የወጣት እጅ ኳስ ብሄራዊ ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ መድረክ ይሳተፋል

የአፍሪካ ዞን 5 የወጣት ወንዶች (ከ18 ዓመትና ከ20 ዓመት በታች) የእጅ ኳስ ዋንጫ ውድድር በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከግንቦት 4 እስከ 9/2016 ዓ.ም የቀጣናውን ሀገራት አፎካክሮ በኢትዮጵያ ታዳጊ ቡድኑ አሸናፊነት ተጠናቋል:: አሸናፊው ከ18 ዓመት ብሄራዊ ቡድንም ለአፍሪካ ወጣቶች እጅ ኳስ ቻምፒዮና ማለፍ ችሏል:: ከ20 ዓመት በታች ቡድን በበኩሉ ለዋንጫ ተፎካካሪ ቢሆንም ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ፈጽሟል::

የዓለም እጅ ኳስ ፌዴሬሽን እና የአፍሪካ እጅ ኳስ ኮፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በትብብር ያዘጋጁት የወጣት ወንዶች እጅ ኳስ የዋንጫ ውድድር ስምንት ሀገራትን አፋልሞ፣ ዞኑን በመወከል የአፍሪካ ወጣቶች እጅ ኳስ ቻምፒዮና ላይ የሚሳተፉ ሀገራትን መለየት ችሏል:: የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በፍጻሜው ውድድር ርዋንዳን ከጨዋታ ብልጫ ጋር አሸንፎ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን አረጋግጧል:: ቡድኑ ያስመዘገበው ድል ሀገርን ያኮራ እንዲሁም ተጫዋቾቹን እና አሠልጣኞቹን ጮቤ ማስረገጥ የቻለ ቢሆንም፣ በርካታ ፈተናዎችን በመሻገር የመጣ ነው:: ከኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሚመደበው በጀት በጊዜ ባለመለቀቁ ምክንያት ቡድኑ ተሰባስቦ ሙሉ ዝግጅት ባያደርግም በአሠልጣኞችና ተጫዋቾች የጋራ ጥረት ችግሮችን አሸንፎ ለታሪካዊ ድል በቅቷል::

በምድብ ሁለት ከሩዋንዳ እና ታንዛኒያ ጋር ተደልድሎ ውድድሩን ያካሄደው ይህ ቡድን በዙር ሁለት ጨዋታ፣ በጥሎ ማለፍ እና በፍጻሜው አንድ አንድ በአጠቃላይ አራት ጨዋታዎችን አድርጎ 3ቱን በድል አንዱን ደግሞ አቻ በመለያየት የወርቅ ሜዳሊያውን እና ዋንጫውን ወስዷል:: ከታንዛኒያ ጋር የነበረውን የመጀመርያ ጨዋታ ተጋጣሚው በማርፈዱ በፎርፌ ነጥብ ወስዶ፣ በሁለተኛው ጨዋታ ሩዋንዳን ገጥሞ 29 አቻ ውጤት አስመዝግቦ እና ቡሩንዲን በግማሽ ፍጻሜ አሸንፎ ለፍጻሜ በቅቷል:: ፈተናዎችን እየተጋፈጠ ዝግጅቱን አድርጎ ለውድድሩ ቢቀርብ የምድቡን ጠንካራ ተፎካካሪ ሩዋንዳን ከጨዋታ ብልጫ ጋር 36 ለ 25 ረቶ ዞኑን በአፍሪካ መድረክ መወከል የሚያስችለውን ትኬት መቁርጥ ችሏል::

ኢትዮጵያ ለመድረኩ ተሳትፎ የበቃችው ከረጅም ዓመታት በኋላ ሲሆን የቡድኑ አሠልጣኞችና ተጫዋቾች በቂ እና የተሟላ ዝግጅትን ሳያደርጉ ውጤት እንዲመጣ ማድረጋቸውን ‹‹ድሉ አንድ በመሆናችን የተመዘገበ ነው›› በማለት ገልጸውታል::

የቡድኑ አሠልጣኝ ተስፋዬ ሙለታ፤ ፈተናዎችን አልፈው ለድል እንዲበቁ አንድ ሆኖ በማነጋገር የሀገር ጥቅም እንዲቀድም ማድረጋቸው ከፍተኛ ሚና እንዳበረከተ ይጠቁማሉ:: ተጋጣሚ ሀገራት ተገቢውን ዝግጅት አድርገው የመጡና ጠንካራ ተፎካካሪ ቢሆኑም ተጫዋቾቻቸው ግን ዋንጫውን መውሰድ ችለዋል:: የነበሩትን ክፍተቶች ማረም ፍጻሜው ላይ በአሳማኝ ሁኔታ እንዲያሸንፉ አድርጓል:: ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው ቡድኑ ተመሳሳይ ውጤት ኢንዲያስመዘግብም ተጫዋቾችን ማበረታታት እና በእቅድ ተገቢው ዝግጀት መደረግ እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል::

የ18 ዓመት በታች ቡድኑ ተጫዋች የሆነው ስጦታው ፍቃዱ በበኩሉ፤ ፈተናዎችን በማለፍ ዋንጫውን አንስተው የረጅም ጊዜ ታሪክን በማደሳቸው ደስታቸው ወደር እንደሌለው አስረድቷል:: ከፓስፖርት እና ከዝግጅት ጋር ብዙ ችግሮች ቢኖሩም በአሠልጣኞችና ተጫዋቾች ጥረት አሽንፎ ለድል በቅተዋል::

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍትህ ወልደሰንበት በውድድሩ ስምንት ሀገራት ተሳትፎን ማድረጋቸውን ገልጸው፤ ለመጀመርያ ጊዜ የተመዘገበ ትልቅ የተሳትፎ ቁጥር እንደሆነና ለዝግጅት የተሰጠው ጊዜ አጭር ቢሆንም በተደረገው ጠንካራ ቅድመ ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ እንደተጠናቀቀ ተናግረዋል::

ከዚህ ቀደም ብሔራዊ ቡድኑን ከየቤቱ በመውሰድ ለውድድር እንደሚያቀርቡና አሁን ከውድድር ላይ መሆኑ ለውጤቱ መመዝገብ ትልቅ ድርሻ ነበረው:: ቡድኑ የዋንጫ እና የወርቅ ሜዳሊያን በማግኘት ለአፍሪካ እጅ ኳስ ዋንጫ በማለፉም ታሪክ ሊጻፍ ችሏል:: ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑም 3ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቁ ትልቅ ስኬት እንደሆነው ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል:: ዝግጅቱ በፌዴሬሽን አቅም ብቻ እንደነበረና በቀጣይ ብሔራዊ ቡድን ተገቢውን ዝግጅት እንዲያደርግ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር እንደሚሠሩም አክለዋል::

ከሁሉም የአፍሪካ ዞኖች ከሁለቱም እድሜ ደረጃዎች ቡድኖች በቀጥታ ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፍ ውድድራቸውን ያከናውናሉ:: ከ7 ዞኖች 14 ቡድኖች በአፍሪካ መድረክ በሚያደርጉት የዋንጫ ፍክክር ከሁለቱ የእድሜ ገደብ የሚያሸንፉ አንድ አንድ ሀገራት አፍሪካን ወክለው በዓለም ዋንጫ የሚሳተፉ ይሆናል:: ከ20 ዓመት በታች ውድድሩን ኡጋንዳ አሸንፋ ዞኑን መወከሏን አረጋግጣለች::

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You