አሜሪካ ከኢራን ጋር በሦስተኛ ወገን በኩል እየተወያየች መሆኗ ተገለጸ

አሜሪካ ከኢራን ጋር በሦስተኛ ወገን በኩል እየተወያየች መሆኗ ተገለጸ። በኢራን ላይ ተደጋጋሚ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን በመጣል የምትታወቀው አሜሪካ በሦስተኛ ወገን በኩል እየተወያየች ነው ተብሏል፡፡

አል አረቢያ አክሲስን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ፤ የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ከኢራን ባለስልጣናት ጋር በመወያየት ላይ ነው።አሜሪካ ከኢራን ጋር መወያየትን የመረጠችው በመካከለኛው ምሥራቅ እየተከሰቱ ያሉ ቀውሶች እንዳይባባሱ እና ለመቆጣጠር እንዲቻል መሆኑ ተገልጿል፡፡

በአሜሪካ በኩል የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን መካከለኛው ምሥራቅ አማካሪ ብሬት ማክጉርክ እና በኢራን የአሜሪካ አምባሳደር አብራም ፓሌይ ከኢራን ጋር እየተደራደሩ ናቸው የተባለ ሲሆን፤ በኢራን በኩል ግን እስካሁን የተደራዳሪዎቹ ማንነት አልተጠቀሰም።እንዲሁም አሜሪካ እና ኢራን በሦስተኛ ወገን እንዲደራደሩ እያደረገ ያለው አካልም ያልተጠቀሰ ሲሆን፤ ውይይቱ ካሳለፍነው ጥር ወር ጀምሮ በመካሄድ ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ውይይት በተለይም የኢራን እና እስራኤል የቀጥታ ግጭት ውስጥ ከገቡበት ሚያዚያ ወር ወዲህ የበለጠ እየተደጋገመ እና እየጠነከረ እንደመጣም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።ባሳለፍነው ጥቅምት ሐማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የእስራኤል እና ኢራን ግንኙነት የበለጠ እየሻከረ መጥቷል፡፡

አሜሪካ በእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት ውስጥ ጣልቃ እንዳትገባ ኢራን ብታስጠነቅቅም፤ ዋሽንግተን በግልጽ ለእስራኤል ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች፡፡ይህን ተከትሎ አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ያሏት ወታደራዊ ማዘዣዎች በኢራን ይደገፋሉ በሚባሉ ታጣቂዎች የጥቃት ኢላማ ሆነዋል፡፡

በተለይም በጆርዳን፣ ኢራቅ እና ሶሪያ ያሉ የአሜሪካ ወታደራዊ ማዘዣዎች የተለያዩ ጥቃቶችን ያስተናገዱ ሲሆን፤ ሦስት የዋሽንግተን ወታደሮች ተገድለዋል ሲል አል ዐይን ዘግቧል፡፡

አዲስ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You