን ለማስቀጠል ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚኖርበት ፌዴሬሽኑ ጠይቋል። ባለው ችግርና ፌዴሬሽኑ በዓለም አቀፉ የስፖርት ፌዴሬሽን ባለመመዝገቡ ምክንያትም በርካታ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን መሳተፍ እንዳልተቻለ ተጠቅሷል።

ማስተር ወንድሙ ደሳለኝ ፌዴሬሽኑ ከተመሰረተ ጥቂት ወራት ብቻ ማስቆጠሩን ገልጸው፤የኦሊምፒክ ስፖርት እንደመሆኑ የሚዲያ አካላትን ትኩረት አግኝቶ ለማህበረሰቡ መተዋወቅ እንደሚኖርበት አሳስበዋል። በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ስፖርቱን በቀላሉ ለማስፋፋት የሚያስችል መንገድ መኖሩን ጠቁመው፤ የባህል ስፖርት ከሆነው ትግል ጋር በማያያዝ እስከ ገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል መድረስ እንደሚቻል መረጋገጡን አክለዋል።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከለንደን ኦሊምፒክ በኋለ የኢላማ ተኩስና ጁዶን በእቅድ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ለማሳተፍ አቅዶ የነበረ ቢሆንም ፌዴሬሽን ባለመመስረቱ ምክንያት እቅዱ ሳይሳካ እንደቀረም አስታውሰዋል። በፓሪስ ኦሊምፒክም በተጋባዥነት የመታደም እድሉ ቢኖርም ጉዳዩ እልባት ማግኘት እንዳልቻለ ተጠቅሷል።

ፌዴሬሽኑን 6 ክልሎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች የመሰረቱት ሲሆን፤ ስፖርቱ በድሬዳዋና ኦሮሚያ ክልል በስፋት ይዘወተር ነበር። ከምስረታው በኋላ ስፖርቱን ለማስፋፋት የበጀትና የቁሳቁስ እጥረት ቢኖርም በክልሎች ውድድርና ስልጠና እንዲያዘጋጅ ጥረት ተደርጓል። ከጃፓን መንግሥት በሚላክ አሰልጣኝ አራት ወንድና ሴት ለማሰልጠን ታቅዶ ጥረቶች እየተደረጉም ነው። ስፖርቱን ለማሳደግ ከባለሀብቱ ድጋፍ እንደሚያስፈልግና ለክልሎችም የመሳሪያና ቴክኒክ እገዛ አስፈላጊ በመሆኑ ችግሩ በአስቸኳይ ተፈቶ ዓለም አቀፍ ግንኙነቱ መጠናከር እንደሚኖርበት ተጠቁሟል።

ፌዴሬሽኑ አዲስ በመሆኑና በበጀት ዓመቱ አጋማሽ በመመስረቱ የበጀት እጥረት እንዳለበትና ሥራ አስፈጻሚው በሚያወጣው ገንዘብ መቆየቱም ተመላክቷል። ገቢን ለመሰብሰብ እቅድ ተነድፎ መመሪያ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ማንኛውም ህጋዊ አካል በኮሚሽን ሕግ መሰረት ከፌዴሬሽኑ ጋር ተባብሮ መስራት ይችላል ተብሏል።

ፌዴሬሽኑ የማህበራትን ደንብ ተከትሎ የተቋቋመ በመሆኑ፣ በዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ደንብን ተከትሎ ደንቦችን የመፈጸም፣ ስፖርት ክለቦችን ማደራጀት፣ ውድድር የማዘጋጀትና ስልጠና መስጠትና ሌሎች ተያያዥ ስልጠናዎች እንዳሉትም አስታውቋል። የሀገር ውስጥና የውጪ ወድድሮችን ለማዘጋጀት አቅዶ እየሰራም ሲሆን፤ በቅርቡ ለሁሉም ክፍት የሆነ ውድድር እንደሚካሄድ ተጠቁማል። በመጨረሻም በስፖርቱ የሚነሱ ቅሬታዎች በመኖራቸው ጥናት ስለሚያስፈልግ ማንኛውም ጁዶን የሚችል አካል ተሰባስቦ በመስራት ስፖርቱን እንዲያሳድግ ፌዴሬሽኑ ጥሪውን አስተላልፏል።

አለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You