የአዲስ አበባ ሙዚየሞች

ሠላም ልጆችዬ እንዴት ናችሁ? ትምህርት ጥናት እንዴት ነው? መቼም ልጆችዬ ነገ ትልቅ ቦታ ደርሳችሁ ሀገራችሁን ለማገልገል በርትታችሁ እየተማራችሁና እያጠናችሁ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ።

ልጆችዬ ኢትዮጵያ የታሪክ፣ የባህል፣ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች ያሉባት ፣ የብርቅዬ እንስሳት መገኛ እና የተፈጥሮ ባለፀጋ ሀገር እንደሆነች ታውቃላችሁ አይደል? መልሳችሁ “እንዴ በሚገባ!” የሚል እንደሆነ ጥርጥር የለኝም።

እናም ልጆችዬ ሀገራችን የተለያዩት ቅርሶች ባለቤት ብቻ ሳትሆን የተለያዩ ሙዚየሞች መገኛም ጭምር መሆኗን ለማሳየት ለዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ሙዚየሞች ላስጎበኛችሁ ነው፡፡ በዚህም ከሙዚየሞቹ መካከል የት? እና በውስጣቸው ምን እንደያዙ አስቃኛችኋለሁ። በመዲናዋ እየኖራችሁ ሙዚየሞቹን ላልጎበኛችሁ ልጆችም ሆነ በተለያየ ምክንያት ወደ ከተማ ለምትመጡ ልጆች ቦታዎቹን እንድትጎበኙ እና በመጠኑም ቢሆን መረጃ እንደሚሰጣችሁ በመተማመን በአዲስ አበባ የሚገኙ ሙዚየሞችን እንደሚከተለው አብረን እንቃኝ።

ልጆችዬ ከ”ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም” እንጀምር አይደል? ይህ ሙዚየም መገኛ ቦታው አምስት ኪሎ ሲሆን፤ የተለያዩ የኢትዮጵያ ቅርሶችን የያዘ ነው። ለምሳሌ የቀድሞ ነገሥታት አልባሳት እንዲሁም መገልገያዎቻቸው በዚህ ሙዚየም ውስጥ ይገኛሉ። በተጨማሪም ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን የሚያሳዩ የተለያዩ የቀደምት ሰዎች ቅሪት አካሎች በዚህ ቦታ ይታያሉ። የሉሲ ወይም ድንቅ ነሽ ቅሪተ አካል በዚህ ሙዚየም የሚገኝ ሲሆን፤ በተጨማሪም ከሦስት ሚሊዮን ዕድሜ በላይ ያላት የ”ሠላም” ቅሪተ አካልም በዚህ ሙዚየም ይገኛል።

በአዲስ አበባ ከሚገኙ ሙዚየሞች መካከል የ”አዲስ አበባ ሙዚየም” በዋነኝነት ይጠቀሳል። ይህ ሙዚየም መገኛው የት ይመስላችኋል ልጆችዬ? መስቀል አደባባይ አካባቢ ነው። በዚህ ሙዚየም የቀድሞ የኢትዮጵያ ነገሥታት አልባሳት፣ ነገሥታቱ የሚጠቀሙባቸው ጥንታዊ ቁሳቁሶች፣ የጦር መሣሪያዎች እና ልዩ ልዩ የብራና መጽሐፍት ጎብኚዎች እንዲያዩት ሆኖ ተዘጋጅቷል።

ልጆች “የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሙዚየም” በኢትዮጵያ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ የሚገኝ ሌላው ሙዚየም ነው። መገኛ ቦታው ስድስት ኪሎ ሲሆን፤ ይህ ሙዚየም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የዩኒቨርሲቲ ሙዚየም ነው። በተጨማሪም በቀድሞ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግሥት በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ጊቢ ይገኛል።

የተለያዩ የኢትዮጵያ ባህላዊ ቅርሶች ያሉበት ሙዝየም ነው። በውስጡ ምን እንጎበኛለን ብላችሁ ከጠየቃችሁም ከዚህ ቀደም ንጉሥ የነበሩት የቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ የግል ቁሳቁሶች፣ የተለያዩ አልባሳት፣ የመኝታ ክፍል፣ ምስሎች፣ መጽሀፍት እና የባለቤታቸው እቴጌ መነን መገልገያ ቁሳቁሶች በዚህ ሙዚየም ይገኛሉ።

ልጆችዬ ስለሙዚየሞቹ ስታነቡ ምን ተሰማችሁ? ምነው ሄደን በጎበኘን አላላችሁም? ለማንኛውም የሙዚየም ጥቆማችንን አልጨረስንም። ሌላም አለን ስሙ ‹‹አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት የተፈጥሮ ቅርስ መዘክር›› ይሰኛል። መገኛ ቦታው ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ትምህርት ክፍል አራት ኪሎ ካምፓስ ነው። በዚህ ሙዚየም ከአንድ ሺ በላይ የእንስሳት ቅሪተ አካል ይገኙበታል።

‹‹የሳይንስ ሙዚየም›› በቅርቡ ከተሠሩ መዚየሞች አንዱ ነው ። ሙዚየሙ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር አማካኝነት መሠራቱ ይታወቃል። ይህ ሙዚየም የመጀመሪያው የሳይንስ ሙዚየም ለመሆን በቅቷል። በውስጡም በርካታ ማሳያ ስክሪኖች ሮቦቶችንን እና የተለያዩ ነገሮች ይዟል። ይህ ሙዚየም የቀለበት ቅርጽ ያለውና መሃሉ ላይ የጉልላት ቅርጽ ያለው ህንጻን የያዘ ሲሆን በሰባት ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው።

ልጆችዬ ሙዚየሞችን መጎብኘት ስለ ሀገር ባህል ፣ታሪክ ፣ቅርስ እና ምን ያህል በተፈጥሮ የታደለች ሀገር እንደሆነች ለመረዳት ያስችላል። እናም በተቻለ መጠን በአቅራቢያችሁ የሚገኙ ሙዚየሞችን ከወላጆቻችሁ ጋር በመጎብኘት ስለ ሀገራችሁ በሚገባ እንድትረዱ ያግዛችኋል። ልጆችዬ ለዛሬ በዚህ እናብቃ፡፡ ለሳምንት በሌላ ርዕሰ ጉዳይ እንደምንገናኝ በመመኘት እንሰነባበት።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You